ለመዳን መታገል  ወይስ እያለቀሱ መሞት ምኞታችን ሕዝብ በአገሩ በሰላም እንዲኖር ወይስ ሞቶ ለገነት እንዲበቃ? – አገሬ አዲስ       

ሰኔ 14ቀን 2014ዓም(21-06-2022)

288834028 141798798444586 915168036526131923 nየሰው ልጅ ሲፈጠር የመሞቱን ግዳጅ ተረክቦ መሆኑ እንግዳና አጠያያቂ አይደለም።ለዘለዓለም የሚኖር ሕይወት ይዞ የሚፈጠር እንስሳም ሆነ እጽዋት የሆነ ፍጡር የለም።በዕድሜ ብዛት አርጅቶ፣ሰውነቱ ደክሞና ዝሎ መሞቱ የተፈጥሮ ሕግ ነው።ከተፈጥሮው ውጭ ሞቱን የሚያፋጥኑ ሌላ ተጨማሪ አስገዳጅ ሁኔታዎችም አሉበት።በበሽታ ተለክፎ፣በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጠቅቶ፣በአውሬ ተበልቶ መሞንትም ያስተናግዳል።የመፈጠሩ መንገድ አንድ ቢሆንም የመሞቻው መንገድ ብዙ ነው።በዚህም ሆነ በዚያ ከሞት የሚያመልጥ ምንም አይነት ፍጡር የለም።ሆኖም ግን  የሰው ዘር ለመከራና ለስቃይ ብቻ ተፈጥሮ፣መልካም ኑሮ ሳይኖር ወደ አለመኖር ለመሸጋገር ብቻ ሳይሆን  ባለችው ውስን የሕይወት ዘመኑ በተፈጥሮ በሚያገኛቸውና በጥረቱ በሚያፈራቸው መልካም ምርቶች ሁሉ ተደስቶ የዕድሜው ጣራ ሲደርስ በሞት ለመሰናበት የተለዬ ዕድል አለው።ይህንን የሁሉም ሊሆን የሚገባ የመልካም ኑሮ ጸጋ ዕድሉን ነጥቀው  የግላቸው በማድረግ የሕይወትን መልካም ገጽ ለማጣጣም  የሚበቁት በጣም ጥቂቶች ናቸው።ብዙዎቹ ግን ሲወለዱ ጀምሮ የመከራ ጽዋ ይጎነጫሉ።ሳይወለዱ በጽንሳቸው የሚጨነገፉ፣በምጥ ስቃይ የሚሞቱና የእናታቸውንም ሕይወት ለመቀጠፍ ሰበብ የሚሆኑ፣ከተወለዱም በዃላ በበሽታ፣በርሃብና ችግር፣በጦርነትና  በአመጸኞች እጅ የሚሞቱ በዕድሜ ገደብ ዝለውና ደክመው  በተፈጥሮ ሞት ህይወታቸው ከሚያልፈው እጅጉን ይበዛሉ። በነዚህ የሞት ምክንያቶች ውስጥ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ከሚሞቱት የሰው ልጆች መካከል አፍሪካ በተባለው ክፍለሀጉር የሚኖረው ሕዝብ ትልቁን ቁጥር ይይዛል።ኢትዮጵያም የዚያው ክፍለሃጉር አካል ስለሆነች የሚኖርባት ሕዝብ የመከራው ተሸካሚ ነው።

የተፈጥሮ አደጋ በማንኛውም ጊዜ የሚደርስ ቢሆንም ቅድመዝግጅት በማድረግ አደጋውን ማሶገድ አለያም መጠኑን መቀነስ  ይቻላል።በእርግዝና ወቅት  ጽንስ እንዳይጨነግፍና በወሊድ ጊዜ ሕጻኑም ሆነ ወላጅ እንዳይጎዱ ክትትልና ምክር መስጠት፣በድርቅ ጊዜ የርሃብ አደጋ ተከስቶ ሰው እንዳይሞት ድርቅን ለመመከት የሚያስችሉ ዝግጅቶች በማድረግ አለያም በመኸር ወቅት በብዛት አምርቶ ለክፉ ቀን በጎተራ በመክተት እርሃብን ማሶገድ ይቻላል።በሃይለኛ ዝናብ ሳቢያ ወንዝ ሞልቶ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርስ ግድብና ድልድይ በመሥራት መከላከል፣በውስጥና በውጭ በሚከሰት የአካል ህመም ፣ከወረርሽኝና ከተላላፊ በሽታ ለመዳን መድሃኒት መቀመምና የሕክምና ተቋም ማቋቋም፣ከአውሬ ጥቃት ለመዳን ቤትና አጥር ብሎም መከላከያ ማዘጋጀት፣ በአዳጋች የመንገድ ጉዞ ላለመጎዳትና ገደል ላለመግባት ጫካ መንጥሮና አቀበት ደልድሎ መንገድ መቀዬስ፣ጨለማውን በብርሃን፣ብርዱን በሙቀት፣ወበቁን በለሰለሰ አዬር በመተካትየሚያስችል ችሎታን በመፍጠርና ተደራሽ በማድረግ፣ከአመጸኛ ወንበዴና ሽፍታ ለመዳን ሕግና ፍትሕ ማስፈን፣ከወራሪ ለመዳን ብቃት ያለው የመከላከያ ሃይል  መፍጠር የሰውን ከባድ ኑሮና መከራ ብሎም  ያለጊዜው የመሞቻ መንገዶች ይቀንሳል ያሶግዳልም።

እነዚህን የመከላከያ ዘዴዎች ሊዘረጋ የሚችል መንግሥት የተባለ ከሕዝቡ ተውጣጥቶ የሚቋቋም ሕዝባዊ አካል ሲኖር ነው።ይህ በሕዝቡ ፈቃድና ፍላጎት የሚቋቋም መንግሥት ሃላፊነቱን ሳይወጣ ቢቀር በሚደርሰው ጥቃትና ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል።የሕዝብ አገልጋይና አደራ ተሸካሚ በመሆኑ በእንዝህላልነቱ በሚደርሰው ጉዳት ከተጠያቂነት አያመልጥም።ሲጀመርም ሃላፊነቱን እወጣለሁ ብሎ የማያምን የመንግሥትን ሥልጣን ለመረከብ መሽቀዳደም አይኖርበትም።ሃላፊነትን መረከብ ማለት የግልን ጥቅምና ዝና ለማስከበር ሳይሆን  ባለው ችሎታ ዝቅ ብሎ ህብረተሰቡን ለማገልገል እራሱን አሳልፎ የሰጠ ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው።

ለዚህ አይነቱ የመንግሥት ተቋም የታደሉት በዓለማችን በጣም ጥቂት አገራት ናቸው።እነሱም ቢሆኑ አልጋ ባልጋ ሆኖላቸው ያገኙት ትሩፋት ሳይሆን በብዙ ትግልና መስዋእትነት ያገኙት ውጤት ነው።ሙሉ ለሙሉም ባይሆን ከመከራውና ከስጋቱ  ይልቅ የተሟላ ኑሮ ባለቤቶች ሆነዋል።የቀራቸውንም ለማሟላት ጥረታቸውን አላቆሙም።እንዳለመታደል ሆኖ ግን እነሱ ያለፉበትን መከራ በሌላው ላይ እንዲደርስ የሚያደርጉት ጫና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።እነሱ ሲጠግቡ ሌላው ተርቦ እንዲኖርና እርሃብን እንደ መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙ ብዙ ናቸው።ለነሱ መበልጸግ የሌላውን መደህዬትና መቆርቆዝ እንደ ዋስትና  አድርገው ይቆጥሩታል።ለዚያ የሚያገለግሉ የጥቅም አጋሮቻቸውን በመመልመልና በሥልጣን ኮርቻ ላይ በማስቀመጥ ብዙሃኑን የመከራ ሰለባ ለማድረግ የማይገለብጡት ድንጋይ የለም። አገራት በራሳቸው የተፈጥሮ ሃብትና ችሎታቸው ሳያድጉና ሳይሻሻሉ የነሱ ጥገኛ ሆነው እንዲቀሩ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሕዝብ እርስ በራሱ እንዲባላ፣በጎሳና በሃይማኖት ሰበብ ተለያይቶ እንዲጫረስና ለነሱ  መግቢያ ቀዳዳ እንዲፈጥር የማድረጉ ተግባር የተለመደና የታወቀ ነው።

የሚያሳዝነው ይህንን ለመረዳት ያልቻለ መኖሩና በተቀደደለት የጥፋት ጎዳና የሚነጉደው ቁጥሩ ከሚገምቱት በላይ መሆኑ ነው።በኢትዮጵያም ላለፉት 50 ዓመቶች የተከሰተው አገር አፍራሽ ፣ሕዝብ አጫራሽ የሆነ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍናና የሥልጣን ቅብብሎሽ የዚሁ ሴራ አካል ነው።

ሕዝቡ እያለው የሌለው ሆኖ ከብስቁልና ኑሮ ፣ከአዳፋ ልብስና ካልተሟላ ጉርስ ያለፈ የሚያጓጓና የሚማርክ ኑሮ የለውም።በትንሽ በሽታ እንደቅጠል ይረግፋል።ይህም ኑሮ ሆነና በራሱ አገር መሬት ላይ እንዳይኖር የራሱ አገር ዜጋ ጠላት ሆኖ ተሰልፎበታል።ይህም ኑሮ ሆነና የቀዬሳት የጭራሮ ጎጆ እንደቤት ተቆጥራ የሚቀኑባትና በእሳት የምትጋይ ሆናለች፣ይህም ኑሮ ሆነና ባዶ እግራቸውን ገታ ለብሰው ከብት የሚጠብቁ ልጆች ታፍነው ቀብድ ይጠዬቅባቸዋል፣ይገደላሉም።ይህም ኑሮ ሆነና ድህነት ያባረረውን ሰላማዊ ሕዝብ ፧ደፋ ቀና ብሎ ጫካ መንጥሮ ካለማው የሃገሩ መሬት ያፈናቅሉታል።ይህም ኑሮ ሆነና በዝባዥና ነፍጠኛ ተብሎ እንደ ወራሪ የውጭ ጠላት የማርያም ጠላት ተደርጎ መከራ ይደርስበታል፣ለሃገር ነጻነትና ልዑላዊነት ተጋድሎ ያደረጉና መስዋእት ሆነው የአገር ባለቤትነትን ጸጋ ያጎናጸፉ አርበኞች ነፍጠኛ ተብለው ልጅና የልጅ ልጆቻቸው ውግዝ ከማሪዎስ ይወርድባቸዋል።ይህ ሁሉ ግን ከድህነት የሚያወጣ ሳይሆን ሁሉም በድህነት አሮንቋ ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርግ የባዕዳን  የሴራ ውጤት ነው።አንድ አማራ አርሶ አደር ደሃ ቢሞት አንድ ደሃ ኦሮሞም ሆነ ሌላው ደሃ በማግሥቱ ሃብታም አይሆንም፣ሌላውም እንዲሁ።ድህነትን ለማጥፋትና በሰላምና  በእኩልነት ለመኖር ማጥፋት የሚገባው ደሃን ሳይሆን የድህነት ምንጩን ነው።ያም ለባዕዳን መሣሪያ የሆነውን መንግሥትና የዘረጋውን የጎሰኝነት ሥርዓት ነው።ሰላምና ፍትሕ ወዳዱ ሕዝብ ተባብሮ ካልቆመ ዛሬ በሚወድቀው አማራ ምትክ ሌላው ነገ ይወድቃል። በተረኝነት መንፈስ የመነዳት ውጤቱ ይኸው ነው።ገዳይ እንደገደለ፣ዘራፊ እንደዘረፈ፣ባንዳና አድርባይም እንዲሁ በያዘው ሙያና ደረጃ አያመሽም፤የጊዜ ጉዳይ ነው በተራው የስቃይ ገፈት ይጋታል።የእጁን ያገኛል።

በዝባዥና ጨቋኝ ተብሎ መከራውን የሚያዬው የአማራ ልጆች እነዚህን ይመስላሉ

 

የፈረደበት አማራ ማህበረሰብ በኑሮ ደረጃ  የበታች ቢሆንም ለአገሩ ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅርና የሚከፍለው መስዋእትነት ከሁሉም በላይ ያደርገዋል።እነዚህ በፎቶው ላይ የሚታዩት የአማራው አርሶ አደር ልጆች ከላይ ቀዳዳ ልብስ ቢለብሱም፣ለእንቅፋትና ለእሾህ በተጋለጠ ባዶ እግር ቢሄዱም  በውስጣቸው የከበረ አገራዊ ጃኖ የለበሱ የሞራልና የሃቅ ጌታ፣ታላቃቸውን አክባሪ የሆኑ የአገር ወዳድ የአማራ ቤተሰቦች ናቸው።ለዚያም ነው አገር ጠሎች ጠላት አድርገው ለማጥቃት የሚሽቀዳደሙት።ይህንን  የሰውነት ጸጋ በመላበሳቸው ነው ከሌሎቹ ልቀውና  ደምቀው በታሪክ ለመታዬት የበቁት።የመልካም ታሪክ ደሃ የሆነ ቅናት ያሳበደው የህብረተሰብ ክፍል በነዚህ ንጹሃን ላይ ካራ ስሎ ደማቸውን ሲያፈስ ማዬት እንደሰው ለሚያስብ ሁሉ ይዘገንናል።ማንኛውም ማህበረሰብ በስሙ ጨካኞች ግፍ ሲፈጽሙ እያዬ ዝም ካለ በተባባሪነት ከመጠዬቅ አይድንም።ሌላውም የተጠቂው አማራ ማህበረሰብ ተወላጅ በግፍ የሚገደለውን ሕዝብ እዬቀበሩ በሰማይ ቤት ነፍስሕን ለገነት ያብቃው ከማለት ይልቅ ለመኖር በተፈጠረባት አገር በሰላም ኑሮ በዕድሜ ተሸንፎ ወይም፣በማይችለው በሽታ ሲረታና ሲያልፍ መቅበሩ የተሻለና የተገባ ነው።በሚታዬውና በሚዳሰሰው መሬት ላይ የመኖር መብቱ ሳይከበርለት በጨካኞች እጅ ታርዶ ሲሞት  በሰማይ ቤት የገነት ኑሮ መመኘቱ ለተጎጅውም ሆነ ለቀባሪው ወዳጅ ዘመድ አይጠቅምም። ከነጭነቱ ወደ ከርሰመቃብር ገባ እንጂ  የድሃውን የስቃይና የመከራ ሸክም አያቃልልለትም።የሚያቃልልለት በሰውነት ደረጃ ተከብሮ እንደሰው ሆኖ ማለፉ ነው።ለዚያ ሁሉም የመከራ ተሸካሚ የሆነ ፍጡር (ሕዝብ)የመከራውን ሸክም ለማራገፍ ተባብሮ መነሳትና መታገል ይኖርበታል። ዛሬ በጥቃት የሚሞተው ሕዝብ ዕድል ነገ በቀባሪው ላይ ላለመድረሱ ዋስትና የለም።ገዳዮች የሚደሰቱትና የሚረኩት አንዱ ሟችና ተቀባሪ ሌላው ቀባሪና በተራው ሟች ሆኖ የሚፈሰውን ደምና እምባ በማዬት ነው።ስለሆነም ከማልቀስ ሰፈር ወጥቶ አስለቃሽ የሆነውን ሥርዓትና ቡድን ማሶገድ የመከራ ዘመኑ መቋጫ ይሆናል።በሰማይ ቤትም የሰው ልጅ የሚዳኘው በመሬት ላይ በፈጸመው ሥራ ስለሆነ ክፉ መንግሥትን በማውረድና ፣ክፉ ሰዎችን በማሶገድ የገነትን መንገድ ከሚጠርጉት አንዱ ፈጣሪ የሚሻውና የሚፈቅደው ምድራዊ ተግባር ነው።እዬሱስ ክርስቶስም ሆነ ነብዩ ሞሃመድ ያስተማሩትና የታገሉት ክፋትና ጭካኔን የሠይጣንን ተግባር ነበር።የሰይጣን ሥራ በሰዎች ይገለጣልና ክፉዎችን ማሶገድ ሰይጣንን ማሶገድ ነው።ለሰይጣን ጥፊ ፊትን አመቻቹ አላለም።

የሰይጣናትን ጎራና ሰልፍ ለይቶ ማወቅ ለዘመቻው መሳካት ወሳኝ ነው።ስለሆነም ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ የሆኑት የተለያዬ ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ስብስቦች በሙሉ በአምላክ አምሳል የተፈጠረን የሰው ልጅ የሚገሉ፣የሚያርዱ፣አምላክ በፈጠረው መሬት ላይ እንዳይኖር የሚያደርጉ ሁሉ ጸረ አምላክ ናቸው።በነዚህ ላይ ተባብሮ መነሳት ተገቢና ጊዜው የሚጠይቀው ግዴታ ነው።እነዚህ ጨካኞች ክርስቲያንም ሙስሊምም አለመሆናቸውን በሁለቱም እምነት ተከታዮች ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ማሳያ ነው።ሃይማኖቱንና ጎሳውን ለይቶ የማያውቅ በሆድ ውስጥ ያለ ጽንስ፣የሶስትና ያስራአምስት ቀናት ጨቅላ(ህጻን) የማረድ ጭካኔ ከሰው ዘር የይጠበቅም።የጀግና ሙያም ሆኖ አያኮራም።ይህ የክፉዎች ጥቃት በማልቀስና በጸሎት ብቻ የሚወጡት ችግር አይደለም።ሲሆን ጠላት ካለበት ድረስ ሄዶ ማጥቃት አለያም በግፍ የሚጨፈጨፉት በገፍ እንዳይጨፈጨፉ፣እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል የትጥቅም ሆነ የስንቅ ዝግጅት እንዲኖራቸው ማድረጉ ከሞቱ በዃላ ከማልቀስና በገነት ያኑርህ ከማለት የተሻለና ዘላቂ መፍትሔ ነው።

የድሆች እምባና ደም አይፍሰስ! ያልታጠቀው አማራ ይታጠቅ!!ይደራጅ!!

የጎሰኞችና የባዕዳን ሕብረት ይፍረስ!!!ገዳዮችና አስገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ!!!

አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.