ከዓለም አቀፍ የዐማራ ጉባኤ የተሰጠ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

International Amhara Association Logoሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.
June 19, 2022

PDF መግለጫከዓለም አቀፍ የዐማራ ጉባኤ የተሰጠ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ጠብቆ ያኖረው የዐማራ ሕዝብ በተለይ ከትህነግ መምጣት ጀመሮ ሲጨፈጨፍ ሲሳደድ የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ሲካሄድበት ቆይቷል። አሁን ደግሞ የኦነግ ኦሮሞ የዐብይ አገዛዝ ከዘር ማጥፋትና ማፅዳት በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ በዐማራው ላይ ወረራ በማካሄድ ኢትዮጵያን አፈራርሶ “ኦሮሚያ” የሚባል ሀገር ለመመስረት ደፋ ቀና ይላል። እኛ በዓለም ዙሪያ የምንገኝ ዐማሮች ይህን ግልጽም ስውርም ደባ እንዲቀጥል መፍቀድ ተባባሪነት ስለሚሆን በተናጠል የምናደርገውን የዐማራ የህልውና ትግል በተቀናጀ ስልታዊ መንገድ ለማካሄድ መሰረት የጣልንበት የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ የዐማራ ጉባኤ በሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. (June 18, 2022) እና ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. (June 19, 2022) አካሂደናል።

በዚህ ጉባኤ የዐማራን ዘር ማጥፋትና ማፅዳት በጽኑ አውግዘን ከዚህ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች አሳልፈናል።

፩. ጉበኤው እየተካሄድ እያለ ጊምቢ በሚባል የወለጋ ወረዳ ከ 2500 በላይ ዐማሮች በመጨፍጨፋቸዉ በጥልቅ የተሰማንን ሃዘን በመግለፅ፣ የተደረገውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በጥብቅ በማውገዝ፣ ጉባኤው የ“ኦሮሚያ” ገዢ ሽመልስ አብዲሳ እና ጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው ዐብይ አሕመድ  ባስቸኳይ ከስልጣን ወርደው በዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀል በህግ መጠየቅ አለባቸው ብለን ወስነናል።

፪. “እኔም ፋኖ ነኝ” በሚለው መርሆ መሰረት ፋኖነንትን ማዕከል ያደረገ ሁለገብየትግል ስልት መቀየስና ለዐማራ ህዝብ ህልውና ከሚታገሉ ሃይሎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር አማራጭ የሌለው የትግል ስልት እንደሆነ ወስነናል። ይህንን የወሰንነው የዐማራውን የትግል አቅጣጫ የሚመራ፣ የተለያዩ የዐማራ ማህበራትን ያካተተ የፖለቲካ ማዕከል አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘብ ነው።

፫. በዐማራ ላይ ያነጣጠሩ ብዥታ ፈጣሪ የውጭ እና የውስጥ የሃሰት ትርክቶችን ለመናድና ትክክለኛውን የዐማራና የኢትዮጵያ ታሪክ መርምሮ የሚያሳውቅና የዛሬውን የነፃነት ትግል አቅጣጫ የሚያስይዝ ምሁራዊ የጥናት ቡድን አስፈላጊነትን ተገንዝበን ቡድኑ እንዲስማራ ወስነናል።

፬. በዐማራው ላይ በጦርነት፣ በፓለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ለሚደርሱበት ጉዳቶች አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ ለማሰባሰብ የተለያዩ የዐማራ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ግልጽ በሆነና ተጠያቂነት ባለው መንገድ እንዲሠሩ ወስነናል።

፭. የሰላማዊው ትግል ዘርፍ የፋኖን ትግል መንፈስና እሴቶች በሚያንጽባርቅ መልክ በዉጭ አገር የሚኖሩ ዐማሮችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በቆራጥነት ዐብይ አገዛዝ ተቋማት ላይ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አድማ በትብብር ይደረግበት ዘንድ ጉባኤው ጥሪ ያደርጋል።

፮. በዐማራው አጠቃላይ ትግል የተለያዩ ድርጅቶች በጋራ የትግል መርህ ዙሪያ እንዲሠሩ የሚያስተባብር አቅምና ሃይል ለመፍጠር የሚያበቃ አስተባባሪ ኮሚቴ አስፈላጊነትን ጉባኤው ተረድቶ ኮሚቴው እንዲቋቋም ወስኗል።

፯. ጉባኤው የዐማራውን የህልውና ትግል ቅድሚያ ከሚሰጡ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ጋር የትግል መደጋገፍን ወሳኝነት በመረዳት ለመተባበር ውሳኔ አድርጓል።

የዓለም አቀፍ የዐማራ ጉባኤ ቀጣይነት እንዲኖረው የመጀመሪያውን ጉባኤ ያዘጋጁትንና ሌሎችንም በማካተት በተከታታይ ጉባኤ እንዲጠሩ ስምምነት ላይ ደርሰናል። በጉባኤው የተነሱ የዐማራውን የህልውና ትግልና አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጉባኤው የተወያየበትን ዝርዝር ሰነድ ያወጣል።

ዐማራው በራሱና በአገሩ ጉዳዮች አድራጊ ፈጣሪ መሆኑን ያረጋግጣል!

ኢትዮጵያ ክብሯን ታስጠብቃለች!

የዓለም አቀፍ ጉባኤ

ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.