በህገመንግስቱም ቢሆን ወልቃይት ጠገዴና ራያ የአማራ እንጅ የትግራይ ሊሆኑ አይችሉም!!!

images 2 1መሰረት ተስፉ ([email protected])

 1. ሀወሐትና የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚዎች ወልቃይትና ራያ በህገመንግስቱ መሰረት የትግራይ አካላት ናቸው ሲሉ እንሰማለን።
 2. በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ሃሳብ በግልፅ ከማቅረቤ በፊት ግን ስለወልቃይት ጠገዴና ራያ ታሪካዊ ዳራ የተወሰነ ነገር ለማለት ወደድኩ::  እንደሚታወቀው ከ1984 ዓ.ም በፊት ወልቃይት ጠገዴofficially በጎንደር፤ ራያ ደግሞ በወሎ ስር የነበሩ ቦታዎች ናቸው።
 3. ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ህወሃት “ታላቋን ትግራይን” ለመመስረት በነበረው ህልም ምክንያትበአንድ በኩል ግዛት ለማስፋፋት ለም መሬቶችን የትግራይ አካል ለማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭው አለም ጋር ለመገናኘት የሚያስችለው ኮሪዶር ለማግኘት በማሰብ እዚህም እዛም ማማተሩ አልቀረም። ስለሆነም በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተለይ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ወልቃይት ጠገዴ መስፋፋት መጀመሩ ይታወቃል።
 4. በዚህ ረገድ ያለውን እውነታ ግልፅ ለማድረግ ያህል የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በትጥቅ ትግሉ ሂደት ረዘም ላለ ጌዜ አባላቱ በሚለብሷቸው ካኔትራዎችናበሚዘጋጁ አንዳንድ ፅሁፎች ላይይታተም የነበረው የትግራይ ካርታ ወልቃይት ጠገዴንና ራያን አይጨምርም ነበር። ህወሃት በግዛት መስፋፋቱ የፀና አቋም መውሰድ ከጀመረ በኋላ ግን እነዚህን ፅሁፎችና ካኔትራዎች ድራሻቸውን እንዳጠፋቸው ሁኔታውን የሚያውቁ የሚመሰክሩት ሃቅ ነው።
 5. የህወሃት የቀድሞ አመራሮች የነበሩት እነአቶ አብራሃም ያየህም ደርግ ሊወድቅ አከባቢ ባደረጉት ቃለመጠይቅ የህወሃትን የግዛት መስፋፋት እቅድ በዝርዝር ገልፀውት እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው።እነዚህ አመራሮች በወቅቱ ባደረጉት ቃለመጠይቅ  ህወሐት የትግራይ አካል ያልሆኑትን ወልቃይት ጠገዴንና ራያን፤ አልፎም እስከ አልውሃ ምላሽ ቆርጦ ወደ ትግራይ የማካለል ህልም እንደነበረው በግልፅ ማስረዳታቸውን የሚያሳይ ዩቱብ ፈልጎ ማዳመጥ ይቻላል። ይህ ተስፋፊ የሆነ ፍላጎት ትክክል እንዳልነበረ እነአቶ አብራሃም ያየህ አፅኖት ሰጥተው እንደገለፁት አስታውሳለሁ።
 6. 6. ኋላ ላይ ትጥቅ ትግሉ ተጠናክሮ ቀጠለና በአስራ ዘጠኝ ሰማንያ ሶስት ዓ.ም ደርግከስልጣን ሲወገድ ተጠናቀቀ። ከዚህ ጊዜጀምሮ ለሃያ ሰባት አመታት ሁሉም የሃገሪቱ እጣ ፋንታዎች የሚወሰኑት በህወሃት አመራሮች መሆኑ ላብዛኞቻችን ግልፅ ነው ብየ አምናለሁ። በነዚያ ሃያ ሰባት አመታት ውስጥ ህወሃቶች ግልፅ አመራር ሰጥተው ይቅርና ካፋቸው አንድ ቃል ቢወጣ እንኳ እንደፈጣሪ ቃል የሚከበርበት፣ ምጣድ አቀብሉን ቢሉ ሞግዱን ረሳችሁት የሚል መልስ የሚያገኙበት፣ ገርፈውም ሆነ ገድለው ራሳቸው የሚጮሁበት እንዲሁም ያሻቸውን ነገር ሁሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚችሉትን ሁሉ አድርገው በጊዜው ተሳክቶላቸው ነበር።
 7. በመሆኑም ደርግ ወድቆ ህወሐቶች በበላይነት ሃገሪቷን እንደተቆጣጠሩ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሲያልሙት የነበረውን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ተግባራዊ ካደረጓቸው እቅዶች አንዱና ዋነኛው ወልቃይት ጠገዴንና ራያን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ officially ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ማድረግ ነበር። ማካለሉን ተግባራዊ ባደረጉ ማግስት ደግሞ ከተዋጊዎቻቸው የተቀነሱ (በወቅቱ አጠራር demobilized የተደረጉ) አባሎቻቸውንና ሌሎች አከባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ተጋሩዎችን ማስፈራቸው ይታወቃል።
 8. ህወሃቶች ይህን ለማድረግ ያስቻላቸው በወቅቱ የነበራቸው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጡንቻ እንጅ ህጋዊ መንገድ አልነበረም። የ1984 አ.ም ቻርተርና በተለይ ደግሞ ዃላ ላይ የፀደቀው ህገመንግስት “ክልሎች የሚዋቀሩት በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍላጎት ነው” ይላሉ እንጅ የሄ አከባቢ አማራ ነው፣ ያኛው ደግሞ ትግራይ ነው የሚል ድንጋጌ አላስቀመጡም።
 9. የወልቃይት ጠገዴም ሆን የራያ ነዋሪዎች ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ ስነልቦናዊ ውቅራችን፣ ጂኦግራፊያዊ አሰፋፈራችንና ማንነታችን የሚተሳሰረው ከአማራ ክልል ጋር በመሆኑ መካለል ያለብን ወደ አማራ ክልል እንጅ ወደ ትግራይ ክልል አይደለም ብለው በፅናት እየተቃወሙ ነው ወደ ትግራይ እንዲካለሉ የተደረጉት።
 10. ህወሃቶች ወልቃይት ጠገዴንና ራያን ከላይ በተገለፀው ኢ-ፍትሃዊ መንገድ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ካደረጉና የነዋሪዎቹን ማንነት ከነጠቁበት ጊዜ አንስተው ተቃውሞ ማቅረብ የጀመሩት  የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በሌሎች አከባቢዎች የሚኖሩ አማራዎችና ኢትዮጵያውያንም ነበሩ።
 11. ህወሃቶች ወልቃይትንና ራያን በሃይል ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ማድረጋቸው ሳያንስ ጭራሽ የቦታዎቹ ባለቤት የነበሩት አማራዎች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ወጋቸውንና ልምዳቸውን እንዳይጠቀሙና እንዳያከብሩ መከልከል ጀመሩ። ለምሳሌ የየአከባቢዎቹ አማራ የሆኑ ነዋሪዎች አማርኛ ዘፈኖችን እንዳያዳምጡ፣ የአማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦችን እንዳይደግፉ፣  የነሱንም ማሊያዎች እንዳይለብሱ፣ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ቀለማት ያሉበትን ሰንደቅ አላማ እንዳይጠቀሙ ሲከለከሉ እንደነበር በተለያዩ ጊዚያት ምርር ብለው ገልፀዋል፤ አሁንም ሲገልፁ ይደመጣሉ። ይህ ለምን ይሆናል ብለው የጠየቁ አማራዎችም ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተሳድደዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል።
 12. በዚህ መልክ ግፍና ሰቆቃ በአጠቃላይም ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ተግባር የተፈፀመባቸው አማራ የሆኑ የሁለቱም አከባቢ ነዋሪዎች ተሰባስበው የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በማቋቋም አደረጃጀቶቻቸውን አጠናክረው መብቶቻቸውንና ፍትህን ለማስከበር ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም። ኮሚቴዎቹ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ለህዝብ በማሳወቅ ህጋዊ ጥረት ማድረግ ቢጀምሩም በህወሃት ሳንባ ሲተነፍሱ የነበሩት ሁሉም የመንግስት ተቋማት ግን ፍትሃዊ የሆነ ምላሽ ሊሰጧቸው አልቻሉም። እንዲያውም ማንነታቸውን ለማስመለስ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለማጥፋት ህወሃት ገዳይ ቡድን ወደ ጎንደር መላኩ ይታወቃል።  ይሁን እንጅ በጎንደር ህዝብና በራሳቸው  በነኮሎኔል ደመቀ ጀግንነት የህወሐት የአፈና ሙከራ እንደከሸፈ በታሪክ የተመዘገበና ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሃቅ ሆኖ አልፏል። በነገራችን ላይ እነኮሎኔል ደመቀ ከጎንደር ህዝብ ጋር ሆነው የህወሐትን ጠለፋ ያከሸፉባት ሃምሌ አምስት ዃላ ላይም ህወሐትን ለመጣል እርሾ ሆና እንዳገለገለች እገረመንገዴን ለማስታወስ እወዳለሁ።
 13. ከዚህ ጎን ለጎንም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎችና በውጭም የሚኖሩ አማራዎች የወልቃይት ጠገዴንና የራያን ህዝብ የማንነት ማስመለስ ጥያቄዎች ፍትሃዊነት እውቅና ሰጥተው ከጎናቸው በመሰለፍ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ድምፃቸውን ማሰማት ብቻ ሳይሆን በያሉበት የድጋፍ ኮሚቴዎችን በማቋቋም በሃሳብ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ለማጠናከር ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል። በተለይ ብአዴን ውስጥ የነበርን በርከት ያልን ታጋዮች ደግሞ ወልቃይትና ራያ ወደ ትግራይ ከተካለሉበት ኢ-ፍትሃዊነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ጋር እያያያዝን የህወሃትን ተስፋፊነት በመግለፅ በመድረክም ሆነ ከመድረክ ውጭ ፊት ለፊት ለመታገል ሞክረናል።
 14. በአስመላሽ ኮሚቴዎቹ በተለይና እነሱንም በሚደግፏቸው ሌሎች አማራዎችና ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ሲነሱ የነበሩ የማንነት ማስመለስ ጥያቄዎች ፍትሃዊ ምላሽ ሳያገኙ ለውጥ የሚባለው ነገር መጥቶ ህወሃቶች መቀሌ ሄደው ተወሸቁ። በዚህ ጊዜ የኮሚቴዎቹና የነዋሪዎቹ  ጥያቄዎች እየጎሉ እንደመጡ የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋቸዋል። መንግስትም ጥያቄዎቹን በሚገባ አይቶ አግባብነት ያለው መልስ እንደሚሰጥ ቃል እንደገባ የዜና ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
 15. ህዝቡ በአስመላሽ ኮሞቴዎቹ እየተመራ የመንግስትን ህጋዊና ፍትሃዊ  የሆነ መልስ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት ህወሃቶች ሰሜን እዝን ከጀርባው ወግተው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ሚዛን በማዛባት ኢትዮጵያን ለነሱዳን ወረራ ያጋለጠ እጅግ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት በመፈፀም የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ ጥለው አልፈዋል። በዚህ ብቻ ግን አላበቁም። በወልቃይት ጠገዴና ራያ የፈፀሙት የማንነት ዘረፋ ሳይበቃቸው ይባስ ብለው ሌላ ተጨማሪ ዘረፋ ለማካሄድ በአማራ ይዞታዎች ላይም ጥቃት ሰነዘሩ።
 16. 16. ደግነቱ ከህወሃት ስግብግብ ባህሪና ከፍተኛ የሆነ የጦርነት ዝግጅት በመነሳት ጥቃት ይፈፀምብኛል ብሎ ሲያስብ የነበረው የአማራ ህዝባዊ ሃይል በየአከባቢው በተጠንቀቅ ቆሞ ክልሉን ይጠብቅ ስለነበረ ልክ ጥቃቱ እንደተፈፀመ ወዲያዉኑ በመሰባሰብ መከላከል ካደረገ በኋላ  ከመከላከያና ከልዩ ሃይል ጋር ተባብሮ መልሶ በማጥቃት የህወሃትን የወረራ ሙከራ ማክሸፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
 17. 17. የአማራን ህዝባዊና ልዩ ሃይል እንዲሁም የመከላከያን መልሶ ማጥቃት መቋቋም ያልቻለው የህወሃት ዘራፊ ቡድን ነጥቋቸው የነበሩትን የወልቃይት ጠገዴንና የራያን አከባቢዎች ብዙም ሳይቆይ ጥሏቸው እግሩ ወዳመራው አቅጣጫ የሸሸ መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዚህ ጊዜ የማንነት ዘረፋ የተፈፀመባቸው የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ማንነታቸውን መልሰው በእጃቸው ለማስገባት ቻሉ። ነዋሪዎቹ ማንነታቸውንና መኖሪያወቻቸውን መልሰው በይዞታቸው ስር ካስገቡ በኋላ (after having restored their residence and identity) ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይህንኑ  በሆታና በጭፈራ በአደባባይ አበሰሩ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በራሳቸው ተነሳሽነት ማንነታቸውን ያወጁት የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች “ከትግራይ እንዲኖረን የምንፈልገው መልካም ጉርብትና እንጅ የትኛውንም አይነት አስተዳደር አይደለም” በማለት ፍላጎታቸውን በአደባባይ እየገለፁና እያሳወቁ ይገኛሉ። ይህን የህዝቦች የማንነት ፍላጎት መሰረት በማድረግም የአማራ ክልል ህዝባዊ ሃይልና የክልሉ መንግስት የሚችለውን ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።
 18. 18. ነገር ግን ህወሓት ለሁለተኛ ግዜ ወረራ ፈፅሞ በተባበረ ክንድ ተመትቶ ወደ መቀሌ በመመለስ ላይ እያለ የፌደራል መንግስቱ ጦርነቱ እንዲቆም ትዕዛዝ በመስጠቱ ምክንያት ወልቃይት እንጅ ራያ አሁንም በህወሃት ቁጥጥር ስር ይገኛል። የፌደራል መንግስቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “ህገመንግስት በማስከበር” ስም እንደሆነ ለመገመት የሚከብድ አይመስለኝም። የፌደራል መንግስቱ ህወሓት ኮሪደር አግኝቶ ከውጭ መንግስታት ጋር በመገናኘት ለስልጣኔ ያሰጋኛል ብሎ ባያስብ ኖሮ ወልቃይትን አሁንም “ህገመንግስት በማስከበር ስም” አሳልፎ ይሰጥ እንዳልነበረ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
 19. 19. ከዚህ በላይ ከተገለፀው ነጥብ ጋር በተያያዘ በተለይ የመንግስት ደጋፊ ነን የሚሉ አማራዎች ጠቅላይ ሚ/ሩ እንደየመድረኩ ባህሪና ሁኔታ የሚቀያየረውን ሃሳቡን እየሰሙ እንኳ  “እሱ ወልቃይት የአማራ ነው የሚል አቋም አለው፤ ችግሩ ያለው በክልሉ መንግስትና በአስመላሽ ኮሚቴው ነው” እያሉ ሲዘባርቁ ስሰማ የአማራ ፖለቲካ ራሱን እየበላ እንዳለ ይሰማኝ ጀምሯል።
 20. 20. ወጣም ወረደ ግን ወልቃይትና ራያ በህገመንግስቱም ቢሆን የአማራ እንጅ የትግራይ አካል ሊሆኑ ፈፅሞ አይችሉም። ምክንያቱም ከላይ በተራ ቁጥር 7 እና 8 ላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ወልቃይትና ራያ ከመጀመሪያውም ወደ ትግራይ የተካለሉት ህገመንግስቱ የሚያስቀምጠውን  የህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍላጎት መስፈርቶች በመጨፍለቅ እንደሆነ በግልፅ ስለሚታወቅ ነው።
 21. 21. በዚህ አግባብ ሲታይ የህወሓት ሰዎች ወልቃይትና ራያ ላይ ያደረጉት የመሬት ማካለል ከመሰረቱም ቢሆን ፉርሽ (void ab initio) መሆኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። በመሆኑም ፈረንጆቹ Restitution እንደሚሉት የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ማንነታቸውንና መኖሪያዎቻቸውን ካስመለሱ በኋላ በሙሉ ፍላጎታቸው ተነሳስተው ወደመረጡት የአማራ ክልል መጠቃለልተፈጥሯዊ መብታቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የሚቀረው ይህን ያፈጠጠ እውነታ ህጋዊ እውቃና እንዲኖረው ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ርብርብና ተሳትፎ ወሳኝ ነው እላለሁ።
 22. 22. ይህ በመሆኑ ምክንያት ማንነቴ ተገ’ፏል የሚል ሌላ አካል ካለ ደግሞ ጥያቄውን በህጋዊ መንገድ አቅርቦ መፍትሄ ከመፈለግ የሚያግደው አንዳችም ገደብ አይኖርም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ!

ቸር እንሰንብት!!!

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.