ለአማራ ወያኔዎች የመጀመሪያና የመጨረሻ መልእክት

 ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)

“መልእክት” ያልኩት አቀራረቤን ቀለል በማድረግ የአንባቢያንን ቀልብ ላለመግፈፍ ነው፡፡ እንጂ መነሻየ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው፡፡ ማስጠንቀቂያም ይባል መልእክት ዋናው ጉዳይ በግሌ የተሰማኝንና የማምንበትን ለወገኖቼ ድኅነት ስልም የምጽፈው ነገር ለባለአድራሻዎቹ መድረሱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ድረገጾች ትብብር በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እባካችሁን ለሁሉም ካድሬ መልእክቴን አድርሱልኝ፡፡

ሰው ክርስቶስን መሆን እንዳይችል ጠላት መንገድ እየዘጋበት መቸገሩ የሚታወቅ ነው፡፡ መሆን  ቢፈልግ ግን ይችላል፤ የሚከለክለው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ክርስቶስ ራሱም ያለው “እንደኔ ሁኑ፤ እኔን ምሰሉ” ነው፡፡ ችግሩ ክርስቶስን ለመሆን ወይም ቢያንስ ለመምሰል የእምነት ጽናትና እውነተኛ ፍቅርን የተላበሰ ስብዕና ማጣት ነው፡፡ ተራራን ሊያዞር የሚችል እምነት፣ የሚጠላንን ብቻም ሳይሆን የሚገድለንንም ጭምር  የሚያፈቅርና ለጨካኞች የሚራራ ልብ፣ የማይወላውል እምነትንና የማያዳላ ፍቅርን የሚገልጥ በጎ ሥራ ካለ ከፈጣሪና ከአንድያ ልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ውህደት መፍጠርና ጓደኛ መሆን የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ የሚጠይቀው እውነተኛ የልብ መሰበርን ብቻ ነው፡፡

ክርስቶሳዊ ተምሳሌትነትን በተወሰነ ደረጃ በመውሰድ አካሄድን ማረቅና ማስተካከል ይቻላል፡፡ ከወቅቱ አቢይ ሃይማኖታዊ ክንውን እንጀምር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከፆመ በኋላ በሰይጣን ሦስት ጥያቄዎች ቀርበውለት በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስኪ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ”፡፡ የክርስቶስም መልስ “ ‹ሰው የሚኖረው እግዚአብሔር በሚናገረው ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም› ተብሎ ተጽፏል፡፡” አዎ፣ ለአስተዋይ ሰው በእንጀራ ብቻ መኖር እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሰይጣን በሚያስፈልገን ነገር ይመጣብናል፡፡ ሰይጣንና የስለላ ድርጅቶች ተመሳሳይነት አላቸው፤ በምትወደው ነገር ይመጡብህና ወጥመዳቸው ውስጥ ይከቱሃል(cf. blackmailing)፡፡ ክርስቶስንም በዚያ ቀዳዳ የመጣበት አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ካለምንም ምግብ በመክረሙ ተርቦ ነበርና ይሸነፍልኛል ብሎ ነው፡፡ እንዳሰበው ግን አልሆነለትም፡፡ ያ ምናልባት ሥነ መለኮታዊ ጣጣ ስላለው ለምድራዊ ሕይወት ጥሩ አብነት ላይሆን ይችላል፡፡ እናም የአርባ ቀኑን የክርስቶስ ፆም እንርሳውና አብዛኛው የአሁኑ ዘመን ሰው አንድ የምግብ ሰዓት አልፎበት አይደለም ትንሽ ሆዱ ጎደል ካለ እናቱን ከመሸጥ እንደማይመለስ እናስብ፡፡ አሰብን?…

ፈተናዎች በጥቅሉ የሥጋና የነፍስ ተብለው በሁለት ዐቢይ ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በአማርኛ ፈተናን የሚገልጡ ቃላት ውሱን ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ እንግሊዝኛው ሳይሻል አይቀርም፡፡ “test, quiz, exam, examination, temptation, assessment …” የሚባሉ ቃላት አሏቸው፡፡ እነዚህ ቃላት በዐውድ ውስጥ መገኘት ሳያስፈልጋቸው በቁማቸው የሚሰጡት የተወሰነ ምስል አለ፡፡ እኔ አሁን እዚህ ላይ ልጠቅሰው የምፈልገው የፈተና ዓይነት በእንግሊዝኛው አጠራር temptation የሚለውን ነው፡፡ የአባታችን ሆይ ጸሎት ውስጥ “ Our Father who art in heaven … lead us not into temptation but deliver us from evil.” እንደሚል፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳንወጣ የክርስቶስን ደቀ መዝሙርና የግምጃ ቤት ኃላፊ የአስቆሮቱ ይሁዳን እናስታውስ፡፡ ከገቢ ገንዘቦች አሥር መቶኛውን ለራሱ እንዲያደርግ ተፈቅዶለት የነበረው ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር ክፉኛ የተለከፈ ነበር – ልክ እንደወያኔ፡፡ ይህ በሽታው ተባብሶበት በመጨረሻው ክርስቶስን ራሱን በሠላሣ አላድ ለጠላቶቹ አሳልፎ ሸጦታል፡፡ ገንዘቡን ግን አልተጠቀመበትም፡፡ ያልተጠቀመበትም ምክንያት ክፍያውን እንደተቀበለና ክርስቶስን ያሳድዱት በነበሩ አይሁዳውያን እንዳስያዘው የሰረፀበት ሰይጣን ለጸጸት አጋልጦት በመለየቱ ምክንያት ራሱን ሰቅሎ ስለሞተ ነው፡፡ የይሁዳ ነፍስ አልተማረችም፡፡ ይህን እውነት ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኘዋለን – ሊማር አለመቻሉንም ጭምር፡፡

ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ወደፈተና ይገባል፡፡ ለሆዱና ስለሆዱ በሆዱ የሚፈተን አለ፤ በሆድ መፈተን መጥፎ ፈተና ነው፡፡ ሀገርን የሚያሸጥ የሆድ ፍቅር የተጠናወተው ሰው ደግሞ በሕይወት ዘመኑ በሚኖረው የስብዕና መመሰቃቀል ብቻም ሣይሆን ልጆችን ወልዶ ቢያልፍ በሀፍረት አንገታቸውን ይደፋሉ፤ በሕዝብ ዘንድም መጠቋቆሚያ ይሆናሉ፡፡ታሪኩ የጠቆረና የትውልድ ማፈሪያ ይሆናል – አሁንም እንደወያኔ፡፡

አንድ ሰው ፈተናን ወደቀ የምንለው ነባር እምነቱንና ታማኝነቱን ለሆነ ጥቅም ሲል ክዶ ከትክክለኛው መንገድ ሲወጣ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ታሪክ ስንመለከት ሁለት በፈተና የወደቁ አካላትን እናገኛለን፡፡

ዋናው ተፈታኝና ፈተናውን ከመነሻው የወደቀው ከትግሬው ብሔር የወጣውና ሕወሃት በመባል የሚታወቀው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሕዝብ ኃይል ነው፡፡ ለዚህ ድርጅት በፈተና መውደቅ መንስኤው ዓላማና ለጥቅም ነው፡፡ የሚታወቅን ነገር መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡

ሁለተኞቹ ተፈታኞች ሁሉን ነገር እያወቁ ለፍርፋሪ እንጀራና ለማያዙበት የይስሙላ ሥልጣን ሲሉ በሕወሃት ሥር በባርነት አድረው የወጡበትን ሕዝብ ለወያኔ የሸጡ ይሁዳ አማሮች – ብአዴን ተብዬዎቹ – ናቸው፡፡ በሃይማኖታዊ አገላለጽ ሕወሃትን ልምጭ አስይዘውና በሁለንተናዊ ዘመናዊ መረጃ ደግፈው ጃዝ ብለው የላኩት የታላቁ ወንድም (The Big Brother) ባለሟሎችን የሉሲፈር ደቀ መዛሙርት ልንላቸው እንችላለን፡፡ ታሪካዊ ቂም በቀል አርግዘው ኢትዮጵያን ለማጥፋትና በእግረ መንገድም ቤት ያፈራውን ሥልጣንና ሀብት በግል ለመቆጣጠር የተነሡ የትግሬ ወያኔዎችን  በሉሲፈር አጣማጅ በሰይጣን በራሱ ልንመስላቸው እንችላለን፡፡ ለሆዳቸው ያደሩ በተለይም የዕልቂት ዐዋጅ ከታወጀበት የአማራው ሕዝብ እንደተገኙ የሚነገርላቸው ከሃዲዎችን ደግሞ በሰይጣን አገልጋይነት ልንፈርጃቸው እንችላለን፡፡ የሆነው ሆኖ ትግሬም ይሁን አማራ ወይም ሌላ ከእውነተኛው የጤናማ ኅሊና መንገድ ወጥተው ኢትዮጵያን ለማውደም እስከተሰለፉ ድረስ ሁሉም የጥፋት ወኪሎችና የክፉ መንፈስ ምርኮኞች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አጥፊ ኃይል ደግሞ የዓለም አቀፉ የጥፋት ኃይል ቅርንጫፍ ነው፡፡ ይህ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሸር ጥልፍልፍ ወይም ሤራ (Conspiracy) የሚካሄድ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ዕቅድ ጅማሮው ቀደም ቢልም በሁሉም አቅጣጫ በተቀነባበረ ዘመቻ ወደስኬት ጫፍ የደረሱ የመሰሉት ግና አሁን በምንገኝበት የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው – የመሠረት ግንባታው ደርዝ መያዝ የጀመረው ግን የዛሬ 300 ዓመታት አካባቢ በ18ኛው መ/ክ/ዘመን መግቢያ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሚያሠማሯቸው ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪዎች ዘርና ቀለም፣ ፆታና ሃይማኖት ሳይገድባቸው እንደ እስስት ከየሚሄዱበት አካባቢ ሕዝብ ጋር እየተመሳሰሉ ሀገርንና ሕዝብን በቅርበት ይቆጣጠራሉ – ሲያሻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያሻቸው ደግሞ ሽጉጥ በመያዝ በመስቀል ከቀላጤ ‘politico-psuedo-religious’ ዘመቻ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስና የባሕርይ አባታቸውን ሊቀ ትጉሃን ዲያብሎስን ለማስደሰት ይጥራሉ፡፡ በመንግሥታት ጀርባ ሥውር መንግሥታትን በማቋቋም ሁሉንም ነገር በዐይነ ቁራኛ ይከታተላሉ – ሊያውም በ“ሁሉን ተመልካች” አንዲት ዐይናቸው! በዓለም አቀፍ ግዙፍ ካምፓኒዎቻቸው አማካይነትም የዓለምን ሀብትና ንብረት ይዘርፋሉ፤ ነዳጅና የተፈጥሮ ማዕድናትን እያሰሱ ለማይጠረቁት ሥውር ቱጃሮቻቸውና የምሥጢራውያን ድርጅቶቻቸው አለቆች ያስረክባሉ – ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው፤ ጦሩም ስለላውም አስተዳደሩም ምኑም ምናምኑም በነሱው ቁጥጥር ስለሚገኝ የ‹ሪሶርስ›ና የሰው ኃይል ችግር የለባቸውም፡፡ ጦርነቶችን ይፈጥራሉ፤ ሲፈልጉ ያጣላሉ – ሳይፈልጉ ያስታርቃሉ፡፡ መሣሪያዎቻቸውን ለተዋጊ ወገኖች በግልጥና በድብቅ ይሸጣሉ፡፡ ትውልድን ከሃይማኖትና ከባህል አውጥተው መና ለማስቀረት፣ ከሞራልና ሥነ ምግባር ማዕቀፎች ለይተው ባዶ ለማስቀረት እነሆሊውድን ከመሳሰሉ ተቋሞቻቸው ባፎሜታዊ ፊልሞችንና ሙዚቃዎችን በዓለም ይበትናሉ፡፡ ሀሺሺንና መጠጦችን በማምረት በሥውር ያሰራጫሉ፡፡ የሚገርመው እነዚህ ኃይሎች ፀረ-ሀሽሽ መስለው ቢቀርቡም ውሸታቸውን ነው፤ ከአፍጋስታን እስከ ኮሎምቢያና ሜክሲኮ የዐደንዛዥ ዕፅ ምርትና ገበያን የተቆጣጠሩት እነሱው መሆናቸውን የሚገልጡ መረጃዎች የአደባባይ ምሥጢር ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡ ወያኔም እንደዚሁ ወጣቱን በጫትና በመጠጥ እያደነዘዘ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር መጣሩን አንርሳ፡፡ በብዙ ነገር መመሳሰላቸውን ልብ እንበል፡፡ ወያኔን የሚገዛ ህግ እንደሌለ ሁሉ እነሱንም የሚገዛ ህግ የለም፡፡ የነሱን ደንቆሮ በሀሰት የዶክትሬት ዲግሪ የምስክር ወረቀት ለዓለም አቀፍ ተልእኮ ቢያሰማሩት ታማኝነቱ እንጂ ትምህርቱ ብዙም ፋይዳ ስለሌለው በአጭበርባሪነት የሚጠይቀው የለም – በወያኔ ቤትም ለባለሥልጣን ያልተበተነ የዲግሪ ዓይነት የለም – ባዶ ጭንቅላት ላይ ጥቁር ቆብና ጥቁር ካባ፡፡ ከነሱ ቁጥጥር የሚወጣን ሀገር መሪ(ዎች) በስለላ ድርጅቶቻቸው ልዩ ኮማንዶና በጨረር አነጣጥሮ ተኳሽ የፓራትሩፐር እስኳድ ያስወግዳሉ – ለሀገሩ የሚቆምን ሀገር ወዳድ ግለሰብም በዚህ መልክ ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር ያደርጋሉ (ነፍስ ይማር – ኢቅእ(?))፡፡ (ቅን ታዛዦቻቸው ሊያፈነግጡ ወይም ጌታ ሊለውጡ ካሰቡም ይሄው የቅጣት በትር አይቀርላቸውም (ነፍስ ይማር – መዜአ (?))፡፡ … በሚያስወግዷቸው ምትክም የነሱን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር መለስ ዜናዊን የመሰለ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሀገር ወሮበላ በዴሞክራሲ ጭምብላቸው ለላንቲካው ይጎልቱታል – ዋናውን መዘውር በእጅ አዙር የሚይዙት ግን እነሱው ናቸው፡፡ በዓለም ባንክና በአይ ኤም ኤፍ፣ በኔቶና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አማካይነትም በማይወዱት ሀገር ላይ የኢኮኖሚና ወታደራዊ ማዕቀብ ይጥላሉ፤ እንዳስፈላጊነቱም ጦርነት ያውጃሉ፡፡ ከነሱ ዕይታና ቁጥጥር ውጪ የሚሆን አንዳችም ነገር የለም፡፡ ነፍስና ሥጋህን ብቻ ሳይሆን የምታስበውንም ሁሉ ጭምር በ“Mind Control system”  ሊቆጣጠሩ ይሞክራሉ፡፡ ከፈለጉም በሰው ሠራሽ የመሬት መናወጥና ሱናሚ አንድን ሀገር ሊያደባዩ፣ አለዚያም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መራጃ ዝናብን ከልክለው በድርቅ ሊመቱ፣ በሌላም በኩል ከመጠን በላይ ዝናብን አዝንበው በጎርፍና በመሬት መንሸራተት ናዳ ሕዝብንና መንግሥታትን ሊያስለቅሱ ይችላሉ፡፡ በአጭሩ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ደግሞም እውነት ነው፡፡ ወያኔዎችስ? ሥልቱና አፈጻጸሙ ይለያይ እንጂ አንድና አንድ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካ (ተመስገን ደሳለኝ)

የወያኔዎች የአንድ ለአምስት የጥርነፋ ሥልት የዚሁ የዓለም አቀፍ ዘመቻ አካል ነው፡፡ በአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ዕዳ ውስጥ የሚዶሉህም በዐይናቸው ሥር አውለው ሊቆጣጠሩህ ነው፡፡ በብድር የተያዘ ሰው ደግሞ ታውቃለህ – ውልፊት ሊል አይችልም፡፡ ሌላ ነገር አምሮህ ብታንጋጥጥ- ማንጋጠጥም አይደለም ለማሰብም ብታስብ ራሱ ያስወነጅልሃል፡፡ ያኔ በአሸባሪነት ባትጠየቅ እንኳን በገንዘብ ዕዳ ያለህን ንብረት ያሸጡሃል ወይም የፍትሃ ብሄር ወንጀልህ ተቀባብቶ ወደ ተሟላ ደረቅ ወንጀል ይዞርብህና ቃሊቲ ልትወርድ ትችላለህ፤ ለማንኛውም እሥር ቤት ውስጥ ነህ – የእሥር ቤቱ ስፋትና ጥበት ላይ የጋራ መግባባት ላይ እስከደረስን ድረስ፡፡ በቤትህ ውስጥ ሳይቀር ከአንተ ዕውቀት ውጪ ተከታታይ ሊመደብብህና መላ እስትንፋስህ ወደ ማዕከላዊ መረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤት ሊያመራ ይችላል፤ ስልክህ ሊጠለፍ፣ ኢሜልህ ሊጠለፍ፣ ፌስቡክህ ሊጠለፍ፣ ሚስትህ ልትጠለፍ፣ ልጆችህና ጓደኞችህ ጭምር ሊጠለፉ፣ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ አንተ ራስህም ልትጠለፍና የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ብዙ ሰይጣናዊ ነገሮች ሊደርሱብህ ይችላሉ፡፡ የእነአልማዝ ሠይፉን፣ የእነብርቱካን ሚዴቅሳን፣ የእነደበበ እሸቱን፣ የነስዬ አብርሃን ዝምታ ያዬ አንዳች ነገር ቢጠረጥር ሊፈረድበት አይገባም፡፡ በስማም የተባለበት ሰይጣን ይመስል በአርምሞ የተቀመጡበትን ምክንያት ከነሱ በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ አሣሪህና የስቃይህ ምንጭ ሲደርቅ ጮቤ መርገጡ ዲያብሎሳዊ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ለሰባት ቀን ሀዘን መቀመጡና በፈጣሪ ሥራ ገብቶ በ“ለምን ወሰድክብኝ” እዬዬ ማለቱ ሃይማኖታዊ መደላድል ያለው አይመስለኝም – የቃል መቀነት መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውም ይህን ዕንቆቅልሽ በአመስጥሮ ለመጠቆም ነው (አመስጥሮው እዚህ ላይ አበቃ እንጂ)፡፡ ለማንኛውም በዲያብሎስ ግዛት መብቴ ተረገጠ ሰው መሆኔ ተዘነጋ ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ነው፡፡ ከሁሉ በባሰ ሁኔታ የጎንህ ፍላጭ ሚስትህ ወይም የአብራክህ ክፋይ ልጅህ ሊሰልሉህ ቢችሉ የዘመኑ የትልቁ ወንድምህ ፋሽን ነውና አይግረምህ፡፡ ወያኔ የትልቁ ዓለም አቀፍ ዘመቻ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤት (Head Quarter) ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ከጆርጅ ኦርዌል ድንቅ መጽሐፍ (ከ “1984” ውስጥ) እስኪ ቀጣዩን ጥቅስ እንመልከት፡፡

 

He [Winston Smith] took a twenty-five cent piece out of his pocket. There, too, in tiny clear lettering, the same slogans were inscribed, and on the other face of the coin the head of Big Brother. Even from the coin the eyes pursued you. On coins, on stamps, on the covers of books, on banners, on posters, and on the wrappings of a cigarette packet—everywhere. Always the eyes watching you and the voice enveloping you. Asleep or awake, working or eating, indoors or out of doors, in the bath or in bed—no escape. Nothing was your own except the few cubic centimetres inside your skull.

 

ተዛማጅ ትርጉም፡- (ዊንስተን ስሚዝ) ሃያ አምስት ሳንቲም ከኪሱ አወጣ፡፡ በዚያች ሣንቲም ላይም በአንደኛው ገጽ በጥቃቅን ፊደላት የተለመደው መፈክር ተጽፏል፤ በሌላኛው ገጽ ላይ ደግሞ የታላቁ ወንድም የራስ ምስል ጉብ ብሏል፡፡ [(መፈክሩ – ‹ ጦርነት ሰላም ነው፤ ነጻነት ባርነት ነው፤ ድንቁርና ጥንካሬ ነው፡፡› የሚል ነው1፡፡)] ከዚህች ትንሽዬ ሣንቲም የምታየው የታላቁ ወንድም ዐይኖች ትክ ብለው ሲያዩህ መግቢያ ያሳጡሃል፡፡ በሣንቲሞች፣ በቴምብሮች፣ በመጽሐፍ ሽፋኖች፣ በዓርማዎች፣ በፖስተሮች፣ በሲጋራ ወረቀቶች፣ የትም ይሁን የትም እነዚህ የታላቁ ወንድም ዐይኖች ያፈጡብሃል፡፡ ምን ጊዜም ዐይኖቹ መግቢያ መውጫህን ይከታተላሉ፤ ድምፆቹም የጆሮ ታምቡርህን ያለ ዕረፍት ይጠልዛሉ፡፡ ተኝተህም ሆነ ሳትተኛ፣ ሥራ ላይም ሆንክ ምግብ ላይ፣ ከቤት ውስጥም ሆንክ ከቤት ውጪ፣ መታጠቢያ ቤትም ውስጥ ሁን በአልጋህ ላይ … የትም ሁን የት ከታላቁ ወንድም ዐይኖችና የዘወትር ክትትል ማምለጫ የለህም፡፡ ጭንቅላትህ ውስጥ ከሚገኘው ነጭ አንጎል ውጪ የኔ ነው የምትለው የግል ንብረት እንዲኖርህ አይፈቀድልህም፡፡ [እርሱንም ቢሆን አንተ አታዝበትም!]

 

በዲያብሎስ መንፈስ የሚነዳውን የአፍራሽ ኃይል (The Negative Energy) ዓለማቀፋዊ የጥፋት አድማስ በአጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት የሀገራችን ጉዳይም ከዚሁ ኃይል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ከዘመን ፍርድ ማምለጥ አስቸጋሪ ነውና፡፡ ዓለማችን የሁለት ተፃራሪ ኃይላት መስተጋብራዊ ውጤት ናት፤ እነሱም ገምቢ ወይም አወንታዊ ኃይልና አፍራሽ ወይም አጥፊ ኃይል ናቸው፡፡ ማንም ሰው ከነዚህ ሁለት እርስ በርስ ተጠፋፊ ነባራዊ ሁኔታዎች ውጪ አይደለም፡፡ በምንገኝበት መሬታዊ/ምድራዊ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት አንዱ ካለ ሌላው አይኖሩም፡፡ ገምቢ ካለ አፍራሽ አለ፡፡ በዬቋንቋዎቻችንም ደግ – ክፉ፣ ፍቅር – ጥላቻ፣ ቸር – ንፉግ፣ ሃቀኛ – ዋሾ፣ ወዘተ. የመኖራቸው እውነታ ይህንን ለማጠየቅ ይመስላል፡፡ ችግሩ ምጣኔያቸው ላይ የሚታየው የሚዛን መዛነፍ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ግዘፍ ነስቶ ከታዬ ለምሳሌ የክፋት መንፈስ ከተንሠራፋ ሀገርና ሕዝብ ይጎዳሉ፤ እንደሀገረ ኢትዮጵያ ለአጠቃላይ ውድመት ሊዳረጉም ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነት አስቀያሚ ሁኔታ የሚፈጠረው ኅሊናን በመሸጥ ለሆድና ለጥቅም ማደር ሲከሰት ነው፡፡ ሰዎች ኑሯቸውን ያሸነፉና ያለፈላቸው እየመሰላቸው ብዙ ጣጣ ውስጥ ይገባሉ፤ በዚያም ሳቢያ ከፍለው የማይጨርሱት ዕዳ ውስጥ ይነከራሉ፡፡ የብአዴኖች ወንድምና እህቶቻችን ዕኩይ ተግባርም ከዚህ የሚመደብ ነው – በደቂቃዎች ውስጥ ዕዳሪና ሽንት ለሚሆን የሆድ ቀለብ (እህልና ውኃ)  ሀገርንና ሕዝብን የመሰሉ ዘላለማውያን ኅላዌያት ሲክዱ ማየት የታሪክ አሰቃቂ ፍርድና ምፀት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጅብ ቲበላህ... በልተኸው ተቀደስ - ከጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ (የቀድሞው ጦቢያ መጽሄት አምደኛ)  

ሕወሃት ኢትዮጵያን እያጠፋ ያለው ለዓላማና ለጥቅም ነው፡፡ የሕወሃት ተባባሪዎች የሆኑት ብአዴንና ሌሎቹ ኢትዮጵያን በማጥፋት ላይ ከሚገኘው ሕወሃት ጋር እየተባበሩ ያሉት ወገኖች ግን ለዓላማ ሣይሆን አንድም በድንቁርና ነው፤ አንድም በሆዳምነት ነው፡፡ አማራ አማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ዓላማ ነድፎ ከፀረ-አማራ ኃይሎች ጋር በማበር ሊንቀሳቀስ ይችላል ተብሎ መቼም አይጠበቅም፤ በውነቱ የብአዴኖችን ነገር ስናጤነው የእርግማን ካልሆነ የሌላ አይመስልም፤ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አማራ ካልታመመ በስተቀር ዘመዶቹን ለመፍጀት በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ሳይቀር በመታገያ ዓላማና ግብነት ቀርፆ የሚንቀሳቀስን ሰይጣናዊ ኃይል ሊተባበር አይችልምና ነው፤ በምንም ዓይነት መንገድ፡፡ ተጠየቃዊ አካሄዱም ይህን ታሪካዊ ህፀፅ ሊዳኝበት የሚያስቸለው ክፍተት የለውም – “ዕብደት ነው!” ብሎ የሚያልፈው ካልሆነ በስተቀር፡፡ በመሆኑም ብአዴን ውስጥ የሚገኙ አማሮች በየትኛውም ሚዛን ቢለኩ አንድም የለየላቸው ዕብዶች ወይም የለየላቸው ደናቁርት ማይማን ወይም ደግሞ ፀላኤ ሠናያት የሠፈረባቸው የክፉ መናፍስት ዋሻዎች ቢሆኑ እንጂ ለአማራ የሚቆረቆሩ አማሮች ሊሆኑ አይችሉም – ቃል ቢቸግረኝ እንጂ “ማይም” ማለቴ ራሱ ስህተት ነው፡፡ ማይምነት ከሀገር መሸጥና መለወጥ አይገናኝምና፡፡ ብአዴኖች አማራ አይደሉም ሲባል ደግሞ የደምና የአጥንት ጉዳይ ሳይሆን በፍካሬያዊ ትርጉሙ ነው፡፡ አማራን ከሚያጠፋ፣ ኢትዮጵያን ለመቅበር ጉድጓድ ከማሰ፣ ሀገርን ከሸጠና ከለወጠ ኃይል ጋር ያለ ሀፍረት አብሮ እየሠራ የሚገኝ “ሰው” አማራ ነኝ ቢል እንዴት ማመን እንደሚቻል ብአዴኖችን ራሳቸውን መጠየቅ ነው፡፡ በጣሊያን ጊዜ ከቅኝ ገዢው ባዕድ ወገን ጋር በባንዳነት ያገለግሉ የነበሩ ብዙዎቹ የዛሬዎቹ ገዢዎቻችን ወላጆች በንጽጽር ከብአዴኖች ይሻላሉ፡፡ ምክንያቱም የዚያኔዎቹ ባንዳዎች የካዱት መላዋን ኢትዮጵያን እንጂ የወጡበትን ጎሣና ነገድ አልነበረምና፤ በዚያ ላይ ጣሊያንም ቢሆን የወያኔን ያህል ቀርቶ ካልነኩት የማይነካና በጭካኔው ከወያኔ ፍጹም የማይወዳደር በአንጻራዊ አነጋገር እጅግ ሲበዛ ሰብኣዊ የነበረ ኃይል ነው፡፡ የኒህኞቹ ድርጊት ግን ዘግናኝ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወንድምህን፤እህትህን፤ አባትና እናትህን፣ በጥቅሉ በዘመኑ ቋንቋ ዘርህንና ቤተሰብህን እንደዐይጥ ከሚጨፈጭፍ የባንዳ ውላጅ ጋር መተባበር፣ ከዚያም ባለፈ ሰሞኑን እንደምንሰማው የጠላትን አንደበት በመዋስ በእንደራሴነትም ቢሆን የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ በአደባባይ መዝለፍ በምንም ዓይነት መለኪያ ጤናማነትን አያሳይም፡፡ (Shall we say proxy badmouthing or insulting?) ይህ ዓይነቱ የብአዴን ድፍረት የኅሊና መታወርንና የአንጎል ጤንነት መቃወስን በግልጥ የሚያመለክት ነው፡፡ የአእምሮ ህክምናም ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡…

አሁን ምን ማድረግ ይቻላል? በዚህ መቀጠሉ ያዋጣል ወይ? እስከመቼስ በባለ አንድ ጥርስ ማርሽ ብቻ ማሽከርከር ይቻላል?

ሰዎች ከፈለጉ ለማንኛውም ችግራቸው መፍትሔ መፈለግና ማግኘትም ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ችግር ውስጥ መገኘትን ማወቅ ነው፡፡ ይህ በራሱ የመፍትሔውን ግማሽ መንገድ እንደመጓዝ ይቆጠራል፡፡ ከዚያም ንስሃ መግባት ነው፡፡ ንስሃ መግባት ሲባል በዚህ ዐውድ መሠረት በሆነ ታሪካዊ አጋጣሚ በተፈጠረ ስህተት ገብተው የሚዋኙበትን የጥፋት ባህር ተረድቶ ከዚያ ለመውጣት ከልብ መጸጸት ማለት ነው፡፡ ጥፋት ሰብኣዊ ነው፡፡ ማንም ሰው ትንሽም ይሁን ትልቅ ስህተት ይሠራል፡፡ ከስህተት ጎዳና ለመውጣትና ተበዳይን ከልብ ይቅርታ ጠይቆ ለመካስ የሚተጋን ሰው ደግሞ ፈጣሪ ይወደዋል፡፡ ሰው ሲባል ከሌሎች እንስሳት የሚለየውና ክፉንና ደግን መለየት የሚያስችለው አንጎል ያለው በመሆኑ ከስህተቱ እየተማረ፣ ደካማ ጎኑን እያስወገደና ጠንካራ ጎኑን ይበልጥ እያሻሻለ ወደበለጠ አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት መራመድ ይጠበቅበታል፡፡ ጥፋቱን እንደልማት ቆጥሮ በኩራት የሚጀነን ሰው ከወያኔ የሚመደብ የመከነ አእምሮ ባለቤት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናነበው ብዙዎች ቅዱሳንና ሰማዕታት ስህተትን ይሠሩ ነበር፡፡ ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ እነቅዱስ ዳዊት፣ እነሶሎሞን፣ እነጴጥሮስ … ሁሉም ይሳሳቱ ነበር፡፡ ግና በጸጸት ዕንባቸው ስህተታቸውን እያጠቡ ከእግዚአብሔር ምሕረትን እንዳገኙ ቅዱሣት መጻሕፍቱ ያስረዳሉ፡፡ ክርስቶስንና ክርስቶሳውያንን በጦር ያሳድድ የነበረው ኃጢኣተኛው ሳዖል፣ በኋላ ላይ በደገኛው የኢየሱስ መንፈስ ተመርቶ አንገቱን ለሠይፍ እስኪሰጥ ድረስ የክርስቶስ አገልጋይ ሊሆንና በቅዱስ ጳውሎስነቱ ሊታወቅ በቅቷል፡፡ አንድ ነገር እንድገም፡- አንዱ “ወንድሜ ሰባት ጊዜ ስህተትን ቢሠራብኝ ሰባት ጊዜ ሁሉ ይቅር ልለው ይገባኛልን?” ሲል ክርስቶስን ይጠይቀዋል፤ በርሱ ቤት ሰባት ብዙ ቁጥር መሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስ ግን በሚገርም ሁኔታ “ሰባት ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ሰባት ጊዜ ሰባም ቢሆን ይቅር በለው” ሲል ነው የመለሰለት፡፡ አራት መቶ ዘጠና ጊዜ ቆጥረህ ይቅር በል ለማለት አይደለም – ይቅር ባይነት ገደብ እንደሌለው ነው የዚያ አስተምህሮ ማዕከላዊ አንድምታ፡፡ ይህ ምሳሌ ሁለት መልእክት አለው፡፡ አንዱ ለበዳዮች – ሌላኛው ለተበዳዮች፡፡ በበዳይ ወገን በኩል ያየነው እንደሆነ “ብዙ በድያለሁና ይቅር ስለማልባል በጥፋት ጎዳና እንደተጓዝኩ ዕድሜየኝ ልፍጅ” ከማለት ያድናል፡፡ በተበዳይ ወገን በኩል ሆነን ያየነው እንደሆነ “ዕድሜ ልኩን ሲጫወትብኝ ኖሮ አሁን እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር እንዳይደርስበት ስለፈራ ልታረቅህ ይለኛል፤ ደግሞስ ለስንት ጊዜ ያህል ከበደለኝ በኋላ ለምን ብዬ ነው ይቅርታውን የምቀበለው?” ከሚል ሰይጣናዊ ግብዝነት ይታደጋል፡፡ እናስ ምን እናድርግ?

ንስሃ ለመግባት ቅድመ ሁኔታ የለውም፡፡ አንድ ሰው ንስሃ መግባት የሚያስፈልገው ጥፋት በማጥፋቱ ነው እንጂ ባያጠፋማ ለምን? ለይቅርታ ደግሞ የጥፋት ደረጃ ማነስ ወይ መብዛት ለድርድር አይቀርብም፡፡ ዋናው ከልብ መጸጸትና ጥፋትን እርግፍ አድርጎ መተው ነው፡፡

በኢሳት እንደምንከታተለው ከብአዴኖች ምሥጢር እየሾለከ ወደተቃውሞው ጎራ እንደሚገባ ተነግሯል – ከኢሳት አንጻር የመረጃ ምንጭን የማጋለጥ ምሥጢሩ እስካሁን ባይገባኝም (ይህ ዓይነቱ ልበ ሙሉነት የመረጃ ምንጭን በማድረቅ ረገድ አሉታዊ ሚና እንደማይጫወት ባውቅ ደስ ባለኝ)፡፡ ለማንኛውም ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡ በራሱ ግን በቂ አይደለም፡፡ በጣም ኢምንት ነው፡፡ ሙሤን ማስታወስ ይገባል፡፡ ሙሤ በፈርዖን መንግሥት ውስጥ ሆኖ ወገኖቹን ከሚጨፈጭፍ ኃይል ጋር – ሳያውቅ ነው – ይሠራ ነበር፡፡ ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ግን 40 ሺህ እስራኤላውያንን ይዞ ከምድረ ግብጽ በመውጣት ሕዝቡን ከአስከፊ አገዛዝ ነጻ አውጥቷል፡፡ ብአዴኖችም ይህን ለማድረግ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሰፊው የአማራ መሬት የአፓርታይድንና የፋሺዝምን ሥርዓት ሕዝባቸው ላይ መጫናቸውን ትተው ከነፃነት ታጋዮች ጋር በኅቡዕ ኅብረት መፍጠርና የነፃነትን ጊዜ ማፋጠን አለባቸው፡፡ እስካሁን የሠሩት ጥፋት ፊታቸው ላይ እየተደቀነ ሊረብሻቸው አይገባም፡፡ ያን በንስሃ ማጠብ የሚቻለው የሠሩትን ስህተት የሚክስ መልካም ሥራ ሢሰሩ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ንስሃ ሲገባ ያጠፋ የነበረውን ጥፋት ዳግመኛ ላለመሥራት ቃል የሚገባበትና የዚያን ተቃራኒ ደግ ሥራ ለመሥራት በዚያውም በደሉን ለማካካስ (atonement) ሌት ተቀን የሚተጋበት ዕድል ያገኛል፡፡ ንስሃ መግባት ሲጀመር ከሙስናና ከደም ማፍሰስ፣ ንጹሓንን በፖለቲካ ሰበብ ከማሰርና ከማንገላታት መቆጠብ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት የሚጓዝ ሕይወት መጨረሻው አያምርም፡፡ ብአዴንም ሆነ ሌላው የወያኔ ተባባሪ እሚበላው ያው አንዲት እንጀራ ናት – ከዚያች አታልፍም፡፡ በተረፈ በቅንጦቱ ረገድ ቢጠጣ ዊስኪና ቢራ ነው፡፡ ቢተኛ ሞዝቮልድ አልጋ ላይ ነው፡፡  ይህ ደግሞ ይሰለቻል፤ በወንጀልና በኃጢኣት ወገንን ሸጦ በሚገኝ የደም ገንዘብ ተንፈላስሶ መኖር የሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሰው የሆነ ሰው በደም ደለል ውስጥ መንቦራጨቁ እየተከሰተለት ሲመጣ በሂደት አእምሮውን የሚያስጨንቅ ነገር ይገጥመዋል፡፡ ጭንቀትን ለመሸፈን ከጧት እስከማታ በመጠጥ ብርጭቆ ውስጥ ቢወተፉ ኅሊና ቀስ እያለ መንቃቱ አይቀርምና በሁለትዮሽ የዞረ ድምር – በመጥፎ ሥራና በመጠጥ – መሰቃየት ይከተላል፡፡ ያኔ የሚከሰተውን የኅሊና ጅራፍ ደግሞ የሚቋቋመው የለም፡፡ ስለዚህ ብአዴኖች ከገባችሁበት አረንቋ በአፋጣኝ እንድትወጡ ብታውቁትም ባታውቁትም በኅያው እግዚአብሔር ስም እማጸናችኋለሁ፡፡ ይህን የምላችሁ ለሕዝብ በማዘን ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ የምትሠሩት መጥፎ ሥራ ከሚያመጣባችሁ የዕልቂት ማዕበል እንድትተርፉ በቅንነት ለእናንተም በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ማትረፍ ካልተቻለው ምን ይጠቅመዋል? ይላል መጽሐፉ፡፡ የምሕረት በር ሳትዘጋ አሁኑኑ በንስሃ ታጠቡ፡፡ ሕዝባችሁ አምርሮ ጸልዮኣል፤ ጸሎቱም ተሰምቷል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ክብርንና ሞጎስን አግኝቶ መልስ የሚሰጥበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ ምልክቶቹም ሁሉ እየታዩ ነው፡፡ አንዱን ልንገራችሁ – ያ ወጣት ብላቴና ረዳት አብራሪ – ምንም ነገር ሳይቸግረው – ከነአውሮፕላኑ ለምን ያን የመሰለ ታሪክ የሠራ ይመስላችኋል? አስቡት፤ አስቡበትም፡፡ በዚህ መልክ ጥሪው የሚተላለፍላቸውና የነፃነት ፍልሚያውን የሚቀላቀሉ ወጣቶች በሠልፍ እየተጠባበቁ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከድጡ ወደ ማጡ

አፄ ቴዎድሮስ በጣም ጨካኝ እንደነበሩ ይነገራል፤ ምናልባትም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደዚያ ደረጃ ተገፍተውም ሊሆን ይችላል፡፡ እርሳቸውም ያን ጠባያቸውን እንደሚያውቁና ሕዝብን ለመቅጣት ከፈጣሪ እንደተላኩ ለሚቀርቧቸው ይናገሩ እንደነበር ተጽፏል፡፡ አንድ ወቅት መነኮሳትን ከያሉበት ይጠሩና በየተራ እያስገቡ “ለመሆኑ እግዚአብሔር አሁን ምን እየሠራ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም የመሰለውን ይመልሳል፡፡ እርሳቸውን ያስደሰተች መልስ ግን አንድ ኮሣሣና ለነፍሳቸው ያልሳሱ (ሞትን የናቁ ማለቴ ነው) መነኩሴ “እግዚአብሔር በአሁኑ ሰዓት ቁናውን እየሰፋ ነው!” ሲሉ የተናገሩት ነው፡፡ አዎ፣ እሳቸውም አመኑበት፡፡ የሠሩትን ጥፋት ስለሚያውቁ፣ በሠፈሩት ቁና መሠፈርም ደንብ መሆኑን ስለሚረዱ አንገታቸውን ነቅንቀው በአግራሞት ነበር ያን መልስ የተቀበሉትና ባህታዊውን አመስግነው ወደመጡበት በክብር የሸኙት፡፡ ሌሎችን በትዝብት ዐይናቸው መግረፋቸውን ማስታወስ ካስፈለገ ግን ይሄውና አስታወስኩ፡፡

ወያኔንና ግብረ አበሮቹን ለመቅጣት እግዚአብሔር ቁናውን ሠፍቶ ጨርሷል፡፡ ወያኔን ያሣወረው ትዕቢት መቃብር ካልከተተው የማይለቀው ሆኖ እንጂ የወያኔ ጉድጓድ ከተማሰ፣ ልጡም ከተራሰና የመግነዝ በፍታውም ከተዘጋጀ ቆይቷል፡፡ የሚቀረው ሥርዓተ ግንዘቱና ጉዞ ፍትሃቱ ብቻ ነው፡፡ ያም በቅርቡ ይከናወናል፡፡ ለመሆኑ አሁን ሀገሪቷን ማን እያስተዳደራት እንደሆነ በግልፅ የሚያውቅ አለ? እኔ ከፈጣ ውጪ በሰው ደረጃ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር ሰው አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው የሆነ የወያኔ ቡድን መኖሩን አልክድም፤  ዋናው ግን በኪነ ጥበቡ እንደምንለው በዚያ ልዩ መለኮታዊ ኪነ ጥበብ ነው ውለን የምንገባው፡፡ ለማንኛውም መላው የኢትዮጵያ ጠላቶች ሂሳባቸውን የሚያወራርዱበትና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ወያኔ የናኘው ማንኛቸውም የዘረኝነትና የጎሰኝነት አቧራ እንደጉም በንኖ የሚጠፋበት የነፃነት ዘመን ደጅ ላይ ቆሟል፡፡ ይህን ነፃነት ማንም ፈቅዶ አይሰጠንም፤ ማንምም ታግሎ አይነጥቀንም፡፡ የዕንባችን፣ የጸሎታችንና የመገፋታችን ውጤት፣ በወያኔዎች ደባ ለዓመታት የፈሰሰው ደማችን የሚያመጣልን መለኮታዊ ፀጋ እንጂ የሰው ስጦታ አይደለም፡፡ በየከተማው እንደሚያፋድሱት እነአባ መሸ በከንቱን የመሰሉ ሳይሆን በሩቅ ገዳማትና በሥውር ሥፍራዎች ቀን ከሌት ወደፈጣሪ የሚያለቅሱ አባቶችና እናቶች አሉን፡፡ ቢያንስ እነሱን አያሣፍራቸውምና መልሱን በቅርብ እንጠብቃለን፡፡ ኢትዮጵያችን ጥቂቶች በቁንጣን የሚሰቃዩባትና ሚሊዮኖች በጠኔ የሚረፈረፉባት ሀገር ሆና እንደማትቀር ቃል ኪዳን አለ፤ ሀገራችን የቃል ኪዳን ምድር ናት፡፡ እናም አይዞን!!!

ብአዴኖች ግን ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ይህ ጥሪየ ዘርን መሠረት ባያደርግብኝ ደስ ባለኝ፡፡ ነገር ግን ይበልጥ የሚያሣዝኑኝ እነሱ በመሆናቸው ነው ይህን የተለዬ ጥሪ እነሱ ላይ በማተኮር ማስተላለፍ የወደድኩት፡፡ ፈጣሪ መንሹን ሊጨብጥ – ገለባን ከምርቱ ሊለይ የማበራያ ዐውድማውን ለቅልቆ ጨርሷል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፤ ከያዘው አሼሼ ገዳሜና አሥረሽ ምቺውም ይመለስ፡፡ የዚህ ዳንኪራና ጮቤ ወጪ የሚሸፈነው ከምሥኪኑ ሕዝብ እየተመዘበረና በሙስና እየተዛቀ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ በዚህ የጥፋት መንገድ እየነጎዳችሁ ያላችሁ ወገኖችም ለቁሣዊ ፍላጎቶቻችሁና ለሰይጣናዊ ሱሶቻችሁ ልጓም አብጁላቸው፡፡ ይህን ስል ወንድም በወንድሙ ላይ የሚፈጽመውን ግፍና በደል ያቁም፣ ወደኅሊናውም ተመልሶ ለሁሉም እኩል በሆነ ህግ ይተዳደር ለማለት እንጂ ሃይማኖታዊ ንስሃ ግቡና ፁሙ ቁረቡ ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ለዚያ ዓይነቱ ስብከት ይህ መድረክ ምቹ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ሰላም ክረሙልኝ፡፡

 

መሰነባበቻ፡-

To the future or to the past, to a time when thought is free, when men are different from one another and do not live alone—to a time when truth exists and what is done cannot be undone: From the age of uniformity, from the age of solitude, from the age of Big Brother, from the age of doublethink—greetings!

 

ውርስ ትርጉም፡- ይድረስ የማላይህ የወደፊቱ ወይም ያልኖርኩብህ የኋለኛው ዘመን ትውልድ – በነፃነት ማሰብ ላልተከለከልከው፣ ሰብኣዊ ልዩነቶችህን ተረድተህ በሰላምና በፍቅር ተግባብተህ መኖር ለቻልከው፣ አምነህበት የምትሠራውን የሚያጨናግፍብህ ሳይኖር በእውነትና ስለእውነት መኖር ለበቃሃው ዕድለኛ ትውልድ ሰላምታየ ከዚህ ከተመሳስሎ የመኖር ዘመን፣ ከዚህ የብቸኝነት መንፈስ ሰውን ከሚያሰቃይበት የብህትውና ዘመን፣ ከዚህ ከታላቅ ወንድም የሰቆቃ ዘመን፣ ከዚህ ከአድርባይነትና አስመሳይነት ዘመን ባለህበት ይድረስህ፡፡ (ጆርጅ ኦርዌል፣ “1984”)

 

 

1 WAR IS PEACE

FREEDOM IS SLAVERY

IGNORANCE IS STRENGTH

3 Comments

  1. Oh Netsanet!

    A great person! Thank you for your super article!
    Thank you!
    Thank you!
    Thank you!

    God Bless you!

  2. So after all this boring and lengthy nonsense, your “threat” to the “amhara woyanes” is a call that punishment is coming from above?

    Get a life dude!!

  3. You aspire to restore back a country in which one language is going to be spoken and superiority of one ethnic group is exercised. I understand that you don’t know the current real situation in other regions of Ethiopia except yours – Amhara region.
    I want to assure you and your fellow that no one lets you to administer a single part of Kebele in other regions as you you don’t no except more than one Ethiopian language i.e you mother tongue . That is a great opportunity for us to easily identify who you are.
    Simply you may restore back the eliminated system when the dead people start to awake up as per indicated in bible.

Comments are closed.