ጎሰኞች ፅንፈኞች – ከአልማዝ አሰፋ

ከአልማዝ አሰፋ
[email protected]

ኢትዮጵያ ውቢቷ : ታምራለች አገሬ : የበዛ ቀለሟ
በቋንቋ በሕዝቧ : በባህል ሀብቷ : በታሪክ አቋሟ
በልፅጋ የታየች : ጠንክራ ጎብዛ : ጎልብቶ አቅሟ
ያሳዝናል ማየት : በጎሰኞች ፅንፈኞች : ሲሰበር ቅስሟ::

የባህልሽ ውበት : አሸንዳ እሬቻ : መስቀልን ጨምሮ
የማንነት መግለጫ : ክብርሽ ማመስገኛ : የአገር ተመክሮ
ኢትዮጵያዊነት አብቦ : ጎልቶ ሲታይ አምሮ
ሊያጠፋሽ አሰበ :የእንግዴ ልጅሽ : ከጠላት አብሮ::

የአስተዳደር ጉድለት : አላኖር ብሎን
ሰርተን ሰው እንዳንሆን
መንገድ ዘግቶብን
ከመሞት መሰንበትን
ምርጫ አድርገን
ጥቂት የታደልነው : ለስደት ወጣን::

በባእድ መሬት ላይ : በሰላም ኖረን
በቆዳችን ቀለም : ዝቅ አርገው ቢያዩን
የመኖር መብታችን ግን
ተከብሮ ተጠብቆልን
የተሟላ ሕይወት በማግኘት እጅግ ታድለን
የአንድነትን ዋጋና ጥቅሙን
መረዳት አቅቶን
እንደማይተዋወቅ: እርስበርስ ተናንቀን
ከፍቅር ይልቅ : ጥላቻ አዝለን
እኔ ኦሮሞ ቄሮ እያልን
ሰው እያስገደልን
እኔ አማራ ፋኖ እያልን
ሕይወት እያስጠፋን
እኔ ተገሃሩ እያልን
ሕዝብ እያስፈጀን
በጎሳ በሽታ ቆስለን
በስብሰን ገምተን
ሰብአዊነት ከድቶን
ሰው መሆን ተሳነን::

እንዴት አያዝን ልቤ : ተናውጦ መንፈሴ
ምን ልበል ፈጣሪን : መልስ አጣሁ ለራሴ
ወንድም ወንድም ሲገድል : እኔስ መታገሴ
እሬሳ ሲቃጠል : እርጉዝ ስትታረድ : እንዴት ቻለች ነፍሴ?

እንዴት ዝም ይባላል : ያገር ልጅ ሲጣላ
እንዴትስ ይቻላል ማየት : ያገር ልጅ ሲባላ
ያገሬ ሕዝብ ሲራብ : አጥቶ የሚበላ
ማደሪያ በማጣት በየመንገዱ ዳር ወድቆ የሰው ገላ
አገር የሕዝብ ቀርቶ : ስትሆን የደላላ
ጎሰኛ ፅንፈኛ ሕዝብን እያመሰ ሲያጋድል ሲያባላ
ይህንን እያየ : ሰውን ለማስከበር : የማይፈልግ መላ
ምን አይነት አመራር ነው ያለው : በስልጣን ከለላ?

በወደቀ ዘይቤ : በጎሳ ነግዶ : ስልጣን ላይ ሊወጣ
ታሪክን የማያውቅ ደንቆሮ : ሚያናድድ ሚያስቆጣ
ጎሰኛ ፅንፈኛ የኢትዮጵያን ታሪክ ክዶ : በተረት ሲንጣጣ
እንዴት ላሳልፈው : እውነት ቦታ ሲያጣ
እየተረዳሁት : ውሸት ሃቅ ሆኖ : አፍጥጦ ሲመጣ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነፋስ ሰውን ነዳው! - በላይነህ አባተ

አገሬ ቆንጂቷ : ኢትዮጵያ ተብለሽ
በዓለም ታሪክ ላይ : እጅግ ተደንቀሽ
በሶስትሺ አመታት ነፃነት : እጅግ አብበሽ
ለጥቁሮች ጥንካሬ : ተስፋ በር ከፍተሽ
የሰው ልጅ መነሻ : ሉሲን ወልደሽ
በገዛ ልጆችሽ : እንዴት አረከስሽ?

ይህንን እያወቀ : አውነት የተሳነውን
በልጆችሽ መሃል : ጥላቻ የፈጠረውን
የአንቺን ማንነት : መኖርሽን የካደውን
እንዴት አድርጌ እኔ : ጎሰኛን ፅንፈኛን
እንደሰው ልቁጠረው?

ለሰላሳ ዓመት : ጎሰኝነት ነግሶ
ሕዝብ ተቸግሮ ስናይ : እንባውን አፍሶ
አንገት እየደፋ : ሲሄድ አጎንብሶ
ሰው ለሰው ወንድሙ : ጥላቻን ደግሶ
እኔ ተረኛ ነኝ ብሎ : ስልጣን ካባ ለብሶ
ለኢትዮጵያ ቆማለሁ ያለውን ቃል : ካጠፈ መልሶ
ምን አይነት ክህደት ነው : ማለፍ እድበስብሶ?

ልንገርሽ ኢትዮጵያ : ውዲቷ እናቴ
ከአንቺ ተውልጄ : ሆነሽኝ መስተዋቴ
በእናት አገር ስቃይ : ቢጎዳም ስሜቴ
በባእድ አገር ብኖር : ባልሰጋም ለሕይወቴ
ፍቅርን ላስተማርሽን : ለእኔም ጎረቤቴ
እንዴት ይረሳኛል : ያ ቆንጆ እድገቴ?

ዛሬ ግን እንባሽ : ጠራጊ አጥቶ
ያ ይጦረኛል ያልሽው ልጅሽ : ለጥፋት ጎልብቶ
ወንድሙን ሲገድል ሲታይ : ሰባዊነት ጠፍቶ
ጎሰኛ ፅንፈኛ ልጅሽ : ሆነልሽ እንኩቶ::

በጣም የተረሳው : ማሰብ የተሳነን
ማን እንደቀደመ : ጎሳ ወይስ ሰው ይሆን?
ብዬ ብጠይቀው : ቸሩ ፈጣሪን
የፈጡርኩት እኔ : የሰው ልጅ እንጂ : አይደለም ጎሳን::

ታዲያስ የዘመኑ : ሰው መሳይ አውሬዎች
ለሰው ክብር የሌላቸው : በጎሳ አማኞች
ፈጣሪን ከመስማት : ሆነው ከሃዲዎች
የጠቡትን ጡት : መልሰው ቆራጮች
ያበላቸውን እጅ : መልሰው ነካሾች
ዘመን ያፈራቸው : የጊዜው ይሁዳዎች
ሰው የሚያጠፉ : የሰይጣን ቁራጮች
ሕዝብ ሚያጋድሉ : የሰው ልጅ ብኩኖች
ኦሮሞ አማራ: የትግራይ ፅንፈኞች
የቄሮ የፋኖ የተጋህሮ ጎሰኞች
እግዚአብሔር ይፍረዳችሁ : የአንድነት ጠላቶች:;

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተጠየቅ (ዘ-ጌርሣም)

Leave a Reply

Your email address will not be published.