ከተማ አስተዳደሩ የ”መቀመጭት ተራራን” “አቡነ ኤርምያስ ተራራ” ብሎ ሰይሟል። ሦስት የቤት ሥራዎችንም ሰጥቷቸዋል

280687200 306216078366024 803665062155480373 nከተማ አስተዳደሩ ስያሜውን ይፋ ባደረገበት ሰዓት ባስተላለፈው መልእክቱ በተፈጥሮ በተራራ የተከበበችው ወልድያ ከተማ ተራራማ መልክዓ ምድሮቿ ከጫፍ እስከ ስር፤ ከመሐል እስከ ዳር ድንቅ ሰብአዊ ምስጢራትን ያዘሉ ናቸው ብሏል።

ለአብነትም ከጉባርጃ ተራራ በስተምዕራብ ግርጌ፤ ከጥንቱ የማክሰኞ ገበያ ከነበረበት ቦታ ራስጌ፤ ከ”ጉባ” እና ከ”መቀመጭት” ተራራ በስተምስራቅ ግርጌ ላይ የሚገኘው “አባወንታ ወይራ” በመባል ከሚታወቀው ፕላቶማ ቦታ ታላቁ ባለከራማው ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከዛፉ ስር ተቀምጠው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ስለሀገር፣ ስለወገን ዱዓ እንዳደረጉበት ይታወቃል፡፡ ይህ እንደቀላል የምናየው አይደለም፤ እንደ ወሎየነት ባሕል፣ ሥርዐት፣ ወግ ማዕረግ እንኳንስ ታላቁ ሼህ ጊዜ ሰጥተው ዱዓ ያደረጉበት ቦታ ይቅርና የጎበኙት ቦታ ታላቅ ክብር አለው፤ ለዚያም ነው የአካባቢው ማኅበረሰብ ቦታውን ልዩ ትርጉም ሰጥቶ ጠብቆና አክብሮ አሁን ላይ መስጊድ ተገንብቶበት ቁርዓን የሚቀራበት ሶላት የሚደርስበት የአምልኮ መፈጸሚያ ለመሆን በቅቷል ብሏል ከተማ አስተዳደሩ።

በተያያዘ ሁኔታ አንዳንዴ በተሳሳተ በፖለቲካዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤ የፖለቲካ መሪ መስመር ሲስት ሕዝብ ምን ግዜም አስተዋይ፣ በሳል ከመሪው ቀድሞ የሚያስብ ብቻ ሳይሆን፣ መሪው እንዲጨምት፣ እንዲሶብር ዱዓ ያደርጋል፤ ጸሎት ያደርሳል እንጂ ስህተቱን በመደገፍ አይታወርም። አፄ ዮሐንስ ከአንድ ዓመት አካባቢ በላይ ብዙም ባልዘለለው የሥልጣን ጊዜያቸው እስልምና አስተምህሮ ላይ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ፣ የወሎ፣ የየጁ አካባቢ ሕዝበ ክርስቲያን ሙስሊም ወገኖቹን “አይዟችሁ ያለፍላጎታችሁ በዐዋጅ ተገዳችሁ እምነታችሁን አትቀይሩም፤ ከጎናችሁ” ብሎ በማጽናናት የምትሞትን ነፍስ ዋሽቶ ማትረፍ ታላቅነት ብቻ ሳይሆን ጽድቅም ነውና ለአፄው እንደራሴዎች እምነታቸውን ወደ ክርስትና ቀይረዋል ብሎ ሪፖርት ያቀረበ ታላቅ አስተዋይ፥ ሳይማር ሊቅ፣ ሳያነብ ተርጓሚ የሆነ ሕዝብ ነው። ይህን ሪፖርቱ እንዳደረገ ብዙም ሳይርቅ ከአካባቢው ሼህ ማሩፍ ካሳ የተባሉ ታላቅ አበጋር ወደ አኪራ ተጠሩ (ከስጋ ሕይወት ተለዩ)። በወቅቱ የነበሩ የአካባቢው ካህናትም ታላቁን ሼሕ ከመካነ መቃብራቸው በጨረቃ ቀበሩ። ቀን ላይ ቁልቋል ገንዘው ከበሮ እየመቱ ቤተ ክርስቲያን ቀበሩ። ይህ ዘመን የማይሽረው የሙሉ ስብዕ ታሪካዊ ክስተት በ08 ጀነቶ በር ቀበሌ አስተዳደር “ሞላ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን” የቁልቋሉ ቀብር በመባል ይታወቃል። ይህ የሆነው እንደ አሁኑ ያልሰከነ ምዕራባውያን ለማደንዘዣ የፈጠሩት ፌስቡክ ሳይፀነስ፣ ትውልዱ ሳይበረዝ፣ የምስጢር ጠባቂነት ወጋችን ትል ሳይወጋው በደገኛው የአባት እናቶቻችን ዘመን መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አውስቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቆንጆ ሴቶችን በሚገባ ለማፍቀር የሚያስችሉ 7ቱ ልዩ ልዩ የስህበት ህጎች

ከተማ አስተዳደሩ አንድም ሰው ለጉዳት ሳይዳረግ የአንድነት ምስጢር የመቻቻልን ልዩ ጸጋ በከርሳቸው የያዙ ልዩ ባለታሪክ ተራራዎች እንጂ ተራ ተራራና ተራ መሬት ብቻ አይደሉም መልክዓ ምድሮቿ ወልድያ። ለአሁኑ የሃይማኖት ግጭት ነጋዴዎች ይህን ዓይነት በሳልና አስተማሪ ታሪክ ጀባ ብቻ ሳይሆ ልናስጎበኛቸው ይገባልም ብሏል።

በመሆኑም ከአምስት ወራት በላይ በዘለቁት አስከፊ ጊዜያት የሁሉም ቤተ እምነት ሰብሳቢ፤ ከእምነት ይልቅ ሰብኣዊነትን ባስቀደሙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ብሔረስብ አስተዳደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በወገቡ ታላቅ ምስጢር ያዘለውን የ”መቀመጭት” ተራራን “አቡነ ኤርምያስ ተራራ” ተብሎ መሰየሙን አብስሯል፡፡

የተራራውን ስያሜ የሰጠው ከተማ አስተዳደሩ አቡነ ኤርምያስ ያደረጉትን ውለታ የተራራው ስም ሊመጥን ወይም ሊገልጽ ሳይሆን፣ የሚከተሉትን ሦስት ዋና ዋና እና ተያያዥ የቤት ሥራዎች ለመስጠት መሆኑን አስታውቋል።

አንደኛ የዕፅዋት ሳይንስ መድኃኒት ቅመማ ጋር ተያይዞ ለምርምር የሚሆኑ ሀገር በቀል ዕፅዋቶች በስፋት ስለሚገኙበት ተራራ በመሆኑ የጥንት መጻሕፍትን በመተርጎም የሚመራመሩ ሊቃውንትን በማሰማራት የምርምር ማዕከል እንደሚያደርጉት ታላቅ ተስፋ ስለጣልንባቸው።

ሁለተኛ ከተማዋ እየሰፋች በሄደች ቊጥር ተከብረው የኖሩ ደኖቻችን በከተማዋ መስፋፋት ምክንያት እየመጣ ያለውን የደኖች መራቆት ለመግታት ተራራው በርሳቸው ስም መሰየሙ እንኳንስ ነባሩ ደን ሊመናመን ይበልጥ ተከብሮ እንዲቀጥል ትልቅ ዐቅም መሆኑን በማመመን ነው።

በሦስተኛ ደረጃ ብፁዕነታቸው ከወረራ በኋላም “ከጓሳ ማጨጃው እስከ ጭረት መንቀያው (ከቆላ እስከ ደጋው)” እምነት ሳይለዩ በመልሶ ግንባታ የሚያደርጉት በሰብአዊ መስፈርት አሁንም ሌላው አኩሪ ጸጋችን ነው፤ ከዚህ አንጻር ከሀገር ውስጥ እስከ ሀገር ውጪ ከክርስትና እስከ እስልምና እና ሌሎችም ምሁራንና ተቋማትን በማስተባበር “ድሮ አባቶቻችን የመድኃኒት ቅመማ ባለሙያ ነበሩ” እያልን ከማውራት ይልቅ “ብፁዕነታቸው የዐዋቂነት ትንሣኤያችንን መልሰው ይገነቡታል” የሚል ሙሉ እምነት በማሳደር “አቡነ ኤርምያስ ተራራ” ብለን አንድን ተራራ በስማቸው ሰይመናል

ተጨማሪ ያንብቡ:  “መንግሥቱ ኃ/ማርያም የአገራቸው ናፍቆትና ፍቅር አሁንም በልባቸው የነደደ ነው፤ አለ።” - ገነት አየለ

እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል ከተማ አስተዳደሩ።

ከፍ ካለው ተራራ ስር እና ጫፍ ያለውን ታላቅ የአንድነት ምስጢር ከፍ ያለ ዕይታ ባለው አባት መሰየሙ ክብሩ ለከተማ አስተዳደሩ እና ለተሰየመለት ሰው ሳይሆን፣ የብፁዕነታቸውን አገልግሎት ለቀመሰው እና ላጣጣመው ለመላው የወልድያና አካባቢው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰማው ሁሉ ክብር ነው ሲል ከተማ አስተዳደሩ አስረድቷል።

ወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን

ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.