አርቲስት/ ዘማሪ/ ሙሉቀን መለሰ 

/

ሙሉቀን መለሰ በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ዳማ ኪዳነምህረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ, ም ተወለደ ። አስር ዓመት ሲሆነው ወላጅ እናቱ በሞት ስለተለዩት አዲስ አበባ የሚኖሩት አጎቱ ላስተምረው ብለው አመጡት ።

ኮልፌ ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ት/ቤት ትምህርቱን መማር ቢጀምርም የአጎቱ ሚስት ይጠሉት ስለነበረ በብስጭት በትምህርቱ ብዙ ሳይገፋ ትምህርቱን አቋረጠ።

ኮልፌ አካባቢ ልጆችን የሚያሳድጉ እንዳሉ በመስማቱ ሄዶ ጠየቅ ። እነሱም ተቀበሉት። የተቋሙ አስተዳደር በጣም ይወዱት ስለነበረ ሲጠሩት ሁሉ ” ኤሊቪስ ” እያሉ ነበር። ከውጭ ሀገርም ልብስ ይዘውለት ከመምጣታቸውም በተጨማሪ ውጭ ልከው እንደሚያስተምሩት በተደጋጋሚ ቃል ይገቡለት ነበረ ። አብዝተውም ይንከባከቡት ነበረ። ውለታቸውንም ዛሬ ድረስ ያስታውሰዋል።

በዚሁ የልጆች ማሳደጊያ ጊቢ ውስጥ የሙዚቃ ት/ቤት ተከፈቶ ነበረ ። አስተማሪውም አቶ ተፈራ አቡነወልድ ነበሩ ።

ሙሉቀን ለስድት ወራት ከተማረ በኃላ እህቱ በጠና በመታመሞ ምክንያት ወደ ትውልድ ቀየው ጎጃም አቀና። ያን ግዜ ነበረ ሌላ አክስቱ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚኖሩ ያወቀው ። ከጎጃምም መልስ አክስቱ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የካ ሚካኤል አካባቢ ይዘውት መጥተው ከእሳቸው ጋር መኖር ጀመረ ።

አክስቱ የወታደር ሚስት ስለሆኑ ገቢያቸው ሰለማይበቃ ጠላ ይነግዳሉ። የአክስቱ የኑሮ ሁኔታ አልመች ስላለው አንድ ቀን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል አቀና። ለመቀጠር ቢጠይቅ ስላልተቀበሉት በእርዳታ መልክ ሻይ የማፍላት ስራ ሰጡት። የሻይ ማፍያ ምድጃው በኮረንቲ የሚሰራ ስለነበረ በአንድ ቀን ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ይዞታል። በዚሁ ሻይ የማፍላት ስራ ለስድስት ወራት ከሰራ በኃላ ስራውን ጥሎ በመውጣት ለተወሰነ ወራት ተንከራተተ ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጳውሎስ ኞኞ ቀልዶች - ጋዜጠኛና ደራሲ

ከአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ትንሽ ወረድ ብሎ አንድ ሻይ ቤት ዳግም ስራ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። የሻይ ቤቱ ባለቤት ሙሉቀንን ይወደው ስለነበረ ይረዳውም ነበረ። ሙሉቀን ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ ነበረው። ሻይ ቤት ውስጥ ጓደኛው ተቀምጦ ሀርሞኒካ ሲጫወት ሙሉቀን ይዘፍን ነበረ።

አንድ ቀን ሙሉቀን እና ጓደኞቹ ሲጫወቱ አምሽተው ወደ ሶስት ሰዓት ገደማ አንዱን ጓደኛውን ለመሸኘት እየሄዱ ሳለ ደጃች ውቤ ሲደርሱ የውቤ በርሀ ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች በጣም ያስደምሙት ነበረ ። ካሉት የውቤ በርሀ ቤቶች ውስጥ አንዱ ይበልጥ አሸብርቆ የነበረ ሲሆን ጓደኛሞቹ ይሄ ቤት ምንድን ነው ብለው ጠየቁ ። ይኸማ ፈጣን “ኦርኬስትራ የሚጫወቱበት ፓትሪስ ሉምባ ናይት ክለብ ነው ። ” ይባላሉ ።

ከፓትሪስ ሉምባ ፊት ለፊት ወዳለ ሱቅ ሄደው ” የዚህ ናይት ክለብ ባለቤት ማን ነው ? ” ብለው ጠየቁ ” ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ይባላሉ። ” በማለት የሱቁ ባለቤት መለሱላቸው። “ስራ ይሰጡኝ ይሆን ” ሲል ሙሉቀን ጠየቀ።

ባለሱቁም እስክሪቢቶና ወረቀት ሰጥቶት ፃፍና ጠይቃቸው አለው። ሙሉቀንም ስራ እንደሚፈልግ በፅሁፍ አስፍሮ በፍርሃት ተውጠው ወደ ናይት ክለቡ አቀኑ ።

ሙሉቀንም ለኦርኬስትራ ብድን መሪ ሲሰጠው አነበበውና በጣም ሳቀበት። ” ምንድን ነው ” አሉ ወይዘሮ አሰገደች ከተቀመጡበት ስፍራ ሆነው ። ሰውየውም ያነበበውን ከነገራቸው በኃላ በፅሁፍ ያሰፈረውን ወረቀት ሰጣቸው። “ፈትነውና ካለፈ ጥሩ . . . ካላለፈ ሌላ ስራ እሰጠዋለሁ ” አሉ። የልጅነት መልኩና ጉስቁልናው ሳያሳዝናቸው የቀሩ አይመስልም።

በፈተናውም ጊዜ በባዶ እግሩ በቁምጣ መድረክ ላይ ወጥቶ እንደ ጥላሁን ገሠሠ እና አለማየሁ እሸቴ “ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነብሴ ” እና ” እንክርዳድን ” ዘፈነ ። ብዙ የናይት ክለቡ ሴቶች ዘፈኑን ወደዱትና አራት መቶ ብር አዋጡለት ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ማነዉ? ክፍል አንድ (በንጉሤ ዶሌቦ)

በነገታውም ካኪ ልብስ ተገዛለት፣ ሱፍ ልብስ ተለካ እግሩንም ታጥቦ ቢትልስ ጫማ አደረገ።

ሙሉቀን በ1960ዎቹ መጀመሪያ ዘፈን ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ቤት በመጀመሩ እዛው ክፍል ተሰጠው፣ ምግብ ከዚያው በነፃ ይመገብ ጀመረ። ወደ ናይት ክለቡም በርካታ ሰው ይተም ጀመረ ። ወይዘሮ አሰገደችም እሱ ማታ ማታ ሊዘፍን እሳቸው ደግሞ በወር ዘጠና ብር ሊከፍሉት ሙሉቀንን የኮንትራት ውል አስፈረሙት ።

የቀድሞ የአሜሪካ ቤተ መፀሀፍት አጠገብ “ዙላ ናይት ክለብ “ገባ ። ሰለሞን ተሰማ የደረሰውን “የዘላለም እንቅልፍ” እና አቡበከር አሽኬ የደረሰውን ” ያላየነው የለም ” ይዞ በቴሌቪዥን ቀረበ ።

አዲስ አበባ ሙሉቀንን ያውቀውም ጀመረ ። ሊስ ኦርኬስትራ አስተዋዋቂ በቅፅል ስማቸው” ይቀጥላል” አራት መቶ ብር አንክፍልህ እና እኛ ጋር ስራ ብለው ጥያቄ አቀረቡለት። እሺ ብሎ ስራውን ቢጀምርም ወር ደርሶ ደሞዝ ሲቀበል አንድ መቶ ብር ብቻ እየከፈሉት ሲቸገር እለቃለሁ ብሎ ሲጠይቅ ልጅ ስለነበረ ውል ፈርመሃል እንከስሀለን ሲሉ አስፈራሩት።

ሙሉቀን ፓሊስ ኦርኬስትራ በተቀጠረ በሶስተኛው ቀን በመቀሌ “የወይዘሪት ትግራይ የቁንጅና ውድድር “ይደረግ ስለነበረ ከኦርኬስትራው ጋር ወደ መቀሌ አቀና። በስፍራውም ሙሉቀን የጥላሁን ገሠሠን ሙዚቃ በመጫወቱ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት አገኘ። ከኦርኬስትራው ባንድ አለማየሁ እሸቴ ለቆ ስለነበረ ሙሉቀንን ” ምትኩ ” ሲሉ ተጨማሪ ስም ሰጡት ።

ተስፋዬ አበበ የደረሳቸው ሶስት የዘፈን ድርሰቶችን ማለትም “እምቧይ ሎሚ መስሎ፣ እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ፣ ልጅነት ” የተሰኙትን ሙሉቀን በህዝብ ፊት በመዝፈኑ ታዋቂ ሆነ። በተለያዩ ጋዜጣዎች ላይም ኮከብ ድምፃዊ ሲሉ አሞካሹት ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ (1931-2021)

ለፓሊስ ኦርኬስትራ ለሶስት አመት ካገለገለ በኃላ ከኦርኬስትራ ቡድኑ ለቆ ማታ ክለቦች ላይ መስራት ጀመረ ።

ወደ አስር የሚጠጉ የሙሉቀን መለስ የሙዚቃ ስራዎች በሸክላ የታተሙ ሲሆን ከአቢዬቱ በኃላ ዳግም በካሴት ታትመው ህዝብ ዘንድ እንዲደርሱ ተደርጎል ።

ሙሉቀን ከዘፈኖችህ በጣም የምትወደው የቱን ነው ተብሎ ሲጠየቅ ሁሉንም በእኩል መጠን እንደሚያያቸውና በጣም የሚያረካውና በዘፈኑ እና በዜማው አብዝቶ የሚወደው ” “ሰውነቷ” እና ” ሆዴ ነው ጠላትሽ ” የሚወዳቸው ሲሆን በሙዚቃ ጥራትና አሰራሩ ደግሞ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀናበተራቸው ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈናቸው ” ቼ በለው እና ” ውቢት ” የተሰኙትን እንደሆነ ይገልፃል ።

ሙሉቀን በአሁን ሰዓት በሀገረ አሜሪካ የሚኖር ሲሆን በሀይማኖቱ ምክንያት ከሙዚቃ ዓለም እራሱን አግልሏል ።

ከእርቲስት ሙሉቀን መለሰ የሚወዱት የሚዚቃ ስራው ምን የሚለው ነው ? ከቻሉ የሙዚቃ ርዕሱን እና ሁለት ስንኝ ግጥሙን ኮሜንት ላይ ይፃፉ !

ከአንድምታ መጽሔት ሀሳብ በመውሰድ ተሻሽሎ የቀረበ

ፔትሮስ አሸናፊ

Leave a Reply

Your email address will not be published.