በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል!!! (መኢአድ)

AEUPከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሠጠ መግለጫ

የአማራ ህዝብ የእልቂት ሰነድ በ1967 ደደቢት ላይ ተጠንስሶ ለ27 ዓመታት ዘር የማጥፋት ተግባሩ ሲተረክ፣ ሲተገበር ቆይቶ ህወሓት ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት በተባረረ ማግስት ድርጊቱ ሥልጣን በተረከበው የብልፅግና መንግስት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ የአማራ ህዝብ መታረጃ ቄራ ከሆኑት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መካከል ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ አርሲ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ እንዲሁም የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሁሉም ዞኖች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

አማራው በሚኖርባቸው የሀገሪቱ መአዘናት ሁሉ መንግስታዊ መዋቅርን ጨምሮ በመጠቀም በእቅድ ተለይቶ ሲገደል፣ ሲፈናቀል እና ሲሳደድ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርጎ፤ በችግር ሲማቅቅ በርካታ አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የለውጥ ዘመን በተባሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል ደግሞ እጅግ በተባባሰ ሁኔታ ዘር ማንዘሩ ይጨፈጨፋል፤ የመኖሪያ ቀዬውና ከተሞቹ ይወድማሉ፡፡ ከሞት የተረፈው በሚሊዬን የሚቆጠር አማራም በገዛ ሀገሩ ስደተኛ ሆኖ ያለበቂ መጠለያ የዕለት ጉርሱን ሳይቀር ተመፅዋች ሆኖ ይገኛል፡፡

በአማራ ህዝብ ላይ እየተካሄደ ያለውን ግልፅ የሆነ የዘር ፍጅት ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋና ውድመት አይቶ እንዳላየ በግዴለሽነት የሚያልፍ መንግስት ድብቅ ዓላማውን በግልፅ እያስፈፀመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብሎ ድርጅታችን መኢአድ በፅኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም የተያዘው የተስፋፊነት እና የዘር አጥፊነት አጀንዳ ወደ ሙሉ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያሻግር እንጂ ወደ ሀገራዊ ሰላምም ሆነ ወደ ሌሎች አዲስ ሀገራት ምስረታ የሚወስድ አለመሆኑን በመረዳት የብልፅግና መንግስት ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ህዝብ በቁመናውና በፖለቲካ ጥያቄዎቹ ልክ የሚመጥነው መሪ እና የፖለቲካ ድርጅት እስካላገኘ ድረስ ከህወሓት ኢህአዴግ ተቆርጦ የቀረው የብልፅግና መንግስት የጀመረውን አማራውን የማሳደድ ስራ እንደሚቀጥልበት የአማራ ህዝብ ከወዲሁ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ራሱን ከዘላለማዊ ጥፋት እንዲያድን እያሳሰብን፤ ድርጅታችን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በሕዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ማሳደድ፣ ማፈናቀል እና ጭፍጨፋ አጥብቆ እያወገዘ፤ የሚከተሉትን አስቸኳይ ጥሪዎች ያቀርባል፡-

  1. መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በግልፅ እንዲያወግዝ፣
  2. መላው የዓለም ማህበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የዓለም የፍትህ ተቋማት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዓለም አቀፍ ሲቪክ ማህበራት፣ የዓለም አቀፉ ኃይማኖት ተቋማት፣ አለም አቀፉ የዘር ፍጅት ተቆጣጣሪ ተቋም ወ.ዘ.ተ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ፍጅት ወንጀል በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በግልፅ እናሳስባለን፡፡
  3. በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለውን የአማራን ህዝብ የጅምላ የዘር ፍጅት ወንጀል በማውገዝ ወንጀለኞቹ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለሕግ  እንዲቀርቡ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡
  4. በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ላይ የምትገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አማራን በጅምላ ዘር የማጥፋት ወንጀልን ገለልተኛ ሆናችሁ የድርጊቱን አስከፊነት ለመላው የዓለም ህዝብ ተደራሽ ታደርጉ ዘንድ እናሳስባለን፡፡
  5. ለሀገሪቱ የፀጥታ አካላት በሙሉ በአባቶቻችሁ፣ በእናቶቻችሁ በህፃናት ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ በአጠቃላይም በወገኖቻችሁ ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ እና አስከፊ ወንጀል እየተፈፀመ በመሆኑ ቀዳሚ ኃላፊነታችሁ የሆነውን የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ተግባራችሁን ገለልተኛ ሆናችሁ እንድትወጡና ወንጀለኞችንም ለሕግ እንድታቀርቡ ስንል እናሳስባለን፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፋኖ አማራ በሸዋ የተላለፈ መግለጫ!

“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

AEUP 1

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.