ጊምቢ ኤሎሄ ጊምቢ ቶሌ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

290684552 3309915649279615 7045677791337159006 n
ጊምቢ ኤሎሄ ጊምቢ ቶሌ
ትእዛዝ ወርዶ ከእገሌ
ከሥልጣኑ ሉያ ሃሌ
ለማይካድራ ጅኒ ቆሌ
መስዋእት ሊቀርብ
በንጹሕ ደም መቅጃ አኮሌ
ዱበርቶኒ ፊ ኢጆሌ**
ተጨፍጭፈው
በወለጋ ጊምቢ ፎሌ
ካንዲት ጎጆ አሥር ሞቶ
ለኦነግ ዛር ተሠውቶ
መሬት ጭረው እህል ዘርተው
የሚኖሩ ከብት አርብተው
የማይጽፉ ማያነቡ
ጥያቂያቸው
ወጥተው ወርደው ቤት ሲገቡ
ሰላም ዋለ ቤተሰቡ?
መጣ ቀረ ወይ ዝናቡ?
ብቻ ሆኖ
አራት ኪሎ የሚያውቃቸው
አራት ኪሎን የማያውቁ
እንደ ዶሮ ተከታትፈው
እንደ አውሬ እየታነቁ
እንዲያ ሲያልቁ
ያስተዳድር የተባለው
የመመከት ሥልጣን ያለው
በከፈሉት ግብር ሰብቶ
ባመረቱት ቀለብ ገዝፎ
ካገር ጠላት ዲናር ልፎ
ይሁዳኛ እየሳመ
ሲሰጣቸው አሳልፎ
ጊምቢ ሆና ጎልጎታቸው
ቤትልሄምም ራሷ ጊምቢ
መንደራቸው ድንገት ሆኖ
የቀያፋው ትልቅ ግቢ
አርብ ማልዳ ደርሶባቸው
የኛ ያሉት ወገናቸው
ጴጥሮስኛ ሲክዳቸው
በጥላቻ ጅራፍ ገርፎ
የሮም አሽከር ሲይዛቸው
በክላሽ ጥይት ተቸንክረው
ገና ሳትወጣ ነፍሳቸው
እጣ ወጥቶ በልብሳቸው
ንብረታቸው ሲከፋፈል
ለወራሪ / ጃርት ፍልፈል
አስገርፎ አሰቅሎ
ጲላጦስ እጁን ቢታጠብ
የሌለበት አስመስሎ
የፈሰሰው ደም የወሎ
ያለበደሉ ተገድሎ
በወለጋ ጸሐይ ተንኖ
ሰማይ ጠቅሶ እንደ አውሎ
ገና ይወቅ/ሳል ዘላለም
ገና ይጮ/ኻል ለሁሌ
ጊምቢ ኤሎሄ! ጊምቢ ቶሌ!

* አኮሌ = ማለቢያ ቅል፣ ጮጮ፣ የፈሳሽ ማስቀመጫ
** ዱበርቶኒ ፊ ኢጆሌ = ሴቶችና ልጆች

መታሰቢያነቱ በሰኔ ወር 2022 ዓ.ም. በወለጋ በአማራነታቸው ተለይተው በመንግሥት መራሽ ጭፍጨፋ በጭካኔ ለተፈጁት ሰላማውያን እና ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ይሁን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቀና በይ አፍሪካ ! - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

1 Comment

  1. ሞቼ ቢሆን ያኔ
    የሰማይን ክፋት
    የዝናብን መጥፋት
    ከሰኔ እስከ ሰኔ፤
    ብቻ እንዳማረርኩኝ
    ምነው ሞቼ ቢሆን!
    እያልኩ ነው እኔ።
    እንዲህ አውሬ ሆኖ
    ከታትፎ ሊጥለኝ
    የገዛ ወገኔ፤
    የሚቀብረው አጥቶ
    በጅብ በአሞራ
    ሊበላ አስከሬኔ፤
    በሰባሰባቱ
    በዚያ በከፋው ድርቅ
    በሰው በላው ጠኔ፤
    ምነው በቀረሁኝ
    እዚያቹ መንደሬ
    ባልረዘመ ቀኔ።
    እንዲህ እድሜ ሰጥቶኝ
    የሰው ክፋት ሳላይ
    አውሪያዊ ጭካኔ፤
    ምነው በራብ ጥማት
    በተፈጥሮ ክስተት
    ሞቼ ቢሆን ያኔ።

    ከከፋው የሰሜን ኢትዮጵያ ረሃብ የደርግ መንግሥት በቀረጸው የወገን አድን የርኅራኄ ፖሊሲ ወደ ወለጋ፣ ባሌና ጎጃም ተወስደው ኑሯቸውን ሲገፉ ለነበሩ እና ዛሬ የጭካኔ፤ የእልቂት ጥቃት ዒላማ ለተደረጉ ሰዎች ጥልቅ ሐዘን መታሰቢያ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.