አማራነትና ኢትዮጵያዊነት – ጠገናው ጎሹ

July 23, 2022
ጠገናው ጎሹ

ይህችን አጭር አስተያየቴን ስሰነዝር በትእግሥት አንብቦ ለመጨረስና ገንቢ ምላሽ ለመስጠት የሚቸገሩ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን እገምታለሁ ። የፖለቲካ ባህላችን ከለመድነው ወይም “ከሚ ቸን”  የተለየ ሃሳብን በጥሞና እና ሂሳዊ በሆነ መንገድ የማየትንና ገንቢነት ያለው  የጋራ  አረዳድን የመፍጠርን አስፈላጊነት በማበረታታት ረገድ  ብዙ የሚቀረው መሆኑን ስለምረዳ የማይጠበቅ አይሆንብኝም  ።

አማራ ማስተዋል ጀምሯል። አማራው በአማራነቱ እንዳይደራጅ የሸፈነውን ኢትዮጵያዊነት ግርዶሽ ቀድዶታል

ይህንን ጥቅስ የወሰድኩት በእጅጉ ከማደንቃቸውና እጅግ በጣት ከሚቆጠሩ እህቶቻችን አንዷ የሆነቸው መስከረም አበራ ሰሞኑን ካደረገችው ቃለ ምልልስ ነው። ለዚህ ሂሳዊ አስተያየቴና አመለካከቴ መነሻ የሆነኝም ይኸው የፖለቲካ አመለካከትንና እምነትን የሚገለፀው ጥቅስ ነው ። እንደ እኔ የፖለቲካ አመለካከትና እምነት ይህ “ኢትዮጵያዊነት ግርዶሽ … ” የሚለው አገላለፅ በእጅጉ ደምሳሳና አሳሳች ነው። ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት ላለበት የአማራ ማህበረሰብ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ትግልም የመልካም ግብአትነት እሴት የሚኖረው አይመስለኝም።

አዎ! የአማራ ማህበረሰብ እኩይና አደገኛ የጎሳ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ኢላማ ከመሆኑ አንፃር በሚፈልገው መንገድ የመደራጀቱና እራሱን የመከላከሉ ጥያቄ አወዛጋቢ አይደለም ።

ፈታኙ ጥያቄ እውን ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እና ለአማራ ማህበረሰብ መብት የሚደረገውን ትግል በቅደም ተከተል እየነጣጠሉ (አሁን የብሔረሰብ እና ቀጥሎ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት እያሉ ወይም በተቃራኔው እያስቀመጡ) የሚፈለገውን በጎ ውጤት እውን ማድረግ ይቻላልን? የሚለው ነው። ከስሜታዊነት ሳይሆን በጥሞና ካየነውና እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ የምንሻ ከሆነ ይህንን ጥያቄ  ሰንካላ ሰብብ እየደረደሩ ከመሸሽ ይልቅ መጋፈጡ ነው የሚሻለው።

ኢትዮጵያዊነት አስጠቅቶሃልና ለጊዚያዊ ጥቅም ያበዱ የጎሳ ፖለቲካ ቁማርተኞችን ፈለግ ካልተከተልክ  አለቀልህ”  የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ ግን የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ብቸኛ መንገድ የሆነው የዴሞክራሲ ሽታ የለውም።   የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ከሌላውም ይምጣ ከአማራው ማህበረሰብ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን እንቅፋትነት እንጅ አጋዥነት ፈፅሞ  የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ!!  (በአገሬ አዲስ)    

የአማራውና ሌሎች ኢትዮጵያን የሚሉ ወገኖች መጠቃት ምክንያቱ “የኢትዮጵያዊነት ግርዶሽ ነው” የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብና እምነት የተገፉ ማህበረሰቦችን በአጠቃላይ እና በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ በፍፁም  ከገቡበት መከራና ውርደት አይታደጋቸውም ።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የአማራውና የሌሎች ኢትዮጵያን የሚሉ ወገኖች መጠቃት ዋነኛው ምክንያት በወጉ ነቅቶ ፣ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅ ነድፎ ፣ የፖለቲካ ንግድን ተፀይፎ፣ በጎጥ ልጅነት መጠራራቱን ሲሆን ትቶ ቢያንስ ግን ተቆጣጥሮ፣ የአማራነትና የኢትዮጵያዊነት ቁርኝት ጊዜና ሁኔታ እያየ ቦግና ብልጭ የሚል ሳይሆን እጅግ ውድ የማንነት እሴት መሆኑን አምኖ ተቀብሎ ለዘመኑ የሚመጥን የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ የማድረግ  የፖለቲካ አውድ  ውድቀት እንጅ በብሄረሰብ ወይም በጎሳ የፖለቲካ ቀረጢት ውስጥ የመግባትና ያለመግባት ጉዳይ አይደለም።

አዎ! ፈተናው በቅንነት፧ በመርህ፣ በዓላማ፣ በግልፅነት እና በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት (በእውነተኛ የአገር ፍቅር መንፈስ) ላይ ቆሞ ለመታገል ያለመቻል ክፉ ውድቀት እንጅ መጀመሪያ በመንደር ማንነትና ቀጥሎ በኢትዮጵያዊነት የሚል እጅግ ኋላ ቀርና ጨርሶ ከውድቀት የማያድን የፖለቲካ ጨዋታ ተሳታፊ ከመሆን ወይም ካለመሆን ላይ አይደለም።

እንደዚያ ቢሆንማ ኖሮ አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) በሚል በአማራው መከራና ሰቆቃ ስም እየማሉና እየተገዘቱ እራሳቸውን እንደ ብቸኛ የነፃነትና የፍትህ ታጋዮች ሲሰብኩን የነበሩት እነ በለጠ ሞላ ከአነሳሳቸውም አስልተው የተነሱበትን በመርጫ ስም የሚገኘውን ወንበርና ጥቅም ካረጋገጡ በኋላ ለዘመናት መንበሩ ላይ ሲባልጉ የኖሩትን ገዥ ቡድኖች በሚያስንቅ ሁኔታ ሲሳለቁብን ባላየንና ባልሰማን ነበር።

አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንጅ ከርካሽና አደገኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጋር ዥዋዥዌ የመይጫወት ጉዳይ አይደለም። የጎሳ/የቋንቋ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ የወንጀለኛ ፖለቲካ ነጋዴዎች ምሽግ እንጅ የህዝብ የነፃነትና የፍትህ ትግል የሚወለድበት አውድ ፈፅሞ አይደለም ። እናም “አማራው መጀመሪያ ከጋረደበት የኢትዮጵያዊነት ግርዶሽ ተላቆ በአማራነቱ ከተደራጅና ከተጠናከረ በኋላ ነው ያወለቀውን ግርዶሽ እንደገና አንስቶ ከሌሎች ጋር በመደራደር ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን የሚያደርገው” የሚል አይነት ፖለቲካ ጨርሶ ስሜት አይሰጥምና እንደገና ቆም እያሉና ትንፋሽ እየወሰዱ ማሰብን ይጠይቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አድዋን ከሚኒልክ የመለየት አባዜ የኦነጋውያን ቅዥት - ጥሩነህ

አዎ! የአማራው ማህበረሰብ መከራና ውርደት ማቆሚያ ያጣው አማራነቱን ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ለጠላት በማይመች ሁኔታ ማቆራኘቱ ሳይሆን ይህንን ወርቃማ እሴቱን ለድል በሚያበቃ ሁኔታ የሚያስኬድለት የፖለቲካ መሪ ወይም አመራር ወይም ድርጅት አምጦ ለመውለድ ያለመቻሉ ውድቀት ነው።  የአማራው ማህበረሰብ  ዘመን ጠገብና ትልቁ ጥያቄ ለእራሱና ለሁሉም ወገኖቹ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን የማድረግ  እንጅ በአማራነት የጎሳ ፖለቲካ ከረጤት ውስጥ እራሱን ለማግኘት የመቻል ወይም ያለመቻል ጉዳይ አይደለም።

ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያዊነት መከበርና መጎልበት መሠረታዊው ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንጅ “ዴሞክራሲያዊ ብሔረሰብነት ወይም ጎሰኝነት” ፈፅሞ አይደለም። በኢትዮጵያዊነት (በዜግነት) ጃንጥላ ሥር የማያስብና የማይሰባሰብ የትኛውም የፖለቲካ ንቃትና አደረጃጀት እንኳንስ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ለማምጣት ጊዜያዊ  ህመምንም ትርጉም ባለው ሁኔታ አያስታግስም። ለዚህ ደግሞ ከእኛው ከእራሳችን የበለጠ አስረጅ የለም። አያስፈልገንምም።

ለመሆኑ አማራ አማራነቱን እና ኢትዮጵያዊነት ኩሩነቱን ፣ የሥነ ልቦና ጥንካሬውን ፣ የሞራል ልእልናውን እና ማህበራዊ እሴቱን ከዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ጋር አቆራኝቶ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊነቱን ለማረጋገጥ መታገሉ ለምንና እንዴት ነው ተጠቂ የሚያደርገው? ለምንና እንዴትስ ነው የማይቻል መንገድ አስመስለን የምንሰለው?

“ኢትዮጵያዊነት ግርዶሽ  ሆኖ አስጠቃህ” የሚል ከስሜታዊነት የማያልፍ ፖለቲካ  ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው?  እነ እገሌ በጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና እና ፖሊሲ ሊያጠፉህ ነውና ኢትዮጵያዊነትህ ይቆይህና በእነርሱ የፖለቲካ ኢንጅነሪንግ ምህዋር ላይ ካልተሽከረከርክ ወዮልህ” የሚሉት የፖለቲካ አስተምህሮት ወደ የትና እስከየት ይወስደናል?

ማንም ከየመንደሩ እየተጠራራ እና ቡና ሻይ እየተገባበዘ የዚህን ወይም የዚያን ጎሳ ወይም ማህበረሰብ በደልና መከራ በመጠቀም የፖለቲካ ፓርቲ  መሥርቶ በምርጫ ስም ወንበሩንና የሚያስገኘውን ጥቅም ካረጋገጠ በኋላ ” ለአገር መቀጠልና  ለሰላም ስል ከገዳይና አስገዳይ ገዥዎች ጋር እየተመካከርኩ ስለምሠራ አትጨቀጭቁኝ”  የሚልበትን የፖለቲካ አውድ እንደ ትክክለኛ የዴሞክራሲያዊት አገር መሥረታ መንገድ መውሰድ ፈፅሞ የአማራ ማህበረሰብ የነፃነትና የፍትህ መንገድ ሊሆን አይችልም።  ይህንን አይነት የለየለት የፖለቲካ ነጋዴ የሚተራመስበትን የፖለቲካ አውድ  እንደ የእኩልነትና የዴሞክራሲ አገር አዋላጅ አድርጎ ማስተማር ምናልባትም ለጊዜያዊ ግልብ ስሜት ይመች እንደሆነ እንጅ  የዘላቂ መፍትሄ ግብአትነት የለውም።

 

እንኳንስ በተረኛ ፧ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ  ቁማርተኞች የመኖር ህልውናው ላይ አደጋ የተደቀነበት ማህበረሰብ ማንም ቢሆን በሃሳብ ከመሞገትና ከመታገል አልፎ በሌላው ላይ ጉዳት እስካላደረሰ ድረስ መደራጀት መብቱ ነው ።

የአማራነቱና የኢትዮጵያዊነቱ ታሪክና እሴት እና እጣ ፈንታ ተለያይተው የማያውቁት  የአማራ ማህበረሰብ  ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን የሚያደርገውን የጋራ ግል ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከማገዝ ይልቅ በእኩያን  የጎሳ ፖለቲካ ከረጤት ውስጥ እራሱን እንዲጠረንፍ ማድረግ ፈፅሞ አይጠቅምም።

አዎ! ይህ ማህበረሰብ በፈለገው መንገድ የመደራጀቱ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትን መዳረሻ ማእከል ወደ አደረገ የትግል መስመር እንዲሰባሰብ ከማገዝ  ይልቅ “ኢትዮጵያዊነትህ አስጠቃህ ወይም ኢትዮጵያዊነት ለህልውና እና ለነፃነት ትግል ግርዶሽ ሆነብህ” የሚለው እጅግ ስሜታዊ ቃለ ነቢብ ጨርሶ ትክክል አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላም ምንድነው? (ታደሰ ብሩ)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.