የአማራው ሃብት የሆነው የአባይ ወንዝ ግድብ ችሮታ ያስታረቀን ፣ መቻቻልን ያላብሰን ይሆን ወይስ ያፋጀናል ?

 “በጋራ እንደ ኢትዮጵያዊነት ለመኖር የኔነትን ስሜት ማስወገድ ” “ከኬኛነት እኛነት ይቅደም”

Nile ethiopian registrarተዘራ አሰጉ

ታላቁ የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እድትቀጥል ነፍሱን፣ ህይወቱንና እሱነቱን ገብሯል፣ አሁንም በትዕግስት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይህ ክሳቴ ማንም ኢትዮጵያዊ የማይክደው ሃቅ ነው።

ኢትዮጵያዊው የአማራ ምድር በአምላክ የተባረከ ፣ የአባይ ምንጭ ፣ የተፋሰስ ወንዞች ማቆሪያ የሆነው የጊዮን /የጣና/ ሃይቅ አካቶ የድንግል ማሪያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ ሆነ እናቱ ወላዲተ አምላክ የእግራቸው ማረፊያ እና ፀሎት ያደረሱበት ምድር ነው።

መላ ኢትዮጵያዊው ሊያውቀው የሚገባው የአማራው መሬት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ምድር በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ፣ እንደ አባይ ወንዝ ያሉ ዓለምን የሚያስደምሙ ረጃጅም ወንዞች ፣ ሃይቆች ወዘተ ባለቤት የሆነና በግብርና ምርት በኩል የጥጥ፣ የሰሊጥ ፣ የሙጫ፣ የዕጣን፣የጤፍና ወዘተ ምርቶች እያመረተ  ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆድ እያጠገበ የሚኖር ኩሩ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ ነው።

ወደ ዝርዝሩ ፅንሰ ሃሳብ ከማኮብኮባችን በፊት አንዳንድ መደርደሪያ ሃሳቦችን እንጠቃቅስ።

የአማራ ሕዝብና ምድር የላሊበላ ወቅር ቤተክርስቲያናት ፣  የፋሲለደስ ግንብ ፣ የሰሜን ተራሮች ፣ የብርቅየ የቱሪስት መስዕብ የሆኑ የዱር እንስሳት ፣ ዐይን ግቡ የሆኑ አዕዋፋት  ወዘተ ባለቤት ነው።

እፁብ ድንቅ የሆኑት ውቅር ቤተክርስቲያኖች ፣ መስጊዶችና ግንቦቹ ከአሰራራቸው ውቅር ፣ ከተገነቡበት ዘመን እና ከእንፀት ልህቀታቸው አንፃር ሲተነተኑ በሰው እጅና ህሳቤ ተገነቡ ለማለት ስለሚከብድ ገንቢዎችም እግዚአብሔርን አማኝ ፣ አገላጋይ ና ተማፃኝ ስለነበሩ “አምላክ በሰጣቸው መንፈሳዊ እገዛ፣ ኃይልና እጅ ተገንብተዋል” ለማለት ያስደፍራል።

ይህን መሰረት አድርገን የአባይን ግድብ ማለትም “ኮሚኒስታዊያንና ሻጥረኞች” በማንወደውና፣ በሻጥር በተተበተበ፣ በማይስማማን አጠራር “ ህዳሴ ግድብ” ብለው ቢጠሩትም በሚገባው ስም “አባይ” ቅኔያዊ የስም እና ወርቅ ትርጓሜ ስላለው በሚመጥነው ስም “አባይ ግድብ” እያልን በመሰየም ማብራሪያችን ጀባ እንላለን።

ቅድስ ቃሉ እንደሚናገረው አባይ ከጊዮን ምድር ፈልቆ ምድረ አህዛብን ማለትም ሱዳን ፣ ግብፅን፣ ሪዋንዳን ፣ ብሩንዲን ወዘተ ሲቀልብ እና በኢኮኖሚ ሲያስፈነጥር ፣ ሃብቱን ሲገብርላቸው፣ ብትዝብት ዐይኑ እየታዘበ ‘አባይ የጊዜ መነፅሩ” ክሳቴውን እየታዘበ ዘመናት አልፈዋል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እጃችሁን ከአማራው ላይ አንሱ! - ግርማ በላይ

የጊዮኑ አባይ ከሰከላ ፈልቆ የርብ ወንዝን ፣ የመገጭን፣ የአንገረብን ፣ የበለስ፣ የተከዜን እና ሌሎች ገባር ወንዞችን ለጣና ገብሮ አሻፈረኝ ብሎ ሲጓዝ “ የበይ ተመልካች ኢትዮጵያውያን ና የአባይ ልጆች”፣ አባይ፣ አባይ የአለም ሲሳይ ያለቀየው ፣ ያለ ሃገሩ መገበሩ” እያሉ የአባይ ወንዝ ፣ የጣና ሀይቅና የገባር ወንዞቹ ባለቤቶቹ ማሲንቆ ይዘውና ወንዙ ዳር ቁመው በምፀት እና በእንጉርጉሮ “ለምን ግን የእኛ አባይ? እያሉ ቅኔ ሲቀኙለት ፣ መቸስ ነው ከኛ ተፈጥረህ ለኛ የምትሆነው ? ብለው ሲማፀኑት ፣ ሲሟገቱት እና በትዕግስት ይለማመኑት ነበር።

የአባይ ልጋሴ በአምላክ ፍቃድ እሱን ለሚያምኑት  ለኢትዮጲስ /ለኢትሄል/ ልጆች በባለቤትነት ቢቸርም “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” እንደሚለው ቅላፄ እንዲሁም “ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እየተባባሉ በቁጭት ወንዙን አመንጭዎች  ቢወቀሱትም አባይ ግን፣

ለሁሉም ጊዜውን

     ይጠብቅለታል

     በማለት ሰለሞን ቀድሞ

     ተናግሮታል፣

   ኧረ ተው ልጆቼ

   አባት ፣ እናቶቼ

   ወንድም እህቶቼ፣

   እኔን ማማርሩ፣

   ምንድን ነው መውቀሱ፣

   ጊዜ ለሚፈታው

   አይበጅ መጣደፉ፣

   ጊዜው እስኪመጣ

   አምላክን እመኑ” እያለ

አባይ እያጉረመረመና ወጭት ሰባሪዎችንና አልጠግብ ባዮችን እነ ምስር /ግብፅን/ና ሱዳንን  እያስጠነቀቀ ፣ አልጠረቃ ባይነታቸውና ምስጋና ቢስነታቸውን በለሆሳስ እየሸረደደ ይቀልባቸው ነበር።

የአባይ ልጆች የሃዘንና ይቁጭት እንጉርጉሮ ዕንባ ፈሰሰ ። ምድረ ግብፅ፣ ሱዳንና መሰል ሃገሮችን ጊዜው ደርሶ ውሃና አፈር ብቻ ሳይሆን የአባይ ውሃ ወደ ላይ ተኖ በምድራቸው ዶፍ ቀላቅሎ ደም አዘነበ።

ከዚያም የአባይ ልጆች “ኢትዮጵያ ታበፅህ እደዊሃ አበ እግዚአብሔር “ በሚል ስነ መንፈሳዊ ቃል ፣ ማቅ ለብሰው ፣ አፈር ልሰው ፣ በውሃ ጥም በደረቀው ጉሮሯቸው ና በዕራብ በተሰለገው ሆዳቸው  “ ወይ ውረድ ፣ ካልሆነ ፍረድ” እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አርገው ፣ ፀለዮ ዕንባቸውን ወደ ሰማይ “የሎሄ፣ የሎሄ” እያሉ እረጩ።

አምላክም ሰማ። አባይም ለባለቤቶቹ ለጊዮን ልጆቹ አደላ፣ ‘እቡይነቱን፣ አባይነቱን” ወደ ጎን ብሎ “ ቃል ኪዳኑን አደሰ”።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የምክር ቤት ውሎ ትዝብቶቼና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች - በዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ

እንዲህም ሲል ለኢትዮጵያ ተቀኘ ጊዮናዊው አባይ፣

ምንኛ መልካም ነው

  ትዕግስተኛ መሆን፣

  ወሃ እየተጠሙ

  በዕራብ እያለቁ፣

    የሎሄ  ማለቱ

    አምላክ ማመስገኑ፣

ለነገ እያሰቡ

በፍዳ መኖሩ፣

  ይሄንም ሰምቼ

  በዕንባ ተነክቼ፣

ይሄው ልክስ መጣሁ

ግፉነን አይቼ።

ብሎ በመቀኘት “ አባይ የወላጆችን ፣ የባለቤቶችን የኢትዮጵያንን ዕንባ ለማበስ ፣ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ የጊዮን አማራ ምድር ፈሰሰ / ለወገኑ አደላ።

እንግዲህ የሰነበተው እና የሰሞነኛው ቅጥ የለሹ የፓለቲካ ጡዘት በግብፅ እና በሱዳን ብቻ ሳይሆን በኛዎቹም የብሄር ፓለቲከኞች በአሻጥር ሲወሳሰብ ፣ “ያልወለድትን ልጅ የእኔ ነው እንደማለት አባይን ግድቡ ያለወንዙ አይታሰብምና ከባለቤቶቹ አማራዎች እጅ እንደወልቃይት ፣ ጠገዴ እና ራያ ፈልቅቆ ለመውሰድ የልተቆፈረ፣ ያልተሞከረና ያልተፈነቀለ ነገር የለም።

ከስሙ ጀምሮ አማራ አማራ እንዳይሸት ግድቡን “የአባይ ግድብ” ከማለት ይልቅ “የህዳሴ ግድብ “ ብሎ መሰየሙ ፣ የግድቡን መገኛ ስፍራ’ በአማራ ክልል ጉባ ወረዳ ‘ እንዳይባል ፣ ከባለቤቱ የአማራ አካባቢ በማራቅ “ለሱዳን ቅርብ እና የግብፅ ስነ ልቡና ላላቸው በቤንሻጉል ክልል ጉባ ወረዳ” ብሎ የአባይን መገኛና ምንጭ ከባለመክሊቱ የአማራ ሕዝብ ለማሸሸት የተሞከረው ሙከራ አጃይብ የሚያሰኝ፣ የሚያስተዛዝብ ከመሆኑ ባሻገር ህውሃትም ሆነ ተረኞች የአባይን ግድብ በካርታቸው ለማካለል ተፍጨርጭረዋል ፣ ግን የአባይ አዚም ይህን ሁሉ ሻጥር እየፈረካከሰው ነው።

እንግዲህ ሰሞኑን ፣ አባይ በአምላክ ፈቃድ ፣ በኃይለ መንፈሱ እንደ እነ ላሊበላ፣ ፋሲለደስ ግንብ ፣ እንደ ጊዮን ወንዝ ፀጋ ወዘተ ተገነባ ፣ ብርሃንም በብርሃን አምላክ ተራዳይነት አፈለቀ።

የአማራው ሕዝብ   ምንም ግለኞቹ ፣ ሊመፃደቁ ቢውተረተሩም ፣ ትዕግስት ተላብሶ “ አባይ የኢትዮጺስ / የኢትየል / አምላክ ለኢትዮጵያ የሰጠው ፀጋ ነው ፣ ከተጋመድን ለሁላችን ተርፎ ለተረፈው ዓለም በረከት ነው” እያሉና የአንድነት ና የሰላምን ዜማ እየዘመሩ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ውርደት ጥቁር ቀን (ሮበሌ አባቢያ)

ምንም አዲስ አበባ “ በረራ” በአማሮች ተቆርቁራ ፣ “ የአማራ እይደለም” እነ “ኬኛ” ቢሉም ፣ አማሮች ለኢትዮጵያ ብለው ቢሰውም እና ቢገፉም፣ ቂም ይዘው ፣ ቂም ቋጥረው “ ጊዬናዊውን አባይን እና ግድባችን ተውልን” አላሉም። ለምን ቢሉ አማራ ሆደ ሰፊ፣ አስተዋይ፣ ለኢትዮጵያ ሲባል ፣”መገፋት ፣ ያተርፋል” ፣ “ የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና” የለውም የሚል ዕምነት አንግቦ የሚሆነውን ሁሉ በአርሞሞ እየተመለከተ ነው።

ነገሩና ግለኝነቱ. “ከእፍ እስክ ገደፉ” በላይ ሆኖ እንደ ዓመት ባህል ዛር እያጓሩ ባለጊዜዎችና ተረኞች ፣ መሰሬነታቸውን አንግበው“ አባይ ግድብ ኬኛ” የሚል ፈሊጥ ካመጡ ፣ ያኔ ነገሩ ይለዋወጣል “ እናንተም በጭብጧችሁ ፣ እኛም በጭብጧችን “ የሚባልበት ጊዜ እንዳይመጣ እንመክራለን።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት በአንድነት ካባ ያምራል “አዲስ አበባም ፣ ደብረማርቆስ ጎንደር፣ መቀሌ ፣ ወለጋ ፣ ሲዳሞ ፣ ባህርዳር፣ ስልጤ ፣ ጋምቤላ ፣ አሶሳ፣ ሐረር ፣ ድሬድዋ ፣ ጉራጌ ፣ ወላይታ ወዘተ እስከ ቡና ፣እንሰት ፣ ጥእሎ ፣ ጥጥ ፣ ሰሊጡ፣ ሙጫ፣ ዕጣኑ ፣ የአባይ ግድቡ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን የጋራ ማንነታችን ፣ ፀጋችን ፣ መክሊታችን ነው” ብለን “ ኬኛን ገለል አርገን የእኛ” ብለን ብንቀጥል ይበጃል እንላለን። ልግብፆቹ ፣ ለእንግሊዞቹ እና ለሱዳኖች ያልበጀ ስግብግብነት ፣ ግለኝነት፣ የኬኛነት ወዘተ ህሳቤና ስሜት ኢትዮጵያዊ ሆነ በወንድማማች ለኖረው ሕዝብ አይመከርም።

ኢትዮጵያና ፀጋዎቿ የጋራ የኛነታችን መሰረት ነው።

ካልሆነ እዳንተዛዘብ ብለን እንመክራለን።

 

ተዘራ አሰጉ – ከምድረ እንግሊዝ

Leave a Reply

Your email address will not be published.