ሰማእታቱን የማያከብር ራሱን አያከብርም፤ ለራሱ ክብር የሌለውም ሌሎች እንዲያብሩት መጠበቅ የለበትም! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ ([email protected]

በዛሬው እለት አይሁዳውያን ፒትስ በርግ በሚባል የአሜሪካ ከተማ ከአራት ዓመታት በፊት በግፍ የተገደሉትን ሰማእታት እያስታወሱ ነው፡፡ ዲግሪ ጭነናል እያሉ የሚኮፈርሱና ጣታቸውን እያፍተለሉ ሲደስኩሩ የሚውሉ የአማራ ምሁራን ግን በዘሩ ምክንያት ያለቀውን ህፃን፣ እርጉዝ፣ ሽማግሌና ባልቴት አማራ ችላ ብለው የነፍሰ ገዳዮችንን፣ የሌቦችንና የቀጣፊዎችን የስልጣን ድርድር አፋቸውን ከፍተው እየተመለከቱ ነው፡፡

እንደ ፈረንጅ አቆጣጠር ጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ም.  ከቤተ ምኩራባቸው የተጨፈጨፉት አይሁዳውያን ቁጥር 11 ነው፡፡ የሰው ህይወት በቁጥር መለካት የለበትም እንጅ ይህ አሐዝ በእየቀኑ በተለያዬ ምክንያት በዘሩ ወይም በቋንቋው ምክንያት ተሚያልቀው አማራ ጋር ሲወዳደር ተቁጥርም የማይገባ ነው፡፡

አማራ ከአርባ አምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በዘሩ ምክንያት ተጨፍጭፏል፡፡ በወልቃይት በላንባ ዲና እየተፈለገ ተመንጥሯል፤ ተሲዖሉ ባዶ ስድስት ገብቶ ተጠብሷል፤ እንዲሰደድ ተገዷል፤ የተረፈውም ካድራ ወንዝ ተረሽኗል፡፡ በበደኖ ዘሩ፣ ቋንቋውና ሃይማኖቱ እየታዬ ከነነፍሱ ገደል ተወርውሯል፡፡ በአርባ ጉጉና በአሩሲ ነገሌ ታርዷል፡፡ እንደ ጉራ ፈርዳ ታሎ ቦታዎችም በእነ ሽፈራው ሽጉጤ አይነት አውሬዎች ትዕዛዝ ዘሩ እየተመረጠ እትብታቸው ያልደረቀ ህፃናትንና አቅም ደካማ አዝውንትና ባልቴቶችን አዝሎ በእግሩ አገር አቋርጦ እንዲሰደድ ተገዷል፡፡

በአለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ደግሞ እጅግ በከፋ ሁኔታ በጭራቆች ከመኖሪያ ቤቱና ከአምልኮት ሥፍራው  አንገቱ እንደ በግ እየታረደና  እንደ ደመራ እየተቃጠለ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ  የዘር ፍጅት ሲፈጠምና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር አማራ ሲያልቅ የአስራ አንዱን አይሁዳውያን ያህል የአማራ ሰማእታትን በሚገባ ሁኔታ የሚያስታውስ ጠፍቷል፡፡  እንኳን ከሰላሳ ዓመታት በፊት በወልቃይትና በበደኖ  የደረሰው ጪፍጨፋ ትናንት በወለጋ በብዙ ሺህ አማራዎች የደረሰው እልቂትና ስደትም ተዘንግቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሽብር ቡድኑ የዘር ማጥፋት ወንጀል

ከሰውነቱና ከክብሩ ሆዱን የመረጠ ድምጡን አጥፍቶ እንደ ቅንቡርስ ሲጎሰጉስ ኖሮ መቃብር ለመግባት ወስኗል፡፡  ከቅንቡርስ የከፋው አሳማም “የዘር ፍጅትም ሆነ የዘር ማጥራት ወንጀል አልተፈጠመም” የሚለውን የጪራቆች ዘፈን እየዘፈነ  የወጣበትን ሕብረተሰብ ደም እረግጦ እንጀራውን ለመጋገር ጅራቱን እንደ ቡችላ ያወናውናል፡፡

ከአሳማዎች ያልተሻለው መጋዣም “የጎሳ ግጭት በሽግግር ወቅት ሊሆን የሚችል ነው” የሚል አረመኔአዊ ሰበብ እየደረደረ ተቤታቸው ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ፤ ተቤተ ክርስትያንና ተመስጊድም ሲጸልዩ በታረዱትና በተቃጠሉት ነፍስ ቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ ሲታረዱ ይገለፍጡ እንደነበሩት አሕዛብ ሮማውያን በሰማእታት ነፍስ ያፌዛል፡፡

አማራ በዘሩ እየተመረጠ በሚጨፈጨፍበትና በሚሰደድበት ወቅት አንድ ሆኖ በመታገል ፋንታ  አንዳንዱ ከርፋፋና ሊጠዋጥ ካድሬም ተመንደር ምሽግ ውስጥ ገብቶ እየተቧቀሰ የዘሩን መጥፊያ ዘመን ያሳጥራል፡፡

ዘሩ እየተመረጠ በመጨፍጨፍና በመሰደድ ላይ ያለው አማራ ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው ተነበሩት አይሁዳውያን ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል፡፡ ትምህርት መቅሰሙም ሰማእታትን ተማክበርና ተማስታወስ ይጀምራል፡፡ በዘራቸውና በቋንቋቸው የታረዱትን ማስታወስና ማክበር ራስን ማክበር መሆኑን መረዳት ያስፈጋል፡፡ ሰማእታቱን የማያከብር ራሱን እንደማያከብር፤ ለራሱ ክብር የሌለውም ሌሎች እንዲያከብሩት መጠበቅ  እንደሌለበትና ክብረ የለሽ ሆኖ  መኖርን መመረጡን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡

ተነክብርህ መቃብር እንድትገባ የሞተን አትርሳ፤ የወደቀንም አንሳ! አመሰግናለሁ፡፡

ጥቅምት አስራ አምስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.