ደግሞም የሰላሜ ሰው የታመንኩበት – አስቻለው ከበደ አበበ

ያለፉትን አራት ዓመታት የመራውን ግለሰብ አብይ አህመድን ብንመለከት በሕዝብና በአገር ስም የሚሰጠውንም ሆነ በብድርና በእርዳታ የሚገኘውን ገንዘብ እንደ ግል ሃብቱ ሲበትን፣ለምን  እንዲህ ይሆናል ብለው የጠዬቁትን ምን አገባችሁ እያለ ሲሳደብና ሲያንጓጥጥ ማዬቱ የተለመደ ነው

የዛሬ ወር ገደማ የተከበረው የመስቀል በዓልን አሰመልክቶ ጠ/ሚ አብይ እንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው ላይ እንዲህ ብለውን ነበር፡፡ “ …እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን አንስተውብናል…”ጠ/ሚ ይህን አባባል ቀጥታ ከመጽሐፍ ቀዱስ ነው የወሰዱት፡፡ ይህውም በመዝሙረ ዳዊት መዝ 40(41)፣9ና ዬሐ 13፣18 ካለው ነው፡፡

ደግሞም የሰላሜ ሰው፣ የታመንኩበት፣ እንጀራዬን  የበላ፣ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ፡፡

ይህ ጥቅስ ትንቢታዊ ሲሆን ከአንድ ሺህ አመት በኋላ በክርስቶስ ላይ ይሁዳ በፈጸመው ክህደት ትንቢቱ ተፈጽሞል፡፡ በዬሐንስ ወንጌል ላይ ስለዚሁ ትንቢት ፍጻሜ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይሁዳ ከአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት አንዱ የነበረና በገንዘብ ተደልሎ ክርስቶስን አሳልፎ የሰጠ የክርስቶስ ቅርብ ሰው ነበር፡፡

ጠ/ሚሩ እስከ አሁን ባደረጉት የስልጣን ጉዞ በተለይም በቅርብ ግዜያት፣ ከወያኔ ጋር ሶስተኛው ዙር ጦርነት ከተነሳ ቦኋላ በጣም ቅርብ በሆኑ ባለስልጣናቶቻቸው(Inner circle) የተከዱ እንደሆነ ነው ጥቅሳቸው የሚናገረው፡፡ ይህን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ የፃፉበት መልእክት አግባብ የሚያመለክተው የአሁን ሁኔታን ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ በጦርነት መኃል እያለንና ከዚያ በኋላ ጠ/ሚ የሚቀንሷቸውን ባለስልጣናት መጠበቅ ለመተዛዘቢያነት ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡

የብሔር ፖለቲካ ኢትዮጵያን መምራትና የህዝቡን ኑሮ ማመስ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ጠ/ሚ የጠቀሱት ጥቅስ ለማን በትክክለኛው አግባብ ይሰራል ብለን ብንጠይቅ ለአነድ መሕበረስብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ኢትዮጵያ ላይ በፖለቲካና ኢኮነሚ ረገድ ስልጣንን የተቆጣጠሩ ሶስት ኃይሎች ተመልክተናል፡፡ ሻብያ (1983 ዓ.ም. – 2000ዓ.ም.) ወያኔ (1983ዓ.ም. – 2010ዓ.ም.) ኦሕዴድ- ብልጽግና (2010ዓ..ም.- እስከ አሁን) በየተራ ኢትዮጵያ ላይ ርስትና ጉልት ሰርተው ሲፈራረቁባት ቆይተዋል፡፡

ሻቢያ የኢትዮጵያንን ኢኮኖሚ እንደ ሬድሲ(Red Sea) ባሉ ታላላቅ የኢኮኖሚ ተቋማት ተጽኖ ስር ሊያደርግ ቢሞክርም በወያኔ የአይንህ ቀለም አላማረኝም ምት ተመትቶ ከኢትዬጵያ ሰማይ ስር ተሰውሮ ስንብቷል፡፡ ወያኔ ሻብያን ሲመታ ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ሃገራችን ናት ብለው የሞቱላትና የተጉላሉላትን ኤርትራውያን ሃብትና ንብረት ከስራቸው ነቅሎ አፈሩን አራግፎ ነው ያስወጣቸው፡፡ ያን ግዜም ከኤርትራዊያን ጋር ሲነግዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የኤርትራውያኑን ንብረት ወርሰው ለወያኔ አስራት አበርክተው ህይወት ቀጠለ፡፡

በኋላ ግን እኒሁ ሲሶው ለወያኔ ያሉ ሰዎች የወያኔ የማፍያ አሰራር መሸከም እንዳቃተቸው ይናገሩ ነበር፡፡ በተለይ አዜብ መስፍንን አልቻልናትም እሷ እኮ ሃያ ሚሊዎን ብር ባንክ ካለህ ቀጥታ መጥታ አዲስ የቢዝነስ መስመር ይከፈትልሃል ብላ 65% ለኔ 35% ይበቀሃል የምትል ነች ይሏት ነበር፡፡ ይህን አንድ ፒያሳ አካባቢ ይነግድ ከነበረ ስልጤ ኢነቨስተር ሰምቼለሁ፡፡ አረ መርካቶ ብትሄዱ ለተሳካለት ነጋዴ ሁሉ የሚባል አባባል ነበር፡፡ የእሱ/እሷ ንስሃ አባት እኮ ጄነራል እንትና  ነው ይሉኃል፡፡ ስንቱ የትግራይ ጄነራል ነገደ እንዲሁም በትግራይ ስም ተነገደ፡፡

አሁን በኦህዴድ-ብልጽግና ዘመን ነገሩ ልዩ ነው አሉ፡፡ አሉ ያለኩበት ምክንያት ከሃገር ውጭ ስላለሁ፣ የአይን እማኝነት መስጠት አልችልምና ነው፡፡ ነገር ግን በወሳኝ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ቦታወች ላይ የተሸሙትን ባለስልጣናት ስብጥር ስንቃኝና ንግግራቸውን ስንገመግም “የአሁኑ ይባስ” የሚለው አባባል ጆሮዬ ላይ ከበሮውን ይመታል፡፡

ፈረሰኛውና አድራሹ፣ ድሉን ግን ሁሌ ጋላቢው ስለሚቀማው ያ ማሕረሰብ አንዳንድ ነገር ልበል፡፡ አምሐራ ለሚለው ስያሜ አም ማለት ተራራ ነው፣ ሐራ ደህሞ ህዝብ፡፡ ስለዚህም አምሐራ ማለት የተራራ ላይ ህዝብ ነው ብለው የሚበይኑ አሉ፡፡ በዚህ እረገድ የቀድሞው ፕሬዚደንት መንግስቱ ሐ/ማሪያም ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ትረጉም እሳቸው ስልጣ ከመያዘቸው በፊትም የሚነገር ነበር፡፡ ምናልባት ስለዚያ ትርጉም ገለጻ የሰጣቸው ዘመዳቸው ዶ/ር ካሳ ከበደ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዶ/ር ካሳ ከበደ እስራኤል ሃገር የተማረና በመጨረሻም ደርግ ሲወድቅ በኦፕሬሽን ሰለሞን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን  ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤሎች በአይሮፕላን ይዞ እስራኤል የገባ ነው፡፡

አማራ ማለት እኛ ነን የሚሉ ትግሬዎችም አሉ፡፡ በሽሬና ተምቤን አካባቢ ያሉ ትግሬዎች ከሶስትኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከአክሱም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ስንሄድ አማረብን ስንል በትግሬኛ አማርና አልን ይላሉ፡፡ ይህ በእንዲ እንዳለ ወያኔ አማራውን ይዞ ይጓዝ የነበረው ግን አቅፎ ሳይሆን አሰናክሎ ነበር፡፡

እርግጥ ነው ወያኔ ስለ ወንድሙ አማራ በማኒፌስቶ ደረጃ ምንም ክፉ ያውራ ምን አማራው ግን መንትያ ወንድሙ ነበር፣ ነውምም፡፡ ሁለቱም የአንድ ግዕዝ ልጆች ናቸው፡፡ ግዕዝ ‘ወልደ’ ወይንም ልጅ ይላል፡፡ ትግሬው ል የምትለውን ፊደል ይገድፍና ወድ-ወዲ አንተ ልጅ ይላል፡፡ አማራው ደግሞ ወ የምተለውን ፊደል ገድፎ ልድ-ልጅ ይላል፡፡ ልጅ ሲጻፍ በውስጡ ከሚይዘው አናባቢው ፊደል ጋር በመሆኑ ለእጀእ ስለሆነ ለእጅ ከሚለው ኢጀ በጉራጌኛ ደግሞ አንተ ልጅ ማለት ይሆናል፡፡ እንግዴህ ከገባህ ሁሉም ሰፈር ያለህው አንተ ልጅ ስማ፡፡

ወያኔ ወደ ቤተ መንግስት ያደረገውን ጉዞ ቀና ያደረገለት አማራው ነው፡፡ አማራው ተሸክሞ አደረሰው ከዚያም የወያኔ የቤተሰብ አገዛዝ (Oligarchy) ቀጠለ፡፡ ዛሬ ላይ የምናየው ትግሬ ሁሉ በወያኔ ዘመን እንደተጠቀመ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሰማው አድርገው ከስልጣን ተገፈተሩ፡፡ ነገሩ ጎጃሞቹ ወገኖቼን እንዳላሰከፋ እንጂ፤ በላይ በገደለ ጎጃሜ ዘፈነ፣ አይነት ነገር ትንሽ አያጣም፡፡

አማራው በወያኔ ዘመን ምን አገኝ ብለን ብንጠይቅ፣ በግፍና መከራ ስደት፣ አንገት አቀርቅሮ መኖርና ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ዜግነትን ነው፡፡ በህዝብ ቆጠራ ላይ የጠፉ አማሮች እስከ አሁን አልተገኙም፡፡ የአማራ እናቶች ሁን ተብለው እንዲመክኑ ተደርገዋል፡፡ በየባዶ ምናምኑ ቁጥሩ ብዙ ሺህ የሆኖ አማሮች ተሰውረው ጠፍተዋል፡፡ ምኑ ቅጡ…

በብልጽግና ዘመን ደግሞ፣ ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ እንደነገሩን ኦሮአማራ የሚባል የማደናበሪያና የማስመሰያ ድልድይ ፈጥረው አማራውን መሸጋገሪያ ያደረገ የኦህዴግ ተወከልት በአማራ ምድር ላይ ተፈጠሩ፡፡ ይሄ ድልድይ፣ ይሄ ፈረስ ማን ነው ብለን እራሳችንን ከጠየቅን የው መልሱ የሚሆነው የአማራ ብልጽግና ነው፡፡

ኦሮሙማው እስከአሁን ትርጉሙ ሊገባኛ ባይችልም፣ ለስልጣን ከበቃ ቦኋላ የአማራውን ሃብት ንብረት ማቃጠል፣ ሴቱን መድፈርና ግድያው በተለይ በኦሮሚያ ደርቶ አይተናል፡፡ ወያኔ ከስልጣን ከመወገዱ በፊት “የኦሮሞ ደም የኔ ደም ነው!” ብሎ የወጣው ጎነደሬ – አማራው፣ ዛሬ ከሽግግር በኋላ ልጆቹ ተነውረዋል፡፡ ያውም በወለጋ እንደሰማንው የስድስት አመት ልጅ “ወላሂ፣ወላሂ ከዚህ በኋላ አማራ አልሆንም” እስክትል ድረስ፡፡ ዋ!

ኦሮሙማ ለምን ተፈጠረ ብለን ብንጠይቅ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ለመተካት ነው፡፡ ጀዋር መሃመድ እራሱ ኦሮሙማ ርእዮት አለም(Ideology) ነው ብሎናልና፡፡ አንድ ግዜ በብሔራዊ ቤተ መዛግብት የአምባሳዳር ብርሃኑ ዲነቃ መጽሐፍ “ቄሳርና አብዬት ” ይገመገም ነበር፡፡ በመጽሐፉ ላይ ጽሁፍ አቅራቢው፣ ቢነጋ ተወልደ የተባለ ዲፐሎማት ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንደ ቃየን፣ አንገዳደል! - ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ

ቢነጋ የኢ.ን.ሳ መሪ የነበረው የብንያም ተወልደ ወንድም ነው፡፡ በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሶስተኛ ሰው ሆኖ ሰርቷልም፡፡ እሱ ጽሑፉን ሲያቀርብ እኔ አወያይ ነበርኩ፡፡ ከዚያ ግምገማ በኋላ አንድ ሶስት ቀን ከዚህ ልጅ ጋር ተገናኝተን ነበር፡፡ በወተደሩ ውስጥ ያለውን ሙስና በጣም ተጸይፎ ሲናገር ሰምቼለሁ፡፡ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲም እንድህ ብሎ ነግሮኛል፡፡ በካፒታሊዝም ርእዮት አለም የሚደረግ ትግል የትም ደርሶ አያውቅም፡፡ ስለዚህም አብዮታዊ ዲሞክራሲ የወያኔ ህዝብን ማሰባሰቢያና ማታገያ መስመር ነው፡፡ እነ አቦይ ፀሃዬ አብታዊ ዲሞክራሲ ከማታገያ መስመር ውጭ ምንም እንዳለሆነ ነው ይነግሩን የነበረው፡፡ አይገርማችሁም ኦሮሙማ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ምትክ ሆኖ ብቅ ማለቱ?

አማራው ለምን በሌላ ወገኑ ላይ ይታመናል? ሁል ግዜስ እየተከዳ እስከመቼ ይኖራል? ደግሞም የሰላሜ ሰው፣ እንጀራዬን ከእኔ ጋር የበላ፣ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ ሲል በነፍሱ ይቃትታል? እያሉ ወገኖች መጠየቅ ሲጀምሩ ኦፌኮዎች(ኦሮሞ ፍድራሊስት ኮንፍረንስ) እንዳሉን ኢትዬጵያ ጸንታ ያለችው በአማራ ትዕግስት አይደለምን እያሉ ቀልድ ይሁን እውነት፣ ወለፈንዴን ይዘምራሉ፡፡የአማራን የጽናትን ምስጢር ግን ላካፍላችሁ፡፡

አማርኛ የደቡብ ሴም ቋንቋዎች ከሚባሉት ጉራጊኛ፣አርጎባኛና ሃርሪ ጋር የሚመደብ ቋንቋ ነው፡፡አማርኛ በመዝገበ ቃላቱ የያዛቸው ቃላቶች እስከ ሰባ በመቶ የሚያክለው ሴማዊ ቃላት ቢሆኑም፣ብዙ ቃላቶችን ከአገውኛ፣ ኦሮሚኛ፣ሲዳማኛ፣ወላይተኛ …ወስዷል፡፡በስዋሰው (Grammar) ህጉም ከብዙ ኩሻዊና ኦሞዊ ቋንቋዎች ጋር ይዛመዳል፡፡

ይህ ለምን ሆነ ካልን ደግሞ? ከ 330ዓ.ም. እስከ 1890ዎቹ ድረስ ከ1500 አመታት በላይ ከሰሜን ከአክሱማዊው ግዛት ወደታች እስከ ከፋና ሐረር የተደረገ ታላቅ ፍልሰትና ቅልቅል በመኖሩ ነው፡፡በኋላም 16ኛው ክ/ዘመን ላይ የምናያው ኦሮሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ላይ ያደረገው ጉዞ የዚሁ ክፍል አካል ነው፡፡

በ13ኛው ክ/ዘመን ሞቶሎሚ የሚባል የወላይታ ንጉስ አስከ ሰሜን ሸዋና ጎጃም ድረስ ያደረገው የግዛት ማስፋፋት ከኢትዮጵያ ህዝቦች ስብጥርና ድብልቅልቅ ጋር አብሮ የሚገለጥ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር የጎጃም አገዎች ጭፈራ በመጠኑም ቢሆን የወላይታን ጭፈራ ይመስላል፡፡ የሰሜን ወሎ አገዎች ጭፈራ ግን ያው የአማራ ድለቃ አይነት ነው፡፡

አቡነ ተክለሐይማኖት የሚባሉና የሸዋ ቡልጋ ተወላጅ የ12ኛው ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ቅዱስ  በዚያን ግዜ እናታቸው በምርኮ ወደ ወላይታ ሄዳ እንደነበር ገድላቸው ያትታል፡፡ በኋላም እኚሁ ቅዱስ ከረድእዎቻቸው ጋር የወንጌል ብርሐንን   በወላይታ፣ ጋሞ እስከ ደቡብ ኦሞ፣ በአሪሲና ሃድያ… ሁሉ መስበክ ችለው ነበር፡፡ ለዚህም ስራቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ብቻ ሳትሆን የካቶሊክም ቤ/ክ ከቅዱሳኗ አንዱ አድርጋ ትወስዳቸዋለች፡፡ ወንጌላውያን  የፐሮትሰታንት እምነት ተከታዮችም የወንጌል አርበኝነታቸውን መስክረው የጻፉት ጽሑፍ አለ፡፡

ኢትዮጵያን ስተዲስ ውስጥ የፊሎሎጂ የዶ/ት ትምህርታቸውን ሲሰሩ የነበሩ መ/ር ደሴ የአማርኛን ጥንታዊነት የሚያስረዳ ጽሑፍ ሲያቀርቡ በኢንስትዩቱ ታደሚ ነበርኩ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በአንዳንድ የአክሱም ሐውልቶች ላይ ‘እኔ’ የሚል ጽሑፍ ተጽፎ መገኘቱን ጠቅሰውና ይህም አማርኛ በመሆኑ፣ ስድስተኛ ክ/ዘመን ላይ በትግራይ ውስጥ በተተረጎመው ገሪማ ወንጌል ውስጥ ብዙ የአማርኛ ቃላት በመገኘታቸው አማርኛ በ5ኛው ክ/ዘመን በነ አፄ ካሌብ ዘመን ጀምሮ በአክሱማውያን ወታደሮች ዘንድ መናገር ሳይጀመር እንዳልቀረ ሃተታ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ ጽሑፍ የቀረበው ከዘጠኝ አመት በፊት ነበር፡፡

እኔ ባለኝ መረጃ አማራ የሚባል ህዝብ እንዳለ ለመጀመሪያ ግዜ ከአረቦች የሰማንው በ10ኛው – 11ኛው ክ/ዘመን ባለው ግዜ ውስጥ ነው፡፡ በደጋማው የየመን ግዛትና በቀይ ባህር ዳርቻ መካከል በዚያን ግዜ ነጂድ አልአማሐራ የተባሉ አሁን ካለው ወሎ ክፍለ ሃገር ሄደው የመንን የገዙ ህዝቦች እንደነበሩ በዚያን ግዜ የነበሩ አረቦች ጽፈዋል፡፡ ያም የሆነው በ2ኛዋ የየመን ንግስት ሳባ፣ ቢልቂስ ዘመን ግዜ ነበር፡፡ ከ1021 ዓ.ም. – 1159ዓ.ም.ከነገሱት የአማራ ነገስታት መካከል ቃዲ አቡ መሃመድ ስሩር አማራ አልፋቲክ ዝናው ገኖ ይነገርለታል፡፡ አምሃራ የሚል የጥንት የቦታ ስም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍሮበት የሚገኝ ቦታ ቢኖር የዛሬው ወሎ ነው፡፡

አማርኛ ቋንቋ ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ግዜ ሲገናኙ በሚፈጥሩት ውስን የሆነ የመጀመሪያ ግዜ የመግባቢያ ሂደቶችና(Pidginization) የሁለት ቋንቋ ማለተም የሴምና የአገው(ኩሽ) ቋንቋ ውህድ ሆኖ(Creolization) በአክሱም ወታደሮችና በአገው(ላስታ ቤተመንግስት) ውስጥ ይነገር ነበር፡፡ በኋላ የሰለሞናዊው ስርወ መንግስት እየተስፋፋ ሲሄድ ከ12ኛው ክ/ ዘመን በኋላ የቤተ መንግስት ቋንቋ ሆነ፡፡ ይህን ነው እንግዲህ የቋንቋ ሊቃውንቱ የሚነግሩን፡፡ ከዚያም ጀብዱ የሚል የኦሮሞ ቃል ሲወርስ ከ ፊደል “ደ” ፊደል ጀ ፈጠረ፡፡ ጨጨብሳ የሚለውን ቃል ለማናገርም ከፊደል “ጠ” ፊደል “ጨ”ን ፈጠረ፡፡ መቼ ቋንቋዎቹ ተጣሉና ፖለቲከኞቹ እንጂ፡፡

የሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ከአጼ ይኩኑአምለክ (1262 ዓ.ም.) እስከ አጼ ኃይለስላሴ(1966 ዓ.ም.) ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ በእዚህ ስርወ መንግስት ውስጥ ሁለት ታላቅ አጼዎች ኤርትራን፣ኢትዮጵያን፣ጅቡቲንና ከፊል ጎረቤት ሃገር ሶማሊያን በመግዛት ይታወቀሉ፡፡ አጼ አምደጽዮንና አጼ ዘረያቆብ ዋንኛው ናቸው፡፡ ሁለቱም አማርኛ ተናጋሪ ቢሆኑም ስለ እናት አባቶቻቸው ስንናገር የአሁኑ የብሔር ብያኔ አይመለከታቸውም፡፡

የአምደጽንን አክሱማዊ ጦርነት ስልትና ባለቱን ብሌንሳባንና የዘረያቆብ ከአክሱም ተፈልጎ መጥቶ ሸዋ ላይ መንገሱንና ሚስቱን የሃድያዋን ንግስት እሌኒ ስናስብ አሁን በግርድፉ አማራ የተባለው ሁሉ የማሌሊት – ወያኔዎችን የሰታሊን ብያኔ ሰለባዎች ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡ እኒህ ነገስታት ከአክሱም ጽዮንና በኤርትራ ከሚገኘው ደብረቢዘን ጋር ታላቅ ቁርኝት የነበራቸው ናቸው፡፡

የሸዋው ደብረ ብርሃን ከተማ ከስድስት መቶ አመት በፊት ሲመሰረት በሺህ የሚቆጠሩ መነኮሳትና በብዙ አስር ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከኤረትራና ትግራይ መጥተው በሸዋ ሰፍረዋል፡፡ አንድ ግዜ በኤርትራ ቲቪ፣ ያውም ኢትዮጵያና ኤርትራ በተጣሉበት የመጀመሪያው አስር አመታት፣ በኤርትራ ገዳማት(ከደዋርባ ጀምሮ…)  ከአምደጽዮን ጀምሮ እስከ አጼ ናኦድ ግዜ ድረስ ከኢትዮጵያውያን ነገስታት ለኤርትራ ገዳማት የተበረከቱ ንዋየ ቅድሳትን በዘጋቢው ፊልም ውስጥ ተመልክቼለሁ፡፡

እውነት ነው አማራው የዳበረና የበለጸገ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፡፡ አማርኛ ተናጋሪዎች ባይትዋርና ግዞተኛ ሲሆኑ መቶ አመታት አልፏቸዋል፡፡ በ1630ዎቹ በፈረንሳይ ሃገር በእንግልት የሞተው ጎነደሬው- አማራ ታሪክ አሳዛኝነቱ ልብ የሚነካ ነው፡፡ ፀጋ ክርስቶስ በ1602 ዓ.ም. በጎንደር የተወለደና አባቱም ንጉስ ያቆብ በመባል ይታወቃል፡፡ ፈረንጆቹ ይህን ሰው (Zaga Christ)  ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ አባቱን ንጉስ ሱሶኒዎስ ከገደለበት በኋላ እናቱ ወንደሙ ቆጽሜና እርሱን ለማትረፍ በሁለት አቅጣጫ ትልካቸዋለች፡፡ ፀጋ ክርስቶስ በሱዳን፣ግብጽ፣ግሪክ፣ጣልያን አድርጎ ፈረንሳይ ይደርሳል፡፡ ቆጽሜ ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰዶ እስከ ኬፕ ታዎን መድረስ ችሏል ይባላል፡፡

ፀጋ ክርስቶስ አውሮፓ በነበረበት ግዜ ተከራካሪ መንፈስ የነበረው ልዑል ነበር፡፡ አውሮፕያውያኑን በነበረው የአክሱም-ላሊበላ ስልጣኔ ይሞግት ነበር፡፡ ያው እኛ ከናንተ የምንሻለበት መንገድ አለ እያለ ነበር ሙግቱ፡፡ በኋላ ሲሞት ፈረንሳይ ውስጥ መቃብሩ ላይ እንዲህ ብለው ጻፉለት፡፡ “እዚህ የአብሲኒያው ንጉስ አርፏል፣ እውነተኛ ይሆን ወይም አስመሳዩ” የተቀበረውም ከፖርቱጋሉ ልዑል ጎን ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፍቅር ፏፏቴ - (በፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

የቆጽሜ ታሪክ አነጋጋሪ ነው፡፡ ከንባታና ሃድያ ውስጥ የሱ ልጆች ነን የሚሉ አሉ፡፡ እኔ እራሴ ከሃያ አምስት አመት በፊት በአካል አግኝቼ ያዋራዃቸው ከንባታዎች አሉ፡፡ እነሱ እንደሚሉት አቤቱ ሁንሐመልማል ከሱሶኒዎስ ተጣልቶ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በመጓዝ፣ በዚያ ከነበሩ ህዝቦች ጋር በመደባለቅ የጥምር ንግስና ግዛት መስርቶ ነበር፡፡ ለእኒህ ህዝቦች አሁን አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው ነው፡፡ የአማራና ትግሬ ዝርያ ከስድስት መቶ አመት በፊት አለብን የሚሉ ህዝቦች፣ በወላይታ(ሃይዞ፣ መንዜ፣ ወሎ፣ ካውና…)፣ በጋሞ፣ አማሮ፣ ሲዳማ.. ይገኛሉ፡፡

ሲዳማዎቹ እንደሚሉት አሁን የምንናገረው ቋንቋ ሆፊኛ ነው፡፡ ድሮ ግን የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች ነበርን ነው የሚሉት፡፡ እኔ እንደ እድል ሆኖ በ1988 ዓ.ም. ሲዳማ፣ ሃገረሰላም(ሁላ) ውስጥ የሂሳብ መምህር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ሰላምታቸው፣ ዳዬ ቡሹ ነው፡፡ መልሱም አነራ ዳኤ፡፡ ሰላምታ ሰጪው፣ አፈር ልሁንልህ ሲልህ መልስህ፣ እኔ ልሁን ነው፡፡ መቼም የአማራና ጉራጌ ነገር አፈር ስሆንልህ አይደለምን? እንግዲህ የጉራጊኛውን ሰላምታ እናስታውስ፣ እግረኛ አፈር፣ አነም፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ልጅ ሌ/ጀ ሞሆዚ በቅርቡ እኔ የሚኒልክ 2ኛው ዘር ነኝ ሲሉ ዝም ብለው አይደለም፡፡ አጼ ኃ/ስላሴ እ.ኤ.አ. 1964 ዓ.ም. ኡጋንዳን ሊጎበኙ ሲሄዱ የኡጋንዳው ጠ/ሚ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ በደምና ስጋ የሚዛመዷቸው የኢትዮጵያው ንጉስ፣ አጼ ኃ/ስላሴ በመካከላቸው በመገኘታቸውን የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል አለ ስለሚባለው አንድ አያትን መጋራት አፈ ታሪክ አውስተው ነበር፡፡

ሩዋንዳ ውስጥ የሚገኙ ቱሲዎችም እራሳቸውን እንደ ቤተእስራኤል የመቁጠር ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ ይህን ሩዋንዳ ኤምባሲ ውስጥ ከሩዋንዳው አታሼ፣ እስራኤል ሄደው የሰለጠኑ ነበሩ፣ ሰምቼአለሁ፡፡1993ዓ.ም. ኢትዮጵያ ኤርፎረስ ውስጥ የሰለጠኑ ሩዋንዳዊያን በሚመረቁበት እለት ኤምባሲ ውስት በእንግድነት በተገኘሁበት ግዜ ነው ሩዋንዳዊያን በሙሴ ዘመን ቤተእስራኤሎቹ ወደ ደቡብ መጥተው እስከ ሩዋንደ መስፈራቸውን ሲናገሩ የሰማሁት፡፡ ለሁት ሶስት አመት ገደማም ከሩዋንዳዎቹ ጋር ግንኙነት ነበረኝ፡፡

አክራሪ ሁቱዎች በሩዋንዳው ዘር ጭፍጨፋ ግዜ ቱሲዎችን ሲገድሉ፣ ወደ መጣችሁበት ስፍራ ተመለሱ እያሉ ቪክቶሪያ ሃይቅ ውስጥ ይከቷቸው ነበር፡፡ ምክነያቱም ከቪክቶረያ ሃይቅ የሚነሳው ነጭ ናይል ሱዳን ካረቱም ላይ  ከበሉ ናይል(አባይ) ጋር ይገናኛልና አስከሬናቸውን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ነበር፡፡ የዘር ጭፍጨፋው ካበቃ በኋላ ሩዋንዳዎች ይህን መገለል ለማጥፋት አረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ባንዲራቸውን ወደ ሰማያዊ ባንዲራ ቀይረዋል፡፡

ከመቶ አመት በፊት ልጅ እያሱ በነገሱበት ወቅት ከኢትዮጵያ ሄደው ታንዛኒያ የሰፈሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ኛቱሬ(?) ተብለው ነው የሚታወቁት፡፡ እኒህ ከወሎና ጎነድር የሄዱ ህዝቦች አሁንም ድረስ ስማቸው፣ ሺህበሺ፣ አመዴ፣ አሰጎዶም…ነው፡፡ አሁንም ድረስ የአያቶቻቸው መነሻ የሆነው ቦታ በስም ጎንደርና ወሎን ይጠራሉ፡፡ አያቶቻቸው የሚበሉት ምግብ ጢፊ(ጤፍ) እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በአጼ ኃ/ስላሴ ዘመን ለመመለስ ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ ታንዛኒያን ከኮሎኒስት ኃይሎች ለመታደግ ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ ነገድ ናቸው፡፡ ስለነዚ ህዝቦች 120 በተባለው የእሁድ መዝናኛ ፐሮግራም ዶክመንተሪ ተስርቷል፡፡

በአለማችን ትልቁ ተራራ ኪሊማነጃሮ በታንዛኒያና ኬኒያ ድነበር አካባቢ ይገኛል፡፡ ወደ ተራራው የሚወጣው ግን በታንዛኒያ በኩል ነው፡፡ በታንዛኒያ የሚገኙ ጎሳዎች በኢትዮጵያ የሚነገረውን የንጉስ ሰለሞንና የንግስት ሳባ ልጅ ቀዳማይ ምንሊክ ታሪክ የራሳቸው አድርገው ይተርካሉ፡፡ ቀዳማይ ምንሊክ ሊሞት ሲል ከአባቱ የወረሰው ቀለበት ሾልኮ ኪሊማነጃሮ ተራራ ላይ እንደጠፋና ወደ ፊት በሚመጣው በሰለሞን አልጋ ወራሽ እሲኪገኝ ድረስ በዚያው እንደሚቆይ ይተርካሉ፡፡

ሌላው የፀጋ ክርስቶስ አይነተት የአጼ ቴውድሮስ ልጅ የነበረው መሸሻ ቴውድሮስም ይኸው እጣ ፋንታ ደርሶበታል፡፡ በእነግሊዝ ሰራዊት ተማርኮ ወደ ህንድ ከሄደ በኋላ በዚያ የንጉስ ናዚም ጠባቂ ዘብን ተቀላቀለ፡፡ ስሙም ተቀይሮ ሱለይማን ቢንሃፍቱ በመባል ነበር የሚታዋቀው፡፡ እ.ኤ.አ. 1882ዓ..ም. ላይ ከኢጥዮጵያ ደብዳቤ ስለደረሰኝ ብሎ ግንባሩ ላይ ያለውን የመስቀል ምልክትና የማረኩትን ሰዎች ስም ጠርቶ ተመልሼ ሄጄ ኢትዮጵያ ውስጥ መንገስ አለብኝ ሲል የእንግሊዝ አገዛዝን በህንድ ጠይቆ ነበር፡፡ እንግዲህ ከመቶ አመታት በፊት በስደት የተጀመረው የአማራው እንግለልት አሁንም በሃገር ውስጥ እንደቀጠለ ነው ከላይ ከተነሱት ታሪኮች የምንረዳው፡፡

ሶሶሎጂስቱ፣አስተማሪውና ጸሐፊው ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፣ ግሬተር ኢትዮጵያ በተባለው መጽሐፋቸው፣ ስለ አማርኛ ቋንቋ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤

ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገሩ አብዛኞቹ ቋንቋዎች አስራ ስምንት የድምጽ ቅንብር መስመሮች(Phonological Marks) ውስጥ አማርኛ አስራ ስድስቱን ይይዛል፡፡ እንዲሁም የሃገሪቷ ቋንቋዎች ካለቸው፣ የቃል አረፍተ ነገር ምስረታ ስምነት ህጎች(Syntax)  ስድስቱ አማርኛ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህን ካሉ በኋላ፣ አማርኛን ኢትዬጵያ ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች የተለየና አይነተኛ ነው ይሉታል፡፡

ተርጓሚና ሃያሲ የነበሩት ሳህለስላሴ ብርሃነማርያም (የጉራጌ ተወላጂ ናቸው)፣ ኢህአዲግ ስልጣን እንደያዘ አንድ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ እኚህ ሰው አሜሪካን ሃገር የተማሩ ነበር፡፡ በጣልያን ባህል  ኢንስቲቱይት ውስጥ ፔን ኢትዮጵያ 2005ዓ.ም. ባዘጋጀው፣ ትርጉምን በተመለከተ ፕሮግራም ላይ  የእሳቸው አወያይ ሆኜ በመቅረቤ ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ እሳቻው ምን አሉ? “አማርኛን ለምን ኢትዮጵያኛ ብለን ይዘን አንቀጥልም?” በግዜው ወያኔ – ኢህአዲግ ይህ ቃል አቀረሸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም የጽዮን ልጆች በስታሊን በትር ኮሚኒዝም ፍቅር ተይዘው የአልባኒያ ኮሚኒስቶች ስለነበሩ ነው፡፡

አማራው የሁሉም እልዳልሆነ ሁሉ እንደ ብሔር ተዋርዶ ይመታ ጀመር፡፡ በቋንቋ ረገድ ስመለከተው አማርኛ(አማራ) ከብሔርነት ከፍ ያለና ከኢትዮጵያዊነት ለጥቆ የሚገኝ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ እንጂ ሌላ ማንነት የለውም፡፡ ኦሮሞውም ከገባው ያው ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ከሁለት እናትና አባት ይፈጠራል፡፡ አራት አያቶች፣ ስምንት ቅድመ አያቶች፣ አስራ ስድስት ቅም አያቶች… የ አንድን ትውልድ ዘመን በሰላሳ እድሜ ብናባዛው አያት ቅድመ አያት እያልን አስር ግዜ ወደ ላይ ብንሄድ፣ አስረኛው መስመር ላይ 1024 ሰዎች እናገኛለን፡፡ በአጠቃላይ ድምሩ ደግሞ 4094 ሰዎች የኛ አያቶች መስመር ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ጥያቄው የሚሆነው እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሃገር ውስጥ፣ ብዙ ፍልሰትና ጦርነት በተደረገባት፣ የሰሜኑ ደቡብ፣ የደቡቡ ሰሜን በሄደባት፣ ምስራቅና ምእራቡ በተቀላቀለባት፣ አንድ ሰው የዛሬ 300 አመት ገደማ 4094 ሰዎች አያቶቹና ቅም አያቶቹ በውስጡ ይዞ በሚገኝበት ሃገር፣ ስንቱ ውስጥ ምን ያህል ቋንቋ ይነገራል ነው? እንግዲህ የምትበጠብጡ ኦሮሞዎች፣ትግሬዎች፣አማሮች… መልስ ስጡን፡፡

እራሴን በተመለከተ የአፍ መፍቺያ ቋንቋ እንጂ ብሔር የለኝም፡፡ ሁሉኑም ነኝ ባይ ነኝ፡፡ የዲ.ኤን.ኤ ውጤትም ያን ነው ያሳየው፡፡ አሁን የምኖርበት ካናደዳ ከመጣሁ ቦኋላ የዛሬ አምስት አመት ገደማ የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ በማይሄሪቴጅ በኩል አደረግሁ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ-ኢትዮጵያም ሰው አይደለሁ ነገሩ እንዲ ሆነ፡፡ 63.2% የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል፣ 17.4% ሶማሌ፣ 10.3% ሰሜን አፍሪካ፣ 7.4% መካከለኛው ምስራቅ 1.7% ናይጄሪያ ሆኖ ተገኘሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፖለቲካችን  ከዜሮ ድምር (zero sum politics ) እንዲላቀቅ ምሁራን ሳትታክቱ  ሃሳብ አዋጡ። (መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ)

ይህች የናይጄሪዋ ዘር ፍላታ እየተባሉ ከሚጠሩት፣ ከናይጄሪ እየተነሱ ጎንደርን ከሚወሩት አሁንም ድረስ ከሉ ዘላን ህዝቦች የገኘሁት ይመስለኛል፡፡ ወቼ ጉድ ነገሩ በእዚህ መቼ አበቃ፣ ሁለት የዲ፣ኤን.ኤ ካሲን እህቶች መጡ፡፡ አንዷ ኤርትራዊት በሁለት አመቷ ወያኔ ካአዲስስ አበባ ያባረራ ትግሬ ነች፡፡ ሌላኛዋ ደግሞ  ሞስሊም ኦሮሞ  ነች፡፡ እንደ ቅድመ ተከተላቸው 48%ና 30% ቤተ እስራኦል ናቸው፡፡ ሁለቱም ውስጥ የሶማሌ ዲ.ኤን.ኤ አለ፡፡ የሰሜን አፍሪካ ዝርያም አላቸው፡፡ ከዚያ ቀድሞ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በዘጠነኛው ክ/ዘ ላይ የጥንት ጥቁር ግብጻውያን ህዝቦች በስደተ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፣ በተለይም ወደ ዛሬ ሸዋና ወሎ፡፡ እንግዲህ ታሪክ እንደሚነግረን የሱማሌ ወታደሮችን አስከትሎ ወደ ደጋ ኢትዮጵያ በ15ኛው ክ/ዘ የዘመተው ግራኝ አህመድም የሞተው ንፋስ መውጪያ ጎንደር ላይ ነው፡፡

እሚገርማችሁ ነገር 73% የቤተእስራኤል ዝርያ የሆነ የጋሞ ገጠርማ አካባቢ ተወላጅ አግኝቼለሁ፡፡ የደኤ.ኤን.ኤ ውጤቴን ለአንድ በዚሁ ሰሜን አሜሪካ ለሚኖር የኦሮሞ ተወላጂ ነግሬው ሁሉም ህዝብ በዘረመሉ አንድ ነው፡፡ ስለዚህም በብሔር ፖለቲካ መስመር መሰለፍ ይቸግረኛል አልኩት፡፡ እንግዲህ ይሄ ሰው ከሃገርቤት ጀምሮ እዚህ ድረስ የተማረ ነው፡፡ ነገር ግን መልሱ “ዲ.ኤን.ኤ የሚባለው ቡልሽት ሳይንስ ነው” ሆነ፡፡ የሚገርማችሁ ነገር እሱ እራሱ የአክሰቱን ልጅ ወንደሜ ነው ብሎ ለማመምጣት ፎረም ሞልቶ ልጁ ደ.ኤን.ኤ ሲመረመር የእህት ልጅ እንደሆነ ተረጋግጦ፣ ጉዳዩ ውድቅ ሆኖበታል፡፡ እንዲህ ያሉ ወድቅ የተደረጉ ጉዳዮች በዚህ ሰሜን አሜሪካ ብዙ ናቸው፡፡

እንግዲህ ጎበዝ ምን እናድርግ እዚህ በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ የብሔር ፖለቲከኞች ተደብቀው የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ያደርጋሉ ግን ውጤቱን አይናገሯትም፡፡ ከወለጋ እስከ ሃረር፣ ከአጋሜ እስከ ቦረና በጎፈንድሚ አሰመርምረን፣ በዘረመል ደረጃ አንድ መሆናችንን ለማረጋገጥ ፍቃደኘነቱ ካለ ብትጠይቁልኛ፣ ለሃገር ሲባል የማናረገው ነገር የለምና ስራውን ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡

የአማራ እንክርትን ሳስብ፣ የኤርትራ ጀነራሎችና አቦ ሌንጮ ባቲ ሁሌም ትዝ ይሉኛል፡፡ ኤርትራ ነፃ ለመውጣት  በምትፈልግበት ግዜ ሁን ብለው አማራን የሚያጠለሽ ታሪክ እየፈጠሩ ያወሩ እነደነበር፣ ያም ለትግላቸው ውጤት እነዳሰገኘላቸው ተናግረው፣ አሁን ግን የፀፀታቻው መኆኑን ተናግረው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሌንጮ ባቲም፡፡ የኦሮሞን የብሔር ትግል ወደ ላይ ለማምጣት ኢትዮጵያ የሚለውን አስተሳሰብ ዲኮንስትራክት ያደርጉ እንደነበር ነግረውናል፡፡ እንዲህም ብለው ተናገሩ፣ አሁን የኔን መልክ ብታይ ከአማራ መልክ በምን ይለያል ሲሉ ጠየቁና አማራና ኦሮሞውን ያጋመደ አንድች ኃይል እንዳለ እንድንደርስበት ጥያቄውን ክፍት አድርገው ተውት፡፡

ወያኔ ግን እስከአሁን ትግሬው ልዩ ህዝብ እንደሆነ እነደሰበከች ትገኛለች፡፡ በስታሊን በትር አማረውን ስትደበድብም ኖራለች፡፡ የሚገርመው ነገር አብዛኞቹ የኦሮሞና ትግራይ ነባር ታጋዮች እንደ መኢሶን፣ ኢህአፓ…የመሳሰሉ ኮሚኒስት ፓረቲዎች አባል የነበሩና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመደብ ትግል ነው ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ሲዋጉም የነበረው ለመደብ ትግል ነበር፡፡ በዚያ አልሆን ሲላቸው ነው ከመደብ ጨቆና ወደ ብሔር ጭቆና ትርክት እራሳቸውን የሸጋገሩት፡፡

ሸጋ ሆኖ የለውጡን ጉዞ የጀመረው የአብይ መንግስትም ቀስ በቀስ ወደ በላኢሰብነት ሲቀየር ተመልክተንዋል፡፡አማራውን ይዞ ተነስቶ በየፌረማታው ላይ የኋልዮሽ እየረገጠው ይገኛል፡፡ ስለአማራ ትንሽ ምክነያተዊነት ያሳዩ ኦሮሞዎች እንኳን አልቀረላቸውም፡፡አቶ ሌንጮ ባቲ በሆነ ምልኩ ከዚህ ይመደባሉ ባይ ነኝ፡፡ የቅርብ የነበሩ ሰዎችን ማራቂያ የሆነው አምባሳደርነት ተሰጥቷቸው በሳውዲ አረብያ ይገኛሉ፡፡

ሰዎች ማንም ይበሏቸው ማን ጀነራል ባጫ ደበሌም እንዲሁ የኬንያ አምባሳደር ሆነው ይገኛሉ፡፡ ብራቅ በሆነው ድምጻቸውና ሞገሰቸው ሲናገሩ የልብ ያደርሳሉ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በቴሌቪዥን ቃለመጠይቃቸው ላይ፣ እኛ ከአማራ ልጆች ጋር በአንድነት እየተጫወትን ልዩነታችንን ሳናውቅ ነው ያደግነው አሉ፡፡ ከዚያም ብዙ አልቆዩም አምባሳደር ሆነው ተሸሙ፡፡ ይህቺ ሃገር ጥሩ ኦሮምኛና አማርኛ ተናጋሪዎች አልበረከትላትስ አሉ? ሌንጮ ባቲ፣ ጀ/ል ባጫ ደበሌ፣ ኢነጂነር ስለሺህ በቀለ(የአሁኑ የአሜሪካን አምባሳደር)…

እንደእውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አውቀውት ሳይሆን በሂደት አማርኛ ቋንቋ ፈጥረዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በማንኛውም የአለማችን ክፍል የሚገኙ ህዝቦች በተፈጠሩበት መንገድ ነው፡፡ የመጣው የብሔር ፖለቲካ ሁሉ ግን አማራውን እየተጠቀመበት ረግጦት ያልፋል፡፡ ከብሔር በላይ የሆነው አማራው ሲጠቃ ደግሞ ወርዶ በብሔር መልክ ተደራጅቶ እራሱን የመከላከል መብት አለው፡፡ ያም ለኢትዮጵያን ሁሉ ቀን ወጥቶላቸው የዜግነት ክብር አስኪያገኙ ድረስ ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ የሆሊውድ ሙቪ ላይ ያሁትን ነገር ላከፍለችሁ፡፡ ፊልሙ አድቬንቸር ነው፡፡ በፊልሙ ውስጥ የደቡብ አሜሪካ ጫካን የሚያውቅ ገፀባህሪ አለ፡፡ በእሱ እውቀት ላይ ተመርኩዘው የሚከተሉት ሰዎችም አሉ፡፡ አንድ ቀን በምሽት እሳት ማብራት ፑማዎችን(የነብር ዝርያ ነው) እንዴት ወደ ሰው እንዳይቀርቡ እንደሚያረጋቸው ይነግራቸውና ከዚያ ውጭ ግን ለአንድ ፑማ ሰውም ሆን ዛፍ ላይ የሚነጠለጠለው ዝንጀሮ በአንድ እይታ ምግብ አድርጎ እንደሚያቸው ይነግራቸዋል፡፡

ብሔር ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ እናትና አባቱ ምን ቋንቋ ተናጋሪዎች ነቸው ብሎ ይጠይቃል፣ ከዚያም ይህ ሰው አማራ…ብሎ ሰይሞ ወይ ቤትህን ያቃጥላል፣ ወይ ልጆችና ሴቶችን ይደፍራል፣ ሃብት ንብረትህን ይዘርፋል… በአንድ ሰው ሶስተ መቶ የአያቶች ግዜ ወደ ኋላ ስላለው 4096 ሰዎች ዝርያ ለመጠየቅ ግዜውም እውቀቱም የለውም፡፡

ብሔር ሆነን ስንባላ ይዃው ሃምሳ አመት ገደማ አለፈን፡፡ አሁን ደግሞ በታሪካችን በአጭር ግዜ ብዙ ሰው ያለቀበትን ጦርነት አደረግን፡፡ ድሉም ድርድሩም በአንድ ላይ እየተካሄደ ነው፡፡ ከስድስት ወር ወይም ከስምንት ወር ቦኋላ ምን ይሆናል? ብቻ ሴትዮዋ እንዳለችው፣

አሽካኖኝ አሽካኖኛ አሽካኖኝ ስመለስ

ልጄን አቀብሉኝ እወንዙ ዳር ድረስ፡፡

ወያኔ አምጦ ተጨንቆ የወለደው ልጅ፣ እሳት ሆኖ እይበላው ነው፡፡ ቀጥሎስ የወያኔ የበኩር ልጅ የሆነው ኦህዲድ- ብልጽግና(ብአዴን ብኩረናው ኮርቻ በመሆን ሸጧልና) እጣ ፋንታው ምን ይሆናል? አይ ብልጽግና እጅህ ከምን? ደም በደም ሆኗል ነገሩ፡፡

ጠ/ሚ አብይ በመስቀል ባእል የነገሩንን …ተረከዛቸውን አነሱብን… ነገር ስንቋጭ እንዲህ ተብሎ ትንቢት የተነገረለት ይሁዳ ክህደቱን ከፈጸመ በኋል ራሱን ሰቅሎ ነው ህይወቱን ያጠፋው፡፡ እሺ ወያኔ በዚህ መንገድ ራሱን በማጥፋት ተሸኘ እንበል፣ ብልጽግናስ?

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ

 

 

1 Comment

  1. አቶ አስቻለው ይህን ጽሁፍ አይቶ አለማድነቅ ወንጀል ነው። የሚገርመው ብርሀኑ ነጋ፣መራራ ጉዲና፣አረጋዊ በርሄ ከስድብ በስተቀር መች ነው እንዲህ ያለ አካዳሚያዊ ትንተናና አስተማሪ የሆነ ጽሁፍ የሚያቀርቡት? ባለሁበት አገር አንድ ምሁር በተማረበት የትምህርት ዘርፍ ካልሰራ እውቀቱን በስልጠና ካልካበ በየአመቱ 25℅ ይቀንሳል ቀጣሪም አያገኝም። በምድረ ኢትዮጵያ ግን እንደ ግራዝማች ቀኛዝማች እስኪሞቱ ድረስ ይኮፈሱበታል። ነገሩን ለማሳጠር አቶ አስቻለውን ኢትዮጵያዊ ክብር እየሰጠሁ ከላይ የተጠቀሱትን አራጅና ቢላ አቀባዮችን ግን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቶ እላቸው ይሆን እንጅ ዶክተር ፕሮፌሰር ብሎ የመጥራት ግዴታ እንደሌለብኝ ለአንባቢና ለነሱም ማሳወቅ እወዳለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.