ህይወት፣ ሰላምና ዕድገት በሚል አርዕስት በዶ/ር በቀለ ገሰሰ ለቀረበው አጠር  መጠን  ያለ  ገለጻ  የተሰጠ  ወንዳማዊ  ሂስ!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ጥቅምት 30 2022

ህይወት፣ ሰላምና ዕድገት በሚል አርዕስት  ዘአበሻ ድረ-ገጽ ላይ ለአንባቢያን ያቀረብከውን ጽሁፍህን ተመለከትኩት። ጽሁፉ ማለፊያ ነው። በመሰረቱ የማንኛውም ህዝብ ህልምና ፍላጎት ሰላምና ዕድገት መሆን አለባቸው። እንዳልከውም ሰላም ሳይኖር ዕድገት በፍጹም ሊኖር አይችልም። የህይወትም ትርጉሙ ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ በስላም መኖርና የተሟላ ዕድገት መጎናጸፍ ነው። እየአንዳንዱ ለአቅመ-አዳም የደረሰና ትምህርቱን የጨረሰ፣ ወይም አንዳች ሙያን ተምሮ ያጠናቀቀ ስራ ካገኘ በኋላ ቤተሰብ መመስረትና ልጆች መውለድ ይፈልጋል። ይህ ሁሉ ሊሆንና ህብረተሰብም በተከታታይነት ከአንዱ ትውልድ ወደሚቀጥለው ሊተላለፍ የሚችለው በአንድ አገር ውስጥና በአካባቢው ሰለም ሲሰፍና ቀስ በቀስም የተሟላና የተስተካከለ ዕድገት ሲመጣ  ብቻ ነው።

የሚነሳውና መነሳትም ያለበት ጥያቄ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር የሚያደርጉ ምክንያቶችን መፈለጉ ነው። ለምሳሌ የእኛ ህብረተሰብ ካለፉት 48 ዓመታት ጀምሮ እፎይ ብሎ አያውቅም። ስራው ሁሉ ጦርነት ሆኗል። ለጦርነት ምክንያት የሆኑትና የሚሆኑት  ኃይሎች ደግሞ ተራውና ያልተማረው ህዝብ ሳይሆን ተማርን፣ አውቀናል የሚሉና ስልጣን ላይ ካልወጣን ብለው እዚህና እዚያ የሚራወጡት፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት ተብለው የሚጠሩ ኃይሎች ናቸው። በዓለም ላይ የተካሄዱትን የጦርነት ታሪኮች ለተከታተለ ደግሞ በመጀመሪያ ለጦርነት ዋናው ምክንያት ስልጣንን  የጨበጡ ኃይሎች ናቸው። ቢያንስ የአንደኛውንና የሁለተኛውን ዓለም ጦርነቶች ታሪክ ስንመለከት ቀስቃሾቹ ስልጣንን የጨበጡና የሌላውን አገር ብሄራዊ  ነፃነት ደፍረንና አስገብረን ቅኝ-ግዛት እናደርገዋለን ብለው ባሰቡ ነው። በዚህ ዓይነቱ አርቆ አለማሰብ ጦርነት የተነሳ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዋህ ህዝቦች ህይወታቸውን ሰውተዋል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተካሄዱትንና የሚካሄዱትን ጦርነቶች ለተመለከተ ደግሞ የጦርነቶች ቀስቃሽ ኃይሎች ኢምፖፔሪያሊስት ኃይሎች ናቸው። ከዚሁ ሁኔታ ስንነሳ ባለፉት 50 ዓመታት በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጦርነት የውክልና ጦርነት ነው። ይህም ማለት የራሳችን ጦርነት አይደለም። ጦርነትን የምናካሂደው ለውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን መሳሪያን ብምድራችንና በህዝባችን ላይ መሞከሪያ ለማድረግ ነው። እንደሚታወቀውና ተማርኩኝ ለሚል ሰው ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ በጦርነት አማካይነት አገር የሚገነባ ሳይሆን የሚፈራርስ ነው። ጦርነት የሰውን ሃይልና የጥሬ-ሀብትን፣ እንዲሁም በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቀጠር ገነዝብን አውዳሚ ነው። ከጦርነት፣ በተለይ ደግሞ ከእርስ በርስ ጦርነት አንዳችም ነገር አይገኝም። አሸናፊ ሆኖ የሚወጣውም ታሪክን የሚሰራ ሳይሆን አገርን አውዳሚ ነው። በጦርነት አማካይነት ህይወቱ እንዲቀጠፍ የሚደረገው በዚኸኛው ወይም በዚያኛው ወገን የሚሰለፍ እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ባዮግራፊ አለው። ቤተሰብም የመሰረተ ሊኖር ይችላል። ታዲያ በማይገባ የወንድማማች ጦረነት ህይወቱ ሲያልፍ የሱ ህይወት መቀጠፍ ቤተሰቦቹን ብቻ ሳይሆን የተወለደበትንና ያደገበትን መንደር ህዝብ በሙሉ ያሳዝናል። በእሱ መሞት ምክንያት የተነሳ እስከዚያ ድረስ ያካበተው ልምድና ትውውቅ በሙሉ እንዳለ ይወድማል። ባጭሩ በጦርነት አማካይነት የተነሳ አንድ ህብረተሰብና ማህበረሰብ እንዳለ ይናጋል። መንፈሱ ይረበሻል። ለመፍጠርና ለመኖር ያለው ኃይል በሙሉ ይሟሽሻል። ታዲያ ተማርን የሚሉና ጦርነትን የሚያካሄዱ ወገኖቻችን እነዚህን ነገሮች በሙሉ ለምን አያጤኑም? እንዳያጤኑ፣ ወይም እንዳያወጡና እንዳያወርዱ የሚያግዳቸውስ ምን ነገር አለ? በጦርነትስ አማካይነት ምን የሚያተርፉት ነገር አለ? እናተርፋለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ በጣም ተሳስተዋል።

ታዲያ ሀቁ ይህ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን በቂ ምክንያት ሳይኖረን ለምን የኢምፔሪያሊስቶችን ጦርነት እናካሄዳለን? ስልጣን ላይ ከወጣንስ በኋላ ምን ነገር ልንሰራ ነው? እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ የዓለምን ታሪክ፣ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የሚካሄደውን ጦርነት ለተመለከተ እንደኛ በስተቀር የውጭ ኃያላን ተቀጣሪ በመሆን ጦርነት በራሱ ህዝብ፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖቱ ላይ  የሚያካሂድ የሶስተኛው ዓለም ኤሊት የለም። ቬትናሞችና ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ሲያካሂዱ በውጭ ኃይል መደፈር የለብንም፣ መታዘዝና መገዛትም የለብንም በማለት ነው። የእኛው አገር ትግል ግን የውጭ ጠላትን ለመከላከል የሚካሄድ ትግል ሳይሆን የተለያዩ ምክንያቶችን በመፈለግና የውጭ ተቀጣሪ በመሆን በህዝባችን ላይ ጦርነትን ማካሄድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጫልቱ እንደ ሄለን ከቡርቃ ዝምታ የቀጠለው መርዛማ ብዕር

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ እኛ ሰዎችና በአምላክ ምስልም የተፈጠርን ነን ብለን እናስባለን። የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያለንና አገራችንም ከመጀመሪያዎቹ አገሮች ውስጥ የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበለች አገር ናት ብለን እንኮራለን። በእግዚአብሄር አምሳልነት መፈጠርና ባህልን አዳብሮ ሃይማኖትን መቀበልና በክርስቶስ ማመለክ በመሰረቱ መንፈስን መሰብሰብ ነበረበት። እንደሚባለው የሰው ልጅ ባህልን ሲያዳብር፣ በስራ-ክፍፍል አማካይነት ተሰማርቶ የተለያዩ ነገሮችን ሲያመርትና፣ እንዲያም ሲል ከተማዎችን ገንብቶና ልዩ ልዩ ተቋማትን ሲመሰርት በዚያው መጠንም መንፈሱ የረጋ ይሆና፤ አርቆ አሳቢ ይሆናል። ጭንቅላቱ ስለሚዳብርም መጥፎ መጥፎ ነገሮችን ከማሰብ ይልቅ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ያስባል። ስለሆነም አንደኛው የሌላኛው ጠላት አይሆንም። በመተጋገዝና በህብረትም ማህበረሰብን ስለሚመሰርትና ስለሚያጠነክር ናፍቆቱ ሁሉ የመጨረሻ መጨረሻ የተሟላ ሰላምንና ዕድገትን ማግኘት ነው። ይህ ከመሆኑ ይልቅ የአገራችን ኤሊት መንፈሱ የተረበሸ ያህል፣ ወይም ደግሞ በአፈጣጠሩ ጭንቅላቱ በተበላሸ መልክ የተዋቀረ ወይም የተቀረጸ ይመስል ጦርነትን ቀስቃሽ ሆኗል። የተማረው ትምህርት ሁሉ ከንቱ በመሆን ታሪክንና ባህልን በማውደም ምስኪን ህዝብን ሲያሰቃይ ይታያል።  ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የእኛ ኢትዮጵያውያን ጭንቅላት አንዳች የጎደለው ነገር አለ። እልከኛ፣ አመጸኛና አፈኛ በመሆን ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ለመሆን በቅቷል። የአብዛኛዎችን በፖለቲካ ስም የሚታገሉትንና ለነፃነታችን እንታገላለን ብለው ወደ ጫካ የገቡትንና፣ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ህይወት እንዲቀሰፍ ያደረጉትን የህይወት ታሪክ ስንመረመር አንዳቸውም ለሰው ልጅና ለአንድ ማህበረሰብ የሚያስፈልጉ ጠለቅ ያሉ ዕውቀቶችን ያልቀመሱና ከእነሱም ጋር ያልተዋወቁ ናቸው። ለሰው ልጅ ጭንቅላት መዳበር የሚያስፈልጉ ዕውቀቶች፣ ለምሳሌ ፍልስፍና፣ ሶስይሎጂ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ አርኪቴክቸረና የከተማ ግንባታ ዕውቀት፣ የሰነ-ልቦናና ሌሎች ዕውቀቶች ጋር ያልተዋወቁና ለመከታተልም የሚፈልጉ አይደሉም። ስለሆነም ስለስው ልጅ ህይወት ያላቸው አስተሳሰብ ምን እንደሆነ አይታወቅም። እራሳቸውም ሰው መሆናቸውን የሚያውቁም አይመስሉም። ሰው ቢሆኑ ወይም ደግሞ እንደሰው ልጅ ቢያስቡ ኖሮ ሌላውን ተመሳሳዩን ወገኖቻቸውን ባልገደሉ ወይም ባላሰቃዩ ነበር። ባጭሩ እንደነዚህ ዐይነት ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ የኢምፔሪያሊስት ተላላኪያዎች ኢትዮጵያውያን  ለእነሱ ህይወት ትርጉም የለውም። ኤስቴቲክስ፣ ሙዚቃ፣ ጥሩ ጥሩ አርኪቴክቸሮችና ጋርደኖች ምን እንደሆኑ የሚያውቁት ነገር የለም። ስራና የስራ ባህልም ምን እንደሆነ አያውቁም። ለመብላት ብቻ ብለው ይበላሉ። ለምን እንደሚበሉና ምን ዐይነትስ ምግብ ለጤንነታቸው የሚስማማ መሆኑን የሚያውቁት ነገር የለም። ባጭሩ እነዚህ ሰዎች የራሳቸው ህይውት ትርጉም ስለሌለው፣ ጭንቅላታቸው የተረበሸ ከመሆኑ የተነሳ ሊረኩ የሚችሉት ሌላውን አምሳያቸውን ወንድማቸውን ወይም እህታቸውን ሲገድሉ ብቻ ነው። ህይወታቸው በሙሉ ከማሰቃይትና አገርን ከመበታተን ጋር የተያያዘ ብቻ ነው።  እንደዚህ ዐይነቱ የህይውት ፍልስፍና ከአገራችን በስተቀር  በሌሎች የአፍሪካ አገሮች አይታይም። ለማንኛውም ከዚህ ዐይነቱ የኑሮን ትርጉም ከማያውቅና ለስልጣን ብቻ ከሚቅበዘበበዝ ትውልድ ሰላምንና ዕድገትን መጠበቀ አይቻልም። ዕድገትም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስለማይገባው ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ የውጭ ኃይሎች በመሰበክና በመታለል የተዘባረረቀ ነገር ከመስራት በስተቀር መንፍስን የሚሰበስብ፣ ተከታታይነት የሚኖረውና ሚዛናዊነት ያለው ወይም የተስተካከለ ዕድገትን ሊያመጣ አይችልም። ለተስተካከለና ተከታታይነት ለሚኖረው ዕድገት ደግሞ ጠለቅ ያለ የፍልፍና፣ የኢኮኖሚክ ቲዎሪ፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ሌሎችም ዕውቀቶች ያስፈልጋሉ። ስለሆነም አሁን ስልጣን ላይ ካለውና ለስልጣን ከሚታገለው የሚቅበዘበዝ ኃይል አንዳችም ጤናማ ነገር በፍጹም መጠበቅ አንችልም። ከእንደዚህ ዐይነት ኃይሎች ሰላምና ዕድገት የምንጠብቅ ከሆነ ስለምና ዕድገት ምን እንደሆኑ መፍጹም አልገባንም ማለት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕገ-መንግስቱን ለማሻሻል ለሚደረገው ሕዝባዊ ውይይት ይጠቅማሉ የምንላቸው ሐሳቦች (ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን)

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ሰለሰላምና ዕድገት የሚኖረን ትርጉም ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል። በእኔ ዕምነት በደፈናው ዕድገት ብሎ ነገር የለም። አንዳች ኢኮኖሚያዊና ህብረትሰብአዊ ዕድገት በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና መታገዝ አለበት። በአሁኑ ዘመን ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባልና በዓለም ኤሊቶች ተቀባይነትን ያገኛ በዕድገት ስም የሚካሄድ ፀረ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ተስፋፍቷል።  በተለም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ በነፃ ገበያ ስም የጥገና ለውጦች ተካሂደዋል ተብሎን ተነግሮናል። ወደ ነፃ ገበያ ለመምጣትና ዕድገትን ለመጎናጸፍ ደግሞ የወያኔ አገዛዝ በውጭ ኤክስፐርቶች በመመከር የተቋም ማስተካከያ ፕሮግራም(Structural Adjustment Programms )  ተግባራዊ አድርጓል። የዛሬው የአቢይ አገዛዝም ሌላ አማራጭ ከመፈለግ በስተቀር ከወያኔው የተወላገደና ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አልላቀቅም በማለት ህዝባችንን ወደድህነት ገፍትሮታል። ሰፊው ህዝባችን በዋጋ ግሽበት እየተሰቃየ ነው። ይህንን አስመልክቶ አንዳቸውም ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚስት በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ጥናት በማካሄድና በመተቸት አማራጭ መፍትሄ ያቀረበ የለም። ታዲያ ሁላችንም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያልን እንጮሃለን። እንደሚታወቀው የአንድ አገርና ህዝብ መሰረት ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተወሳሰበ ኢኮኖሚ መኖር ነው። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካና የመንግስት ጥያቄዎች በበቂው መመለስ አለባቸው።ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሰፋ ያለና ለተሟላ ዕድገት የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ የሚቻለው። ይህ ፖሊሲ ደግሞ ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ውጭ የሆነና በራስ መተማመን የሚነደፍና ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።  ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወደ አንዳች ስርዓት ያምራ አያምራ ወሳኝ አይደለም። ዋናው ግንዛቤ መሆን ያለበት በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመጀመሪያ ደረጃ  የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) ማሟላት አለበት። ለመስራትና ምርታማ ለመሆን ማንኛውም ሰው ሆነ ህዝብ የግዴታ በመጀመሪያ ደረጃ መብላትና መጠጣት አለበት። ካለበለዚያ ሊያስብና ሊሰራ አይችልም። ከዚህም ባሻገር የግዴታ መጠለያ፣ ህክምናና ትምህርት ማግኘት አለበት። እነዚህ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው ወደ ተከታዩ ደረጃ ማለፍ የሚቻለው። አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገትም ለኢኮኖሚ ዕድገት ተብሎ የሚታቀድ የሚሆን ሳይሆን አንድን ህዝብ እንደሰው ሊኖር የሚያስችለው መሆን አለበት። ፍላጎቱ ተሟልቶ በነፃነት እንዲያስብ የሚያስችለው መሆን አለበት። በአጠቃላይ ሲታይ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ከሌሎች ነገሮች ነጥለን ማየት የለብንም። የሰው ልጅ ማቴሪያላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊና ጥበባዊም ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ከሌሎች ነገሮች ጋር በማያያዝ ብቻ ነው። በንጽሁ የማቴሪያሊስት አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ አመጽኛ ህብረተሰብ እንዲፈለፈል ያደርጋል። በታላላቅ የአሜሪካን ከተማዎች፣ በደቡብ የአሜሪካ፣ እንደሳኦ ፖሎ በመሳሰሉትና በጆሀንስበርግ በመሳሰሉት ከተማዎች ውስጥ የሚታያውና ለአገዛዝም የማይመች ሁኔታ በመፈጠር በተለይም ሰላምን ለሚፈልገው ህዝብ በሰላም እንዳይኖር ያደርገዋል። ወያኔም ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ ያደረገው ፖሊሲ  ስነ-ምግባር የሌለው፣ አመጸኛ የሆነና የባለገ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት ነኝ እንዲፈጠር ያደረገ ነው። ይህ ዐይነቱም የህብረተሰብ ክፍል በኢምፐሪያሊስት ኃይሎች የሚፈለግና የሚደገፍ ሲሆን፣ በዚህ ዐይነቱ ኃይል አማካይነት ጥሬ-ሀብት ይበዘበዛል፣ ሀብረተሰብአዊ ቀውስ ይፈጠራል፣ የአካባቢ ቀውስ ይመጣል፣ በዚያውም አማካይነት ሰፊ ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ ይደረጋል። አቅጣጫው ሁሉ የጠፋበት ህዝብ ግራ እየተጋባ ይኖራል ማለት ነው። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ግልጽ አስተያየት እንዲኖረን ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሚዛኑን ከሳተ ውዳሴ እና ስሜታዊነት ከሚነዳው የፖለቲካ አባዜ እስካልወጣን ድረስ ... - ጠገናው ጎሹ

የሚገርመው ነገር ሰላምንና ዕድገትን አስመልክቶ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዚህ ዙሪያ ሲያጠናና ሲከራከር በፍጹም አይታይም። በድረ-ገጾች ላይ የሚወጡትን ጽሁፎች ለተከታተለ 99% የሚሆኑት ከዕድገትና ከሰላም ጋር የሚያያዙ ጽሆፎችም አይደሉም። የአብዛኛዎቻችን አስተሳሰብም ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በፍጹም የተያያዘ አይደደለም። ዛሬ አደጉ የሚባሉትን አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገትና የህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ስንመለከት አስተሳሰባቸው፣ ክርክራቸውና አጻጻፈቸው በሙሉ ከዕድገት፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ዋና ዓላማቸውም የመጨረሻ መጨረሻ ህብረ-ብሄርን መገንባት ነው። አንድ ህብረ-ብሄር( Nation-State) ሊገነባ የሚችለው በተለይም በኢኮኖሚ ሳይንስ ላይ ግልጽ አስተሳሰብ ሲኖር ብቻ ነው። ታዲያ ከዚህ ሃቅ ስንነሳ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ምን እንደምንፈልግም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው። ስለሆነም በዚህ ላይ ግልጽ አስተያየትና አቋም እስከሌለን ድረስ ስለ ኢትዮጵያ ማውራቱ ትርጉም የለውም። እንደምክታተለው ከሆነ አንደኛው ከሌላው ለመማርም የሚፈልግ ያለ አይመስለኛም። ሁሉም በየፊና ካላሳይንሳዊ መመሪያና ካለአንዳች ዐይነት የፍልስፍና ዕምነት ዝም ብሎ በደፈናው ይጽፋል። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት  ሁኔታ ውስጥ አንድን አገርና ህዝብ ነፃ ማውጣት እንዴት ይቻላል? ሰሞኑን በአንድ ታላቅ ስብስባ ላይ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተካፋዮች በተሳተፍኩበት ሰለ ዕድገትና ሰላም(Peace & Development) ሰሚናር ላይ የታዘብኩት ነገር አብዛኛዎች ከአፍሪካ አገር የመጡ ምሁራንና ዲፕሎማቶች ስለ ዕድገት ያላቸው አስተሳሰብ ከእኛው በብዙ እጅ ዘልቆ የሄደ መሆኑን ነው። ሰሚናሩንም በዙም መከታተል ይቻል ነበር። ታዲያ በዚህ ዐይነቱ ሰሚናር ላይ ከእኔ በስተቀር ሌላ ኢትዮጵያዊ አልተሳተፈም። ዕድገትንና ህብረተሰብን አስመልክቶ በዙም አማካይነት የራሴን ዕውቀት በዙም አማካይነት ከአንዴም ሁለቴም ጥሪ ባቀርብ እስካሁን ድረስ ከሶስት ሰው በላይ በፍጹም ለመሳተፍ ህግጁነቱን ያስታወቀ የለም።  ያም ሆኖ ተስፋ ሳይቆርጡ መስራት ያስፈልጋል። አገራችን እንዳትወድም ከፈልግናና ህዝባችንም መንፈሱን ሰብሰብ አድርጎ ወደ ተሟላ ዕድገት ላይ እንዲሰማራ ከፈለግን የግዴታ ሃሳብ ላሃሳብ መወያየት አለብን። ካለበለዚያ ባንዲራ ማውለብለብና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ መጮሁ ትርጉም የለውም። መልካም ግንዛቤ!!

[email protected]

 ሰፋ ላለ ጥናት ይህንን ድረ-ገጽ ተመልከቱ

www.fekadubekele.com

በተረፈ ይህንን በፕሮፌሰር ዋልተነጉስ ዳርጌ የተጻፈ በጣም ጠቃሚ መጽሀፍ ያንቡ!

The Reason for Life

Prof. Waltenegus Dargie

2 Comments

  1. የአማርኛው ሂስ የሚለው ቃል ትርጉም አሻሚ ነው። በእንግሊዘኛው Critique እና criticism የሚሉት ለትርጓሜው ይጠጉታል እንዳንል አንድ ጥፋትን ብቻ ሲፈልግ ሌላው ቃል ደግሞ ገምቢም አፍራሽ ሆኖ ሊሰራ ይችላል። እንግዲህ ይህ የኋለኛው የእንግሊዘኛ ትርጉም በእኔ ግምት ሂስ ለሚለው የአማርኛ ቃል ተቀራራቢ ይሆናል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ለእኔ እንደሚገባኝ ሂስ ማለት እግሩን ቆርጦ ሩጥ ማለት እንዳለሆነ ነው። ያው ለሚያነክሰው ሃሳብም ሆነ አፈንግጦ አልያዝ አልጨበጥ የሚለውን እይታ አለዝቦ ወደ መስመር ለማስገባት የሚደረግ የሃሳብ ስርግብ ነው።
    የሃገራችን ገመና ከ 48 ዓመታት በፊትም የነበረ ነው። ችግራችን፤ መራባችን፤ መገዳደላችን ዘንተ ዓለም የሆነ እንጂ እንደተባለው ከ 48 ዓመት በፊት የጀመረ አይደለም። የ 48 ዓመቱን የበለጠ የሚያጎላው ንጉሱን በሃይል ከስልጣን አውርዶ እልፎችን አፈር የመለሰው ወታደራዊው መንግስት ከንጉሱ ዘመን እጅግ የከፋ መሆኑ ነው። በምስራቅም፤ በሰሜንም ሲቆራቆስ ቆይቶ ድንገት የዓለም የፓለቲካ ንፋስ አቅጣጫ ሲለውጥ ያ ተፈጥሮን እንቆጣጠራለን እያለ ያፋከረው መንግስት አውሎ ንፋስ እንደመታው ደመና ተበተነ። ለሃገር፤ ለወገን በቁርጠኝነት የተፋለሙ የቁርጥ ቀን ልጆች በጠራራ ጸሃይ በወያኔና በሻቢያ ጥምረት እየተለቀሙ በየሜዳው ተጣሉ፤ ተሰደድ፤ ባጭሩ ለልመና ተዳረጉ። ይህ የወያኔና የሻቢያ ጥምረት ብዙም ሳይቆይ ቅራኔአቸው ከሮ ያው ሌባ ሲካፈል እንጂ ሲሰርቅ አይጣላም እንዲሉ ድባ በማያበቅል በባድሜ መሬት አሳበው ከሁለቱም ወገን እልፎች እረገፉ። በጊዜው በስፍራው ተገኝቶ ስለ ግጭቱ የዘገበ አንድ ጋዜጠኛ ሁለት መላጣ ሰዎች በማበጠሪያ እንደሚጣሉት ነው በማለት ነበር መገዳደላችን የገለጠው። እበደት ከዚህ በላይ የለም። 30 ዓመት ስትገድልና ስትጋደል ኑረህ፤ ወያኔ 17 ዓመት የትግራይን ህዝብ ለመከራ ሲዳርግ ኖሮ አሁን እንሆ የከተማ አለቃ ሲሆን እንደገና ከበረሃ አጋሩ ጋር ፍልሚያ። ከዚያ በህዋላ በኤርትራም ሆነ ከቁርስራሽ በቀረችው ኢትዮጵያ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ቋሚ ስለሚመሰክር እዚህ ላይ መድገም ሰውን ማሰልቸት ነው። ጉዳዪ ችግራችን በሆነ ባልሆነው ሁሉ ቡራ ከረዪ ማለት እንወዳለን። አልሞ ተኳሽ፤ ታንክ ተራማጅ፤ እልፍ ገዳይ የሚባለው ሁሉ አሁን ፉርሽ ነው። ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ እዚያ አይን ውስጥ ከገባህ የምድር ከርስ ውስጥ ሆንክ ጫካ ውስጥ አደኖ ወደማትመለስበት ዓለም ይሸኝሃል። ያዙኝ ልቀቁኝ ምንም ተገን ለሌላቸው ሴቶችና ህጻናት ማስፈራሪያና ዘረፋ ማሳለጫ እንጂ በዘመናዊ ስልት ከሰለጠነ ወታደራዊ ተቋም ጋር የሚያዋጋ ጉራ አይደለም። መለወጥ ያለበት አስተሳሰባችን ነው። የብቀላ አስተሳሰባችን።
    የበፊቱ ጠ/ሚና የወያኔ አመራሮች ጦርነት ባህላችን ነው ሲሉ አለማፈራቸው። የትግራይ ህዝብ በእናንተ ታፍኖ እንጂ የጦርነት ባህሪ የለውም። ግን እናንተ ወንብዳችሁ አወናበዳችሁት። የአሁኑ ጠ/ሚ ደግሞ “መግደል መሸነፍ” ነው እያለን እልፎች እየረገፉ ነው። ዘንግተን እንጂ እኮ ያኔም ” ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ተብለን ነበር። ተግባር የለሽ የማታለያ ቃሎች። አይ ሃገር ሁሌ ባለህበት ሂድ። ፍቀቅ የማይል ህይወት። Viktor E. Frankl, Man’s Search for Meaning በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዲህ ይላል። “I do not forget any good deed done to me & I do not carry a grudge for a bad one.” ችግራችን የመበቀል ልባችን ሁሌ መካካስን ስለሚሻ ነው። አንተም ተው አንቺም ተይ የሚል በጠፋበት በዚህ ብርሃን መስሎ በጨለመ ዓለም ውስጥ ይቅርታ የሌለው ልብ ሁሌ ሃዘንተኛ ነው። የህዝባችን መከራ ጣራ ላይ ያወጣነው እኛው ነን። ተምረናል፤ አውቀናል፤ መጥቀናል እያለን ህዝባችን በየሰበቡ የምናባላ። አውሮፓ አሜሪካ ተጠልሎ እየኖረ ወለጋ፤ ጎንደር፤ ሃረር ሽዋ ደውሎ የዘር ፓለቲካውን የሚቆሰቁስ የቁም ሙት ምሁር ተብየዎች ነን የህዝባችን ገመና ዘመን ተሻጋሪ ያደረግነው። ዛሬ በዘርህና በቋንቋህ ወይም በክልልህ ተገን ይዘህ ጡሩንባ የምትነፋለት ጉዳይ ነገ ፉርሽ ይሆናል። ለዚህ ማስረጃው እልፍ አዕላፍ ሰዎች ያለቁበት የሶቪዪቱ የፓለቲካ እይታና የተለጣፊ ሃገሮች መፈራረስ ነው። Svetlana Alexievich የጻፈችውን – Secondhand Time: The Last of the Soviets ያነበበ ሰው የፓለቲካን ከንቱነት አበጥሮ ይረዳል።
    በተረፈ ፕሮፌሰር ዋልተነጉስ ዳርጌን በኮምፒውተር ሳይንሱ በኩል የጻፏቸውን አንዳንድ ነገሮች አንብቤአለሁ። The Reason for Life የተሰኘው መጽሃፋቸውንም ፈልጌ አነባለሁ። በመሰረቱ ዶ/ር በቀለም ሆነ አንተ ያቀረባችሁት ሃሳብ ልዪነት የለውም። የሁለታችሁም ሃሳብ ገንቢ ነው። ምድሪቱም የምትሻው አስታራቂ ሃሳብን እንጂ እሳት የሚያቀብሉትን አይደለም። በዚሁ እንበርታ። በቃኝ!

  2. ዶ/ረ ፈቃዱ በቀለ ጊዜዎን ሰዉተዉ በጽሑፌ ላይ ለሰጡት ገንቢ ግምገማ በጣሙን አመሰግኖታለሁ። በደንብ እንደጠቀሱት ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጦርነትና ወረራ ቀስቃሾች ናቸዉ። በዚህ መልክ ነዉ በባርነት፤ በቅኝ አገዛዝና በዝዉር ቅኝ አገዛዝ ዓለምን (በተለይ አፍሪቃን) የሚቦጠቡጧትና የራሳቸዉን ኢኮኖሚ የሚገነቡት። ሆዳቸዉን አስቀድመዉ ለነዚህና ለዉስጥ አምባገነን ኃይላት እያገለገሉ ህዝባቸዉን ለእንግልት የሚጋብዙ ሰዎች በሙሉ ግን ማፈሪያዎች ናቸዉ።

    ይሄን ስንል ሁሉንም ባንድ ላይ ከመጨፍለቅ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለእዉነት ቆመዉ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ብዙ አእላፍ ናቸዉ። እጅግ ታታሪና ደግ ህዝብ ነዉ። የተጠማዉ የዲሞክራሲ ሥርዓትንና ሰላምን ነዉ። ዘረኝነት ተጫነባቸዉ እንጂ እርስ በርሱ ተፈቃቅሮና ተደጋግፎ ለብዙ ሺ ዓመታት የኖረና የተከበረ ህዝብ ነዉ። ዛሬ በሩዋንዳ ስለዘረኝነት መስበክ በሕግ ያስቀጣል፤ ከመራር ታሪካቸዉ ተምረዋልና። የኛም ህዝብ የሚፈልገዉን ጠንቅቆ ያዉቃል፤ ሰላም፤ ሰላም፤ ሰላምና መልካም አስተዳደር። በዚህ ላይ መረባረብ ይኖርብናል።

    አቶ ተስፋንም ለገንቢ አስተያየታቸዉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
    በቀለ ገሠሠ

Leave a Reply

Your email address will not be published.