የመለስ ልጆች ድርድር እና “የትጥቅ ይፍቱ” ማጭበርበሪያ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ሀ. የመለስ ልጆች ድርድር

ከድርድሩ ምን እንጠብቅ? የመለስ ራዕይ አስቀጣይ የሆኑት ሕወሃትና ብልጽግና (ኢሕአዴግ ቁ.2) የሚሠሩት ነገር ሁሉ መለስ የሠራውን ኮፒ ፔስት ነው ለማለት ያስደፍራል። ይሄንን ከተገነዘብን ድርድሩ በምን መልኩ ያልቅ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አይከብደንም።  ልናስተውለው የሚገባን ነገር የጦርነቱ መንስኤ ተብሎ ለኛ የሚነገረን እና እውነተኛው ምክንያት የተለያዩ መሆናቸውን ነው። ፊትም ሻዕቢያና ወያኔ በባድሜው ጦርነት ጊዜ  ለሕዝቡ የሚነግሩትና በእውነት የተጋጩበት ጉዳይ የተለያየ ነበር። ስለዚህ በውጤቱም እነመለስ እንዲፈጸም ያደረጉት እና ሕዝቡ የጠበቀው የተለያየና የማይገናኝ ሊሆን ችሏል።

ዛሬስ? የኢህአዴግ ክፍልፋዮች ለኛ የነገሩን የግጭታቸው መንስኤ እውነተኛውን ስላልሆነ የድርድሩ ውጤትም እኛ የምንጠብቀው ውጤት አይሆንም ማለት ነው። በዚያን ጊዜው ድርድር “ሻዕቢያ ድንበር ጥሶ የኛ የሆኑትን መሬቶች (ባድመን) ስለወረረ ነው ወደ ጦርነት የገባነው” ሲሉን በጦርነት አሸናፊ እንደመሆናቸው በድርድሩም ያንኑ አስጠብቀው ተነጠቅን ያሉትን መሬት ያስከብራሉ ብለን ጠብቀን ነበር። በተቃራኒው ሌሎችንም መሬቶችን ጨማምረው በመስጠት ድጋሚ ይግባኝ ወደ ማይባልበት ፍርድ ቤት በፈቃደኝነት ሄደው ለሻዕቢያ አስረክበዋል።

ይህ የሚያሳየን የጦርነቱ ዋና ምክንያት ለኛ የተነገረን የድንበር ውዝግብ ጉዳይ እንዳልነበረ ነው። አለበለዚያማ መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን የረገፉበትን ጦርነት በበላይነት ካጠናቀቁ በኋላ ድሉን በድርድሩ ወደ ሽንፈት የሚቀይሩበት ምክንያት ባልኖረ ነበር። ዛሬ እንደሚታወቀው የባድመ ጦርነት በወያኔ እና በሻዕቢያ መካከል የነበረውን የጌታና የኣሽከር ግንኙነት መልክ ለማስያዝና ወያኔ ጌታ እንጂ አሽከር አለመሆኑን ለማሳየት የተደረገ ጦርነት ነበር። የድንበር ጉዳይ ለወያኔ ቁም ነገር አልነበረውም። አሰብና ምጽዋን ያለማንገራገር ያስረከበ ወያኔ ባድመ ለተባለች ጉብታ ብቻ ብሎ ጦርነት መዋጋትም ሆነ መቶ ሺህ ሰው መገበር የሚፈልግ አይደለም።  በተጨማሪም ባድመም ሆነ መረብ እነ መለስ ኤርትራንም ኢትዮጵያንም አፍርሰው ሊመሠርቱ ላሰቧት የታላቋ ትግራይ ሪፕብሊክ መሐል አገር ላይ የሚገኙ ቦታዎች እንጂ የድንበር ሥፍራዎች አይደሉም። ይልቁንም የማያምኑበት የድንበር ውዝግብ የፈጠረውን አጋጣሚ ለቀጣዩ ዘመቻ እንዲያግዝ አመቻችተው፣ ውዝግቡ እንዳይፈታ እያደናቀፉ አካባቢው ላይ ግዙፍ ጦር እንዲሰፍርበት አድርገው ኖረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዐብይ አሕመድን ይጸየፉታል እንጅ አይጠሉትም - መስፍን አረጋ

ዛሬም የጦርነቱ ዋና መንስኤ የጌታና የሎሌን ትክክለኛ ቦታ ማሳወቅን የሚመለከት ነው። ኦህዴድ ጌታ ትህነግ (ወያኔ) ሎሌ መሆናቸው ከታወቀ ሕዝቡ እንደሚያስበውና እንደሚመኘው አሸባሪ የተባለችው ሕወሃት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እንድትወገድ በአገዛዙ ዘንድ ፍላጎት የለም። ልክ ወያኔ ሻዕቢያን በጦርነት አሸንፋ መለስ የባዕዳን ጫና ምንትሴ በሚል ፉገራ ጦሩ አሥመራ እንዳይገባ እና ሻዕቢያን እንዳይደመስሰው እንዳደረገው አሁንም የምዕራባውያን ጫና በሚል ድራማ የወያኔ ሕልውና እንዲቀጥል ይደረጋል ማለት ነው። መለስ ኮፒ ፔስት። አምናም ወያኔ ዱቄትና አቧራ ሆና በቆላ ተምቤን ከተወቀጠችበት ተመልሳ ተቦክታ የተጋገረችበት፣ ነፍስ የተዘራላትም ምክንያቱ በሌላ ሳይሆን በዚሁ ኦህዴዳዊ የመለስ ኮፒ ፔስት የቁማር አስተሳሰብ ነው።

የመለስ ልጆች የጦርነትና የድርድር ባሕል የመለስን የጦርነትና የድርድር ባሕል የሚደግም ነው። ኮፒ ፔስት እንጂ ኦሪጂናል ነገር አያውቁምና። ስለዚህ የመለስ ድርጊት ሊደመሰስ የነበረውን ወራሪውን ሻዕቢያን በሕልውና ያቆየ፣ በድሉ የተገኘውን ኢትዮጵያዊ እድል ያባከነ ከነበረ የልጆቹም ድርጊት በተመሳሳይ ወራሪና አሸባሪውን ሕወሃትን በሕልውና የሚያቆይና በመቶ ሺዎች መስዋእትነት የተገኘውን ድልና እድልም የሚያባክን ነው የሚሆነው። የሚያመጣልንም እፎይታን ሳይሆን ቁጭትን ነው። የክህደትን አንግብጋቢ እሳት ነው የሚያስታቅፈን። ይበልጥ አስቀያሚ የሚያደርገው ደግሞ ያንን መራራ ሕዝባዊና ሀገራዊ ሽንፈት ጣፋጭ ለማስመሰል የሚያጅበው የፖሮፓጋንዳ ማእበል ነው። ዛሬ አንድ ስዩም መስፍን ሳይሆን በኦህዴድ ተከፋይ የሆኑ አእላፍ ስዩም መስፍኖች መኖራቸውን ልብ ስንል ከወዲሁ ከፍተኛ የማቅለሽለሽ ስሜት ይጠናወተናል። ይሁን እንጂ መራራውን እውነት አውቆ መጠበቁ ከከፋ ሕመም ይታደገናልና የመለስ ልጆች ላይ ያልተገባ ተስፋ ሳንጥል የሥነ ልቡና ዝግጅት አድርገን እንቆይ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትንሽ ስለጃዋራዊያን (ለፋሲል የኔአለም መልስ)

ለ.  ሕወሃት ትጥቅ ትፍታ የሚለው የነ አቢይ ማጭበርበሪያ

ዋናው ችግር ሕወሃት የተከለው የጎሳ አፓርታይድ ሥርዐትና የሕወሃት አሸባሪ ባሕርይ ናቸው። መፍትሄውም የሕወሃትን ሕልውና ሰርዞ አፓርታይዳዊ ሥርዐቱን በዜጎች የእኩልነት ሥርዐት መተካት ነው። ድርድሩ ግን ወደዚያ ሊወስደን አይችልም። ትልቁ ጥያቄ ሆኖ የቀረበው ሕወሃት ትጥቅ ትፍታ የሚል ነው።

ይህ ጥያቄም ማጨበርበሪያ የተባለበት አስመሳይ እንጂ ችግሩን በዘለቄታ የማይፈታ መደራደሪያ ስለሆነ ነው። እንዴት? እንዴትማ የነቃ የተደራጀ የታጠቀ ሕዝብ ያሸንፋል ይባል የለ? ከሕወሃት ትጥቋን ብቻ ተቀብሎ ሌሎቹ ችግሮች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታሉ እያሉ ማውራት ትርጉሙ የተቀሙት የአማራ መሬቶች ተመልሰው ወደ ትግራይ እንደሚካለሉ ይነግረናል። ድርጅታዊ ሕልውናዋ ካልተነካባት ለሕወሃት ትጥቅ ትልቁ ችግሯ ሊሆን አይችልም። ሲጀመር ትጥቃችን ከጠላታችን የሚል ብሂልና ታሪክ ያላት ሕወሃት መንግሥት ራሱ የትጥቅ ምንጯ ይሆናል።  ሲቀጥል ሕወሃት ትግራይ ውስጥ ያላትን የድርጅት የበላይነት ተጠቅማ በነዚህ በሚለገሷት የሱዳን አዋሳኝ መሬቶች በኩል ከሀገር ዘርፋ በውጭ አገር ካስቀመጠችው ገንዘብ መሣሪያ እየገዛች ለማስገባት የሚቸግራት አይሆንም። ሦስተኛ ወዳጆቻችን እነ ግብጽና ጋላቢዎቻቸውም ትህነግን ለማስታጠቅ ዐይናቸውን አያሹም።

ይሁን እንጂ ሕወሃት (ትህነግ፣ ወያኔ) በነዚህ መንገዶች አሸባሪነትና አዋኪነቷን መቀጠሏ ለኦህዴድ እንደ መልካም አጋጣሚ እንጂ እንደ እክል የሚታይ አይሆንም። ልክ የሻዕቢያን ሕልውና ማስቀጠልና እና የድንበር ውዝግቡን አለመቋጨትን ከባድመ ጦርነት በኋላ ትግራይ ላይ ግዙፍ ጦር ለማስፈሪያ መልካም ሰበብ አድርጎ መለስ ተጠቅሞባቸው እንደነበረው ማለት ነው። ኦህዴድም የተቆጣጠረውን የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው አሰማርቶ የአማራ፣ አፋርና የትግራይን አካባቢዎች በወታደራዊ ቁጥጥር ለማዋል፣ የሕወሃትን ድክሞ – አሸባሪነት ተፈላጊ ኩነት አድርጎ ይጠቀምበታል ማለት ነው። እድሜ ለማራዘም፣ ሰሜኑን ለማድቀቅ፣ ኦሮሚያን በአንጻራዊነት ለመገንባት። ምክንያቱም ኦህዴዶች ለትግራይም ሆነ ለአማራ/ አፋር ሕዝብ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚያመጣ ራዕይም ሆነ ፍላጎት የሌለው የኦሮሙማ ፍኖተ ካርታ ተከታዮች ናቸውና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል” አሉ . . . ወይ ብሔረ-ጽጌ! - አከለው የሻነው ደሴ

ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም መክሰም የሚገባቸው የሕወሃት ሕልውና እና ሕወሃት የተከለው የጎሳ አፓርታይድ ሥርዐት ናቸው። ይህ ደግሞ የገዢው ኦህዴድ ፍላጎት አይደለም። ብቻውን ከሕወሃት ጋር በሚያደርገው ድርድርም ይህንን ግብ ለማሳካት ሊጥር አይችልም። ለዚህ ነው የሀገር እጣ ፈንታ እና የጦርነቱ ፍጻሜ በሚወሰንበት ድርድር የአማራን ሕዝብም ሆነ የሌሎች ተጠቂዎችን ጉዳይ የኦህዴድ መንግሥት በፍጹም ሊወክል አይችልም እየተባለ የቀረበበት ክሥ ትክክለኛ የሚሆነው።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.