ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ ቁራው እርግብ ነኝ ብሎ ሲመጣ! – በላይነህ አባተ

ሰውን በሥራው መዝን ብትባል በስብከት ወናፍ የነፈስክ፣
ዛሬም እንደ ታች አምናው እጅ እስቲመለጥ ማጨብጨብ የጀመርክ፣
በስልጣን ሽሚያ ግብግብ መቃብር የገቡ ዜጋዎች ስቃይና ሞት ሳይገድህ፣
እግዜር ተሆድ በሽታ ፈውሶ አዙር የሚያይ አንገትን ልጓም ህሊናን ያድልህ፡፡

እውነት እንደ ጥጥ ፍሬ ተድጣ ፍትህ ተነሚዛኗ ተሰብራ፣
ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ ቁራው እርግብ ነኝ እያለ ሲመጣ፣
አንተን የተቀበልከውን ከንቱ “በእንኳን ደሳለን!’ እልልታ፣
የሐቅ የፍትህ አምላክ እንደ መስታዎት አፍጦ ይይህ ጧት ማታ፡፡

ይሁዳን ለዳገመኛ አምነህ እውነትን ተከንች የሰቀልህ፣
ነፍሱ ተስጋው ስትለይ በፍትህ ከፈን ተቋጥኝ ሥር የቀበርህ፣
የእውነት የፍትህ ቀበኞች የፈሪሳውያን ሆኗል ታሪክህ፡፡

የመጽሐፍ ቃል ቆርጥመህ እርቅን ተፍትህ ነጥለህ፣
በእልፍ አእላፉ ሰቆቃ ቀልደህ የአስከሬን ክምር ረግጠህ፣
ከእነ እሲጥፋኖስ ገዳዮች ጋራ “እንኳን ደስ አለን!” የጨፈርህ፣
የሰማእት ነፍስ ዘላለም በውንህ በህልምህ በቅዠትህም ይጎብኝህ፡፡

ሳጥናኤል መላ አያልቅበት የጅል ልብ ሰቅሎ የሚያንዘላዝል፣
አንተ አይሰለችህ እንደ ልጅ በከረሚላ በሚቃም ስኳር መታለል፣
ዛሬም እንደ ትናንቱ ቁራ ሲመጣ እርግብ በል ይሁዳን አምነህ ተከል፡፡

በላይነህ አባተ ([email protected])
ጥቅምት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅ!

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.