ያሳለፈነው ምዕራፍ ላይደገም ተደርጎ መቋጨት ይኖርበታል

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስትና በህውሀት መካከል በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ደስታችንን እየገለፅን ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እንወዳለን።

በዚህ ስምምነት የአፍሪካ ህብረት መሪዎችና ሀገራት ግንባር ቀደም ስፍራ ይዘው ሁለቱን ወገኖች በማስማማት ይህንን ታሪካዊ ሰነድ እንዲፈረም ስለረዱ ደስታችንን ድርብ ያደርገዋል። አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት ሁነኛ ማስረጃ ሆኗል። ከሁሉም በላይ ይህንን ስምምነት እውን እንዲሆን በደሙና ባጥንቱ ኢትዮጵያን ላቆያት መላው የመከላከያ ሰራዊት፣ የፋኖ ሚሊሺያ፣ የአማራና የአፋር ልዩ ሀይሎች የህዝብና የሀገር ባለውለታዎች ናቸው። የዛሬዋ እለት በሰሜን እዝ ላይ ክህደትና ጭፍጨፋ የተካሄደበት ሁለተኛ አመት የምንዘክርበት ቀን ነው። ይህንን ቀን የጥይት ጩኸት በአገራችን ምድር እረጭ ብሎ፣ ህዝባችህ የተጠማውን የሰላም ትንፋሽ እየተነፈሰ ለማክበር በመብቃታችን የዘወትር ጠባቂያችን አምላካችንን ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን።

ይህ የተደረሰው ስምምነት በስራ ላይ እንዲውል ሁለቱም ወገኖች በተወሰነው የጊዜ ገደብ ግዳጆቻቸውን በቅንነት እንዲወጡ የሁላችንም አደራ አለባቸው። እኛ በሀገር ውስጥም በውጭም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ሚድያዎች፣ ትብብራችን ሙሉ ለሙሉ ይህንን ስምምነት ከሚያስፈፅሙት አካላት ጋር እንዲሆን ድርጅታችን በአንክሮ ያሳስባል። ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ልጆቿን፣ በድሃ አቅም የገነባችው መሰረተ ልማቶቿን በዚህ ጦርነት አጥታለች። ይሄ አሳዛኝ ክስተት መቼውም ቢሆን ሁለተኛ የማይደገም መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ስምምነቱ መተግበር ይገባዋል። ያሳለፈነው ምዕራፍ ላይደገም ተደርጎ መቋጨት ይኖርበታል! አልፎም ለሀገራችን ዘለቄታዊ ሰላም እንቅፋት የሆኑት ዘረኝነት፣ የዘር ፖለቲካ፣ በዘር የተደራጀ ሰራዊት የመሳሰሉት አፍራሽ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን ማስወገድ በአፋጣኝ ሊደረግ የሚገባ ትግባራችን ነው፤ ውጤቱን አየነውና።

በሀገራችን በጦርነቱ የተጎዱ ቤተሰቦች፣ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች ወዘተ መልሶ ማቋቋም ቀዳሚ የመንግስትና የህዝብ ስራ መሆን ይገባዋል እንላለን። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያውያን፣ በተለይም በዳያስፖራ የምንኖረው፣ ልዩ የታሪክ ሃላፊነት አለብን። ሁለት አመት ሙሉ ከህዝባችንና ከሰራዊታችን ጎን ቆመን በውስጥም በውጭም የተደረገብንን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ተፋልመናል። አሁንም ብዙ ስራ ይቅረናልና፣ ዘር ጎሳና የፖለተካ አስተሳሰብ ሳይለየን ከህዝባችን ጋር ተሰልፈን አገራችንን መልሰን እናቁማት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤

አምላክ እዚህ ስላደረስከን ተመስገን፣ ሀገራችንን ባርክልን ህዝባችንንም ጠብቅልን።

ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 24፣ 2015

Leave a Reply

Your email address will not be published.