የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ዒላማን እና አቅጣጫን የሳተ አስተሳሰብና አካሄድ! – ጠገናው ጎሹ

November 27, 2022
ጠገናው ጎሹ

 

ባለፈው ሰሞን ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጎብኘት ላይ እያለሁ አንድ ትኩረቴን የሳበ የቪዲዮ ቅንብር አየሁና በጥሞና ተመለከትኩት።

ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ምሥጋና ይግባውና በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን አንድን ርዕሰ ጉዳይ ድራማዊ (dramatized) አድርጎ ማቅረብ የተለመደ በመሆኑ ቅንብሩ አላስደመመኝም።

የአንድን ጉዳይ ምንነት ፣ ለምንነትና እንዴትነት የተሟላ የሚያደርገው ቅርፁና ይዘቱ ሲጣጣሙ ነውና ከእይታ ቀጥሎ በትኩረት (በጥሞና) ለመረዳት የሞከርኩት ስለ ይዘቱ  ነበር። ዋነኛ ይዘቱ (መልእክቱ) ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ትውልድ የሚገደንን ያህል በአሜሪካን አገር ለሚኖረው ዳያስፓራ ትውልድም ሊገደን ይገባልና እጅግ ሰፊ በሆነ ቦታ ላይ ለሚገነባው ትልቅና ባለ ብዙ ዘርፍ ገዳማዊ ካምፓስ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በአስቸኳይ ማግኘት አለብን የሚል መሆኑን የተረዳሁት በተደበላለቀ ስሜት ነበር።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት መነጋገር ካለብን በአንድ በኩል በእኩያን ገዥ ቡድኖች ፣ በአድርባይ ግብረበላዎችና እንዲሁም የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ሃላፊነት በሚመጥን ሁኔታ ለመወጣት በተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ልክ የለሽ ደካማነት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ግዙፍና መሪር ሃቅ እና  በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች የመኖራቸው እውነትነት እንደተጠበቀ ሆኖ በታሰበው ገዳማዊ ቦታ ላይ ሊገነቡ የታሰቡትን ተቋማት ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ተሟልተው በሚገኙበት አሜሪካ የሚኖረው  ዳያስፖራ ጉዳይ እኩል አሳሳቢ እንደሆነ አድርጎ  ለማነፃፀር የተሞከረበት ማብራሪያ እጅግ ፈታኝ የሆነ ድብልቅልቅ ስሜትን ይፈጥራል።

የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ መጋፈጥ ሲሳነን የሰበብ ድሪቶ መደረቱን ስለምንወድ ነው እንጅ የዚህ ዘመቻ ወቅታዊነት (የቅድሚያ ቅድሚ ትኩረት አገናዛቢነት) ፣ ቅንናነት ፣ ሞራላዊ ክብደትና ሚዛናዊነት ለዘመናት የዘለቀውና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለመግለፅ በሚያስቸግር አኳኋን አስከፊና አስፈሪ ሆኖ የቀጠለው የሸፍጠኞችና የጨካኞች ሥርዓት  እያስከተለ ካለው አጠቃላይና የሆነ ቀውስና ወድመት አንፃር ሲፈተሽ በእጅጉ አጠያያቂ ነው ።

ኮሜዲያን እሸቱ ዶንኪ ቲዩብ (donkey tube) ብሎ በሰየመው ማህበራዊ ሚዲያው ተቀነባብሮ (dramatized) ተደርጎ በቀረበው ቪዲዮ መግቢያ ላይ በአንድ የሃይማኖት አባት ብርቱ ለሆነ በጎ ሥራ እንደሚፈለግ የሚያሰተጋባ ድምፅ እንሰማለን ። ቀሳውስቱም እሸቱን በሥርዓት አጅበው ክፍት ሆኖ ይጠብቅ ከነበረው የቤተ ክርስቲያን በር ድረስ ካደረሱት በኋላ “በል ሂድ እንግዲህ” ብለውት ይመለሳሉ።

እርሱም የሥርዓቱን አለባበስና አቀራረብ በጠበቀ ሁኔታ ይፈልጉሃል ወደ ተባሉት የሃይማኖት አባት ሲጠጋ ሲፈለጉት የት እንደጠፋ ከጠየቁትና እርሱም መልስ ከሰጠ በኋላ “አንተ አሜሪካ ያለው ትውልድ አይገድህምን? እዚህ ያለው ብቻ ነው የሚገድህን?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁት “ኧረ ይገደኛል” ሲል ይመልሳል።  እነዚህ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው የፕሮግራሙን  ዓላማና ግብ ግልፅ አደረጉልኝና በጥሞና መከታተሌን ቀጠልኩ። በአሜሪካ (የካሊፎርኒያ ግዛት) የአዲስ የአበባን ግማሽ በሚሆን ቦታ ላይ ታሪካዊነት ያለውና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ “ገዳማዊ ማዕከል” ለመመሥረት  ፕሮጀክት እንደተነደፈና ለዚህም እውን መሆን በብዙ ሚሎዮኖች የሚቆጠር ዶላር በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ የሚገልፅ የዘመቻ ቅንብር መሆኑን ተገነዘብኩ።

ዘመቻው በመሠረተ ሃሳብና በመርህ ደረጃ ሸጋ መሆኑን ለመቀበል ፈፅሞ አይከብድሞ።

እንዲህ አይነት ዘመቻ የተደረገው (የሚደረገው) ማነኛውም አገር ሊያጋጥሙት የሚችሉና  በቀላሉ ሊፈቱ (ሊወገዱ) የሚችሉ ችግሮች ያጋጠማትና እያጋጠማት ያለች አገር ሰዎች ቢሆን ኖሮ እሰይ (ይበል) የሚያሰኝ  እንጅ ጥያቄ የሚያስነሳ ባልሆነ ነበር ።  ዘመቻው መከረኛው የአገሬ ህዝብ እኩያን ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን በጋራ ትግል አስወግዶ የምትበጀውን ዴሞክራሲያዊት አገር እውን እንዲያደርግ የሚስችለው የፖለቲካ ሃይል እና ለዚሁ እውን መሆን የመንፈስ ብርታት (አይበገሬነት) እንዳይለየው ተገቢውን እገዛ የሚያደርግለት የሃይማኖት መሪ በተገቢው ሁኔታ ለማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት የገዛ አገሩና ቀየው ምድረ ሲኦል በሆነበት ወቅትና ሁኔታ ውስጥ እንዲህ አይነት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳተ ዘመቻ ምነው ምኑ ነካን? የሚል ብርቱ ጥያቄ ማስነሳቱ የማይጠበቅ አይደለም።ለዚህ አይነት ዘመቻ የፈጣሪን ፈቃድኝነትና ፍላጎት መፈናፈኛ እንደሌለው መከራከሪያና ማሳመኛ በማነብነብ ጥያቄ የሚያነሳን ሰው ሁሉ “ውጉዝ ከመ አርዮስ” ማለት የሚቃጣቸውና ዝም ለማሰኘት የሚሞክሩ ወገኖች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ለእነዚህ ወገኖች ያለኝ መልስ የኢትዮጵያን ህዝብ መከራና ውርደት ከማንም በላይ የሚያውቅ እውነተኛ አምላክ እንዲህ አይነቱን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳተ አስተሳሰብና አካሄድ የሚወድ እውነተኛ የለም የሚል ነው።

አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን በገዛ ራሳችን እጅግ ልክ የለሽ የአስተሳሰብና የተግባር ውድቀት ምክንያት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን በእጅጉ የሚሹ (ግድ የሚሉ) እጅግ በርካታና አንገብጋቢ ጉዳዮች የሚርመሰመሱባት አገር ሰዎች ሆነን በቀጠልንበት በዚህ እጅግ አስቸጋሪና አስፈሪ ወቅት በአንፃራዊነት አብዛኛው መሠረታዊ አገልግሎት በተሟላበት የባህር ማዶ አገር (አሜሪካ) ለሚኖሩ ወገኖች “ታሪካዊ ፕሮጀክት ነድፈናልና (አስነድፈናልና) ርብርብ በማድረግ የበረከቱ ተሳታፊ ትሆኑ ዘንድ በፈጣሪ ስም እንጠይቃለን” የሚለውን ጥሪ ያለ ጥያቄ ወይም በዝምታ ወይም በምን አገባኝነት ወይም ባስመሳይነት ለማለፍ መሞከር በእጅጉ የተዛባ አስተሳሰብና አካሄድ ነው።

አዎ! ዘመቻውን በበጎ ራዕይነትና በመርህ ደረጃ ለመቀበል የሚያስቸግር ባይሆንም እጅግ ብልሹና ጨካኝ በሆኑ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲከኞች ምክንያት ለንፁሃን ልጆቿ ምድረ ገሃንም (ሲኦል) እንድትሆን የተፈረደባት እናት ምድር ሰዎች ሆነን ባለንበት በዚህ እጅግ አስከፊ ወቅት ባህር ማዶ ታሪካዊ ለሚሰኝ ገዳማዊ ማእከል ግንባታ በሰዓታት ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ካላዋጣችሁ የሚል ዘመቻ መክፈት ምነው ምን ነካን? ያሰኝ እንደሆነ እንጅ የብልህነት (የአዋቂነት) እና የፅድቅ መንገድ ከቶ ሊሆን አይችልም። በዚህ እጅግ የተዛባ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን የሚደሰት እውነተኛ አምላክም የለም።

ለብዙ ዘመናት ከመጣንበትና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከሆነውና እየሆነ ካለው ለመግለፅ በእጅጉ የሚያስቸግር አገራዊ መከራና ውርደት አንፃር የሃይማኖታዊ እምነት  መሪዎችና ሰባኪዎች ምን ያህል ጥረት አደረጉ? የሚለውን ጥያቄ ትርጉም በሚሰጥ አኳኋን ለመመለስ ባልቻልንበት በዚህ እጅግ ፈታኝ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ እንዲህ አይነት ግዙፍ (grandiose) ለሆነ የባህር ማዶ ገዳማዊ ማእከል የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር ሲሆን አሁንኑ ካልሆነም በየትኛውም ጊዜ ለግሱ የሚል ዘመቻ እንኳንስ ከሃይማኖታዊ እምነት መሪዎች ሚዛናዊ ህሊና ካለውና እውነተኛ የአገር ውስጥ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚጠበቅ አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወገን ሆይ ክፉ ሞቶም ይገድላል …እንዳትታለል ! -  ማላጂ

የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን ያላገናዘበ ራዕይና ዓላማ ልክ የለሽ የሆነ የግል ወይም የቡድን ታሪካዊ አሻራ ከማሳረፍ ፍላጎትና ጥቅም ፈፅሞ አያልፍም። በፖለቲካችንም ያጋጠመንና እያጋጠመን ያለው ግዙፍና መሪር እውነትም ይኸው ነው። እየሠራን የማፈራረሳችንና እየተሰባሰብን የመበታተናችን እጅግ ከባድ አባዜ የሚመነጨውም አሻራ ማስቀመጥን ጨምሮ ከዚሁ የግልና የቡድን ዝና፣ ፍላጎትና ጥቅም ፈላጊነት ክፉ አባዜ ነው። 

ለዘመናት ከዓለም ለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች ተመፅዋችነት ለመውጣት ካለመቻላችንም በላይ ሸፍጠኛና ጨካኝ የኢህአዴግ አንጃዎች በቀሰቀሱት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሚሊዮኖች ንፁሃን ህይወት ትርጉም ባጣበትና አጠቃላይ አገራዊ ውድመት በደረሰበት በዚህ እጅግ ፈታኝ ወቅት ለእንዲህ አይነት እጅግ ለገዘፈ የባህር ማዶ ገዳማዊ ማእከል በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ዶላር “ከሰጣችሁ ትፀድቃላችሁ” ማለት ምን የሚሉት ፅድቅ እንደሆነ እንኳን ለማመን ለመገመትም የሚቻል አይመስለኝም።

እዚያው አገራችን በምንለው ምድር ላይ የሚኖር ወገን (ህዝብ) የርሃብ ጠኔ ሰለባ በሆነበት ፣ በብርድ አለንጋ ክፉኛ እየተመታ ባለበት፣ የህመም ስቃይ ቁራኛ በሆነበት፣  በድንቁርና ጨለማ ውስጥ እየዳከረ ባለበት፣ የነገ ፍሬዎች የምንላቸው ህፃናትና ወጣቶች ፊደል የሚቆጥሩበት የጭቃ ጎጆ እንኳን ተነፍጎቸው እጣ ፈንታቸው በተበላሸበት፣ ቤት እምነቶችና ምእምናን በጥፋት ሃይሎች ከምድረ ገፅ እንዲጠፉ እየተደረጉ ባሉበት፣በስመ ባህታዊነትና አጥማቂነት የተሠማሩ መሠሪዎች በየቦታው በገዳምና በቤተ ክርስቲያን ስም ባቋቋሟቸው ማእከላት የፈጣሪን ስም በቀሚስ ፣በካባና በቆብ ለተሸፈነው ዓለማዊ ፍላጎታቸው (ጥቅማቸው)  እያዋሉ የመሆናቸው መሪር ሃቅ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ተባብሶ በቀጠለበት ፣ ከግፍ ግድያ የተረፉ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ከገዛ ቀያቸው ተነቅለው የሚያፅናናቸው አጥተው የሰውና የወገን  ያለህ በሚሉበት እና በግፍ የተገደለ አስከሬን የገዛ አገሩን አፈር እንዳይለብስ በሚደረግበት ግዙፍና መሪር ሁኔታ ውስጥ “በባህር ማዶ ታሪካዊ የሆነ ገዳማዊ ማእከል መሥረተን ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፋለን” የሚል ዘመቻን ያለምንም ጥያቄ ማለፍ ፈፅሞ ትክክል ሊሆን አይችልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው “የገዛ አገራቸውና ቀያቸው ምድረ ሲኦል የሆኑባቸውንና እየሆኑባቸው ያሉትን ንፁሃን ወገኖች ጉዳይ እንዳልተፈጠረ እየቆጠርክ ለምንና እንዴት በመናፈሻና በችግኝ ተከላ ላይ ተጠመድክ? ተብሎ ሲጠየቅ “ለእነርሱው ሙት አካል (ሬሳ) ማረፊያ ጥላ የሚሆናቸው ችግኝ እየተከልኩላቸው ነው” የሚል እጅግ አረመኔያዊ የፖለቲካ ስላቅ ሲሳለቅ ከምር ያልተቆጣና በግልፅና በቀጥታ ወጥቶ ነውር ነው ለማለት ያልደፈረ የሃይማኖት መሪ (አባት)  መከረኛው ህዝብ በዚሁ ጠቅላይ ሚኒስትርና በባልደረቦቹ የብልግና እና የጨካኔ ፖለቲካ ጨዋታ ምክንያት እጅግ ግዙፍና መሪር የግፍ ፅዋ እየተጋተ ባለበት በዚህ እጅግ ፈታኝ ወቅትም “ታሪካዊ ለሆነው የባህር ማዶ ገዳማዊ ማእከል በፍጥነትና በአጥጋቢ ሁኔታ ብትለግሱ በረከቱ ለእናንተ ነው” ሲል ለምንና እንዴት ብሎ አለመጠየቅ ፈጣሪ ለታላቅ ዓላማ የሠራውን ረቂቅ አእምሮ ያለመጠቀም ድንቁርና ነው የሚሆነው።

በእንዲህ አይነት እጅግ ለስሜት ቅርብ በሆኑ (sensitive & sensational) ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሂሳዊ አስተያየት መሰንዘር ቁጥሩ ቀላል ለማይሆን ወገኔ የሃጢአቶች ሁሉ ሃጢአት መስሎ ሊሰማውና የውግዘት ናዳ ለማውረድ ሊቃጣው እንደሚችል በሚገባ እረዳለሁ።

የአገራችን ባህልና ወግ በተለይ የሃይማኖት መሪዎችን፣ ልሂቃንን ፣ አስተማሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አገልጋዮችን አስተሳሰብና አካሄድ ግልፅነትን በተላበሰ ፣ ቀጥተኛ በሆነ እና አግባብነት ባለው አስተያየት ለመተቸት ፈፅሞ የሚያመች ወይም የሚፈቅድ እንዳልሆንም በሚገባ እገነዘባለሁ።

ይህን አስተያየቴን ባለንበት ተቸክለን (የገዛ ውድቀታችን ላስከተለብን መከራና ውርደት ሰንካላ ሰበብ ከመደርደር እና ፈጣሪን ና ውረድ ከማለት ያለፈ ሥራ ሳንሠራ) ፍስሃ (ሃሴት/ደስታ) የሞላበት ዓለማዊና ሰማያዊ ህይወት ለመናፈቃችን ደካማ ልማድ በሚመች አቀራረብ ልግልፀው ብችል ኖሮ ደስ ባለኝ ነበር። ይህ ግን ለዘመናት የመጣንበትና ከአዙሪቱ ወጣን ስንል መልሰን አዙሪቱ ውስጥ እየተዘፈቅን የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ለመስወዕትነት በሚያደርስ ደረጃም ቢሆን ሃይማኖታዊ ተልእኳቸውንና ሃላፊነታቸውን ለመወጣት የተሳናቸው ወገኖች ሰለባዎች ያደረገን በመሆኑ አላደረግሁትም። አላደርገውምም።

ሃይማኖታዊውና ባህላዊው ምንነታችንና ማንነታችን መሠረታዊ አመጣጡንና እሴትነቱን ሳይስት ለዚህ ዘመን ትውልድ ተገቢውንና ገንቢውን ግንዛቤ በሚያስጨብጥ አቀራረብ እና ተግባራዊ በሆነ አርአያነት ለማገዝ እልህ አስጨራሽ የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሁለት  ወይም ከዚያ በላይ የሆኑና ፈፅሞ ለማነፃፀር የሚያስቸግሩ ሁኔታዎችን እያወዳደሩ በእኩል ደረጃ ያሳስቡኛል (ያሳስቡናል) በሚል ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ተፈፃሚ ካላደረግሁ (ካላደረግን) ሞቼ እገኛለሁ/ሞተን እንገኛለን ማለት እንኳንስ ለሃይማኖት መሪና አስተማሪ ለማነኛውም አስተዋይና ሚዛናዊ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው ጨርሶ አይመጥንም።

አዎ! በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ ሰፊና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ገዳማዊ ማዕከል መመሥረትን የሚቃወም ባለ ጤናማ ህሊና የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

ለዘመናት በዘለቀውና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳን ለማየትና ለመስማት ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ በቀጠለው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች (ቁማርተኞች) ምክንያት የገዛ አገሩ ምድረ ሲኦል የሆነችበትን መከረኛ ህዝብ በአሜሪካ ከሚኖረው ዳያስፖራ ጋር እያነፃፀሩ “ይህንና ያንን ያህል ሚሊዮን ዶላር በዚህን ያህል ሰዓት ካልሞላችሁ አንላቀቅም “ የሚል አይነት ዘመቻ በተለይ ከሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች መስማትና ማየት ግን እውን እንዲህ አይነት ኢሚዛናዊ የሆነ (የቅድሚ ያቅድሚያ ትኩረትን ፈፅሞ የሳተ) አስተሳሰብንና አካሄድን ፈቅዶና ባርኮ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ አለን? የሚል እጅግ ከባድና መሪር ጥያቄ ያጭራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዕድገት ወይስ ዉድመት? - ዶ/ር በቀለ ገሠሠ

እጅግ አብዛኛው ፊደል የቆጠርኩ ምእመን (አማኝ) ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የራሱን የመረዳት አቅም፣ መርህና የእምነት ማንነትና እንዴትነት ለአላስፈላጊ ትህትና (ይሉኝታ) አሳልፎ በመስጠት በአገር ውስጥ ከሆነውና እየሆነ ካለው ለመግለፅ የሚያስቸግር እጅግ ግዙፍና መሪር መከራና ውርደት አንፃር ሲገመገሙ ጊዜን፣ ሁኔታን፣ የሰው ሃይል መጠንና አይነትን ፣ የፋይናንስ አቅምን ወይም ባጠቃላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን በእጅጉ የሳቱ አስተሳሰቦችና አካሄዶች በተለይ የሃይማኖት አባትቶች (መሪዎች) ነን በሚሉ ወገኖች እጅግ ድራማዊ (dramatized) በሆነ ዘመቻ ሲስተጋቡ በዚህ ልክ ለምንና እንዴት አስተሳሰባችን ሚዛኑን ሊስት ቻለ? ከየትስ ወደ የት ነው እየነጎድን ያለነው? ብሎ ለመጠየቅ የሞራል አቅም ማጣቱ በእጅጉ አሳፋሪና አስፈሪ ነው።

የሃይማኖታዊ እምነት መሪና አስተማሪ ሊከበርና ሊበረታታ የሚገባው የተሰጠውን የሰማያዊ ዓለም ሃላፊነት ተገቢ በሆነና ሚዛኑን በጠበቀ ምሳሌነት እንጅ በተሸከመው የማእረግ ስም ምክንያት ሊሆን አይደለም ። ማንም ምንም አይነት ማእረግና ሥልጣን ይኑረው አውቆም ሆነ ሳያውቅ ግልፅና የማይታለፍ ስህተት ሲሠራ አግባብነት ባለው፣ በግል ሰብእና ላይ በማያተኩር ፣ እውነትነትን በተላበሰ እና ገንቢነት ባለው አቀራረብ ልክ አይደለም መባል ይኖርበታል።  እውነተኛው አምላክ የሚወደውም ይህንኑ ነው።

እንደዚህ ሆነንና አድርገን ካልተገኘን ሃይማኖታዊና ተያያዥ እሴቶቻችን በስመ የሃይማኖት መሪነት፣ ልሂቅነትና ሰባኪነት ከዓለማዊው የፖለቲካ ነጋዴዎች ባልተናነሰ ለመመለስ ወደ የሚያስቸግር ቁልቁለት እንደሚወርዱብን ለመገመት ነብይነት ፈፅሞ አይጠይቅም።

ሀ) እጅግ እኩያን በሆኑ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ምክንያት አገረ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍፁም ሰቆቃዊ  በሆነ ህይወት ውስጥ የሚገኘውን እጅግ አያሌ ንፁሃን ወገን በአንድ በኩል፣

ለ) ከልዩ ልዩ ምክንያቶች እየመነጩና እየጎለበቱ የሚያስቸግሩ  ችግሮች  የመኖራቸው እውነትነት እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን ችግሮች እየተከታተሉ አስፈላጊውን መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንደ ልብ በሚገኙባት ምድረ አሜሪካ የሚኖረውን ወገን በሌላ በኩል አድርገን ቅን ፣እውነተኛና  ሚዛናዊ በሆነ ህሊናችን ካመዛዘነው ሁለቱም ሁኔታዎች እኩል የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን ግድ የሚሉ ወይም እኩል ወቅታዊ  እንደሆኑ ተደርገው በሃይማኖት አባትና በእሸቱ የቀረቡበት ሁኔታ አሳማኝነት የለውም።

በእኩያን ፖለቲከኞች ምክንያት ቅድስት የምንላት አገር መግለፅ የሚያስቸግር ሁኔታ  የመከራና የሰቆቃ ሰለባ የሆነውን መከረኛ የአገሬ ህዝብ ሁኔታ እና መሠረታዊው አገልግሎት በሚገኝበት አሜሪካ የሚኖረውን ዳያስፖራ እኩል ቅድሚያ የሚሻ አድርጎ ማቅረብ ፈፅሞ ይበል የሚያሰኝ አስተሳሰብና አካሄድ አይደለም።  ለመሆኑ ምን አይነት ህሊና ነው አገሩ ለንፁሃን ልጆቿ እንኳን ለማየትና ለመስማት ለማሰብም የሚያስቸግር ምድረ ሲኦል በሆነችበት መሪር ሁኔታ ውስጥ ሆና በምድረ አሜሪካ የአ.አበባን ግማሽ የሚያህልና በርካታና  ግዙፍ ተቋማትን የሚይይዝ ገዳማዊ ማእከል (grandiose monastery complex)  ይገነባል በሚል ሃሴት የሚያደርገው?  የትኛውስ እውነተኛ አምላክ ነው በዚህ አይነት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረቱ ክፉኛ በተንሸዋረረ አስተሳሰብና አካሄድ ደስ የሚሰኝ?

እንዲህ አይነትን መሪር ጥያቄ  ለአገር ቤትም እኮ ረድተናል ፤አሁንም እየረዳን ነው፤ ወደ ፊትም እንረዳለን በሚል እጅግ ልፍስፍስ (ደምሳሳ) አይነት ምላሽ ለማለፍ መሞከር የራስን ተአማኒነትና ተቀባይነት ነው ይበልጥ ፈተና ላይ የሚጥለው። ምክንያቱም የጥያቄው ጭብጥ “እንደ ማነኛውም እርዳታ ሰጭ (መፅዋች) አካል ለአገር ቤት ሳንቲም ወይም የእለት ጉርስ ሰጥታችኋል ወይም አልሰጣችሁም ሳይሆን አገርና ህዝብ ከሚገኙበት ፍፁማዊ መከራና ሰቆቃ አንፃር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረታችሁ እዚያው አገር ቤት እንጅ ባህር ማዶ  ግዙፍ ገዳማዊ ፕሮጀክት መሆን አልነበረበትም። ይህ ደግሞ በሰማያዊውም ሆነ በምድራዊው ዓለም ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።” የሚል ነውና።

“ገዳማዊው ማእከል ታሪካዊና አኩሪ ከሆኑት የውጭ አገር ገዳማት (እየሩሳሌም) አንዱ ይሆናል” የሚለውን ትንበያ ከመርህና ከአጠቃላይ እውነትነት አንፃር መቀበል አያስቸግርም። ይህ ግን አገሩ በገዛ ራሱ እኩያን ገዥ ቡድኖችና ሸሪኮቻቸው ምድረ ሲኦል ለሆነችበትና እየሆነችበት መድረሻ ላጣ ህዝብ ፈፅሞ ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም። “መጀመሪያ የመቀመጫዬን ” እንደሚባለው ማለት ነው።

እናም እንዲህ አይነቱን በእጅጉ የተዛባ አስተሳሰብና አካሄድ ቀጥተኛ፣ ግልፅና ተገቢ በሆነ አቀራረብ ትክክል እንዳልሆነ ከመንገርና ከመነጋገር ይልቅ “ስለ ድፍረቴ ይቅርታ አድርጉልኝ (ያድርጉልኝ) ወይም የእርሰዎን (የእናንተን) አስተሳሰብና አካሄድ በመተቸት መሳሳቴ ይኸውና ከእርስዎ (ከእናንተ) ፊት ቀርቤ ይቅርታና ቡራኬ እንዳገኝ አድርጎኛልና ፈጣሪ ይመስገን” የሚል አይነት ኑዛዜ ፈፅሞ ጥሩ ምሳሌነት የለውም ።

አዎ! የገዛ አገሩ ምድረ ሲኦል ሆናበት የሰውና የወገን ያለህ እያለ ለሚጮህ ወገን (ህዝብ) የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የጋራ ርብርብ ከማድረግ ይልቅ ጠይቆ ብቻ ሳይሆን ተጠይቆ መሠረታዊ አገልግሎት ከሚያገኘው ዳያስፓራ ጋር እኩል በማነፃፀር እጅግ ግዙፍ የባህር ማዶ ገዳማዊ ፕሮጀክት አዘጋጅቻለሁና (አዘጋጅተናልና) የምትሰጡትን ሁሉ እንደ ሰማያዊ መንገድ ስንቅ እየቆጠራችሁ ስጡ የሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ ለገሃዱም ሆነ ለሰማያዊው ዓለም የሚበጅ ሊሆን አይችልም ብሎ ማሄስና መከራከር ፈፅሞ የስህተትና የሃጢአት መንገድ ሊሆን አይችልም። ይህንን ይሁን ብሎ የሚቀበል እውነተኛ አምላክም የለም። አዎ! እውነተኛው አምላክ ጨርሶ መፈናፈኛ ያጣውን ምስኪን ወገን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ በማድረግ መታደግን የሚባርክ እንጅ የምናደርገው ሁሉ ምንም አይነት ግዝፍና እና ሰዋዊ አድናቆት ቢኖረው በዘፈቀደ ይሁን የሚልና የሚባርክ አይደለም።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እጅግ አያሌ ቁጥር ያለው ህዝብ በሞትና በህይወት መካከል እንዲቃትት ወይም የአፈር በታች ሙት ወገኖችን እጣ ፈንታ እንዲመኝ ያደረጉትንና እያደረጉት ያሉትን ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና ሸሪኮቻቸውን ደፍሮ በመገሰፅ እዚያው አገር ቤት መካሄድ ላለበት የቅድሚያ ቅድሚያ ፕሮጀክት አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ በፈጣሪ ስም ጥሪ ለማድረግ የተሳነው የሃይማኖት መሪነት እጅግ ግዙፍ ስለሆነ የባህር ማዶ ገዳማዊ ማእከል (ፕሮጀክት) አጣዳፊ ዘመቻ እንዲካሄድ በማድረጉ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ቢነሳ ደስ የሚለው እንጅ የሚከፋው እውነተኛ አምላክ ጨርሶ የለም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላቶ ከዶጋሊ እስከ አሻድሊ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

እንደ ማነኛውም የእምነቱ (የሃይማኖቱ) ጉዳይ እና ከልክ ያለፈው የአገሩ (የህዝቡ) መከራና ውርደት እንደሚያሳስበው ግለሰብ ወይም ቡድን ይህ እጅግ ወለፈንዲ (paradoxical) የሆነ ጉዳይ ድብልቅልቅ ስሜትን የሚፈጥርበት የአገሬ ሰው በቁጥር ቀላል እንደማይሆን እገምታለሁ ። ችግሩ ይህንን አስቀያሚ የሆነ ወለፈንዲነት በግልፅና በቀጥታ ከመተቸት ይልቅ ሰንካላ ሰበብ እየደረደረ ውስጥ ለውስጥ በማጉረምረም ክፉ ልማድ የተለከፈው እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ ከመሄዱ ላይ ነው።

ሁለት ጨርሶ የማይቀራረቡ ሁኔታዎችን እንደ ማሳመኛ ምክንያት ለመተንተን ከመቸገር ይልቅ “በቅርፁም ሆነ በዓላማው ይዘት ታሪካዊ የባህር ማዶ ገደማዊ ማእከል በመገንባት ታሪካዊ የሃይማኖት መሪነት አሻራችንን አሳርፈን ለማለፍ ፈልገናልና አግዙን” ቢባል ቢያንስ በግልፅነናት በቀጥተኝነት ደረጃ ስሜት የሚሰጥ ይሆን ነበር።

ያለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን የገዛ ራሳችን አስከፊና አሳፋሪ ውድቀት   ባለመፀየፋችን ምክንያት ነገረ አስተሳሰባችን፣አመለካከታችንና አካሄዳችን ሁሉ ልክ በሌለው ድንቁርና ወይም እያወቁ የመደንቆር ወይም መስሎና አስመስሎ የመኖር ወይም ልኩን በሳተ የግል ወይም የቡድን ፍላጎትና ጥቅም ከተመሰቃቀለብንና ከገባንበት አጠቃላይና አስከፊ የውድቀት አዙሪት ሰብሮ  ለመውጣት አልቻለን ብሎን በእጅጉ ከተቸገርን ዘመናትን አስቆጠርን። ይህ ሁለንተናዊ (ዓለማዊና መንፈሳዊ) ቀውሳችን ደግሞ በህዝብ የመከራና የውርደት ህይወት ላይ ሥልጣነ መንበራቸውን ለማስጠበቅ የትኛውንም እርምጃ እየወሰዱ ካሉት እኩያን ገዥ ቡድኖች በማይተናነስ ሁኔታ ነገረ ሥራችን ሁሉ ወለፈንዲ (paradoxical) አድርጎብናል።

የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በሚሹ ፈተናዎቻችን እና በአስተሳሰባችንና በአካሄዳችን መካከል ባለው እጅግ ሰፊ ልዩነት የሚፈጠር ወለፈንዲ (paradox) ከጊዜ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት የመሄዱ አባዜ አሳስቦን የሚበጀውን ለማድረግ ካልቻልን ፈፅሞ የትም አንደርስም።

ይህ ወለፈንዲነት ከፖለቲካ በሽታነት አልፎ የሃይማኖት ተቋማትን ሲጠናወት የሚፈጥረው ከባድ ፈተና ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ከእኛው ከራሳችን አልፈን ሌላ ማሳያ ፍለጋ መሄድ አያስፈልገንም።

አዎ! በአንድ በኩል እጅግ መጠነ ሰፊና አስከፊ ስለሆነው የአገራችን መከራና ውርደት አጥብቆ መተረክ እና በሌላ በኩል ግን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረታችን የትና መቼ እንደሆነና መሆንም እንዳለበት ለማወቅ ባለመፈለግ ወይም እያወቁ እንዳላወቁ መስሎ በማለፍ ወይም ልክ በሌለው የግልና የቡድን ፍላጎት/ ጥቅም/ዝና በመሸነፍ  ለማመን የሚያስቸግር የባህር ማዶ ፕሮጀክት ጀምረናልና በፈጣሪ ስም ያላችሁን ከቻላችሁ በሰዓታት (በአንድ ምሽት) ካልሆነ ግን ከዛሬ ጀምሮ ገቢ አድርጉ የሚል ዘመቻ የለየለት ወለፈንዲነት (typically paradoxical) ነው።

አዎ! ማድረግ የምንፈልገውን ነገር/ጉዳይ ከማድረጋችን በፊት የትኛው ከየትኛው ይቅደም? ለምን? በማንና ለማን? እንዴት! መቼና የት? ወደ የት? ከዚያስ? የሚሉትን እጅግ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሳንጠይቅና ተገቢውን መልስ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ጥረት ሳናደርግ ለግልብ ስሜት ቅርብ በሆነ ቋንቋ እፁብ ድንቅ አስመስለን በማቅረብ የሄድንበትና አሁንም እየሄድን ያለንበት አስተሳሰብና አካሄድ ምን ያህል አላስፈላጊ ዋጋ  እንዳስከፈለንና እያስከፈለን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስፈልገን የረቀቀ ዓለማዊና ሃይማኖታዊ ትንታኔ ወይም ፍልስፍና ሳይሆን  በመሬት ላይ ያለውን የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ ከምር ልብ የሚል ጤናማና  ሚዛናዊ ህሊና ብቻ ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን አሁን ለምንገኝበት እጅግ አስከፊና አሳፋሪ ለሆነ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ   ውድቀት ከዳረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ አብዛኛው ነገረ ሥራችን  ለችግሮቻችን ወይም ለጉዳዮቻችን ክብደትና አንገብጋቢነት የሚመጥን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት አስተሳሰብንና አካሄድን የተከተለ ሳይሆን ግልፅ ወይም ድብቅ ከሆነ  የግል ወይም የቡድን ስሜትና ፍላጎት  የሚነሳና መዳረሻውም በዚሁ ላይ የተመሠረተ የመሆኑ መሪር እውነታ ነው ።

በተለይ በእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ፣ ግብረበላዎቻቸው እና እንዲሁም ሃይማኖታዊ መሪነታቸውንና ሰባኪነታቸውን በተገቢው መንገድ ለተገቢው (ለትክክለኛው) ተልእኮና ዓላማ ለማዋል በሚቸገሩ ወገኖች ምክንያት ምንነቷና ማንነቷ ምስቅልቅሉ በመውጣባት  እንደ እኛ አይነት አገር ውስጥ  ያሰብነውና ማድረግ የምንፈልገው ነገር  የፈለገውን ያህል እፁብ ድንቅ ቢሆንም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት  አስተሳሰብንና አካሄድን ግምት ውስጥ ካላስገባ  በስተቀር ፈፅሞ የትም አንደርስም።

በመጨረሻም ስለ እሸቱና መሰል  ወጣቶችና ጎልማሶች የሚከተለውን ልበል።

በመሠረቱ እንደ እሸቱ አይነት ጎልማሶች ወይም ወጣቶች ከሰለጠኑበት መደበኛ ሙያ በተጨማሪ የራሳቸውን ተጓዳኝ እውቀትና ተስጥኦ ተጠቅመው የራሳቸውን ህይወት ስኬታማ ለማድረግና ወገንን ለማገዝ የሚያደርጉት ጥረት ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን ግን ከወጣትነትና ከጎልማሳነት የሚወለድ እጅግ የተለጠጠ የግል ዝና ፍለጋ እና የገንዘብና የማቴሪያል ፍቅር በአግባቡ ካልተያዙ እየዋለ ሲያድር ከቁጥጥር ውጭ ይሆኑና ለእራስም ሆነ አሁን ለሚያከብራቸውና ለሚያደንቃቸው ህብረተሰብ  በቀላሉ ሊታረም የማይችል ስህተት እንዳያስከትል አድናቆት ብቻ ሳይሆን ሂሳዊ አስተያየትንም ግድ ይላል።

ምሳሌ ፦ ምንም እንኳ ዋናው ሂሳዊ አስተያየቴ ያተኮረው በሃይማኖት አባቶች  ላይ ቢሆንም እሸቱም እንዲህ አይነት ድራማዊ (dramatized) የሆነ ቅንብር ውስጥ ከመግባቱ በፊት አብሮት የሚኖረውና በሙያ (በሥራ አጋጣሚ) ምክንያት እየተዘዋወረ የታዘበው የመከረኛው ህዝብ ህይወት እና አሜሪካ ያለው ዲያስፖራ ህይወት ጨርሶ በተሳሳተ ንፅፅር ሲቀርብለት በአክብሮት ለምንና እንዴት ብሎ ለመረዳት ሳይሞክርና የራሱን ሃሳብ ለመግለፅ ሳያንገራግር ይህንን ያህል ሚሊዮን ዶላር በአንድ ምሽት ውስጥ አምጡ (ስጡ) የሚል እጅግ ስሜታዊ  ዘመቻ ውስጥ መግባቱ ትክክል እንዳልነበር ተገንዝቦ ገንቢ የእርምት ተሞክሮ መውሰድ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ።

ታዛቢና አድናቂም እንደ እሸቱ አይነት ወገኖችን ማበረታታቱና ማድነቁ ተገቢ ቢሆንም ወደ ፍፁምነት የሚጠጋ (በተገቢ ሂሳዊ አስተያየት ያልታገዘ) ከሆነ ግን ከቁጥጥር ውጭ የሆንና ሙያን፣ ክህሎትንና መልካም ሰብእናን ይፈታተናልና  ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ነው ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.