እውን አብዮት ማለት የነበረውን እንዳልነበር ማድረግ ማለት ነው? – ጠገናው ጎሹ

December 24, 2022
ጠገናው ጎሹ

አብዮት (revolution) እና አዝጋሚ ለውጥ (evolution) የየራሳቸው የሆነ ባህሪና አካሄድ ቢኖራቸውም አንድ ትልቅ ፅንሰ ሃሳብን ይጋራሉ። ይህም ለውጥ (change) ብለን የምንጠራው ፅንሰ ሃሰብ ነው። ሁለቱም የለውጥን አስፈላጊነትን ወይም አይቀሬነንት ነው የሚገልፁት። ሁለቱም በተጨባጩ (በገሃዱ) ዓለማችን ወይም የህይወታችን ምንነትና እንዴትነት ላይ ተመሥርተን የምንመርጣቸውና ሥራ ላይ የምናውላቸው እንጅ አብዮት ማለት ሥርን ነቅሎ የሚጥል እና አዝጋሚ ለውጥ ማለት ደግሞ ገንቢና ዘላቂ በሚል ደምሳሳ አስተሳሰብ ላይ ተቸክለን እውን የምናደርጋቸው ፅንሰ ሃሳቦች አይደሉም።

የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት ከሚለይባቸው ዋነኛ ባህሪያት አንዱ የሚፈልገውን ጉዳይ ለማድረግ እና የማይፈልገውን ላለማድረግ ከሚያስችለው ረቂቅ አእምሮ ጋር መፈጠሩ ነው። ይህ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪውና ችሎታው ነው በዘፈቀደ ወይም በደመ ነፍስ ከሚኖሩ ፍጡራን ተለይቶ ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን በምክንያት (በአመክንዮ) እያስደገፈ እንደ አስፈላጊነቱ እንዲራመድ ያስቻለው ወይም የሚያስቸለው።

የሰው ልጅ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ባህሪያቱና መስተጋብሮቹ ሊያስከትሉ የሚችሉ አወንታዊና አሉታዊ የለውጥ ኩነቶችንና ሂደቶችን በአግባቡ ተረድቶ የሚበጀውን የመምረጥና የማድረግ አቅሙና ችሎታው የሚመነጨውም ከዚሁ መሠረታዊ የአምክንዮነት ብቃቱና ችሎታው ነው።  ፖለቲካን የማታለያ ፣የመጨቆኛና የዝርፊያ መሣሪያ የምናደርገው እኛው ራሳችን እንጅ ፖለቲካ በራሱ ለዚህ አይነት መሣሪያነት የተፈጠረ እንዳልሆነ ሁሉ አብዮትም የግድ ለሥር ነቃይነት ወይም የነበረውን እንዳልነበረ ለማድረግ የተፈጠረ አድርጎ ማየትና ማሳየት በእጅጉ ደምሳሳና የተንሸዋረረ አመለካከት ነው።

ለማመን በእጅጉ በሚያስቸግር ሁኔታ እያጋጠሙን ካሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦቻችንና የሞራል ውድቀቶቻችን አንዱ ለዘመናት እና በተለይም ደግሞ ከአራት ዓመታት ወዲህ እጅግ አስከፊ በሆነ የፖለቲካ ወለድ ወንጀል (በህዝብ ደምና መከራ) የጨቀየውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ኦህዴድ/ብልፅግና በአብዮት (በተደራጀና በተቀናጀ  ህዝባዊ አልገዛም ባይነት) ማስወገድን ሁሉን ነገር ከሥሩ ነቅሎ እንደ ማጣልና አገርን እንደ ማፍረስ የመቁጠራችን እጅግ የወረደ አስተሳሰብና አመለካከት ነው።

እርግጥ ነው እውነተኛ የቀስ በቀስ (የደረጃ በደረጃ) መሠረታዊ የለውጥ ሂደትን ለማስተናገድና ለማስኬድ የሚያስችል ፖለቲካና ፖለቲከኛ ባለበት ሁኔታ ውስጥ አብዮታዊ ትግል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላልና ቆም ብሎ ማሰቡ ተገቢ ነው።ይህ አንፃራዊ የሆነ አመች ሁኔታ ጨርሶ በሌለበት የእንደ እኛ አይነቱ የፖለቲካ አውድ ውስጥ እየጓጎጡ (የመከራን ፅዋ እየተጋቱ) ስለ አብዮት የሰላም ፀርነትና አገር አፍራሽነት መተረክ ጨርሶ ትርጉም አይሰጥም።

ሴረኛ ገዥዎችና ግብረ በላዎቻቸው ወይም አድርባይ ምሁራን ተብየዎቻችን እንደሚተርኩልን  አብዮት ማለት በራሱ (as such) ሙጥፎ ወይም ጥሩ በሚል ደምሳሳ አገላለፅ የሚገለፅ አይደለም። ከተጨባጭ ሁኔታ በሚነሳና በቅጡ በተደራጀ፣ በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው የትግል  ንቅናቄ  ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ እጆቻቸው እጅግ ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል (የንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ) የተጨማለቁ የኢህአዴጋዊያንን/የኦህዴዳዊያንን/የብልፅግናዊያንን ሥርዓት በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ (በአብዮት) ሳይሆን እነርሱው ባዘጋጁትና በሚመሩት የተሃድሶ (reform)  የፖለቲካ ጨዋታ ማስተካከል ይቻላል ብሎ ከማመንና ህዝብን ጨምሮ ከማደንቆር የባሰ የፖለቲካ ደደብነትና የሞራል ክስረት የሚኖር አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሮናቫይረስ ምንድነው? እንዴትስ ነው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው? - SBS Amharic

በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ወንጀል አስከፊ በሆነ ሁኔታ የበሰበሰንና የከረፋን ሥርዓት በሀዝባዊ አልገዛም ባይነት (በአብዮት) የማስወገድንና በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመተካትን አስፈላጊነት ሁሉንም ነገር ከሥሩ ነቅሎ እንደ መጣልና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ እንደ መጣል እየቆጠሩ ማላዘን  ስሜት የሚሰጥ  የፖለቲካ አመለካከትና የሞራል ሰብዕና ፈፅሞ ሊሆን አይችልም ።

አዎ! ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገር ምንነቱንና ማንነቱን መሠረት አድርገው የገድሉትን፣ እየገደሉት ያሉትን፣ ያስገድሉትን ፣እያስገደሉት ያሉትን ፣ ከገዛ አገሩና ቀየው ነቅለው ለምድራዊ ሲኦል የዳረጉትንና እያስደረጉት ያሉትን እና ይህም አልበቃ ብሎ በመከራውና በሰቆቃው የሚሳለቁትን አብይንና ግብረበላዎቹን ከአብዮት (ከአልገዛም ባይነት ትግል) ይልቅ የተሃድሷቸው (ተራ የማጭበርበያ የመደመር ስልታቸው) አካል በመሆን ወይም በሰላምና አገርን በማዳን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታቸው ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መስመር ማምጣት ይቻላል ብሎ ከማመንና እነዚህ እኩያን ገዥ ቡድኖች ያደነቆሩትን መከረኛ ህዝብ ይበልጥ ከማደንቆር የባሰ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት የሚኖር አይመስለኝም።

እጅግ ጨካኝ የሆኑ ተረኛ ጉልቾችን አደብ ለማስገዛት የሚያስችል የአልገዛም ባይነት (አብዮታዊ ትግል) ለማካሄድ ያለመቻላችን እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ የፖለቲካና የሞራል  ውድቀታችንን ለመገንዘብ ለአራት ዓመታት የሆነውንና እየሆነ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ ከምር ልብ ማለት እንጅ የተለየ እውቀትንና የትንታኔ ችሎታን አይጠይቅም ።

ባይገርምም የሚያሳዝነው ደግሞ ፊደል ቆጥሬያለሁ የሚለውና በፖለቲካውም አንቱ የሚያሰኝ ተሞክሮ አለኝ በሚል እወቁልኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የዚሁ “የአብዮት ያፈርሳል” ትርክት ሰለባ የመሆኑ መሪር እውነታ ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ከዚህ በላይ አብዮትን ግድ የማይል መከራና ሰቆቃ የትኛው ነውየትስ ነው ያለው? ምን ያህል ነፍስ በግፍ ሲጨፈጨፍስ  ነው አብዮት የሚያስፈልገን? ምን ያህል ደምስ አገሪቱን ሲያጥለቀልቅ ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ያው የለመደበትን ሰንካላ የትንታኔ ድሪቶ ከመደረት አያልፍም።

የኢትዮጵያን ታላቅነት ፣ የእኩልነትን ሸጋነት፣ የኢትዮጵያዊነትን ሱስነት ፣ ኢትዮጵያ ሆኖ የመኖርንና የመሞትን እሴትነት ፣ የብልፅግና ወንጌልን ገድላዊነት ፣ ወዘተ እየዘመሩና እያዘመሩ ቁልቁል ይዘውት ሲወርዱ ለምና እንዴትብሎ ለመጠየቅና ለማሰብ ጊዜና ትእግሥት ያልነበረው ምሁር ተብየ አሁንም ከባዶ ዲስኩርና የሰነድ ላይ የፖለቲካ ድርሰት ፎቀቅ አላለም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አፈናና የተማሪና ወላጅ ተስፋ ያጨለመው ውሳኔ | Hiber Radio

ይህንን ስል በጣት የሚቆጠሩም ቢሆን ቀድምም ሆነ አሁን ያለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ (ለገዳይና አስገዳይ አልገዛም ባይነት )  ለዘመን ጠገቡ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ጥያቄ ትክክለኛውና ብቸኛው ምርጫ እንደሆነ የሚያምኑና ቢያንስ እውነታውን በቀጥታና በግልፅ የሚጋፈጡ ወገኖች እንዳሉ በመዘንጋት ወይም እውቅና ባለመሥጠት አይደለም። ውስብስቡንና እጅግ የተበላሸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ በቀላሉ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለማምጣት በእጅጉ ፈታኝ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በዚህ ረገድ እንደ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት አይነት ወገኖችን መጥቀስ ይቻላል።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ልደቱ አያሌው የመሰሉ ወገኖች በትምህርትና በልምድ አዳበርነው የሚሉትን የተናጋሪነት (oratory) ብቃት በፅእኑ መርህና የትግል ስልት ላይ ፀንቶ በመቆም ሳይሆን በክስተቶች ምህዋር ላይ እየተሽከረከሩ በአንዴ ከሁሉም የቆሻሻና አደገኛ  የፖለቲካ ሃይሎች ጋር መፈጠር ስለሚኖርበት “የሰላም ወዳጅነት” እና  በሌላ በኩል  ደግሞ ስለ ዴሞከራሲያዊና የእኩልነት ሥርዓት እውን መሆን  የሚተርኩ (የሚደሰኩሩ) ወገኖችን አቀራረብ በይሉኝታ ወይም በሌላ ምክንያት በዝምታ ማለፍ አይጠቅምምና እራሳቸውን ከምር እንዲፈትሹ መንገርና መነጋገር ያስፈልጋል የሚል ፅእኑ አስተያየት አለኝ።

ልደቱ አያሌውን  በአካል ( in person) አላውቀውም። የማውቀው በ1997 የለውጥ ፍለጋ ምኞቱንና ፍላጎቱን በአግባቡ በተደራጀ፣ በተቀነባበረና ዘላቂነት ባለው አኳኋን ወደ ድርጊት ለመለወጥ የተሳነው አዲስ አበቤ ወጣት በትክሻው ላይ ተሸክሞ “የእኛ ማንዴላ” እያለ ሲያሞካሸው ካየሁ (ከታዘብኩ) እለት ጀምሮ ነው። መቸም ነገረ ሥራችን ሁሉ በግልብ የፖለቲካ ስሜት መክነፍ እየሆነብን ተቸግረን ነው እንጅ በዚያን ወቅት ለከሸፈው ወርቃማ የለውጥ አጋጣሚ ልደቱና መሰሎቹ ያደረጉት አስተዋፅኦ መሪር የሆነ ትምህርት ሰጥቶን ባለፈ ነበር። መሳሳት ዘላለማዊ ሃጢአት ነውና እነ ልደቱም በዚሁ መነፅር ይታዩ ለማለት ፈፅሞ አይቃጣኝም። እንደዚህ አይነት ፖለቲከኞች ከስህተታቸው ተምረው የተሻለ የፖለቲካ ሰብእና ላይ ያለመገኘታቸው መሪር ሃቅ ግን በእጅጉ ሊያነጋግረንና ሊያሳስበን ይገባል የሚልፅዕኑ እምነት አለኝ።

ይህ ሁኔታ የአገራችን ፖለቲካ ከክስተቶች ትኩሳት ጋር ከመወጣና ከመወርድ እና ደጋግሞ ከመጨንገፍ (ከመውደቅ) ክፉ አዙሪት ለመውጣት በእጅጉ እንደሚቸገር ደንበኛ ማሳያም ነበር።

ይህ ትምህርት ሊሆነን ባለመቻሉ  የህወሃት/ኢህአዴግን የፖለቲካ አደገኛ መርዝ እየተጋቱ ያደጉትና ያገለገሉት እነ አብይ አህመድ የበላይነት ተረኝነታቸውን ዕውን ለማድረግ የተጠቀሙበትን ተራና ግልብ የማታለያ ዲስኩር ከመቅፅበት ተቀብለን “የዘመናችን መሴዎች” በሚል ዳንኪራ ረግጠን ሳናበቃ ዳግም የአስከፊና ማቆሚያ ያልተበጀለት መከራና ውርደት ሰለባዎች ሆነን አረፍነው ።

ቀደም ሲል የሽግግር ጊዜ ሰነድ እና ከሰሞኑ ደግሞ ስለ ንስሃ ፅፎ ያሠራጨውን መነባንብ እና በአጠቃላይ ሌሎች የፖለቲካ ሥራዎቹን ከምርና ያለምንም አላስፈላጊ ይሉኝታ ለሚከታተልና ለሚገነዘብ የአገሬ ሰው ልደቱ በማይናወጥ መርህና ዓላማ ላይ ፀንቶ የሚቆም ፖለቲከኛ መሆኑን ደፍሮ የሚሟገት አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የብዙሀን ዖሮማራን ስነልቦና ስላለማወቅ - ይድረስ ለቀሼ ፖለቲከኞችና አንጋቾች - ከአባዊርቱ

አዎ! ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ በአያሌ ንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ወንጀል እጆቻቸውና አጠቃላይ ሰብእናቸው የተዘፈቁ እኩያን ገዥዎችን በቅጡ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ከተቻለ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት ካልሆነ በአልገዛም ባይነት (በአብዮት) ከማስወገድና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ከማድረግ ይልቅ ጨርሶ ሊገናኝ በማይችልና በራሳቸው በእኩያን ገዥ ቡድኖች በሚፈጠርና በሚዘወር ወደ መሬት በማይወርድ የሰላምና የአገራዊ ምክክር ድራማ ዴሞክራሲያዊት አገርን ፈፅሞ እውን ማድረግ አይቻልም።

የፖለቲካ አስተሳባችንና አካሄዳችን ተግባር አልባ ዘመቻ (actionless campaign) በሆነበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ የፍትህና የነፃነት ሥርዓት ለውጥን መሻት (መፈለግ) ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።

ዝምታና ውጤታማ ያልሆነ የፖለቲካ ዘመቻ  ለእኩያን ገዥ ቡድኖች አመች ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። አብዮትን ደግሞ እንደ  ሽብርና አሸባሪነት እየቆጠሩ  የጨካኝ ሰይፋቸው ሰለባ አድርገውታል ።  አብዮትን (የመሠረታዊ ለውጥ ትግልን) ዘመኑን በሚመጥን አኳኋን ለማደራጀትና ለማስኬድ ሲያቅተን ሰንካላ ሰበብ እየደረደርን ራሳችንን አቅመ ቢሶችና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች  ሰለባዎች እያደረግን ቀጥለናል ። እጆቻቸውና የፖለቲካ ሰብእናዎቻቸው ከቶ ታጥቦ ሊጠራ በማይችልና ዘመናትን ባስቆጠረ የንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ የተበከሉ ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን ሥርዓት በማያዳግም ሁኔታ ለማስወገድና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ በሚያስችል አኳኋን መንቀሳቀስ እስካልቻልን ድረስ ከቶ የትም አንደርስም። አብዮትን ሁሉንም ነገር እንክት አድርጎ የሚበላ ወይም ሁሉንም ነገር እንዳልነበረ የሚያደርግ አድርጎ መቁጠሩ ወይ ልክ የሌለው ፍርሃት ወይም  ድንቁርና ወይም መከራንና ውርደትን እንደ የመደበኛ የህይወት እጣ ፈንታ መቀበል ወይም የለየለት አድርባይነት (ልክስክስነት) እንጅ ሌላ አሳማኝ ምክንያት የለውም። የባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የግፍ  ሰይፍ ሰለባና የቁም ሙት እየሆኑ  አብዮትን እንደ ጭራቃዊ የትግል አስተሳሰብና አካሄድ መቁጠር በእጅጉ የወረደ የፖለቲካና የሞራል ምንነትና ማንነት ነው። አብዮት አጠቃቀሙ እንጅ በራሱ አጥፊ ወይም አውዳሚ ወይም አገር አፍራሽ እንደሆነ አድርጎ ማሰብና “ጎመን በጤና” (እርሱም አይገኝም) በሚል ውርደትን ተቀብሎ ከመኖር የባሰ ክፉ አባዜ ከቶ የለም።

እናም በእውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊት አገር የምንፈልግ ከሆነ  አብዮትን በማስፈራሪያነት በመጠቀም የመከራና የውርደት ሥርዓታቸውን ለማራዘም የሚቅበዘበዙ እኩያን ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ የትግል ሥልታችንን እኛ እንጅ እናንተ እንድትመርጡልን ፈፅሞ አንፈቅድላችሁም ማለት ይኖርብናል!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.