የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሰረት የለውም!!! – መሰረት

አዲስ አበባ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማእዘናት እንዲሁም ከልዩ ልዩ የአለም ክፍሎች የመጡ ሰዎች የሚገኙባት ከተማ እንደሆነች ይታወቃል። በዚህም መሰረት የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የተለያዩ ባህሎች የሚንፀባረቁባት፣ የተለያዩ ምግቦች የሚቀርቡባት የአገራችን አማካይ ቦታም ናት። ይህ ሆኖ እያለ ግን አብዛኛው አዲስ አበቤ አማርኛን በመግባቢያነትና በስራ ቋንቋነት ይጠቀማል። አዲስ አበባ ከሞላ ጎደል የራሷ የሆነ የመረዳጃና የመደጋገፊያ ተቋማት፣ ባህል፣ ስነልቦናና ማህበራዊ መስተጋብርም አሳድጋለች። ከዚህ በመነሳት ነዋሪዎቿ ራሳቸውን ሲጠሩ አዲስ አበቤ ብለው ነው። ይላሉ ከተባለም  “አራዳና ፋራ” እንጅ ጉራጌ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራዋይ ሶማሊ፣አፋር ወይም ሌላ ሲሉ ብዙ ጊዜ አይደመጡም። ባለቤቶቿም ነዋሪዎቿ የሆኑት እነዚሁ አዲስ አበቤዎች ናቸው።

አዲስ አበባ የአገራችን ዋና ከተማም ናት። በዚህም ምክንያት የራሷ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት።  ተጠሪነቷም ለፌደራል መንግስቱ ነው። አሁን ያለው ህገመንግስት የአዲስ አበባህዝብ ራሱን በራሱ እንደሚያስተዳድር በግልፅ አስቀምጧል። ይህን ህገመንግስት መነሻ አድርጎ የወጣው ቻርተርም የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳድር የሚያስችል የአስተዳደር መዋቅር እንደሚኖረው ደንግጓል። በዚህም መሰረት አዲስ አበባ የራሷ ምክር ቤት፣ አስፈፃሚና የዳኝነት አካላት አሏት፡፤

የአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም ተጠሪነታቸው ለከተማው መስተዳድር ነው። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ቋንቋዎችን ሊያስተምሩ ይችላሉ። ይህ ማለት ግን ቋንቃዎቹ የሚነገሩባቸው ክልሎች አርማዎች ይውለበለባሉ፤ መዝሙሮቻቸውም ይዘመራሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አማርኛ ቋንቋ እንደትምህርት ይሰጣል። ነገር ግን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ላይ የአማራ ክልል አርማ  ሊውለበለብ ወይም የአማራ ክልል የህዝብ መዝሙር ሊዘመር አይችልም። በተመሳሳይ መንገድ በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደትምህርት ይሰጣል። የእንግሊዝ ባንዴራ ግን አይውለበለብም፤ የእንግሊዝ መዝሙርም አይዘመርም። በነዚህ ትምህርት ቤቶች አፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥ ከሆነም በተመሳሳይ መንገድ የኦሮሚያ ክልል አርማ ሊውለበለብ፤ የኦሮሚያ ህዝብ መዝሙርም ሊዘመር አይችልም። በነዚህ የአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሊውለበለብ የሚገባው ሰንደቅ አላማ የፌደደራሉ ሰንደቅ አላማ ነው። አዲስ አበባ አርማ ካለውም ይህ አርማ ሊውለበለብ ይችላል። መዘመር ያለበት መዝሙርም የፌደራል የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ነው። በተመሳሳይ መንገድ አዲስ አበባ የራሱ የሆነ መዝሙር ካለውም ሊዘመር ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከዘመነ ዕኩይ ወደ ዘመነ ሠናይ ያድርሰን !

ከዚህ አንፃር ሲታይ ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የኦርሞሚያ ክልልን አርማ ለማውለብለብ፤ የዚህኑ ክልል መዝሙር ለማዘመር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ግልፅ የሆነ ህገወጥነት እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። ምክንያቱም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ጣልቃ የመግባት ምንም አይነት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊም ስልጣን የለውም። ግንኙነታቸውም ከማንኛውም ክልላዊ መንግስት ጋር እንደሚኖረው የጎንዮሽ  እንጅ ተዕዛዝ ሰጭና ተቀባይ አይነት ፈፅሞ አይደለም።

ይህን ግልፅ የሆነ ህገወጥነት justify ለማድረግ የሚቀርቡት ምክንያቶች ደግሞ እጅግ በጣም የሚገራርሙና ያለፍላጎት የሚያስቁ ናቸው። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች “አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ የኦሮሚያ አርማ እንዲውለበለብና መዝሙሩ እንዲዘመር ለማድረግ እየሞከርን ያለነው ካሪኩለሙን የተዋስነው ከኦሮሚያ ክልል ስለሆነ ነው” የሚለው  አንዱ ነው። እውነት ለመናገር ይህ ምክንያት ምንም ህጋዊ መሰረት ስለሌለው ጠብታ ውሃ እንኳ አይቋጥርም።  ትንሽ ማመዛዘን ለሚችል ሰው ቀርቶ ገና ለእምቦቀቅላ ህፃናትም የሚቀርብ ምክንያት አይደለም። ምክንያቱም (ለምን የኦሮሚያ ክልል እንደተመረጠ ራሱን የቻለ ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም) ከካሪኩለም ጋር የተያያዙ በጎ ልምዶችን ከተለያዩ ክልሎች ወይም ከሌሎች የአለም አገራት መቅሰም የተለመደ አሰራር ነው። ነገር ግን የካሪኩለም ልምዱ የተቀሰመበትን ክልል ወይም አገር ባንዴራ የማውለብለብ፤ የዚህኑ ክልል ወይም አገር መዝሙር የማዘመር ህጋዊም ህነ ሞራላዊ ግዴታ የለም። እንዲህ አይነት የቃ ቃ ጨዋታ አይነት አካሄድ የትም ተደርጎ አያውቅም፤ ወደፊትም ይደረጋል ብየ አላስብም።

በሌላ በኩል ችግሩ የተፈጠረው ዜጎች ባፍ መፍቻ ቋንቋቸው  እንዳይማሩ በሚፈልጉ የጥፋት ሃይሎች  ምክንያት ነው የሚል መሰረት የሌለው መግለጫም ሲሰጥ ሰምተናል። ነገር ግን የተፈጠረው ችግር ባፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መሰጠት የለበትም ከሚል ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ራሳቸውም ያውቁታል። ይህ አባባል ዜጎችን በማሸማቀቅ አጀንዳ አስቀይሮ ፍላጎትን በሃይል ለመጫን ካለ ፍላጎት የሚነሳ ነው። ይልቁንም ችግሩ የተፈጠረው ከፌደራል ጀምሮ እስከከተማ  መስተዳድሩ ባሉ የስራ ሃላፊዎች እውቅና የኦሮሚያን አርማና መዝሙር አዲስ አበባ ላይ በሃይል ለመጫን በተደረገ ሙከራ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ያህል ርቀት ሄዶ መዋሸት ከህዝብ ጋር ያቃቅራል እንጅ አንዳች የሚያስገኘው ፋይዳ አለ ብየ አላምንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነመላኩ ፈንታን የሙስና ጉዳይ ከማጣራት ቢላደንን ማግኘት ይቀል ነበር ማለት ነው?

አንዳንዶቹ ወዶ ገቦች ደግሞ ከልዩ ጥቅም ጋር እያገናኙ መዝሙሩም መዘመር፣ አርማውም መውለብለብ አለበት ሲሉ ይደመጣሉ። ልዩ ጥቅም በሚለው ዙሪያ አለመግባባት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ እንቅበለው ቢባል እንኳ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ተብሎ የአዲስ አበባ ህዝብ መብት መጣስ አለበት የሚል አመክንዮ ሊኖር አይችልም። ለነገሩ ህገመንግስቱ ራሱ ልዩ ጥቅም በሀግ እንጅ በጉልበትና በማናለብኝነት ይወሰናል አይልም። በህግ ቢወሰን እንኳ የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን ህዝብ በሚያስተሳስርና ለትብብር በሚጋብዝ ሁኔታ እንጅ ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ የፈለገውን ማንነት እንዲጭን ወይም ደግሞ በፈለገው ጊዜ ዘው ብሎ ገብቶ ያሻውን ሊያደርግ በሚችልበት አኳኋን ሊሆን ፈፅሞ አይችልም።

እነዚሁ ወዶ ገቦች ሲያሻቸው አርማውም ቢውለበለብ፤ መዝሙሩ ቢዘመርስ ምን ችግር አለው የሚሉብተ ጊዘም አለ። ነገር ግን ጉዳዩ የፍትሃዊነት፣ የህጋዊነትና የእኩልነት እንጅ ከንፈር ከመምጠጥ ጋር የተያያዝ እንዳልሆነ ቢያውቁ ይጠቅማል ብየ አምናለሁ። እዚህ ላይ ግን አንድ መታወቅ ያለበት መሰረታዊ ነጥብ አለ ብየ አምናለሁ።  እንደሚታወቀው አማርኛ የፌደራሉም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የስራ ቋንቋ ነው።  ስለዚህ አዲስ አበባ ትምህት ቤቶች ላይ የፌደራሉና የአዲስ አበባ ህዝብ መዝሙሮች በአማርኛ ይዘመራሉ። የፌደራሉ መንግስት ሰንደቅ አላማም ይውለበለባል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የፌደራሉና የአዲስ አበባ ህዝብ መዝሙሮች  በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ፣ በሶማልኛ፣ በጉራጊኛ ወይም በሌላ ቋንቋ እንዲዘመሩ ማድረግ ይቻላል። ይህን ለማድረግ ግን መጀመሪያ እነዚህ ቋንቋዎች ልክ እንደአማርኛ ሁሉ የፌደራሉና የአዲስ አበባ መስተዳድር ወይም የአዲስ አበባ መስተዳድር የስራ ቋንቃዎች ሆነው ስራ ላይ እንዲውሉ በህግ ሊደነገጉ ይገባል።

ከዚህ ውጭ በመንጎድ የኦሮሚያን አርማ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እናውለብልብ፤ የኦሮሚያን መዝሙር እናዘመር ማለት ግን ከባለጊዜነት ከሚመነጭ ማናለብኝነት የሚነሳ ግልፅ የሆነ ህገወትነትና ከመንግስታዊ መልካም ጠባይ ያፈነገጠ እንቅስቃሴ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይግድብ ሁኔታ ታሪካዊ ሂደት፣ ወቅታዊ ግንዛቤና የወደፊቱ ዕይታ - ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ

ቸር እንሰንብት!!!

መሰረት

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.