ያዲስ አባ ጣጣ ስላቅ (Satire) – በቦቆቅሳ ሉባክ

 

ግንቦት 2014

የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊና ሕጋዊ ባለቤት የእኛ ማሕበረሰብ ነው ሲሉ የዱር እንስሳት ነፃነት ግንባር (ዱ.እ.ነ.ግ) ከፍተኛ ተወካዮች ዛሬ ከቀትር በኋላ በቅርቡ በተመረቀው የአንድነት ፓርክ የእንስሳት መዋያና መናፈሻ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቁ፡፡ በመግለጫው አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት ላይ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ተመርጠው ለእይታ የበቁት ታላላቅ የዱር እንስሳት ተወካዮች እና ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡  የዱር እንስሳት ከፍተኛ ጉባኤ መሪዎች፣ ዋና አክቲቪስት ጦጣና አስመሳይ ነፃ አውጪ ዝንጀሮ በሰጡት መግለጫ፣ የአዲስ አበባ ይዞታ ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ባለቤቶቹ — የዱር እንስሳት ዘር — እንዲዛወር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አሳውቀው ለዚህ አላማቸው መሳካት ሁሉም ፅንፈኛ ሃይሎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

በመግለጫው አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት ላይ የጉባኤው መሪዎች እንደተነተኑት፣ የዓለማችን ታሪክ እንደሚመሰክረው የአዲስ አበባ ቀዳሚና ሕጋዊ ባለቤቶች፣ እንስሳት፣ በተለይም የዱር እንስሳት መሆናቸውን ሁሉም እንዲያውቀው አስረግጠን ለማስገንዘብ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ እነ ድንቅ ነሽ – ሉሲ (Australopethecus afarensis) እና እነ አርዲፒቲከስ ራሚደስ (Ardipethicus ramidus) በአፋር አዋሽና ሃዳር አካባቢዎች፣ እነ ሆሞ ሃቢሊስ (Homo habilis) እና ሆሞ ኢሬክተስ (Homo erectus) ደግሞ በኦሞ ሸለቆዎች አካባቢ ብቅ ብቅ ከማለታቸው በጣም ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ የኛ ቀደምቶች እነ ዳይነሶር (Dinosaur)፣ ማመዝ (Mammoth)፣ ሜጋላኒያ (Megalania) እና ሌሎች ታላላቅ የዱር እንስሳት ዘሮች የአካባቢው ባለቤቶች እንደነበሩ የዓለማችን አመጣጥ ቅድመ ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል፡፡

የጥንቱና የጧቱ እንኳን ቢረሳ፤ በቅርቡ እነ አንበሳ፣ ነብር፣ ዝሆን፣ የሜዳ አህያ፣ አውራሪስ፣ ቀጭኔ ጎሽና ሌሎችም በቦታው ላይ ይርመሰመሱ እንደነበር የሰው ልጆች እፅዋትን እየጨፈጨፉና የወገኖቻችንን ቆዳ እያለፉ የፃፏቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ብለዋል፡፡  እነ አያ ጅቦም እስከ አሁን ድረስ የሰው ልጆች ከርሳቸውን ሞልተው ፈርሳቸውን የሚያስወግዱበትን ምድር በማሰስና ትርፍራፊ በመልቀም እንደ ቆሻሻ ሰብሳቢና አስወጋጅ ለውለታ ቢሱ የሰው ልጅ የማይገባውን ጥቅም ሲሰጡ እንደቆዩ ግልፅ ነው ብለዋል፡፡  ቀጨኔ የሚባለው መኖሪያ ሰፈር መጠሪያ ባካባቢው የቀጭኔ ጎሳ አባላት በብዛት ሰፍረው ስለነበር የተሰጠው ስያሜ እንደሆነ የሰው ልጅ ምሁራን ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሃቅ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ትግላችን፣ አሉ ተወካዮቹ በመቀጠል፤ ትግላችን የአዲስ አበባን ከተማ የዱር እንስሳት ባለቤትነት የማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃ የመደራጀትን፣ ራስን በራስ የማስተዳደርንና እሰከመገንጠል የሚደርስ መብት ማስከበርን እንደሚያጠቃለል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል ብለዋል፡፡ የሰው ልጅ ጎሳዎች፣ ከእኛ በቁጥር በጣም የሚያንሱት እንኳን ሳይቀሩ፣ በጎጥ ተደራጅተው ክልሎች በመመስረት ራሳቸውን የማስተዳደር ሙሉ መብት ሲጎናፀፉ፤ በእኛ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር፣ የታሪክና የቅሪተ አካል ማስረጃ ያለው የቀደመ አካል ይህን መብት መነፈጉ ኢፍትሃዊ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ሲያብራሩ፣ እቅዳቸው አዲስ አበባን የይዞታቸው ማዕከል አድርጎ ማስመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በየብሔራዊ ፓርኩና በጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች ተበትነው፣ ተሸንሽነውና ተከፋፍለው የሚገኙትን የዱር እንስሳት ግዛቶች በማሰባበሰብና አንድ በማድረግ ራሱን የቻለ የታፈረና የተከበረ ክልል መመስረት ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም የዱር እንስሳት ባህላቸው፣ እሴቶቻቸው፣ የመጮህ፣ የማስካካትና የማጓራት መብታቸው፣ በተመቻቸው ቦታ የመጋጥ የመቦጨቅና የመፀዳዳት ተፈጥሮአዊ ፍላጎታቸው ተጠብቆ እንደፈለጉ የሚፈነጩበትና የሚኖሩበት እንስስያ በመባል የሚጠራ ታላቅ ክልል ለመመስረት የታቀደ የትግል አቅጣጫ እንደተነደፈ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባንም ስያሜ የቀድሙትን አባቶቻቸውን ለማስታወስ በእውቁ የቅድመ እንስሳት ታላቅ አባት ስም ‹‹ዳይኖፖሊስ›› ወደሚለው መጠሪያ ለመቀየር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሠረት በሃገሪቱ የሚገኙትን ብሔራዊ ፓርኮችና የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎችን፣ ማለትም እነ ያንጉዲ ራሳን፣ ባሌን፣ ስሜንን፣ ጋምቤላን፣ ነጭ ሳርን፣ ኦሞን፣ አቢያታ-ሻላን፣ አልጣሽን፣ ባቢሌን፣ ማጎን፣ አዋሽን እና ሌሎችንም ያጠቃለለ ሁሉም ክፍሎች በአንድነት የሚዋሃዱበትና በዳይኖፖሊስ የአስተዳደር ማእከልነትና ዋና ከተማነት የሚተዳደሩበት ጠንካራ የታላቋ እንስስያን ነፃ መንግስት ለመፍጠር እቅድ እንዳለ አሳውቀዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕገመንግስት፤ መብት ተረጋግጧል ወይስ ተረግጧል (ተክለሚካኤል አበበ)

አዲስ አበባ ከቀደምቶቻቸው ይዞታ ባስከፊ ጉልበትና በከፍተኛ ጭካኔ የሰው ልጅ በሚባለው ክፉ ነፍጠኛ ከተወረረች በኋላ የደረሰውን አውዳሚ ጥፋት፣ ድምሰሳና ስደት አስታውሰው የህሊና ፀሎት ያደረሱት ተወካዮች በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው በደል የሚሰማቸው ሀዘን ከቀን ወደ ቀን እያመረቀዘ፣ ከዘመን ዘመን እየከረረ፣ አየደለበ፣ ለቂም በቀል፣ አገር ለማጥፋት፣ ለማውደምና ለመከፋፈል ወደ ኋላ እንዳይሉ ደመ ነፍሳቸውን እየገፋፋ እረፍት እየነሳቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡  በዚህ ጊዜ ቦታው ላይ ተገኝተው መርሃ ግብሩን ይከታተሉ የነበሩ አንድ የአዞ ጎሳ አዛውንት ያፈሰሱት እንባ እንደጎርፍ እየወረደ ቦታውን አጥለቅልቆት እንደነበርና በርካታ የእንስሳውን ማሕበረሰብ አባላት እንባ እንዳራጨ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የዱር እንስሳት በተፈፀመባቸው ተደጋጋሚ ወረራና ጭፍጨፋ ብዙዎች ቀደምቶቻቸው ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል በማለት የገለፁት ተወካዮች፣ ከተደጋገጋሚ ወረራ በኋላ ባሁኑ ሰአት አዲስ አበባ ላይ የሚታየው የሲሚንቶ፣ የእንጨት፣ የቆርቆሮ፣ የአስፋልትና የብረታ ብረት ክምችት ቦታውን ወደ ቀድሞ ይዞታው መልሶ ለዱር እንስሳት አመቺ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸው ገልጠዋል፡፡  አዲስ አበባን፣ ወይንም በእነሱ አጠራር ‹‹ዳይኖፖሊስን››፣ ወደ ቀድሞ ተፈጥሮአዊ ይዘቷ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረትና የሁሉም እንስሳት አስተዋፅኦ እንደሚያስፈልግም አስታውሰዋል፡፡

ጭራቁ የሰው ልጅ በሰፊው ወርሮ የሰፈረባቸውን ቦታዎችም ወደ ህጋዊ ባለቤቶቻቸው ለማስመለስ ግዛታችን ላይ ሰፍረው አገር የሁሉም መስሏቸው ኑሮአቸውን የሚገፉት የሰው ልጆች መጤ በሚል ስያሜ ተለይተው ቢቻል በግፊ፣ ካልተቻለ ደግሞ ጥርስ በማፋጨት አያስፈራራን፣ ሲያስፈልግም እየቦተረፍን ይዞታችን ነበር ብለን የምናስበውን ቦታ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡልን ለማድረግ እቅድ ይዘናል ብለዋል፡፡  በዚህ መሠረት አንዳንድ ቦታዎች ላይ መጤዎችን ለማስለቀቅ ባደረግነው ሙከራ፣ በተለይ ባለፉት አራት አመታት፣ የተሳካ ውጤት ስለታየ በዚሁ ቀጥለን ሙሉ በሙሉ ቦታችንን ነፃ እስክናደርግ ድረስ ለከፋውንና ቡትረፋውን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ወንድሞቻችን እነ ምስጥና ትላትል፣ እንዲሁም ሰርሳሪና ቦርቧሪ የማሕበረሰባችን አባላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ክፉውና ወራሪው የሰው ልጅ የጀመረውንና የተከለብንን የከተማ ግንባታ ሂደት በመሸርሸርና በማስተጓጎል ከፍተኛ ትግል ሳያሰልሱ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ የዘመኑ አስፋልት፣ ሲሚንቶ፣ ብረትና ግንብ ግን ለመቦርቦርና ወደ አፈርነት ለመቀየር በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ስለመጣ ወደ ቀድሞ ተፈጥሮአዊ ሁኔታው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡ ለዚህም በበለፀጉት አገሮች በየእንስሳት ማእከሎች ተወስደው አጥሩ ስለሰፋ በነፃነት እንኖራለን ብለው የሚያስቡ የዱር እንስሳት ዳያስፖራዎች ሊያደርጉት የሚችሉት አስተዋፅኦ በቀላሉ ሊገመት አይገባውም ብለዋል፡፡  የዱር እንስሳት ዳያስፖራ አባላትም ይህን ጥሪ ተቀብለው አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ እንዳይቆጠቡ አሳስበዋል፡፡  በዚህ አካባቢውን ወደ ተፈጥሮአዊ ይዞታው ለመመለስ በሚካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል የተለያዩትን ባለድርሻ አካላት አስተባብረው ወደ ቀድሞ ጠፍ ሁኔታው ለመመለስ የዱር አሳማዎችን፣ ከርከሮዎችን፣ ጉማሬዎችን እንዲሁም የቀንና የማታ ጅቦችን ያካተተ የተረኞች ኮሚቴ እንደሚቋቋም ገልፀዋል፡፡

በታሪክ በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያዩ ሰው የተባለው እርኩስ ፍጡር ልጆችና ጎሳዎች እየመጡ ቦታውን እየወረሩ የእንስሳትን ዘር ሲጨፈጭፉ እንደኖሩ ገልጠው፣ እዚህ ምድር ላይ የተፈራረቁት የሰው ልጆች እርስ በርስ እየተፋጁ አንዱ ሌላውን ለማስገበር ሲያደርግ በነበረው ግብ ግብ የገፈቱ ቀማሽ የነበሩት የእንስሳት ቀደምቶች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡  የሰው ልጆች የቀደምቶቻችንን ተፈጥሮአዊ ይዞታ ለመቆጣጠርና ቀደምቶቻችንን ለመመዝበር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው አከርካሪያችንን ለተወሰነ ጊዜ ቢሰብሩብንም፣ አሁን ግን አከርካሪያቸውን እየሰበርን በመመከት ድል ለመቀዳጀት እዛው አከርካሪያችንን የሰበሩበት ቦታ ምኒልክ ቤተ መንግሥት መናፈሻ ድረስ ዘልቀን ገብተን ቦታ ቦታችንን በመያዝ፤ ሲቻል በግድ እያሳመንን፣ ሳይመች ደግሞ እያደናገርን ወደ ወሳኙ የድል ምእራፍ ለመድረስ አመቺ ጊዜ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የሰላማዊ ትግል ስልት አካል ጭምር ነው!

ምንም እንኳን የሃገሪቱን ከፍተኛ የአመራር ሥልጣን የተቆጣጠረው በአቻቻይነት ብቃቱ የተደነቀው ባለ ሁለት ክንፉ የእኛው ጣዎስ ቢሆንም፣ የምናልመውን የጠራና ያልተደበላለቀ እንስሳዊነትን የተላበሰ፣ እኛን እኛን የሚሸትና በእኛ ረዥም ቁመና ልክ የተዋቀረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለምናደርገው ጥረት መሰናክል እየሆነ ስላስቸገረ፣ ቢቻል በተንኮል ጠማቂዋና በጎሰኛዋ ጦጣ፣ ካልሆነ ደግሞ በመሠሪው ገመሬ ዝንጀሮ ተክተን ጠላቶቻችንን በእጥፍ ድርብርብ ለመበቀል እንድንችል አስፈላጊውን የቡርቦራ ሥራ በአርኪ ሁኔታ እያቀላጠፍን ነው በማለት አሁን ያሉበትን ሁኔታ አሳውቀዋል፡፡

የሰው ልጆች እየተፈራረቁ አካባቢውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት እርስ በርሳቸው እየተፋጁ ያደረሱብን በደል ከፍተኛ ነው በማለት ያለፈውን የግፍ አገዛዝ አስከፊነትም በሃዘን ገልፀዋል፡፡  አንዱ የሰው ልጅ ጎሳ ሌላውን ለማስገበር ሲያደርግ በነበረው ፉክክር ብዙ ውድመት ደርሷል ያሉት ተወካዮች፣ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የሰው ልጅ ዘሮች ቦታውን ቢቆጣጠሩትም፣ ‹‹ኬኛ›› ውጪ ለረጅም ጊዜ ባለቤትነቱን ለማስመስከር የሚችል አካል ከየትም ሊገኝ አይችልም ብለዋል፡፡

ከሁሉም ነገር በፊት ባለቤትነታቸው ሲረጋገጥ አንድ ትልቅ ሃውልት አሁን መስቀል አደባባይ እየተባለ የሚጠራው ቦታ ላይ ለማቆም እቅድ እንዳለም ገልጠዋል፡፡  ሃውልቱ በጥይት፣ በጦር፣ በጎራዴና በወጥመድ የወደቁትን ውድ የዱር እንስሳት ሰማዕታት ለማስታወስ፣ የተቦተረፉና የተዘለዘሉ የእንስሳት አካሎችን በደም ተለውሰውና ተቆራርጠው በሚያሳይ መልኩ ትውልድን በቂም በቀል ስሜት አናውዞ እንዲያርገፈግፍና ለአመፅ እንዲያነሳሳ ተደርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

መሃል አዲሰ አበባ የሚገኘው ውሃ ይፈልቅበት የነበረው ቦታም የቀደምቶቻቸው ውሃ መጠጫ፣ መሰባሰቢያ፣ መንሸራሸሪያና ማድፈጫ እንደነበር ገልጠው እሱንም ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡ በቀድሞ ጊዜ እንጦጦ፣ መናገሻ፣ ኤረር፤ ወጨጫ ወዘተ… እያሉ እንደ እንስሳት ባህላዊ ልማድ ድንበሮቻቸውን በጠረናቸው በመከለል ያስከበሯቸውን ቦታዎች በሙሉ ወደ ቀድሞ ግርማ ሞገሳቸው ተመልሰው ቦታውን የታፈረና የተከበረ የእንስስያ ክልል ዋና መናሐሪያ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡  ለዚህም እንዲረዳ ቀደም ብሎ የተጀመረው የወጣት ቡችሎችንና ግልገሎችን ጥርስ የመሞረድ ሥራ እንደቀጠለና ጥርሳቸው የተሞረደ ቡችሎችና ግልገሎች የመናከስ ችሎታቸውን አዳብረው በተመረጡ ቦታዎች ላይ ተሰማርተው የማተራመስ ተልእኳቸውን በሰፊው መያያዛቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ራሱን የእፅዋትያ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (እ.ብ.ነ.ግ) በማለት የሚጠራ የእፅዋትን ዘር እወክላለሁ የሚል ቡድን በእንስስያ ወኪሎች በኩል የተላለፈው መልዕክት ብዙ ታሪካዊ ግድፈቶች ያሉበት ሃሰተኛ፣ ፅንፈኛና በዝቅተኝነት መንፈስ የተሞላ ትርክት ነው ሲል ከላይ የተሰጠውን መግለጫ አጣጥሏል፡፡ ቀደምት ከተባለ ከእኛ ወዲያ ቀደምት ነኝ ሊል የሚገባው ምንም ምድራዊ አካል የለም በሚል ኃይለ-ቃል የጀመረው መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ምንም አይነት ተንቀሳቃሽ ፍጡር ምድር ላይ ይታይ ካልነበረበት የዓለማችን መጀመሪያ ከነበረው የሩቅ ጊዜ ዘመን ጀምሮ አስከ አሁን በቀደምት አባቶቻችን በነፈርን (Fern)፣ በነሞስ (Moss)፣ በነማግኖሊያ (Magnolia) እና በሌሎችም ግርማ ሞገስ በተጎናጸፉ የእፅዋት ዘሮች የተጀመረውን ዓለምን አረንጓዴ በማድረግ ለሁሉም ፍጡራን ማረፊያ፣ መጠለያ፣ ምግብና ትንፋሽ ሰጪ በመሆን እኛ እፅዋት በትጋት ስናገለግል ቆይተን ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃናቸው የእንስስያ ተወካዮች እኛን በማግለል ስልጣን ለመቆናጠጥ ባላቸው የስግብግብነት፣ የዝቅተኝነትና የአተራማሽነት መንፈስ ሳያማክሩንና ፍላጎታችንን ሳያካትቱ የሰጡት መግለጫ አሳዝኖናል ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰለኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡

በመጥረቢያ፣ በመጋዝ፣ በገጀራና በሜንጫ እንዲሁም በአሰከፊ ሰደድ እሳት ላለፉት ረጅም ዘመናት፣ በአሁኑ ዘመን ደግሞ በአካባቢ ብክለትና ውድመት የተጨፈጨፉት እፅዋትና ከምደረ-ገፅ እንዲጠፉ ደባ የተፈፀመባቸው ወገኖቻችን ሃዘን በቅጡ ሳይወጣልን፤ በእንስስያ ተወካዮች በኩል ሥልጣንን በመቀራመት ያንድ ወገን ንብረት ለማድረግ የተደረገው የስግብግብነት ሙከራ ከጁንታ አስተሳሰብ የሚመነጭ ለመሆኑ የመግለጫው መሠረተ ቢስነት ምስክር ነው በማለት ድርጊቱን ነቅፈዋል፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ ሊሰራ የታቀደው ሃውልትም የቆራጣ ዛፍ ጉቶዎችን፣ የተጨፈጨፉ ቅጠሎችን፣ ባጭር እየተቀጩ የጠወለጉ አበባዎችን፣ አፍርተው ለዘር ሊበቁ ሲሉ የረገፉ ፍሬዎችን ምስል ሳያካትት እንዲሰራ የተወሰነው ውሳኔ አግላይና ወገንተኝነት የተጠናወተው ነው በማለት ኮንነዋል፡፡

የእንስስያ ማሕበረሰብ አብሮ የመኖር ባሕል ያዳበረና የተፈጥሮን ሂደት ጠንቅቆ የሚረዳ፣ በትበብር፣ በፍቅርና በአንድነት የሚያምን ነው በማለት የቀጠለው መግለጫ፣ ከዚህ ማሕበረሰብ የወጡ ጥቂት ፅንፈኞች ግን በዝቅተኝነት ስሜት ተገፋፍተው አካባቢውን ለማተረማመስ ቆርጠው መነሳታቸውን ከመግለጫቸው መረዳት ይቻላል ብሏል፡፡ ጦጣና ዝንጀሮ ለባለ አራት እግሮችና ለሌሎች ፍጡራን እንዲሁም ከነሱ ለየት ላሉ የዱር እንስሳት የሚያሳዩትን ንቀትና ጥላቻ ቀጥለውበት በመላው የዱር እንስሳት ማሕበረሰብ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ባላቸው መሰሪ ፍላጎት የተነሳ ካገር ጠባቂውና ከጀግናው አንበሳ ጀምሮ ብዙ የዱር እንስሳትን በመልቲነት ሲያወናብዱ እንደኖሩ ታሪክ ምስክር ነው በማለት መግለጫቸውን አጠቃልለዋል፡፡

በተጨማሪም በዱር እንስሳት ነፃነት ግንባር (ዱ.እ.ነ.ግ) ተወካዮች የተሰጠውን መግለጫ በመቃወም የቤት እንስሳት አንድነት ፓርቲ (ቤ.እ.አ.ፓ) የተሰጠው ከፋፋይ መግለጫ የእኛን ማህበረሰብ በምንም መመዘኛ አይመጥንም፣ እኛን አይወክልም፣ የእኛን አቋምም አያንፀባርቅም ሲል ማሰተባበያ ሰጥቷል፡፡  እኛ የቤት እንስሳትና አጋሮቻችን ከወንድሞቻችን ከሰው ልጆች ጋር ያለንን ትስስር ለማናጋት የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ሙከራ አጥብቀን እናወግዛለን ካለ በኋላ፤  የእኛና የሰው ልጆች ግንኙነት በተፈጥሮ ሕግ የተሳሰረና ሸርሻሪዎች፣ ገንጣዮች፣ ጎሸኞችና ከፋፋዮች ሊሰብሩት የማይችሉት ኃይል ስለሆነ ፀረ የተፈጥሮ ሕግጋት ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አጥብቀን እናስጠነቀቃለን ሲል መግለጫውን አሳርጓል፡፡

ከላይ በሁለቱ ቡድኖች የተሰማው ተቃውሞ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዱር እንስሳት ማሕበረሰብ ውስጥም እንደተለመደው መከፋፈል እንዳለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡  በሆድ ተሳቢዎቹን (አንዳንዶች እግር አልባዎቹ እያሉ በንቀት ይጠሯቸዋል) የእባብንና የዘንዶን ማህበረሰብ የሚወክል አንድ ውሰጠ አዋቂ እንደገለፀው፣ ጦጣና ዝንጀሮ እንዳንድ የዱር እንስሳት ማህበረሰብ አባላትን በንቀት እንደሚመለከቱና ከፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገለሉና የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን እንዳይችሉ ግፊት እንደሚደረግባቸው ገልጧል፡፡  ከዚህ በፊት ‹‹ቦፋ ጉራቻ›› የሚል ስያሜ ለእርጉሙ የሰው ልጅ በመስጠት እኛን ከመርዘኛው የሰው ልጅ ጋር በማመሳሰል ብዙ የመከፋፈል ሴራዎች እየፈፀሙብን ሁኔታዎች ይስተካከሉ ይሆናል እያልን እስካሁን ብንዘልቅም ያለምንም ውጤት እስካሁን ቆይተናል ሲል አማሯል፡፡

እንዲህ አይነቱ ዘለፋና ሌሎች ከፋፋይ ድርጊቶች የእኛን በሆድ ተሳቢ ፍጡራን መልካም ሥነ ምግባር ከሰው ልጅ ወረራና አሳፋሪ ድርጊት ጋር በማመሳሰል ማሕበረሰባችንን ከዱር እንስሳት መድረክ ለማግለል ሆነ ተብሎ የተጠነሰሰ የቀጣይ ሴራ አካል በመሆኑ ጉባኤው ላይ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ ገልጧል፡፡  እኛን የመሰለ ቅዱስ ፍጡር ከአረመኔውና ከመርዛሙ የሰው ልጅ ጋር ለማመሳሰል በምሳሌም ሆነ በሌላ ዘዴ የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው እንዲታወቅልን እንፈልጋለን ብሏል፡፡ ይህ በዱር እንስሳው ማህበረሰብ መካከል ልዩነት ለመዝራት በጦጣና በዝንጀሮ አጋፋሪነት የተሸረበ አደገኛ አካሄድ የምናልማትን ታላቋን እንስስያ ለመፍጠር በሚካሄደው የተፋፋመ ትግል ላይ ቀዝቃዛ የቀበናን ውሃ የመቸለስ ያህል ነው ሲል ምሬቱን በእባብና በዘንዶ ማህበረሰብ ስም ገልጧል፡፡

1 Comment

  1. ቦቆቅሳ ሉባክ:-
    እነዚህን እንሰሶች የአሁኖቹን ተረኛ ገዥወቻችንን ደህና አድርገህ ገልጸሀቸዋልና ከዚህ በላይ መጨመር አይቻልም፡፡
    ለእያንዳንዳቸው ከብቶች ተሽጠውላቸው ትምህርት ቤት ገብተው “ተምረዋል” የተባሉት የአሁኑ የተረኞች ስብስብ ሳይማሩ ቢቀሩና ከብቶቹም ሳይሸጡ ቢቀሩ ይሻል ነበር፡፤
    ሁለቱም ማለትምእነዚህን ከብቶች ለማስተማር የተሸጡት ከብቶችም ሆኑ ተማሩ የተባሉት ሰው መሰል ከብቶች ልዩነት የላቸውምና ፡፡አብይ አህመድና በዙሪያው ያሉት ዘራፍና ተስፋፊ ኦሮሙማውች እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ አያልፍላትም፡፡ ህዝቡም እንደዚሁ፡፤
    በተለይ የአገሪቱ ዋና ነቀርሳ አብይ አህመድ በነቀርሳነቱ ተነቅሎ ካልተጣለ ሰላም አይመጣም፡፤ ነቀርሳኮ ያው ነቀርሳ ነው፡፤ ተቆርጦ ወይንም ተነቅሎ መጣል ነው ያለበት!!!!፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.