የዘድሮዋ ጥምቀት ምን ደመረች? – ቀሲስ አስተርአየ

ጥር ቀን 2013 ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወምንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ቀሲስ አስተርአየ [email protected]

የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን ህገ አረሚ፤ ህገ ልቡና ፤ ህገ ኦሪትን እያስቃኘች፡ የሚከሰቱትን አዳዲስ ክስተቶችን እየደመረች በተፈራራቂው ትውልድ ላይ ከሚሽከረከሩት ዐበይት በዐላት አንዷ ናት። ኢትዮጵያውያን መምህሮቻችን በመላ ኢትዮጵያ እየፈሰሱ በገባርነት ወደ ግብጽ የሚጎርፉትን ወንዞች ሰም፤ በያመቱ የሚገጥሙንን አዳዲስ ክስተቶን ወርቅ እያደረግን እንድንቀኝ አስተምረውናል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ረዥም ዘመኖቿ በያመቱ በጥምቀት የገጠሟትን ተደራራቢ ክስተቶች በቅኔያችን እንቃኝኛቸዋለን፡፡ እናስታውሳቸዋለን፡፡ “የጥምቀት በዓል ሰማያዊነትንና ምድራዊነትን ባህርይ በሰምና ወርቅ አጣምራ ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትቀጥል የቅኔ ምንጫችን ናት፡፡ ሌባ የማይሰርቃት፤ የውስጥና የውጭ ጠላት የማይደመስሳት፡ ምስጥ የማያበላሻት፡ በህዝብ ህሊና ላይ የተጻፈች መጽሐፍም ናት”፡ ብለው አባቶቻችን ነግረውናል፡፡

ምሥጢራዊ ይዘቷን ጥምቀትን የሚያከብረው ሁሉ ዜጋ በእኩል ባይረዳትም በተለያዩ እምነቶች ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለው ኢትዮጵያውያዊ ዜጋ ሁሉ በያመቱ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እያለ በልዩ ስሜት ሲከብራት ኖሯል፡፡

በክርስቶስ የሚያምን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብ በዓለም ያለው ሁሉ ክርስቲያን ቃሉን ያነበንበዋል፡፡ የኛ አባቶች ለጥምቀቱ በዐል ቀን ወስነው፡ ተፈጥሮ ሳይቀር እንዲተባበርበት አድርገው ሌባ በማይሠርቀው ምስጥ በማይበላው በሕዝብ ሕሊና ላይ ቀርጸዋታል፡፡

የበዓሉ መሠረት ክርስቶስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ምንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” እንዳለው (ማቴ 6፡ 33) በጥምቀቱ የተናገራትን አጥብቀን ልንሻት የሚገባን መንፈሳዊት ጽድቅነቷ ናት፡፡ ዘንድሮው ተደራርቦ ወደተደመረባት ክስተት ከመሻገሬ በፊት መንፈሳዊ ይዘቷን እንመልከት፡፡

መንፈሳዊ ይዘቷ

ክርስቶስ በጥምቀት አጠንክሮ የገለጻት ይህች ጽድቅ፤ ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ በአንተ አሕዛብ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከለት” (ገላ 3፡8) እንዳለው ይሁዲውም ሙስሊሙም አባታችን ለሚለው አብርሃም ገና ሳይገረዝ ከሕገ ኦሪት በፊት እግዚአብሔር የሰበከለት ሕገ ወንጌል የምታንጸባርቃት ጽድቅ ናት፡፡

ክርስቶስ ሕግን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጅ እንዳለው፦ ሲጠመቅ የተናገራት ጽድቅ ከሕግ ሁሉ እጅግ የተሻለች የሕግ ፍጻሜ ናት፡፡ የተሻለች መሆኗን ለማሳየት ጽድቅን ከምታውጀው ወንጌል በፊት የነበሩትን ሕገልቡናን፤ ሕገአረሚንና ሕገኦሪትን በመጠኑ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡

ሕገ ልቡና የምትባለው ሰው ያለምክርና ትምህርት ክፉና ደጉን ለይቶ የሚያውቅበት ከእንስሳት የተሻለ የምታደርገው የተፈጥሮ ሰባዊ አቅሙ ናት፡

ሕገአረሚ የምትባለው፤ በራስ ፍላጎትና ስሜት ብቻ በመነዳት ፈቃደ ሥጋውን ያልገደብ በጭካኔ በሰውም በእንስሳም እንዲፈጽም የምትገፋፋ የአራዊት ጠባይ ናት፡፡ “ለእመ ሐልቀ ሰብእ ሡዑ ሰብአ” ማለትም በሷ አምኖ የሚከተላት የሚያርደው እንስሳ ቢያጣ ሰው እንዲያርድ የምታስገድድ ናት፡፡

ሕገኦሪት የምትባለው “ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ ይውለቅ” በሚል መርሆ ፍትህ ርትዕ ማለትም ሚዛናዊ ፍዳ የሚያስከፍል መንግሥት ያላት በሙሴ ዘመን የተከሰተችው ሕግ ናት፡ እነዚህ ህግጋት ማለትም፦ሕገልቡና፤ ሕገአረሚና ሕገኦሪት በመጠን ይለያዩ እንጅ በሁሉም ዘመናት በሕብረተ ሰብ ውስጥ ይንጸባረቃሉ፡፡ “ጥርስ የሰበረ ጥርሱ ይሰበር” የሚትለውን ፍትህ ርትዕ የሚያስጠብቅ ማለትም ሚዛናዊ ፍዳ የሚያስከፍል መንግሥት ያላት ከህገ አርሚ እጅግ የምትሻል ከሕገ ኦሪት የተቀዳች ናት፡፡

ሕገ አረሚ ገዳይና ሟች የሚበዛበት ሕግ አስከባሪ መንግሥት የጠፋባት፡ የገደለ ያለፍርድ በነጻ የሚለቀቅባት አባቶቻችን ዘመነ መንሱት፤ ዘመነ መከራ፤ ዘመነ ደይንና ዘመነ አጸባ እያሉ የሚገልጿት ናት፡፡ ፍጹማን ባይሆኑም በዘመናቸው ከነበረው ሕዝብ ተሽለው የተገኙባቸው ኖህና የአብርሃም የነበሩባቸው ዘመኖች ለሕገ አረሚ መገለጫወች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

አብርሃም ገና ሳይገረዝ ከህገ ኦሪት በፊት እግዚአብሔር የሰበከለት ክርስቶስ በጥምቀቱ መፈጸም አለባት ያላት፡ በተለያዩ ወቅቶችም ደጋገሞ የገለጻት እነ ቅዱስ ጳውሎስ ያንጸባረቋት ጽድቅ ናት፡፡ ጽድቅ በከንቱ ውዳሴ ላይ ከተመሰረተ ከቡድን አድናቆት የምታሸሽ፡፡ ከከንቱ ውዳሴ የምታርቅና እያንዳንዱ ባልንጀራው ከሱ እንደሚሻል በትህትና እንዲቀበል የምታደርግ ለራስ ብቻ የሚጠቅመውን ከመመልከት እንዲርቅ የምታደርግ በክርስቶስ የነበረች ናት” (ፊል 2፡3_5)

ሕገ አረሚን ነቃቅለው ከሚጥሉ የጽድቅን ጥልቅ ባህርይ ከሚገልጹ አባቶቻን ከሚጠቀሷቸው ብዙዎቹ ምሳሌወች በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ም 6 ከ ቁ 1_እስከ 8 የተገለጹት ምሳሩና የእንጨቱ ቅርፍት ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙት ይገባል

በመጽሐፉ እንደተገለጸው ታሪኩ ባጭሩ እንደዚህ ነው፡፡ በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን ከሱ ጋራ የነበሩት ሰወች ቤት ለመስራት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ለቤት የሚሆን እንጨት ፍለጋ ሔዱ፡፡ ከመካክውላቸው አንዱ የተዋስው መጥረቢያ ከእጀታው ተለይቶ በሮ ከዮርዳኖስ ውሀ ውስጥ ገባ፡፡ “የተዋስኩት መጥረቢያ ከውሀው ውስጥ ገባብኝ እያለ” ጮኽ፡፡

ነቢዩ በየት በኩል ነው የወደቀው ብሎ የወደቀበትን አቅጣጫ እንዲያሰው ጠየቀው፡፡ አቅጣጫውን ሲያሳየው መጥረቢያው በወደቀበት አቅጣጫ የእንጨ ቅርፍት አምጥቶ ወደ ባሕሩ ወረወረው፡፡ መንሳፈፍ የሚገባው ቅርፍት የመጥረቢያውን ክብደት ወስዶ በመጠረቢያው ቦታ ሰመጠ፡፡ የሰጠመው መጥረቢያ የቅርፍቱን መንሳፈፍ ወስዶ ከባህሩ ወለል ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ከሰመጠበት ወጣ፡፡

በተመሳሳይ መንገድ፦ ክርስቶስ ሲጠመቅ ሰውን ከሰመጠበት ለማውጣት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም በለበሰው ሥጋ በሰባዊ ባህርይ ውስጥ ገባ፡፡ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ “ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” በማለት የኛን ፍዳ በመሸከም የሱን ጽድቅ ለኛ ሰጥቶ ከዘላለም ጥፋት አዳነን፡፡ ጽድቅ የምትባለው በመጥረቢያውና በቅርፍቱ መካከል የተፈጸመችው፤ በክርስቶስና በሰው መካከል የተፈጸመችው ቤዛነት ናት፡

ቅዱስ አትናቴዎስ የተባለው “ክርስቶስ ቦአ ውስተ መርገም በእንቲአነ እንዘ ኢይቀርቦ መርገም፡አላ ሰምረ ከመ ይጹር መርገመ ዚአነ ወበእንተ ዝንቱ ተብህለ ከመ ውእቱ ቦአ ውስተ መርገም(ሃ ም ፴፡ ቁ ፬) እያለ ገለጸው። ክርስቶስ መርገም የሌለበት ሲሆን እኛን ከከገባንበት መርገም ያወጣን ዘንድ በልደቱ አማካይነት በሰውነታችን፤ በጥምቀቱ ደግሞ በውሀው አማካይነት በሁለንተናችን ሰምጦ ገባ፡፡ ማለትም ተወሀደ፡፡ እስከዚህ የተገለጸችው በቤታችን አተረጓጎም ሰምና ወርቅ ስልት በወርቅነት ስለምትመደበችው ጽድቅ ሲሆን፡ ከዚህ በመቀጠል በሰምነት ተጨማሪ ሆና ወደምንገልጻት ወደ ኢትዮጵያዊነታችን ማለትም ወደ ነጻነታችን እንሻገራለን፡፡

(ተደማሪ)

ክርስስቶ እኛን ያዳነው በመንፈሳዊ መለኮቱ ባቻ አይደለም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈውርቅ “ሞተ በሥጋ ዘያበጥል እዘዘ ሞት ዘውእቱ ዲያብሎስ በከመ ጽሑፍ እንዘ አልቦ መኑሂ ዘየአምር ምሥጢራቲሁ ለሊሁ የአምር ዘገብረ ከመ ያድህነነ”(62፡8) እንዳለው በኛ ላይ ዲያብሎስ ካመጣብንን ከዘላለማዊ ሞት ያዳነን ነጻም ያደረገን በመለኮቱ ብቻ ሳይሆን ከመቤታችን ንስቶ በተወሀደው ሰባዊ አካሉ ድምር ውህደት ነው፡፡

ክርስቶስ በዚህ ዐለም የሚኖረውን ቁስ አካላዊ ሰው ያዳነው በመለኮቱ ብቻ ሳይሆን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን በነሳው ሥጋ ውህደት እንደሆነ ሁሉ፡፡ ሰውም በዚህ ዓለም ሲኖር በእንጀራ ብቻ መኖር እንደማይችል ለማመልከት “ሰው ከግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም”(ማቴ 4፡4) ብሎ ራሱ ክርስቶስ ተናገረ፡፡ ሲጠመቅ “ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” ካለ በኋል ጽድቅን በመፈጸም ብቻ በዚህ ዓለም መኖር እንደማንችልና ተጨማሪ ነገሮች እንደሚያስፈልጉን ለመጠቆም “ይህ ሁሉ ይጨምርላችኋል” አለ፡፡

የቀደሙ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን የጥምቀቱን ስነ ስርአት የጀመሩት በቅድሚያ ጽድቅን በመሻት ቢሆንም፡ በተጨማሪነ (ተውሳክነት)ለአገራዊ ቤዛነት ተጠቅመውበታል፡፡ ምንም እንኳ በተጨማሪነት ለምድራዊ ሕይወታችን ላበረከተው ነገር ይጠቅማል ብለው ባይዘረጉትም፡ የጥምቀቱና የደመራው አከባበር ስርአት በመንፈሳዊነቱ ላይ ለምድራዊ ኑሯችን የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮችን አበርክተዋል፡፡ ካበረቷቸው ብዙ ጠቃሚ ነገሮች በሌላ ክፍለ ዓለም ውስጥ ባሉ ክርስቲያኖች የሌሉ ለኢትዮጵያዊ ነጻነትንና ሰባዊ ክብርን አንጸባራቂወችን የመሳሰሉ ናቸው፡፡

የጥመቀትን በዓል ሰማያዊነትንና ምድራዊነትን ባህርይ በሰምና በወርቅ አጣምራ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ሌባ የማይሰርቃት፤ የውስጥና የውጭ ጠላት የማይደመስሳት፡ ምስጥ የማያበላሻት፡ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር አገር መከላክያ አጥርና መከታ መልእክት ማስተላለፊያ ብሄራዊ መገናኛ ማንም ሊያፍናት የምይችል የማንንም ፈቃድ የማትሻ የብሶታችን መግለጫ አድርገው የቀደሙ አባቶቻችን ሰርተውልናል፡፡

ጽድቅ የተነገረባትን የጥምቀትን በዐል በዚህ ዓለም ነፍስና ሥጋችንን ለመርገጥ ምድራችንን ለመውረስ የሚፈታተኑን የጨለማው ወኪሎች ትእቢተኞች ወራሪወችን እንድንገስጽበት አድርገውልናል፡፡

ይህች ጽድቅ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ክርስቶስን ስትጸንሰው “ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኗቸዋል፡፡ ገዥወችን ከዙፋናቸው አዋርዷቸዋል ትሑታንን ክፍ አድርጓል የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው ባለጠጎችን ባዷቸውን ሰደዳቸው” (ሉቃስ 1፡51_52) በማለት ሰባዊ ክብርን ለማንጸባረቅ ያሰማቻት መፈክር ናት ብለው አስተምረውናል፡፡

በጥምቀቱ በዓል በታቦቱ ዙሪያ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ነፍጣቸውን በትክሻቸው አደርገው አዘማሪወች በመሰንቆ በበገና በጥሩንባ ያስተጋቡት የነበረው እመቤታችን ክርስቶስን ስትጸንሰው የተናገርችውን ሰባዊ ክብርንና ነጻነትን ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ አባቶቻችን ቅዱስ ያዕቆብ “ኦ ሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን ወይጎይይ እምኔክሙ (ያዕቆ ብ ፬፡፯) ማለትም ጋኔንን በመቃወም እንቢ በሉት ይርቃችኋል እግዚአብሔርን ቅረቡት” የሚለውን ተንተርሰው፡ ወራሪወችን ቅኝ ገዥወችን አትታዘዙ እንዲያውም ተቃወሙ እያሉ ጎልማሳው በኢትዮጵያውነቱ ላይ ለሚመጣበት ወራሪ ጠላት በታቦቱ ዙሪያ “እንቢ በል” የምትለዋን የተግሳጽ መፈክር እንዲያሰማባት አድርገዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው መንግስታዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚጠይቅ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ

ዓለም በተለይ አጎራባች አገሮች በወራሪወች እጅ ላይ ወድቀው በሚጨነቁበት ጊዜ፦ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ቅዱስ ጳውሎስ “ለመታዘዝ ባሪያወች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት ባሪወች እንደሆናችሁ አታውቁምን? ወይ ለሞት የኀጢአት ባሪወች ናችሁ ወይም ለጽድቅ ለመታዘዝ ባሪያውች ናችሁ” (ሮሜ፮፡፲፮ ) ያለውን በመጥቀስ ለባርነት ራሳቸውን ያቀረቡትን እየገሰጹ፡ ወጣቱ ለሰው ልጅ ነጻነትና ክብር ሆ ብሎ በመነሳት በጥምቀትን በዐል ሆታውን እንዲያስተጋባ ማድረጋቸው በጅጉ መከበርና መደነቅ የሚገባቸው ናቸው፡፡

“የደከሙትን እጆች አበርቱ፡፡ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ፡፡ ፈሪ ልብ ላለቸው እነሆ አምላክችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ አትፍሩ በሏቸው” (ኢሳይ 35፡ 3_4) በሚለው በነብያት ቃልም የፈራው አደር ባዩ፤ ተስፋ የቆረጠው ከወራሪወች ጋራ እንዳይስማማ ብድራትን ከፋይ በሆነው በግዚአብሔር በማታመን ተቃውሞውን እንዲያጠንክር ያበረታቱ ነበር፡፡

“በክርስቶስ አምነን የጸደቅን ነን፡፡ ከኛ በቀር የጸደቀ የለም” በማለት የሚመጻደቁት አውሮፓውያን የሰው አገር ከመውረር ይልቅ በዘመነ አራዊት ውስጥ የነበሩትን እጅግ ኋላ ቀር የነበሩትን ሰዎች፤ ከህገ አራዊት እንዲወጡ፤ በሕገ ኦሪት የነበሩ ሰዎች ደግሞ ወደ ሕገ ክርስቶስ ማለትም ወደ ጽድቅ እንዲሻገሩ ምሳሌዎች እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ነበሩ። ነገር ግን የተጠመቁበትን ጽድቅ ርስተው፡ በተቃራኒዋ በሕገ አረሚ ውስጥ ሰመጠው በመግባት በሰው ላይ የአራዊት ተግባር መፈጸም ቀጠሉ፡፡

እንዲያውም በኢትዮጵያ ምድር በጥምቀቱ ሚተላለፉትን የነጻነት ነጸብራቅና ተግሳጽ በወኪሎቻቸው አማካይነት ማጣጣልንና ማናናቅን በኢትዮጵያውያን መካከል ማሰራጨት ጀመሩ፡፡ ለጽድቅ ሰም የሆነችውን ኢትዮጵያዊነትን መደምሰስ ባይችሉም፡ በኢትዮጵያውያን ላይ የምትንጸባረቀው የነጻናት መንፈስ ወደ ጎረቤት አገሮች እንዳትሻገር በሚችሉት መንገድ ሁሉ ይጥሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያውያን ጭንቃላት የአገር ፍቅርንና ነጻነትን የቀረጸችው ኦርቶዶካሳዊት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ሲረዱ ጥርሳቸውን ይነክሱባት ጀመር፡፡ የኢትዮጵያውነትን ስነ ሕሊና በቀረጸችባቸውን ዜጎች ላይም ለሚገዟቸው አጎራባች ህዝቦች “ኢትዮጵያውያን ስልጣኔን የማይሹ ያልሰለጠኑ ናቸው” እያሉ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሰፊው ያሰራጩ እንደነበረ ከኢትዮጵያውያን መምህራን ሰምቻለሁ፡፡

ወራሪወች በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያሰራጩትን ከመምህሮቼ እየሰማሁ ያደኩትን ደባና ጥላች፤ ኬንያ በትምህርት በቆየሁባቸው ዓመታት ከኬንያ ከዩጋንዳና ከታንዛንያ ከሱዳን ከሌሎችም አፍሪቃ አገሮች የመጡ ተማሪወች ይህንኑ ደባና ሸፍጥ የቅኝ ገዥወች ለአባቶቻቸው ያሰራጩት እንደነበረ ከወላጆቻቸው እንደሰሙትና የነቁት አፍሪቃውያን የሚሰራጨውን ደባ ይቃወሙ እንደነበረ ተረድቻለሁ፡፡

ወያኔወች የፖለቲካ ቀመራቸውን እንዴት እንደጀመሩት ስመለከትም አውሮፓውያን በኢትዮጵያ ላይ ያካሄዱት የነበረውን ይህንኑ ሰይጣናዊ ደባ እንደተጠቀሙበት ተረዳሁ፡፡ ከአውሮፓውያንና ካንዳንድ አጎራባች አገሮች ድጋፍ ያገኙ ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና በአመረኛ ተናጋሪው ሁሉ ላይ በሰፊው አሰራጩት፡፡

ወያኔወች ለፈጸሙት ደባ፦ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ለዲግሪያቸው መመረቂያ ባቀረቡት መጽሐፋቸው ከዚህ በታች ካሰፈሩት የበለጠ መረጃ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡“የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው” ብለው ጽፈውታል፡፡

ወያኔወች ቤተ ክርስቲያኒቱን እየመቱ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ስትቀርጸው የኖረችው ሊጠራርጉ የሞከሩት በጥምቀቱ በዓል የሚንጸባረቁትን ሰባዊ ክብርን ነጻነትንና የመሳሰሉትን ነው፡፡ የሚተኩትም በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት ነው፡፡ በዚህ አረማዊ ስሜታቸው የብዙ ሕዝብ ሕይወትና ንብረት ቢያጠፉም፡ በመጨረሻ ራሳቸውን አጠፉ እንጅ የጥምቀቱን ሥርአት ጨርሰው ሊያጠፉት አልቻሉም፡፡ ጭርሰው ባያጠፉትም የኢትዮጵያ ህዝብ በየቋንቋው ያንጸባረቅ የነበረውን የጋራ ጀግንነትና እርበኝነት በመጠኑም ቢሆን አኮላሽተውታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይ መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ተቃዋሚ በሌለበት ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ መሄድ እንደሚችሉ ገለፁ

ከብዙ እልቂት በኋል ተፈጸመ የተባለውን እርቅ በጥምቀቱ ክርስቶስ በተናገራት ጽድቅ ስመዝነው፡ ለትግራይ፤ ለአማራውና ለፋር አባቶች እና እናቶች፡ ለሕጻናት፤ ለእንስሣትና ለአዕዋፉ ፋታ ሰጭ በሚስልና ወገን በሞትና በህይወት መካከል ሲንፈራፈር ከማየት ዓይኖቻቸው ቢያርፉም ፡ ሲያርዱና ሲያስተራርዱ የነበሩት ባለስልጣናት ያሳዩት ደስታ መሳሳምና መጨባበጥ እርም የበሉ አርመኔነታቸውን የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን፡ በሞተው ህዝብ ላይ ቆመው የሰርግ እስክስታ የሚያወርዱ መስለው መታየታቸው እጅግ በጣም ያስቅቃል፡፡

ራሳቸው በፈጠሩት ጦርነት የወገን ሬሳ በሸፈነው ምድር ላይና በወገን ደም ወደጭቃነት በተቀየርው አፈር ላይ ቆመው፡፡ ከወገን ደም ጋራ ተቀላቅሎ የሚተነውን አየር እየተነፈሱ ምንም የሀዘን ገጽ ሳይታይባቸው ሲሳሳቁ፤ ሲሳሳሙና እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ ከማየት የባሰ አረመኔነት ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡

በህዝብና በእንስሳ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ያረመኔ ተግባር በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ሲፈተሽ የሃይማኖት መሪወችን በተለይም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ያለነውን መሪወች ከፖለቲከኞች የባሰ አረመኔወች ያደረገን ይመስለኛል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር የተከሰቱት በሕገ አረሚ የሚመሩ ሰወች፡ ከነሱ ዘር የተለየ የመሰላቸውን ዜጋ ሲያርዱና ሲጨፈጭፉ፡ “ዘሩ የሱ እንዳልሆነ ባወቀ ጊዜ ዘር ለማጥፋት ዘሩን በምድር በማፍሰሱ እግዚአብሔር የቀሰፈውን አውናን በምሳሌ እየጠቀስች፡ ሰውን መግደል ይቀርና በሴት ማህጸን ያልተቀረጸውን ዘር መድፋት ይስቀስፋል” (ዘፍ 38፡9) እያለች በምታስተምረን በኢትዮጵያ እርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለን ይምንለውን ሁላችን ካህናት ለምንመራው ወገናችን የችግሩ መጠን የሚጠይቀንን ባለማደረጋችን በህዝብ ፊት መቆም የሚያሳፍረን ይመስለኛል፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስም “ሕጻንን ካባቱ ወገብ ወደ ሴት ማሕጸን የምትልከው በረቂቅ ሰፋድልም የምትጠቀልለው ውሀ ሲሆነ በጥበብህ የምታረጋው የሕይወት መንፈስ እፍ ትልበታለህ በአርባ ቀን ትሰይመዋለህ” (ቅ ገ 232 ቁ 113) ብሎ የጻፈው ቀኖና መመሪያችን ነው፡፡ የተጎዳውንና የታዛበንን ሕዝብ በዚህ መጽሐፈ ቅዳሴ ቀድሰን የምናቆረበው ከሆነ የእግዚአብሔርን የማየት ኃይል መፈታተንና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ መሳለቅ ይመስለኛል፡፡

ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ባንገታቸው ያለውን ምልክት እንዲቆርጡ ተጠይቀው ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በታረዱ ጊዜ የት ነበርን? ቤተ ክርስቲያናችን ያጠመቀቻቸውን የትግራንና ያማራውን ወጣት ፖለቲከኞች እርስ በርሱ ሲስተራርዱት የት ነበርን? ሊቃውንት አባቶቻችን አንገታችንን እንድንሰጥ ያስተማሩንና ያወረሱን ምሳሌነት በህዝብ አንገት ላይ ለተሰነዘረ ሰይፍ ነበር፡፡

ለዚህ ምሳሌነት ዘወትር ከብዙ ምሳሌወቻን ሳልጠቅሳቸው ከማላልፋቸው መካከል በግንባር ቀደም የምጠቅሳቸው የደብረ ሊባኖሱ ሰማእት መምህር ገ/ኢየሱስ ናቸው፡፡ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በወረሩበት ጊዜ የሰላሌን ሕዝብ ሲጨፈጭፉ መምህር ገ/ኢየሱስ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ዘግተው ከሚኖሩባት ዋሻቸው ወጥተው በሰላሌ ህዝብ አንገት ላይ ለተሰነዘረው ሰይፍ አንገታቸው በመስጠት ቅዱስ መጽሐፍ “ከኃጢአት ጋራ እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም” (ዕብ 12፡4 ) የሚለውን በተግባር እንደፈጸሙት በስማቸው በተቋቋመው ትምህርት ቤት ገብቼ በቆየሁበት ጊዜ ከደብረ ሊባኖስ ሊቃውንት መምህሮቼ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስ “ክርስቶስ ቦአ ውስተ መርገም በእንቲአነ እንዘ ኢይቀርቦ መርገም፡ አላ ሰምረ ከመ ይጹር መርገመ ዚአነ ወበእንተ ዝንቱ ተብህለ ከመ ውእቱ ቦአ ውስተ መርገም(፴፡፬) እያለ እንደ ገለጸው። ክርስቶስ መርገም የሌለበት ሲሆን በልደቱ አማካይነት በሰውነታችን ሰምጦ የገባው፡፡ በጥምቀቱም እኛን ያጸድቀን ዘንድ “ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” በማለት በውሀው አማካይነት በሁለንተናችን ሰምጦ የገባው፡ እኛም ይህን የመሰለ ክስተት በህዝባችን መካከል ሲከሰት እንድንገባበት ምሳሌ እንዲሆነን ነበር ፡

ህዝባችን ከገባበት ሕገ አረሚ እንታደገው ዘንድ እንድንገባበት ከሚጠይቀን ከዘንድሮው መርገም የከፋ ሕገ አረሚ ያለ አይመስለኝም ፡፡ እስካሁን በዓለም ነበረች ተብላ የሚነገርላት “ለእመ ሐልቀ ላሕም ሡዑ ስብአ” ማለትም “የምትሰዋው ላም ቢይልቅብህ ሰው ሰዋ” የምትለው ነበረች፡፡ ዘንድሮ በኢትዮጵያ አገራችን የተከሰተችው” “የምታረደው ሰው ካለቅብህ እንስሳ ሰዋ! ረድ !” የምትል እጅግ የከፋች ሕገ አረሚ ናት፡፡ በዘንድሮው ጥምቀት ታሪካችን ላይ የትኛዋ ትደመር? መልሱን ላንባቢ እተወዋለሁ፡፡

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.