ተዋሕዶን ለማወክ የሚፈጸመው የአቢይ አህመድ መንግሥታዊ ሽብር በደል እስከ መቼ?

በተለይ የአደባባይ በዐላቷን ለማወክ የሚሠራው በደል መቼ የተጀመረ ነው?

(ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የጥምቀትን በዐል መቃረብ አስታክኮ ሲፈጸም ያስተዋልኩት  የተለመደው ሕዝብን  የማሸበር እና የ ማስጨነቅ ድርጊት ነው።

ብዙ ሰዎች የተዋሕዶ ክርስትናን የማዋከቡን ሂደት አቢይ አህመድ የጀመረው የሚመስላቸው አሉ። እርግጥ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ከግራኝና ከኦሮሞ አባ ዱላዎች ወረራ ዘመን  ኋላ ከፋሺስት  ጣልያንም አገዛዝ ወቅት ወዲህ እንደ አቢይ አህመድ ያሳደደ፣ ያዋረደ ዘመን አልነበረም ለማለት ይቻላል። ይሁንና በቅርቡ ዘመናችን ታሪክ የተዋሕዶ እምነትንየማጥቃት   በተለይም የአደባባይ በዓላቷን የማዳከም ተልእኮ ከሶሻሊስቱ የደርግ ሥርዐት ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ እንጂ አቢይ አህመድ የጀመረው አይደለም። በደርግ   ዘመን የአደባባይ በዐላት በድምቀት እንዳይከበሩ የተማሪዎችን የፈተና ቀን በዚሁ በጥምቀት በዐል  ማግሥት እንዲሆን በማድረግ፣ በዐሉን የሥራና የስብሰባ እለት በማድረግ እና በሌሎችም ብዙ ብዙ መንገዶች የማወክ ሥራ ተሠርቷል። ይህም ቀላል ጉዳት ሳያደርስ ያለፈ አይደለም።

የተማሩና ደህና ገቢ አላቸው ከሚባሉ የሰፈራችን ቤተሰቦች የማስታውሰው አንድ ቤተስብ ብቻ ነበር በደርግ ዘመን አባት ልጆቻቸውን አዲስ የባህል ልብሶች አልብሰው ልጆቻቸውን ጥምቀት በዐል ሊያከብሩ የሚወስዷቸው። በስተቀር ልጆች በራሳቸው ሄደው ያከብሩ ካልሆነ የተማረና የተሻለ ገቢ አለው ከሚባለው ቤተሰብ መካከል ራሳቸውም በመሳተፍ ልጆቻቸውንም ይዘው በመሄድ ከአካባቢያችን አንድም ትዝ የሚለኝ ቤተሰብ የለም። በዐሉን አክብሮ ከነቤተሰቡ በመታደም የሚያደምቀው አነስተኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ነበር ለማለት ይቻላል። ይህ ለውጥ ደግሞ እንደኔ ትዝብት የደርግን መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ከነበረው የሽብር ጊዜ በኋላ የተከሰተ ነበር።

ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ፖሊስ ከአደባባይ በዐላት አስቀድሞ በሚያወጣቸው የተጠኑ የማሸበሪያ መግለጫዎች የተነሳም ይሁን ሌላ የተማረ ወይም መካከለኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል በነዚህ በዐላት ላይ እንደማይታደም ታዝቢያለሁ። የራሴን የእድሜ ባልንጀሮች በምሳሌነት ስወስድ አንዳቸውም ልጆቻቸውን ይዘው በከተራ፣ በደመራ፣ ወይም በጥምቀት በዐላት ላይ ሲገኙ አላየሁም። የአዲስ አበባ ተወላጆቹን ማለቴ ነው።  በጉዳዩ በማዘን ካነጋገርኳቸው ከብዙዎቹ የተረዳሁት ከፍተኛ ፍርሃትና ሥጋት እንዳለባቸው ነው።

የራሴን ቤተሰብ በምሳሌ ብወስድ እኔ በውጭ ሀገር ባለሁበት ወቅት አንድ ወንድሜ (የአጎቴ ልጅ) የኔን ልጅ የመስቀልን በዐል ሊያሳያት እሽኮኮ ብሏት በሄደበት በመስቀል አደባባይ ለከተራ ቀን ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ በአግአዚ ጦር ተከፍቶባቸው ከቦታው ለመሸሽ ተገድደው ነበር። በወያኔ የሥልጣን ዘመን። በዚሁ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የደመራን በዐል ለማክበር የቤተሰብና የጓደኞቼን ልጆች መስቀል አደባባይ ሄጄ ምእመኑ እንደዚህ ዐይነት ቦታ ድርሽ እንዳይል የሚደረገውን ማዋከብና ማስፈራራት በገዛ ዐይኔ ለመታዘብ ችያለሁ።

ይባስ ብሎ አቢይ አህመድ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በዋለው የመጀመሪያው የመስቀል በዐል ደመራ እለት ከልብሳችን እና ካንገታችን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ካልፈታን ወደ አደባባዩ መሄድ ተከልክለን ነበር። በፌዴራል ፖሊስ። በአጋጣሚ በእለቱ አብረን የነበርነው (በወያኔ አገላለጽ) አንድ ኦሮሞ፣ አንድ አማራና አንድ ትግሬ ነበርን። ሦስታችንም በአልባሳታችን ላይ ያሉትን ወይም በአካላችን የጠመጠምነውን ሰንደቅ ዓላማ እንድንፈታ ስንገደድ እልህና እንባ ቢተናነቀንም ምንም ልናደርግ አልቻልንም።  በዚህም ወቅት ከበዐሉ አስቀድሞ የሚደረገው የተቀነባበረ የፖሊስ መግለጫና የሚዲያ ማስፈራሪያ ከበፊቱም በከፋ መልኩ ቀጥሎ ነበር። ከዚያም ወዲህ በእያንዳንዱ የተዋሕዶ የአደባባይ በዓል ወቅት እንዲህ ዓይነት የተጠና በመግለጫና በሚዲያ የታገዘ መንግሥታዊ ሽብር እስከዛሬ ቀጥሏል። የየካ ሚካኤል ታቦት ማረፊያ ሕዝቡ ላይ በቀጥታ በተደገኑ የፒክአፕ መትረየሶች የታጀበ ነበር።  እርግጥ በዐሉ ሁል ጊዜም ከወትሮውም ድምቅ ብሎ የተከበረ ይመስላል። እውነትም የሕዝቡ ቁጥር እያደገ በመሄዱና ከገጠር ወደ ከተማ ያለውም ፍልሰት በመጨመሩ አከባበሩ እየተሻለ የመጣ ሊመስለን ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮሚያ የሰው ቄራ!?-ከቴዎድሮስ ሐይሌ

ይሁን እንጂ እልፍ እአላፍ በዚህ ሽብር ምክንያት በበዐሉ ሳይታደሙ እየቀሩ ልጆቻቸውም የዚህ ትውፊትና መንፈሳዊ በረከት ተሳታፊ ሳይሆኑ፣ በእድሉ ሳይጠቀሙ እየተጎዱ ነው።   በሽብር  መልእክቶቹ ሳይረቱ በየአደባባዩ በድፍረት የወጡት አእላፍ ምእመናን በፍርሃት ተሸብበው እቤት የዋሉትን እልፍ አእላፍ እንዳይሸፍኑብን።  ይህ መንግሥታዊ የሽብር ድርጊት አስጸያፊ የመብት ድፍጠጣና ጭፍለቃ ስለሆነ ሊወገዝና ሊቆም የሚገባው እጅግ የከፋ የጭቆና ተግባር ነው።

ከእምነተ ቤተክርስትያን አኳያ ስንመለከተው የበዐሉ አከባበር በነዚህ በተጠቀሱት ዘመናት መካከል መንፈሳዊ ይዘቱ እየጎላ መምጣቱ እንዲሁም የወጣቱ ተሳትፎም እጅግ እያደገ መምጣቱ እሙን ነው። ይህ ግን ከመንግሥት ተጽእኖ እና ፍላጎት በተቃራኒ በሕዝቡ ውስጥ በተፈጠረ መነቃቃትና በቤተክርስትያንም ማሕበራት በተደረጉ ሥራዎች የተፈጸመ ነው።

ለማጠቃለል፣ በአቢይ አህመድ ጊዜ በአስከፊ ሁኔታ ቢባባስም፣ በተዋሕዶ ላይ በተለይ በአደባባይ በዐላት ዙሪያ የሚፈጸመው መንግሥታዊ ሽብርና ማዋከብ ከእግዜር የለሹ ደርግ ዘመን ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም።

ስለዚህም ውጊያው ከወገን ጋር ሳይሆን ከክፉ መንፈስ ጋር ነው የሚባለውን ለማመን እንገደዳለን።

መልካም የከተራና የጥምቀት በዐል!

 

 

1 Comment

  1. ዳንኤል ክብረት ሰለመ ወይስ ኮተለከ ወይስ ጰነጠጠ? እንደዛ በዛ በክፉ ዘመን አንገቱን ለካራ የሰጠ ክርስቲያን በየቀኑ እየተሸበለለብን የተቸገርነው? ሊታዘንለት ይገባል ተጠልፎ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.