ውርደት ቀለባቸው የሆነው የአንዳንድ የጥቅም አነፍናፊ ዲያስፖራዎች ቅሌት!

አባቶቻችን ከባዕድ ሃገር ወራሪ ጋር ጦር ገጥመው የተሰዋው ተሰውቶ ፣ የቆሰለው ቆስሎ ፣ በእድል የተረፈው ተርፎ ፣ ጠላትን ድል ነስተውና ሃገራዊ ግዴታቸውን አሳክተው ወደ ቀያቸው ሲመለሱ “ ጉሮ ውሸባ ፣ ጉሮ ወሸባ ጀግና ድል አርጎ ሲገባ “ እያሉ እየፎከሩና እየሸለሉ መመለስ የነበረና ያለ እሴታችን ነው።

ይህ ሆኖ እያለ ግን አንዳንድ የከተማ አዘጥዛጭ ፣ አቃጣሪና ባንዳዎች ቆዳቸውን እየቀያየሩ ከድል ማግስት “ የድል አጥቢያ አርበኛ በመሆን ፣ ለሹመኞች “የእጅ መንሻ “ በማቀረብ ፣ ባልነበሩበት የጦርነት ውሎ እንደነበሩ እየዋሹ ፣ የቅጥፈት ታሪክ እየደሰኮሩ፣ እየቀባጠሩና እያስመሰሉ የደጃዛማችነት ፣ ቀኝ አዝማችነት ፣ ፊት አውራሪነት ወዘተ ሹመትና ጥቅማ ጥቅም ያገኙ እንደ ነበር የታሪክ መዝገብ ያትታል ። ይህን እፀያፉ ክዋናዊ ክስተት ለማውገዝ “ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ተብሎ ቅኔያዊ ስንኝ ተደርድሯል።

ይህን ካልን ዘንዳ ሰሞኑን በዝችው ባልታደለችው በኛይቱ ኢትዮጵያ ሃገራችን ምድር አንድ ተዊነታዊ ኩነት ሊፈፀም እንደሆነ ሰምተናል። እሱም ላጎብዳኤች ፣ ሰርቆ አሰራቂ ፣ ዘርፎ አዘራፊ ፣ ማህበረሰቡ ሳይመርጣቸው ራሳቸውን በራሳቸው በአዕምሯቸው ሳይሆን በጡንቻቸው የዲያስፖራ መሪነን ብለው ለሾሙት፣ ስብህናቸው ለዘቀጠው ፣ ስነምግባራቸው ከሕዝብ ላፈነገጠውና ዘመናዊ የዲያስፖራ ጩልሌ ሌቦች መንግስት ሽልማትና እውቅና ሊሰጥ እንደሆነ በቴሌቭዥኑ መስኮትና በተለያዩ የመንግስት በይነ መረቦች እየተላለፈ ሰምተንዋል።

መቸም “ ጀሮ የማይሰማው፣ ዐይን የማያየው የለም” እና “ምን ሲሉ ሰምታ ዶሮ ምን ብላ ሞተች” እንዲሉ የዘመኑ የዲያስፖራ አሽቃባጭ የጥቅም አነፍናፊዎች ፣ ተራ ኪስ አውላቂዎች ፣ ከዕውቀት ነፃዎችና አፍረተ ቢሶች “ መጥናል መጠናል ሰርቀን አሰርቀን ሂሳብ ልናወራርድ አዲስ አበባ ላይ” እያሉ እየጨፈሩ ከጋሻጃግሬዎቻቸው ሽልማት ሊረከቡ ወደ ሚዳናዋ ሸገር እያቀኑ እንደሆነ እየታዘብንና እያየን ነው።

መቸም ሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ “ለምን ይህ ሆነ?” ብሎ የሚጠይቅ መንግስት ስለሌለ ክፉ ሆነ ደጉ ሁሉ የሚከናወነው በግላጭ ሁኗል ”። ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል “ሕግ ማስከበር “ የሚል የዳቦ ስም ወጥቶለት በተከወነው እልህ አስጨራሽ ጦርነት የውጭ ታዛቢዎች እንደዘገቡትና እውነታው እንደሚያሳየው ከግማሽ ሚሊየን በላይ የትግራይ ወጣቶች ፣ ቁጥሩ ባልተናነሰ መጠን በአማራና በአፋር ወጣቶች ረግፈዋል ፣ ሽማግሌዎች ፣ ሴቶች ፣ ህፃናት ወዘተ ተደፍረዋል ፣ ተፈናቅለዋል።
የተሰውት ኢትዮጵያዊያን ዐፅም በዱር በገደሉ ሳይሰበሰብ ፣ የተፈናቀሉት ሕዝቦች “የመጠለያ ፣ የምግብ ፣ የአልባሳት ፣ የመድሃኒት ወዘተ ያለህ” እያሉ እንዲሁም የቆሰሉት ጥምር የሰራዊቱ አባላት በመከረኞቹ ወላጆቻቸው እጅ ላይ ወድቀውና አልጋ ላይ ተጋድመው ቁስላቸው እያመረቀዘ “ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብን አግባብ ያለው ሕክምናና ድጋፍ እንዲደርግላቸው እሪታቸውን እያቀልጡት ባለበት ወቅት” እፍረት ቢሱ ከርሳም ፣ አነፍናፊው ውሻና አልጥግብ ባዮቹ አንዳንድ የዲያስፖራ አሸክቶች አሸሸ ገዳሜ ሊሉና ከርሳቸውን ሊሞሉ አዲስ አበባ ላይ እየከተሙ እንደሆነ እየሰማን ነው ፣ ይህ የወረደ ክሳቴ ያንገበግባል፣ያበሳጫል ፣ ይቀፋል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጃርት ጉባኤ ርደት (ሥርጉተ ሥላሴ ሲዊዘርላንድ -ዙሪክ)

ዘፋኙ “ዋይ ዋይ ሲሉ የርሃብን ጉንፋን ሲስሉ” ና “ ሃገሬ ቅጥ እጣሽ ፣ የሚበላሽ እንጂ የሚያነሳሽ አጣሽ” ብለው እየተቀኙ የዘመነኞችን የቁልቁለትና የመንሸራተት ዘመን እያመላከቱን ይገኛሉ ። ነገር ግን ቅኔውን “ጀሮ ዳባ ብለው” እነ “ጉድ አይፈሬ” ያሻቸውን እያደረጉ ነው። ይህን ሁሉ የሃገር ጩህት ፣ ፈተናና እሮሮ ችል ብላችሁ የማይጠረቃውን ከርሳችሁን ለመሙላት ሽር ጉድ የምትሉት ሁሉ የበላችሁበት አፋችሁ ደም ፣ ደም ደም ይሸታል ፣ ቢራና ዊስኪ ያቆረቆራችሁበት ጉሮሮ ያቅረዋል ፣ የተኛችሁበት አልጋ ይኮሰኩሳችኋል ፣ የረገጣችሁ መሬት እረመጥ ሁኖ ይፈጃችዋል ፣ በግፍ የተመራችሁት መሬትና የወሳዳችሁት ቤት የምድር ሲሆል ሁኖ እንደሚያቃዣችሁ አትጠራጠሩ። እናንተ ህሊና ባይኖራችሁም ኢትዮጵያ እንደናንተ ያለውን ጅቦችና የሰይጣን ቁራጮች በመንፈስ ኃይሏ ማንቆራጠጡንና እረፍት መንሳቱን ታውቅበታለች ፣

የሚገርመውና የሚከነክነው ነገር ደሞ ለጥምር ጦሩ ፣ ለመከላከያ ሰራዊቱ ፣ ለአባይ ግድብ ፣ ለተፈናቀሉት ወ.ዘ.ተ. ተብሎ የተሰበሰበውን ገንዘብ ተካፍለው ኪሳቸውን ማሳበጣቸው አንሶ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስና መፈክር የተሰበሰበውን ድጋፍ በብሄር ፅንፍ የተተበተበን መንጋ ባለሥልጣን ለማስደሰት በሚል የዞረ ድምር የኦሮሚያ ዲያስፖራ፣ የደቡብ ዲያስፖራ ፣ የአማራ ዲያስፖራ ፣ የሱማሌ ዲያስፖራ ማህበር ወ.ዘ.ተ. በሚል ያረጀ ያፈጀ ስያሜ “ላም በሌለባት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ያልነበረን ክስተት በልብ ወለድ ህሳቤ “ከላይ የተዘረዘሩት አወቃቀሮች ባልተሳተፉበት መድረክ ድጋፉን ያከናወኑትና ገንዘቡን ያሰባሰቡት እነዚህ ስብስቦች ናቸው “ ብሎ መለፈፍና የጥሪ ማስታወቂያ ማሰራጨቱ እንድም የኢትዮጵያዊነትን እድምታ ለማቀጨጭ ፣ የትውልደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያንን አስተዋፅኦ አፈርድሜ ለማብላትና ለማኮሰስ የተደረገ ዐይን ያወጣ ክህደት ነው እንላለን። የኢትዮጵያ አምላክ ይፋረዳችሁ ከማለት ባሻገር ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለኢትዮጵያ ፣ ለኢትዮጵያዊያንና ለውጭ ነዋሪው ሁሉ የማይበጅ ህሳቤ መሆኑን አስረግጠን እነግራችዋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአብይ አህመድ ውሸቶች (2018-2020) ክፈል 1 - ሊባኖስ ዮሃንስ

ዘርፈህ ፣ አዘርፈህ ተሸላልመህ ወደ መኖሪያ ጉሮኖህ ስትመለስ ዐይኑን አጉሮጥርጦ የሚጠብቅህ ፣ ለእምየ ኢትዮጵያ ስል ያዋጣሁትን ገንዘብ አወራርድልኝ ፣ የተሰበሰበው ጣራ የነካ ገንዘብ ለምን ጠቀሞታ አዋልከው? እያለ እና ማስረጃ እሳየኝ ብሎ የሚጠይቅ ፣ ጉሩቦህን ይዞ የሚያፋጥህ ቆራጥ የሃገር ተቆርቋሪ ወገን እንዳለ እወቁ እንላችኋለን ፣ እነ አይጠረቄ።

ከዚያም አልፎ በሕግም ሆነ በሚቻለው መንገድ ሁሉ “ለእምየ ሃገሬ ያበረከቱክትን ገንዘብ ትፏት” የሚል ክንደ ብርቱና ኩሩ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ብዕሩን አሹሎ ፣ ልሳኑን ስሎና እጣ ቱን ቀስሮ የሚጠብቃችሁ ለሃገሩ ታማኝ የሆነ ዲያስፖራ እንዳለ ልትረዱ ይገባል እንላለን።

እነ የዲያስፖራ የድል እጥቢያ አርበኞች እና የጥቅም አነፍናፊ ውሾች እስኪ እንገራችሁ “ታች አምና ህወሃት- ወያኔ ሽዋ እሮቢትን አልፎ ደብረሲና ሲደርስ ብርክ ብርክ እንዳላችሁ እናውቃለን ፣ ታዝበናችኋል ። በአምላክ ተራዳይነት ፣ በመላ ኢትዮጵያዊያን ፣ በመከላከያ ፣ በፋኖና በልዮ ኃይል ቆራጥ ተጋድሎ ወደ ተንቤን በርሃ ህውሃት ተመልሶ ሲወረወር እንደ ”እሽኮኮ” ከተደበቃችሁበት አልጋ ስር ቀና ብላችሁ ጎረራችሁ “ ለማያውቃችው ታወቁ እኛ ማንነታችሁን በደንብ እናውቀዋለን “ ፈሪዎች ፣ ጊዜ አይታችሁ የምትክዱ፣ እና ወሮ በላዎች መሆናችሁን የታሪክ ዶሴያችሁ ይናገራል።

“ግም ለግም አብረህ አዝግም እንዲሉ “ ዐይናችሁን በጨው አጥባችሁ” የቀቢፀ ተስፋ ተሸላሚ ለመሆን ውር ውር ማለታችሁ ባያስደንቀንም ፣ የደም ግብር ልትበሉ ወደ አዱ ገነት እየዘለቃችሁ መሆኑን ተረዱት። መጥኔ ለእናንተ “ ጦር ሜዳ ሳይውሉ ቀኝ እዝማችነት ፣ ዘርፎና አዘርፎ ተሸላሚነት “ በገቢር አንድ ናቸውና መውጫችሁን እንጃ የዘመኑ ባንዳዎች ፣ መጭው ትውልድ በህይወታችሁ ዘመን ሁሉ ጥላሸት እየቀባችሁ ይኖራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራው መከራ ላገሩ ስለሠራ (በዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ)

“የሌባ ዐይነ ደረቅ ፣ መልሶ ልብ አድርቅ “ እንዲሉ መላ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሃገረ ኢትዮጵያ መለወጥ ፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉትና ለአባይ ግድብ ወዘተ ያዋጣነውን ገንዘብ አወራርዱ ፣ ነገ ሲረሳሳ እንቦጭቀዋለን ብላችሁ በማይታወቅ የሂሳብ አካውንት ያጎራችሁትን ገንዘብ ካለበት ፈልፍላችሁ አውጥታችሁ ለታሰበለት ዓላማ አውሉ፣ በአስቸኳይ ለሚመለከተው አካል አስተላልፉና አሳውቁ እንላለን ፣ ካልሆነ “ ምን እንደነካ እንጨት” ስማችሁ እንደገማ ይኖራል እንዲሁም ጊዜ ሲመጣ እፍንጫችሁን ተይዛችሁ የሚያስተፋችሁ የሚሞግት ሳተና የሆነ ትውልድ እንዳለ እወቁ ብለን እንመክራለን።

እነ እሳማ የዲያስፖራ ጉዶች በተሻለ ሃገራት ፣ ስርቶ በሚኖርበት የምዕራቡ ዓለም ፣ ስርቆት ፅዮፍ በሆነበትና በህግ ሁሉ ነገር በሚሳለጥበት ሥልጡን ምድር እየኖራችሁ ፣ በኢትዮጵያ ያሉ በአንዳንድ ሹማምንቶች ልፍስፍነትና ግዴየለሽነት “ሳታጣ ያጣችውን” ሃገረ ኢትዮጵያን መዝረፍና ማዘረፍ እርጉምነት ነው እንላችኋለን።

በሰውና በብሃድ ሃገር አብሮ የሚኖረውን ወንድምህንና እህቶችህን ችላ ብለህና በድለህ ነገ አራት ዓመት ሲሞላው ትቶህ እብስ የሚለውን ፣ ሳይገባው በብሄር ተዋፅኦ በሚል እጓጉል ህሳቤ ስልጣን ላይ የተሰየመን አንዳንድ ግትልትል ባለስልጣን ፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን ተማምናችሁ መበደሉ ፣ መዝረፉ ፣ ማዘረፉና መካድ ለጊዜው ቢያናጥጣችሁም ነገ ግን መግቢያ መውጫ ታጣላችሁ፣ ከማህረሰቡ ትገለላላችሁ ፣ እንቅልፍ ይነሳችሏል እና ህዝብ አንቅሮ ይተፋችኋል እንላለን ።

አረፈደምና እወቁበት ፣ ንፁህ ኢትዮጵያዊነት ፣ ታማኝነትና ፣ ሁሉን የኔ ከማለት የኛ የሚል የጋራ ሃገራዊ ህሳቤን አንግባችሀ በንፅህና ተጓዙ ብለን እንመክራለን ።

ተዘራ አሰጉ።
ከምድረ እንግሊዝ።

2 Comments

 1. ጉሮ ወሸባ ጉሮ ወሸባ ደያስፓራ መሬት ዘርፎ ሲገባ ነው አዲሱ ቅላጼ። ይህ በድጋፍ ሜዳ ለወደቁበት የዜጋን መጨፍጨፍ አላየሁም አልሰማሁም ብለው አገርን ለካዱበት የተሰጣቸው ሽልማት ነው። የሚሰሩት ስራ ወንጀል እንደሆነ ስለሚያውቁ ይሸሹሀል ያ ማለት አንተ የሞራል ልቀት ላይ ነህ ማለት ነው። እኛ ኢትዮጵያ ላይ ስለደረሰው በደል ለአለም ስናሳውቅ እነሱ ያላግጡብናል አንድም የተቃውሞ ሰልፍ ያልወጡ ያልተቃወሙ ሶስት ጊዜ መሬት የወሰዱ እናውቃለን። አንድ ሰው እንዴት የመለሰ ዘራዊን፣የሀይለ ማርያም ደሳለኝን የአብይ መሀመድን ቲ ሸርት በተከታታይ ይለብሳል? ፎቶውንስ ሲመለከቱት ምን ይሰማቸዋል? አንተ ትሸማቀቅ እንደሁ እንጅ እነሱ አይሰማቸውም። የዝሆን ቆዳና የጉማሬ ሆድ ሰጥቷቸዋል።

 2. Well said , ወንድማለም። ሁሉንም አምላክ ከላይ ያያል።
  የበሉት አሲድ ነው
  የጠጡት ሀሞት፣
  ፍርዱ አይዘገይም
  የላይኛው ቤት፣
  ደም እየጎረፈ
  ስደት እየናረ፣
  ፌሽታና ድለቃ
  ፌዝና ኋካታ፣
  ብድሩ ይህ ሆነ
  ሜዳ ላይ ለቀረ፣
  ለዛ ለሃገር ካስማ
  ለወገን መከታ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.