የጠላቶቻችን ሤራ ማክሸፍ የምንችለው፣ ሰው መሆናችንን ተገንዝበን ፣ በአንድነት “ እኛ ሰው ነን ። “ በማለት ሥንቆም ብቻ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የመንግስተ ሰማይ መግቢያ ቁልፍ ተሰጥቶኛል የሚሉ አንድአንድ ፣ የፕሮቴስታንት ሰባኪያን የዓለማዊ ጥቅም ማጋበሻ ሥራ ላይ መጣዳቸው ግልፅ እየሆነ መጥቷል ። ለድሎትና ለምቾት ሲሉ ብቻ  ህቡ በሆነ አገር አፍራሽ  ሤራ ውሥጥ ተጥደው እየተንተከተኩ ነው ። የተቀናጀ  ሤጣናዊ የመከፋፈል  ድርጊት ፤ አገርን ለማፍረስ የተወጠነ ሤራ በቸርቻቸው  ውስጥ ይማሰላል ። “ እመብርሃን አውጪኝ ! “ ማለት ይኽን ጊዜ ነው ።    በየዋሁ እና ወንጌልን አንብቦ በማይረዳው ህዝብ ጢባጢቤ በመጫወት አደንዝዞ የነጭ ባርያ ማድረግ የፕሮቴስንታቱ “ሚሺን እና ጎል “  መሆኑንን የተረዳ ሁሉ ከሐዋርያት ተግባር በእጅጉ ከራቁት ፓስተሮች አርባ ሺ ኪሎሜትር ይርቃል ።

በኢትዮጵያም     ሠርቶ ከመበልፀግ ይልቅ ከሰማይ መና ይወርድልሃል ጠብቅ እያሉ ህዝብ ያለሥራ  አንጋጦ መና ከሰማይ ሲወርድ ለመቅለብ እንዲዘጋጅ ብቻ የሚሰብኩ ጋሃነም የመጨረሻ ቤታቸው የሆነ አያሌ ሰባኪያን አሉ ።

ነገ ሚሊዮን ብሮች በአካውንትህ ይገባል  ! መጪው ጊዜ ያንተ ብልፅግና ነው ! ሰበርኩት ! ወጋሁት በጅዶ ሤጣንን አንከባለልኩት ! “ሊባረባራጨራፎራካራዳራኦራ ! “ በልሣን መናገር ይሉሃል ። ድርቅ ያለ ፈጣጣ ግራ የተጋባ   አስተምህሮ ማአት ዕብድ ሰባኪያን በአገሪቱ  ከተማና ገጠሩን ሲያውኩ እያስተዋልን ነው  ።

ምድረ ሰባኪ ፣ ሐዋርያ ና ፖስተር ተብዬ እንዲደላቀቅ  85 % የኢትዮጵያ ህዝብ በችጋር እንዲገረፍ “ የጌታ ፈቃድ ሆኗል  ። “ ይልሃል ። ይኼ ቱልቱላ !  ፈጣሪ ሰውን እያበላለጠ እንደማይወድ የማናቅ ይመስለዋል ። “ ሐሰትን ይናገር ዘንድ ጌታ ሰው አይደለም ። “

የዛሬን የኢትዮጵያዊውን ሰው  ችግር የፈጠረው የዓለም የሥግብግብ ሥርዓት ነው ። ሰው ሥግብግብ በመሆኑ ነው ኒኩሌር ቦንብ ጭምር በመስራት እርስ በእርሱ በአይነ ቁራኛ እየተያየ የሚኖረው  ። በፈጣሪ ህግ ፣ ደንብና መመሪያ ሰው ቢኖር ኖሮ እኮ ! ድህነት በዓለም ባልኖረ ነበር ። ምድረ ሥግብግብ ኃያል በሆኑት አገራት ፣  በአውሮፖና በአሜሪካ እየኖረ አፍሪካን በመዝረፍ ህዝቧን ያሥርባል ፣ ያሳርዛል እንጂ ፈጣሪ ማንም ሰው እንዲራብና እንዲታረዝ አይፈቅድም ።

የነጮቹ የባዶ ሥብከት አስተምሮም ከአዛኝ ቅቤ አንጓች የዘለለ አይደለም።  በበኩሌ የማሞኘት ፣ አይናችሁን ጨፍኑ እና እንስረቅ ባይነት ላይ የተመሠረተ ነው ። በየሚዲያ ስብከቶቻቸው ይኽው ድራማ ነው የሚሥተዋለው ።

በአገራችንም  አገርን ለማፍረስ ወይም ” ኢትዮጵያ ” የተባለውን የአፍሪካዊያን ኩራት የሆነውን ሥም ለማጥፋት አሊያም ተሸናፊ በማድረግ የጥቁርን ህዝብ አንገት ለመስበር  ሌት ተቀን በገጠርና በከተማ የሚያላዝኑ ሰዎችና የተለያዩ ግለሰቦች የሚዘውሮቸው ማደንቆሪያ ቸርቿች ተፈጥረዋል ። ።

እነዚህ ህዝብን ከሥራ ይልቅ ጩኸት የሚያሥተምሩ ። ፈጣሪን አሳንሰው በማየት ፤ በጩኸት እና በኡኡታ !ብዛት ፣ ይሰማናል ብለው የሚያሥቡ ፣ በትያትረኝነት ደግሞ ፤ ለምፃሙን ፈወስን ፤  እውርን አበራን ፤ ሙታንን አስነሳን ፤ በማለት አሥቂኝ ድራማ በየመድረካቸው የሚያሳዩ  ደረቆች ሆነው እናገኛቸዋለን ።

ይኽንን ስንመለከት ፣ “ እንዴት   ሰው የፈጣሪ ፍጥረት ሆኖ ሣለ  ፣ የፈጣሪውን ሁሉን አዋቂነት ፣ ተመልካችነት ፣ ቻይነት ፣ አድራጊና ፈጣሪነት ዘንግቶ ፣ የፈጣሪን ሚና እጫወታለሁ ?  አንዳችም አይሳነኝም ይላል  ? “

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹በዓሉ ግርማ በባህርዳር ››‎ - ሊያነቡት የሚገባ

ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እና የነበረ ነው ። ቤተክርስቲያንም የተመሠረተችው በክርስቶስ ላይ ነው ። የሁላችንም ነፍስ የምትገኘው በመዳፉ ውስጥ ነው ። እኛ ፍጡር ነን ። የእግዚአብሔር ሸክላ ነን ። ፃድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እኛ ገና በእምነት ና በሥራችን ተመዝነን  ነው ፣ በእርሱ  ለመፅደቅ የምንችለው ።  ትልቁ ወደ ፅድቅ አድራሽ መንገድ ደሞ ወንድማችንን እንደራሳችን መውደድ ነው ። ግን ይኽንን ማድረግ ብዙዎቻችን አልቻልንም ። በተለይም ወጣቱ በለከት አልባው “የፕሮቴስታንቶች መዝሙር ተብዬ ጭፈራ በመማረክ ፍላሎቱን መቆጣጠር አቅቶት   ፤ ገና ወተት እየተጋተ ሣለ ፣ አጥንት ቆርጥሜያለሁ ። ቆሜም መሄድ ጀምሬያለሁ ይለናል ።

ወጣቶች የፓስተሮችን ሴራ እንደ ራዕይ በመቁጠር  ፣ “ራዕያቸው  ሁሉ የፈጣሪ ነው ። “ ብለው በማመን  ለኢየሱስ ክርስቶስ  ወንጌል እውነት ጥብቅና እንደመቆም   ለሐሰተኛ ራእያቸው በማድላት    ለፓስተሮቻቸው ይሟገታሉ ። በበኩሌ ብዙዎቹ ፓስተሮች ሲዖል እንጂ መንግስተ ሰማይ ይገባሉ ብዬ አላስብም ።ህዝብን በድህነት እንዲኖር እያደረጉ ፣ እነሱ እጅግ ከተንቀባረሩ እንዴት አድርገው መንግሥተ ሰማይን ይወርሳሉ?  እንዴት  ፣ አጭበርባሪዎች ፣ ሠራቂዎች ፣ በሐሰት ማዮች ፣ ወንድሞቻቸውን እንደራሳቸው የማይወዱ ። ወዘተ ። ለመንግሥተ ሰማይ ይበቃሉ ?

ክርስቲያኖች ሁሉ በመፀሐፍ ቅዱስ እንደሚመሩ እያወቁ ፣  ፈጣሪያችንን  አቅመ ቢስ አድርገው ፣  እነሱ ሁሉን ቻይ እንደሆኑ በድራማዊ ድርጊት በማሳየት ይህንን ከዕውቀት ያ ተገናኘ  ህዝብ እያሳቱ  “ መንግሥተ ሰማይ የእኔ ናት ማለት ። “  የዋህነት ነው ።

ፈጣሪያችን መድኃኒዓለም በእኛ በሸክለዎቹ ሰዎች የሚመረመር ከቶም  አይደለም ። ለእኛ በጎ ስላደረገልን ሌሎች በጎዳና ላይ ለተሰጡ እልፎች ፣ “ የቡሆ ዕቃቸው “ ባዶ ለሆነ ሚሊዮኖች ፣ በፈጠራት ምድር በሆዳም ፖለቲካኞች ሤራ እየታረዱ ፣ እየተፈጨፉ ላሉት ፍጡሮቹ አይገደውም ብለን ካሰብን ግብዞች ነን ። ከእኛ ከተሟላልን ይልቅ ፈጣሪ ለእነዚህ ዛሬ ለሚያለቅሱ ፣ ለሚያዝኑ፣ለሚራቡ ና ለሚጠሙ ወዘተ  በእጅጉ ያዝናል ።

ዓለም ለሥጋ ያደላች ናት ። የደላው ፣ የተመቸው ፣ የተትረፈረፈው የበለፀገው አገር   ሰው  ፣ ምቾቱና ድሎቱ ሰይጎድል እንዲቀጥል ስለሚያደርገው ስለተጨማሪ ትርፍ እንጂ ፣  ለሚራቡ ፣ ስለታረዙና መጠለያ አልባ ለሆኑ የአፍሪካ ሰዎች ደንታ የለውም ።

የኀጉሪቱ ቱጃሮች ጭምር ለዚህ ለምንዱባን ህዝብ ፈፅሞ ደንታ የላቸውም ። ከመሠርቅ ። ከመዝረፍ የደሃ አገራትን ሀብትና ንብረት አሜሪካና አውሮፓ ውሥጥ ከማካበት  የዘለለ ራዕይ የላቸውም ።

አብዛኛው አፍሪካ በማአድን የበለፀገች ብትሆንም ሀብቷ የድህነቷ ምክንያት ሆኗል ። ብልጡ ፈረንጅ ዜጎቿን ዕውቀት ዓልባ እንዲሆኑ በማድረግ ፣ በድህነት ለሚኖረው ለአንዱ  ሣ ፣ ምግብ ፣ ልብስና የሚተራረድበት መሣሪያ ያቀርባል ። አገሬው  ምድሪቱን  ያለዕውቀት እና ጥበብ  ምንም ሊጠቀምባት ያለመቻሉን እያወቀ ፣ ” ይሄ የአንተ ጎሣ ግዛት  ነው  ፤ ያ የእርሱ ግዛት አይደለም ፣ ለምን ይወስድብሃል ? ” በማለት የአንድ አገር ዜጋ ፣ ፈጣሪ በፈጠራት ምድር ፣ “ ያለገንዘቡ “ በከንቱ እንዲገዳደል   በማድረግ ብዝበዛውን እያደላደለ ነው ። ይኽ አይነቱን ኢ ሰብዓዊነት ሳስተውል  ” ሰው  እንዴት  የአምሳያውን መራብ ፣ መጓሣቆል ፣ በድህነት መቆራመድ ፤ ወዘተ    አይሰቅቀውም ? ” ብዬ እጠይቅና መልሼ ” የአፍሪካን ህዝብ የነጩ ዓለም ከቶ ከሰው ይቆጥረዋልን ? ” በማለት በጥያቄ ጥያቄውን እመልሳለሁ ። …

ተጨማሪ ያንብቡ:  (የሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ) ሁሉም ለበጎ ነው

በነጩ ዓለም ውስጥ ያሉ ጥቂት የኢኮኖሚ የፖለቲካ  የበላይነት ያላቸው ሰዎች ፣ በገዢዎቻቸው በኩል የአፍሪካን ወተት እያለቡ ከመጠጣት ውጪ አህጉሪቱን የማልማት ፤ ህዝቦቿን ከድንቁርና እና ከችጋር የማላቀቅ ቅንጣት ሃሳብ እንደሌላቸው ቢታወቅም ፣ የአፍሪካ ምሁራን ዛሬ የነቁ በመሆኑ ፣  ከገዢዎች የአውቅልሃለሁ ሥብከት ህዝቡን ለማላቀቅና አህጉሪቱን እንደ አውሮፓ ለማበልፀግ  ፣ ፍትህ ፣ ዴሞክራሲ ፣ የዜጎች ሰው የመሆን ነፃነት በአፍሪካ ይንገሥ ዘንድ ሠላማዊ ትግሉ እንዲፋፋም ጥረት እያደረጉ ነው ።  በበኩሌ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ምጡቅ አእምሮ ያላቸው ፖለቲከኞች ፣ ኢኮኖሚስቶች ፣ የማህበራዊ ዘርፍ ባለሙያዎች ፣ ኢጂነሮች ፣ ዶክተሮች ፣ የእርሻ ባለሙያዎች ፣ ወዘተ በብዛት እንዳሉ  አሳምሬ አውቃለሁ ። ይኑሩ እንጂ ሰው መሆናቸውን ብቻ ሥለሚያምኑ ፣ የዘር እና የቋንቋ ሥርዓቱን ሥለሚጠየፉ ፤ የቋንቋ አጥሩም  ሥለማያስጠጋቸው አገርን ለመጥቀም ቢፈልጉም እጅግ አዳጋች የሆነ ፈተና ተጋርጦባቸዋል ። …

” በአፍሪካ ሰው መሆኑን የተገነዘበ ዜጋ በበዛ ቁጥር ፣ በማንኛውም ሰከንድ፣ ኃላፊነቱን ፤ ሟችነቱን ሥለሚያውቅ ፣ ባለው አጭር እድሜ  ከመላው አፍሪካ ዜጋ ጋር ውህደት ፈጥሮ  ፣ ኑሮውን ለማጣፈጥ እዛም እዚህም እየሰራ እስከጊዜው ለመኖር   እንጂ ፤ ልክ ዘላዓለም ዓለም ፣ ነዋሪ እንደሆነ ራሱን በመቁጠር ፣ የሌላውን ህይወት ለመቀማት ጠብመንጃ በማንሳት ፣  ዘመኑንን በመገዳደል አይጨርስም ። እናም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገራት ውሥጥ ሰው መሆኑንን የተገነዘበ መንግሥታዊ ሥርዓት መቋቋም ይኖርበታል ። ” በማለትም ምክራቸውን ይለግሳሉ ።

ዛሬ ምዕመኖቿ ፣ እግዛብሔርን ፈሪና አክባሪ በሆኑ  በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ  ታላቅ ሸፍጥ የተሠራውም ሰውን ከማያስቀድም እና እኔ ቋንቋ ነኝ ። ከሚል አጥራዊ ሥርዓት የተነሳ ነው ።

በዙ ጊዜ እንደፃፍኩት ፤ ኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለችው በመከላከያና በፊደራል ፖሊሥ ውሥጥ ብቻ ነው ።  በትርክት ደረጃ በየቴሌቪዢኑ መኖሯ ይታወቃል።  በተረፈ ቋንቋና ጎሣ ነው ፤ በየክልሉ የሚዘመረው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገንዳው - በእውቀቱ ሥዩም (አሜሪካ እንደመጣ የፃፈው)

አዳም ና ሄዋን የሰው ዘር መገኛ መሆናቸውን በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑ  ዜጎች  ሁሉ ከልባቸው ቢያምኑም በዓለም የሌለው የእኛ የመለሥ ዜናዊ ሥርዓት “ ሰው ቋንቋ ነው።   “ ብሎ “ አንተ ሰው አይደለህም ፤ እንትን ነህ ።እንትን ነህ  ። “ በማለት ሰውነቱን እንዲረሳ በጠብመንጃ አሥገድዶታል ። አንዳንዱንም በእርዳታ ሥንዴ ።

እንሆ ዛሬ    በሰው   መካከል መከፋፈልን የፈጠረው የመለሥ ዜናዊ ቋንቋ ተኮር ሥርዓት ነው ።  ፈጣሪያችን በማይገደው ቋንቋ ፣ ነገድ ና ዘር ተደረጅተው “ የኦሮሞ ቤተክህነት “ በማለት ከመድኃኒታችን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ያፈነገጠ የዲያቢሎስ ሃሳብን ለማራመድ እና ቤተ ክርስቲያኗን “ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፣ የአንድ ለአምሥት መገለጫ “ በማድረግ  ምዕመናንን በቋንቋ እንዲከፋፈሉ  ለማድረግ ፣ ህገ ቤተክርስቲያንን ጥሰው ፣ በራሳቸው ላይ የጵጵስና ቆብ የደፉት በዚህ ሰው መሆንን በካደ የቋንቋ ሥርዓት የተነሳ ነው  ።

ብዙዎች እንዳሉት  ” እነዚህ የእግዛብሔርን ሥልጣን በጉልበት የቀሙ ናቸው ። ”     እናም   ከእግዜር ጋር የተጣላ ከአማኙ  ህዝብ ጋር የተጣላ መሆኑ የታወቀ ነውና ፣ ማንም አማኝ እነሱ ባሉበት ሥፍራ ሁሉ አይገኝም ። መሥቀላቸውንም አይሳለምም ። ምክንያቱም በአንድ እግዚአብሔር ላይ እና በፍጥረቱ ሰው ላይ መከፋፈልን ፈጥረዋልና !

በነዚህ የኃይማኖት አባቶች ክህደት የተነሳ፣ የፈጣሪ ቅጣት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በራፍ ላይ ነው ። ከቅጣቱ በፊት ግን ፣ ለሁላችንም ከሐጢያት  ፣ ከዕብሪት ና ከግብዝነት  የመመለሻ ፣ የንሥሐ ጊዜ ሰጥቶናል ። በዚህ ርህራሄው የምናሾፍ ካለን ፍፃሜያችን ጥርስ ማፏጨት ይሆናል ።

” በፈጠርኳቸው በየዋሃን ሰዎች ፣ ሥሜን በሐሰት እያነሳችሁ ፣ ሐዋርያት ነን …እያላችሁ ። ለራሳችሁ ሥም በመስጠት   አትቀልዱ ። ይላል ። ” የሠራዊት ጌታ ፣ ሁሉን ቻዩ እግዛብሔር ።

በበኩሌ ከገዢዎች ቁጣ ፣ ይልቅ የፈጣሪዬን የመድሃኒዓለምን ቁጣ በእጅጉ እፈራለሁ ። … ለሐጢያን የመጣ ለፃድቃንም ይተርፋልና !

ለማሳረጊያ ከመፅሐፍ ቅዱስ መመርያ የሚሆነን እንካችሁ በማለት ፅሑፊን እቋጫለሁ ።

ሉቃስ 9

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

¹ አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤

² የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥

³ እንዲህም አላቸው፦ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ።

⁴ በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ።

⁵ ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ።

⁶ ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።

 

 

ዕብራውያን 3

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

( ምዕመናንም ይህንን እንመልከት ። )

 

¹ ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤

² ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ።

³ ቤትን የሚያዘጋጀው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው መጠን፥ እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሮአልና።

⁴ እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፥ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው።

⁵ ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፤

⁶ እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።

⁷ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፦

⁸-⁹ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ።

¹⁰ ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ፦ ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤

¹¹ እንዲሁ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ።

¹² ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤

¹³ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤

¹⁴ የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤

¹⁵ እየተባለ፦ ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ።

¹⁶ ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን?

¹⁷ አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን?

¹⁸ ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ?

¹⁹ ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.