ያፈጠጠብን ችግር – አንዱ ዓለም ተፈራ

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሀቅ እንድ መልዕክት አለው። ዛሬ እዚህ ቦታና በዚህ መንገድ፣ ነገ እዚያ ቦታና በሌላ መንገድ እያለ፤ የተለያዩና ያልተያያዙ የሚመስሉ ቀውሶች በፖለቲካው መድረክ ተስፋፍተዋል። እኒህ ኩነቶች አንድነት ያላቸውና የዚህ መልዕክት አካል ናቸው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም! የመንግሥት ዋናው ኃላፊነት፤ ሰላምን ማስፈን፣ ሕዝብን አንድ ማድረግና በማንነቱ እንዲተማመንና እንዲኮራ ማድረግ፣ ልማትን ባገር መገንባት፣ የመሳሰሉት ናቸው። አሁን በአገራችን ያለው ሀቅ፤ በየቦታው በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ተጧጥፈዋል፣ ክልሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያለያዩዋቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር፤ የበላይነትን ለማግኘት የሚችሉትንና ያመቻቸውን ሁሉ ማድረግ፣ በመረዳዳትና ሁሉን ሊጠቅም በሚችለው መንገድ ከመጓዝ ይልቅ፤ “ሌሎችን በመጉዳት፤ ራስን መጥቀም!” ወይንም በሌሎች ላይ በመወጣጣት የራስን የበላይነት ለመጫን ሩጫ ነው። የየክልሎች መሪዎች በአብዛኛው የግል ጥቅማቸውን እንጂ፤ የሚወክሉትን ሕዝብ ጥቅም ቦታ አልሠጡትም።

መልዕክቱ፤ ተጠልቶ የተባረረው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ከመሪዎቹ መወገድ በስተቀር፤ ስርዓቱ እንዳለ ስለተቀመጠ፤ ችግሮች ተባብሰዋል ነው።  ይህ ማለት፤ የመሪዎቹ መለወጥ እንጂ፤ የስርዓቱ መቀጠል የተረጋገጠ መሆኑ ነው። ያለፉት መሪዎች የተጠሉትና የተባረሩት ትግሬዎች ሰለሆኑ አልነበረም። ሕዝቡ ተነሳስቶ ያባረራቸው፤ “ትግሬዎች መጥፎዎች ናቸው!” ብሎ አልነበረም። “ትግሬዎች ከሚገዙኝ ሌሎች ይግዙኝ!” ብሎ አልነበረም። ሕዝቡ ያለው፤ “ከፋፋይ፤ በቋንቋና በትውልድ የተመሠረተው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ፖለቲካ፤ ኢትዮጵያዊ አይደለም!” “አትከፋፍሉን!” “እኛ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሕዝብ ነን!” ብሎ ነበር።

አሁን ያለው መንግሥት፤ ያለፈው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተቀጥላ ብቻ ሳይሆን፤ ራሱን ችሎ እሱን የተካ አካል ነው። እናም የተወገደው ፖለቲካ ጠበቃና አቀንቃኝ ነው። ያገራችን ችግር፣ እየጎደሩ ያሉት ግጭቶችና የማያባራ ሰላም የማጣት ጉዳይ፤ ከዚህ ይመነጫል። ለዚህ መፍትሔ ከመሻታችን በፊት፤ ይሄንን አጥብቆ መረዳት ግድ ይላል። ከዚህ በኋላ ነው ማፍትሔ ማቅረብ የሚቻለው። ላስምርበትና፤ አሁን ላለው ያገራችን የፖለቲካ ችግር መንስዔው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች ቢወገዱም፤ የፖለቲካ እምነታቸው፣ የአስተዳደር ስልታቸው፣ መንግሥታዊ መዋቅሩ፣ መከፋፈሉና መፎካከሩ፤ እናም ባጠቃላይ የዚህ ሁሉ ማሳረጊያው፤ በቦታው ያስቀመጠው ሕገ-መንግሥት እንዳለ መቀመጡ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢህአዴግ የዝምታ ፍራቻ (Sedatephobia) እና ስርወ-ምክንያቱ

ባገራችን በዚህ መቀጠል ተጠቃሚ የሆነ አካል በሥልጣን ላይ አለ። ይሄ አካል፤ ያለው ስርዓት መቀጠሉን እንጂ መፍረሱን አይፈልግም። ስለዚህም፤ ባገራችን ያለው የፖለቲካ ችግር፤ እየተባባሰ ይሄዳል እንጂ አይሻሻልም። የሚያሳዝነው ነገር፤ የመንግሥቱን ሥልጣን የጨበጠው አካል፤ የነበረው ስርዓት ቢወገድና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነቱ ተመልሶ ኢትዮጵያዊ ቢሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ይሄን የሚያጽድቅ ሆኖ ባገር ሰላም ቢሰፍን፣ የበለጠ ተጠቃሚ መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። ነገር ግን፤ ይህ አካል፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ፓለቲካ የተፈጠረና አማኝ ስለሆነ፤ ከያዘው መንገድ በምንም ተዓምር አይወጣም። መፍትሔ የሚባል ነገር ለዚህ አካል አይቀርብም። መደረግ ያለበት፤ ሕዝቡ ራሱ፤ ወደራሱ እንዲመለከት መንገድ መቀየስ ነው። አማራው ለምኖ የባህር ዳሩን መንግሥት አማራ አይደርገውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አቤቱታ በማቅረብ የፌዴራሉን መንግሥት ኢትዮጵያዊ አይደርገውም። በክልል ተጎድጉደን ኢትዮጵያዊነትን አናራምድም።

በትክክል መፍትሔ ተገኝቶ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንድንጓዝ፤ ፓርቲ መመሥረት፣ ጠመንጃ ማንገት፣ “እነሱ እንዲህ አደረጉና እኛም እንዲህ እናድርግ!” የሚለው መንገድ አያዋጣም። የነገዋ ኢትዮጵያ መገንባት ያለባት፤ በያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ነው። እኒህ ኢትዮጵያዊያን ተገናኝተን፣ ቁጥራችን አይሎ ሲገኝ፤ ከፊታችን የሚቆም ምንም ኃይል አይኖርም። መነሻውና መድረሻው፤ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታችን አምነን መቆማችን ነው። አንድ የሚያደርገን፤ ሃይማኖታችን፣ የትውልድ ቦታችን፣ የምንናገረው ቋንቋ፣ በደም ቧንቧችን ውስጥ የሚፈሰው ደም መነሻ ምንጩ፣ ወይንም የሀብታችን ልክ አይደለም። እኒህ የየራሳችን ሆነው ይቀመጣሉ። ኢትዮጵያዊነታችን ግን፤ የጋራ ማንነታችን ነው። ያ ብቻ ነው፤ ርስ በርሳችን ለምናደርገው የፖለቲካ ግንኙነት መሠረቱ።

በርግጥ አሁን ያለው የትውልድና የቋንቋ ፖለቲካ አያፈናፍንም። እናም ያለው ምርጫ፤ ይሄ የፖለቲካ ስርዓት ራሱን የሚያመክንበትን መንገድ መዘየድ ነው። ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን፤ አገራችን የምትድንበት መንገድ ይሄ ብቻ ስለሆነ፤ ወደ መፈራረስ ከመንጎዳችን በፊት፤ ይሄን ማድረግ ግዴታችን ነው። አማራው ክፍተኛ የሆነ፤ ሕልውናውን ፈታኝ ሆኖ የሚያሰጋው ዘመቻ እየተካሄደበት ስለሆነ፤ ራሱን ማዳን አለበት። እንዴት ለሚለው፤ በውስጡ ውይይቶችን በማድረግ የሚዘይድበት ይሆናል። በኔ እምነት፤ የአማራው ዕጣ ከሌሎች አናሳ የትውልድና የቋንቋ ክልሎች ዕጣ ጋር የተሳሰረ ነው። አማራው ከኒህ ጋር ማበር አለበት። አማራው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በከለለለት መሬት የተወሰነ አይደለም። ኦሮሞውም፣ ሶማሌውም፣ አፋሩም፣ ሲዳማውም፣ ሁሉም በየተከለለላቸው መሬት የታጠሩ አይደሉም። የአዲስ አበባ ጉዳይ ከዚህ ጋር የተሳሰረ ነው። የየግጭቶቹ አንዱ ጉዳይ ይህ ነው። ለዚህ መፍትሔ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው። አማራው በየቦታው፤ በሌሎች ክልል መሪዎችና በጎን ባስታጠቋቸው ቡድኖች እየታደነና እየተገደለ ነው። እስላሞች በእምነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው የተነሳ፤ ከፍተኛ በደል ደርሶባቸዋል። የእስልምና ተከታዮች በአማሮች ውስጥ፣ በኦሮሞዎች ውስጥ፣ በጉራጌዎች፣ በሶማሌዎች፣ በአፋሮች፣ በያንዳንዱ ክልል ውስጥ አሉ። በእስልምና ተከታዮች የደረሰው በደል፤ በመላ ኢትዮጵያዊያን የደረሰ በደል ነው። የኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስትያን ተከታዮች በያንዳንዱ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። በነዚህ ላይ የደረሰው በደል፤ በኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ በደል ነው። በመሬት ይዞታ፣ በሃይማኖት ተከታይነት፣ በማንነት ላይ እየደረሰ ያለው በደል፤ የመላ ኢትዮጵያዊያን በደል ነው። ይሄንን መገንዘብ ያለብን እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን። በሥልጣን ላይ ያሉትና አሁን ተጠቃሚ የሆኑት፤ ያቀፉትን ስርዓት ይለውጣሉ ብሎ መጠበቅ፤ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው። እኔ ይሄን አድርጉ ብዬ መፍትሔ አልወረውርም። ውይይቱና ምክክሩ አስፈላጊ ነው። ያ ውይይት፤ ወደ መፍትሔ ይወስዳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከለውጡ በኋላስ? (ተመስገን ደሳለኝ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.