ኦነግ ኦነግ የሚሸተዉ ብልጽግና ሊጸዳ ይገባዋል – ይበቃል ያረጋል ረታ

መጋቢት 2 ቀን 2ሺ15 ዓ.ም.

ከአምስት ዓመት በፊት በጉጉት እና ተስፋ ታጅቦ የተጀመረዉ ለዉጥ፣ ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ፣ ይዘቱ እና አካሄዱ የበለጠ ግልጥ እየሆነ መጥቷል። በሂደቱም የተረዳነዉ፤ ከዘር ፖለቲካ ስሌት ሳይላቀቅ በጠቅላይ ሚንስትሩ ተወጥኖ የሚቀነቀነዉ መደመር የሚለዉ ጽንሰ ሃሳብ፣ በተጓዳኝ መቀነስን አዝሎ በመምጣቱ የተጠበቀዉን ያህል ዉጤት አላመጣም። ከዚህም የተነሳ፣ በመደመር ላይ የተመሰረተዉ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ራዕይ ተግባራዊነቱ ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ ሆኗል። ስለዚህም፤ የገዢዉ ፓርቲ አካል በሆኑት፣ በተለይም በኦሮሞ እና በአማራ ብልጽግና ፓርቲዎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ በግልጽ እየታየ የመጣ ከረር ያለ ቅራኔን ፈጥሯል። በሁለቱም ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እና እየተስጡ ያሉ መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት፣ ክስተቱ ሀገሪቱን ወደ ከፋ ደረጃ ሊወስዳት ይችል ይሆናል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

 

የዚህ ስጋት፣ መንሰዔዉን እና ምንነቱን ለመረዳት፣ ሁለቱ ፓርቲዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ገደማ በማከታተል ያወጧቸዉን ተጻራሪ መግለጫዎች ማየት እና ማጤን በቂ ግንዛቤ ይስጠናል። የሁለቱም መግለጫዎች ዋና ፍሬ ሃሳብ እና ማጠንጠኛ የፖለቲካ አቋም በጥቅሉ የሚከተሉት ሁለት የፖለቲካ ህሳቤዎች ናቸዉ፣

  • የገዢዉን ፓርቲ በበላይነት እየመራ ባለዉ በኦሮሞ ብልጽግና የሚቀነቀነዉ፣ ኦሮሟዊ ስነልቦና ያላት አዲስ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና ለመስራት የሚደረገዉ ጥረት እና ምኞት አንደኛዉ ሲሆን።
  • በተቃራኒዉ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ከብዙ ዘመናት በፊት የተሰራች፤ የነበረች እና ያለች ሆኖም ግን፤ መስተካከል የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን አስተካክሎ፣ የጎደላትም ካለ አሟልቶ እንድትቀጥል የሚመኘዉ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አቋም ነው።

ከዚህ በመነሳት የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አላማ፣ ከላይ የሰፈሩትን ሁለት ተጻራሪ የፖለቲካ አቋሞች መነሻቸዉ፣ መዳረሻቸዉ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖዎች ለመዳሰስ ይሞክራል። በተጨማሪም፣ ለተከስቱት ችግሮች መፍትሄ ቢሆን ይረዳል የምንለዉንም ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ነዉ።

 

የችግሩ መነሻ፤

እንደሚታወቀዉ ይህ የዛሬ አምስት ዓመት የተጀመረዉ ለዉጥ፣ እዉን እንዲሆን ከፍተኛዉን ሚና የተጫወተዉ “ኦሮማራ” በመባል የሚታወቀዉ በቀድሞዉ የኢህአዴግ አባል በነበሩት በኦህዴድ እና በብአዴን አባላት ስዉር ጥምረት የተካሄደዉ ትግል ነዉ። ይህ ስዉር ጥምረት አላማዉን አሳክቶ እራሱን በአደባባይ አዉጥቶ ለሥልጣን ከበቃ በኋላ የተከተለዉ የፖለቲካ ሂደት ዛሬ ለተፈጠረዉ ቅራኔ ዋነኛ መንስኤ ነዉ። ይህ የኦሮማራ የጋራ ጥምረት ካስገኛቸዉ ድሎች በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚገባዉ ከኦህዴድ ፓርቲ፣ ዶ/ር ዐብይን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ማሾሙ ነበር። ይህ ሹመት፣ በወቅቱ በአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ፤ ሀገሪቱንም ለከፍተኛ ዉድቀት እና አንድነቷን ስጋት ላይ የጣለዉ በዘር ላይ የተመሰረተዉን አስከፊ የፖለቲካ ስሪት ማክተሚያ የመጀመርያዉ ምዕራፍም ተደርጎ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

 

ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ፣ ኦሮማራ የሚለው ጥምረት ወደ ቅራኔያዊ ዉጥረት እየተለወጠ በመምጣቱ፤ የጥምረቱ መነሻ ዋነኛ ምክንያት ነዉ ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ይታመን የነበረዉ የአንድነት ምልክት ጥያቄ ላይ ወደቀ። ቀስ በቀስ፣ በሀገሪቱ ላይ  የሚታየዉ የሰላም እጦት፣ በስፋት እየተካሄደ የመጣዉ የዘር ተኮር ጥቃት፣ እንዲሁም በግልጽ የሚታየዉ የኦሮሞ ተርኝነት፣ የተፈጠረዉን ልዩነት አጉልቶ አሳይቷል። ዛሬ እራሱን ብልጽግና ብሎ ሀገሪቱን የሚመራዉ የገዢዉ ፓርቲ፣ ከኢሕአዴግነት ስሙን ቀይሮ መጠነኛ ጥገናዊ ለዉጥ በማድረግ በኦሮሞ ብልጽግና የበላይነት የሚዘወር መሆኑ፣ የኦሮማራ ጥምረት ሰለመክሸፉ ዋነኛ መገለጫ ነዉ።

ለዚህም በተቀዳሚነት ዋነኛ ምክንያት የሆነዉ፣ ሁለቱ የአማራ እና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱበት የፖለቲካ አወቃቀር እና መሰረት በቅጡ ሳይመረመር እና ሳይታረቅ፣ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚል አላማ ታስቦ የተኬደዉ ሂደት ዉጤት ነዉ። የኦሮሞ ፖለቲካ እንደ ሕወኃት በ 1960 ዎቹ በተሳሳተ ትርክት የተጀመረዉን የብሔር ፖለቲካ መሰረት አድርጎ፣ ሥልጣን ለመጨበጥ የተነሳ ሲሆን፣ ይሄዉም የኦሮሞን ብሔር ተጨቋኝ፣ የአማራን ብሔር ጨቋኝ፤ አድርጎ በመፈረጅ፣ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ የመገንጠልን ፖለቲካዊ እቅድ ይዞ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ነዉ። በአንጻሩ ደግሞ፣ የአማራ ፖለቲካ እንደሌሎቹ የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ብሎ የተመሰረት አይደለም። እራሱን ከኢትዮጵያ ለይቶ በብሔር አጥር ያልከለለ፣ ሆኖም ግን በሀገሪቱ በተዘራዉ የሐሰት ትርክት የተነሳ በአማራዉ ላይ የሚደርሰዉን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እና ፍረጃ ለመቃወም በሚል በ ፕ/ሮ  አስራት ወልደየስ መሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የመላዉ አማራ ሕዝብ ድርጅት በሚል ስያሜ በዘመነ ሕወኃት የተጀመረ ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ በእውነት መነፅር - ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ፣ አማራዉ በራሱ ተነሳሽነት የመሠረተዉ የአማራ ድርጅት፤ ሕወኃት በኢትዮጵያ ላይ ለማስፈን ላቀደዉ የዘር ፖለቲካ እንቅፋት አንደሚሆንበት ሰለተረዳ፤ በራሱ አምሳል ጠፍጥፎ የሰራቸዉ ኦህዴድ እና ብአዴን የሚባሉ፣ ከስማቸዉ በስተቀር የኦሮሞንም ሆነ የአማራን ሕዝብ የማይወክሉ ድርጅቶችን መስረተ። በተጓዳኝም፣ መንግስት ያለዉን የሃይል እና የገንዘብ አቅም በመጠቀም በተቀነባባረ የሀሰት ክስ ፕ/ር አስራትን በማሰር እና በማሰቃየት ለሞት ሲዳርግ፣ ፓርቲያቸዉም እንዲዳከም ቢደረግም፣ ፓርቲዉ ከብሔር ፓርቲነት ወደ መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሚባል ሀገራዊ ፓርቲነት ተቀይሯል። ሕወኃት ላለፉት ሠላሳ ዓመታት፣ በኦሮሞ እና በይበልጥም በአማራዉ ማሕበረሰብ ላይ ለፈጸመዉ ወንጀል እና ጥፋት በዋና መሳሪያነት የተጠቀመዉ    ብኦዴን እና ኦህዴድን ነዉ።

 

ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታዎች እየተቀየሩ በሁለቱም ድርጅቶች ዉስጥ እየታቀፉ በመጡ ወጣት አባላት፣ እንዲሁም በሕዝባቸዉ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ እየደረስ ያለዉን ጉዳት የተረዱ አንዳንድ ነባር አመራሮች፣ ዉስጥ ዉስጡን በመደራጀት ብሎም ከዉጭ ካሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በስዉር በመቀናጀት የዉስጥ እና የዉጭ ትግሉን አፋፋሙ። ይህ ትግል፣ እየጎለበተ መጥቶ፣ ኢሕአዴግን ከዉስጡ በመቦርቦር አዳክሞት ለውድቀቱ ዋነኛ ምክንያት በመሆን ለዉጡ እንዲመጣ አድርጓል። ለዉጡን ተከትሎ፣ የዶ/ር ዐብይ መንግስት በሀገርም ሆነ በዉጭ ላሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረገዉ የስላም ጥሪ መሰረት የገቡት ፓርቲዎች ለኦሮማራ ጥምረት መዳከም እና ብሎም መፍረስ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለዚህም ከፍተኛዉን ድርሻ የሚወስዱት፣ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ፣ በተለይም ነባር የኦነግ መስራች አባላት በኦህዴድ ዉስጥ የነበራቸዉ ጉልህ ሚና እና ያሳድሩት የነበረዉ ተጽዕኖ አሁን ላለዉ የኦሮሞ ብልጽግና እርሾ ሆኖታል። በአንጻሩ ደግሞ፤ አማራዉን የሚወክል ቀደም ብሎ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ የቀድሞዉ ብአዴን የቀደመ ግብሩን ሳይተዉ ስሙን ብቻ ቀይሮ ለኦሮሞ ብልጽግና አጃቢ ስር ሚዜ ሆኖ መጣ። ይህ የተዛባ ውህደት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅርጹን እየቀየረ በመሄዱ፣ ይጠበቅ የነበረዉ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ለዉጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሸፈ።

 

የብልጽግና መዳረሻ፤

ለዉጡን ተከትሎ ኦህዴድ በኦሮሞ ብልጽግና ቢተካም፣ እንደ ኢህአዴግ ዘመን የህወኃት አጫፋሪ ሳይሆን እራሱ “የብልጽግናዉ ህወኃት” ሆኖ በመምጣቱ፣ የሀገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካ ለመቆጣጠር ችሏል። ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ እና እድል በመጠቀም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸዉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገቡትን ቃል እና የስጡትን ተስፋ ተግባራዊ እንደማድረግ፣ በእርሳቸዉ መሪነት፣ በኦሮሞ ብልጽግና አስፈጻሚነት የኦሮሞ ተረኝነት ሥጋ ለብሶ በየ አደባባዩ በገሀድ ይታይ ጀመር። ከላይ እንደገለጽነዉ የኦነግ መነሻ የፖለቲካ አቋም፣ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ መገንጥል የሚል ቢሆንም፣ አመቺ ከሆነ እና እድሉ እስከተገኘ ድረስ፣ በኦሮሞ ማንነት እና ስነ ልቦና የተቃኘች አዲስ ኢትዮጵያን መፍጠሩ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ተወስዷል። የዚህም ማሳያዉ፣ የኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና መገላጫዎች ናቸዉ ተብለዉ የሚጠቀሱትን እንደ ሃይማኖት ተቋማት፣ ታሪክ፤ ቋንቋ፣ ሰንደቅ ዓላማ እና የመሳሰሉት ላይ በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በመዝመት የማጥፋት እና የመተካት ስራዎች በግልጽ እየታዩ መጥተዋል። ይህንንም አስመልክቶ በአንድ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ነዉ ተብሎ በተሰማ የድምጽ ቅጂ ላይ የተረኝነቱን አተገባበር በሚገባ ገልጸዉታል።

 

እዚህ ላይ ሊስተዋል እና ሊጠቀስ የሚገባዉ ነገር ቢኖር፣ ከዛሬ 60 ዓመት በፊት በተማሪዎች ንቅናቄ የተጀመረዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ የትግሉ ማጠንጠኛ በተሳሳተ ትርክት የተቀነቀነዉ የብሔር ጭቆናን መነሻ ያደረገ ነበር። ለዚህም እንታገለዋለን ለተባለዉ የ “ብሔር ጭቆና”፣ አማራ እና ትግሬ (የስሜን ኢትዮጵያ ክፍል ) ጨቋኝ፣ ደቡቡ ደግሞ ተጨቋኝ ተደርጎ ነበር በነ ዋለልኝ መኮንን ድርሰት የተፈረጀዉ። ሆኖም ግን፣ በተቀነባበረ የፖለቲካ ስልት፣ ትግሬ ከጨቋኝነት ማዕረግ ወደ ተጨቋኝ ብሔር ካምፕ ሲወርድ፣ አማራዉ ግን ወደ ብቸኛ ጨቋኝ ብሔር ከፍ ተደርጎ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መነሻዉም ሆነ መዳረሻዉም አማራ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ የተነሳ እስከ አሁን ድረስ በሚያሳፍር እና በሚያሳዝን መልኩ፣ አማራዉ በማያዉቀዉ እና ባልሰራዉ ኃጢያአት መከራዉን ያያል። ይህን የጨቋኝ፣ ተጨቋኝ ትርክት እዋጋለሁ፣ ለብሔረስቦች እኩልነት እሞታለሁ ወዘተ… ሲሉ የነበሩ ፖለቲከኞች፣ በተለይም የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች፣ ዛሬ በአደባባይ የኦሮሞ የበላይነት በሀገሪቱ ላይ ገኖ ሲታይ ምነዉ ዝም አሉ? የሚለዉ ጥያቄ ተገቢ መልስ ያሻዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የናዚስት ትህነግ 3ቱ የህልውና መሰረቶች! [መስፍን ማሞ ተሰማ]

 

ዛሬ በገሀድ ለሚታየዉ የተረኝነት መገላጫዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸዉ።

  1. የኢትዮጵያዊያን የጀግንነት፣ የአይበገሬነት እና የቆራጥነት ምሣሌ የሆነዉን የአንባሳ ምልክት፤ ሆን ብሎ ማንቋሸሽ እና በፒኮክ ምስል ለመተካት መሞከር።
  2. ለብዙ ዘመናት የመላዉ ሀገሪቱ ሕዝቦች የእርስ በእርስ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል የቆየዉን የአማርኛ ቋንቋ፣ በተጠና መልኩ ከሀገሪቱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ማዉጣት።
  3. የኦሮምኛን ቋንቋ ለማስፋፋት በሚል ሽፋን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መዝሙርን እና አርማ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ላይ በግድ ለመጫን የተደረገዉ ሙከራ።
  4. የአዲስ አበባ ከተማን ለማዳከም እና ብሎም ከተፈጥሯዊዉ የከተማ እድገት የተነሳ እንዳትሰፋ በማድረግ፣ ከቦ በማፈንና ዙሪያዋን ሸገር በሚል ስያሜ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሥር የሚተዳደር ከተማ በመመስረት ለመቆጣጠር መሞከር።
  5. የማያባራ የዘር ጭፍጨፋ የሚፈጸምበት እና መንግስት እራሱ አሸባሪ ሲል የፈረጀዉ ሸኔ፣ በጠራራ ፅሐይ የጦር አዉድማ ካደረጋት ከኦሮምያ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ዜጎች፣ የዜግነት መብታቸዉ ተጠብቆላቸዉ መግባት ሳይከለከሉ፣ አንጻራዊ ሰላም ከሰፈነበት የአማራ ክልል የሚመጡ ዜግችን፣ ሰላም ማስከበር በሚል ከንቱ ምክንያት እንዳይገቡ መከልከል።
  6. በተለያዩ ክልሎች፣ በተለይም በኦሮምያ ክልል በመንግስት ሃይል በሚደገፉ አሸባሪዎች በሚጨፈጨፉ እና በሚፈናቀሉ ዜጎች ሆን ተብሎ የአማራን ክልል የስደተኞች ክልል በማድረግ፣ በክልሉ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንዲፈጠር፣ በሕዝብ ዘንድ ተቃዉሞ እንዲነሳ በማድረግ ክልሉን የማዳከም ሴራ።
  7. በኢትዮጵያዊነትን ስነ ልቦና ለዘማናት ትዉልድን በማነጽ ታሪኩን፣ ባህሉን እና ሃይማኖቱን እንዲጠብቅ ያደረገችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ ከሀገራዊነቷ አዉርዶ፣ ክልላዊ በማድረግ የማዳከም ብሎም የማጥፋት ዘማቻ።
  8. አጼ ምንሊክን ከታላቁ አድዋ ለመነጠል እና ለማዋረድ የሚካሄደዉ ያላሰለሰ ዘመቻ።
  9. ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የሚገኑበት የአደባባይ በዓላት ላይ ሕዝቡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ስንደቅ ዓላማ ምስል ያለዉ ቀሚስ፣ ነጠላ፣ እንዲሁም የቀደሙ ነገሥታት ምስል ያለበት ማናቸዉ አልባሳት እንዳይለበሱ እና እንዳይሸጡ መከልከል።
  10. ኢትዮጵያ የሚለዉን ስም ሲሰማ የሚያንዘፈዝፈዉ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ስንደቅ ዓላም ሲያይ የሚተናነቀዉ፣ አጼ ምንሊክ ሲነሱ የሚያስጓራዉ ነፍስ ካወቀ ጀምሮ እስክ እርጅና ዘመኑ ኢትዮጵያዊነቱን ሲጽየፍ የኖረ ኦነጋዊ፣ የህገሪቱ ስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር ተደርጎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሾም ምን ለማስፈጸም እና ማሳካት እንደታሰበ ግልጽ ነዉ።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ተጨባጭ ሀቆች፣ ሀገሪቱ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለማሳየት ቀንጨብ ተደርገዉ የቀረቡ ቢሆንም፣ በሀገሪቱ ላይ እየመጣ ያለዉን ከፍተኛ አደጋም ቁልጭ አድርጎ ያሳያሉ። ሰለሆነም፣ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ ሊመጣ ያለዉን ሀገራዊ ቀዉስ ለማስቆም የሚከተለዉን ምክረ ሀሳብ እናቀርባለን።

 

የመፍትሄ ምክረ ሐሳብ፤

ከላይ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርነዉ፣  በአሁኑ ሰዓት በሁለት ጎራ ሆነዉ በሚፋለሙት የፖለቲካ ሃይሎች መካከል በሚደረገዉ ትንቅንቅ፣ የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ለማወቅ እና ለመረዳት አዳጋች እየሆነ መጥቷል። ሆኖም ግን፣ አሸንፎ የሚወጣዉ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል ይወስናል። ከዚህ በመነሳት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በገዢዉ ፓርቲ የሚቀነቀነዉ እና እየተተገበረ ያለዉ ኦነጋዊ አጀንዳ፣ ሀገሪቱን ወደማትወጣበት የእርስ በእርስ እልቂት ይከታታል። ይህን ችግር ከወዲሁ ትገንዝቦ፣ በብልጽግና ስር የተካተቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ብልጽግና በፍጥነት አሰፈላጊዉን እርምት እንዲያደርግ መግፋት እና ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። ይሄንንም ለማሳካት፣ ካለዉ የሕዝብ ብዛት እና ፖለቲካዊ መዋቅር አኳያ፣ የአማራ ብልጽግና ሃላፊነቱን በመዉስድ ሌሎች በብልፅግና ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን በማስተባበር ሀገራዊ ግዴታዉን ሊወጣ ይገባል።

እንደሚታወቀዉ አሁን ባለዉ የፖለቲካ አሰላለፍ የገዢዉን ፓርቲ ሊገዳደር ቀርቶ በበቂ ቁመና ላይ ያለ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰለመኖሩ አጠያያቂ ነዉ። ባለፈዉ ከተካሄደዉ ሀገራዊ ምርጫ በፊት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጎላ ያለ እንቅስቃሴ ያሳዩ የነበሩ እንደ ኢዜማ፣ አብን፣ ኦፌኮ፣ ባልደራስ፣ እናት፣ ኦነግ የሚባሉ ፓርቲዎች ነበሩ። ሆኖም ግን፣ አንዳዶቹ የምርጫዉን ሂደት ተቃዉመዉ ሳይሳተፉ ሲቀሩ፣ የተሳተፉት ደግሞ ከምርጫዉ በኃላ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከተጠበቀዉ በታች ባገኙት አነስተኛ ዉጤት የበለጠ የተዳከሙ ይመስላል። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ በደጋፊዎቻቸዉ ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸዉ የነበሩት የኢዜማ እና የአብን ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የገዢዉ ፓርቲ በወሰደዉ በማር የተለወስ መሰሪ የፖለቲካ ሂደት፣ የተቸራቸዉን የመንግስት ሥልጣን በመቀበላቸዉ፣ የፓርቲያቸዉን ህልዉና አደጋ ላይ እስከ መጣል ደርሰዋል። በተቃራኒዉ፣ ይህ የመንግስት ችሮታ፣ በተወሰነ መልኩ በሕዝብ ዘንድ አድናቆትን እና ሙገሳን አትርፎለታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጎዶሎ ሃሳብ (በአዲሱ ሀይሉ)

 

ይህም በመሆኑ፣ ብልጽግና እየተገበረ ካለዉ የኦነግ አጀንዳ የተነሳ፣ ሀገሪቱን ወደከፋ ደረጃ ይዟት እየሄደ ካለበት የቁልቁለት ጎዳና ለጊዜዉም ቢሆን ታኮ ሆኖ ለማስቆም፣ በወቅቱ ካለዉ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ፣ ያለዉ ብቸኛ ሰላማዊ እማራጭ የአማራ ብልጽግና የጀመረዉን ተቃዉሞ ማበረታታት እና መደገፍ ነዉ። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያካተተች እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ የአማራ ብልጽግና ታሪካዊ አጋጣሚ እና እድል አሁን ተፈጥሮለታል። ይህንን እድል በአግባቡ ለመጠቀም፣ የአማራ ብልጽግና ከመሽኮርመም እና ከዳተኝነት ፖለቲካ በፍጥነት ተላቆ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። የታሰበዉንም የፖለቲካ ግብ ለመምታት፣ የተቀሩትን የብልጽግና አባላት እንዲሁም ከብልጽግና ዉስጥ እና ዉጭ ያሉ ከዘር ፖለቲካ የተላቀቁ የኦሮሞ እና የትግሬ ፖለቲከኞችን በዙርያዉ በማሰባሰብ ሀገራዊ አጀንዳ በመቅረጽ የበሰለ ፖለቲካ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም፣ ትግሉ ፍርያማ እንዲሆን የሕዝብ ድጋፍ በተለይም የሚወክለዉን የአማራ ህዝብ አቅፎ እንዲከተለዉ ማድረግ ተቀዳሚ ስራዉ ሊሆን ይገባል። ይህም እንዲሳካ፣ ሕዝቡ እስካሁን ካየዉ እና ካለፈበት የሕይወት ተሞክሮ የተነሳ፣ በፓርቲዉ ላይ ያለዉን ጥርጣሬ እና አለመተማመን ለመቅረፍ የሚከተሉትን ወሳኝ እርምጃዎችን ከወዲሁ መወሰድ አለበት ብለን እንመክራለን።

 

  • ለእስር የተዳረጉ፣ ሆኖም ግን በቂ ምክንያት እና ተጨባጭ ማስረጃ ያልተገኘባቸዉን የፋኖ እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በፍጥነት አጣርቶ እና ለይቶ ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት።
  • ለኢትዮጵያ ሀገራቸዉ ሲሉ ለነፍሳቸዉ ሳይሳሱ በችግሯ ጊዜ የተዋደቁላትን የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻዉን እና ፋኖን ለይስሙላ ሳይሆን ተገቢዉን እዉቅና፣ ክብር እና ድጋፍ መስጠት።
  • በአማራ ሕዝብ ላይ ለደረሰዉ እና ለሚደርሰዉ ግፍ፣ ስቆቃ እና በደል ሲታገሉ በክልሉ እና በፌደራል መንግስት ጥርስ ተነክሶባቸዉ ከሀላፊነታቸዉ እንዲገለሉ የተደረጉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ወደ ቀደም ቦታቸዉ መመለስ።
  • የክልሉ መንግስት ለሚወክለዉ ሕዝብ፣ ፓርቲዉ ሊያሳካዉ የሚፈልገዉን የፖለቲካ አቋም እና ከሕዝቡም ምን እንደሚጠብቅ እዉነተኛ እና ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ማስቀመጥ።
  • በሕገ መንግስቱ እንደተደነገገዉ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ርእሰ ከተማ ከመሆኗም በላይ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ስለሆነች፣ የአማራ ክልልም እንደማንኛዉም ክልል በከተማዋ ላይ መብት እንዳለዉ በግልጽ ማሳወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም፣ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡትን ኬላ ላይ በመመለስ እንዳይገቡ ማድረጉን በአስቸኳይ እንዲያቆም ማድረግ አለባቸዉ።
  • ማንኛውም ኢትዮጲያዊ በአገሩ በነፃ የመንቀሳቅስ መብቱ እንዲከበር መታገል አለባቸው።
  • በሀገሪቱ ዉስጥ፣ በተለይም በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለዉን የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ጭፍጨፋ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግስት እንዲያስቆም ግልጽ የሆነ ጥርስ ያለዉ አቋም መያዝ አለባቸው።
  • ወልቃይት እና ራያን በተመለከት የክልሉ መንግስት የአማራ ማንነታቸዉን በሚያረጋግጥ መልኩ የማያወላዉል አቋም መያዝ አለባቸው።
  • ከሁሉም በላይ፣ የዘር ፖለቲካ ለሀገራችን ኢትዮጲያ እንደማይበጅና ሕገ መንግሥቱም ይህንን በሚያንፀባርቅ መንገድ መሻሻል አለበት ብለው እንደሚያምኑ ግልፅ አቋም መያዝ አለባቸው።

ይህን ከላይ የተዘረዘሩትን የክልሉ መንግስት እና የአማራ ብልፅግና ፓርቲው ቢያከናዉኑ፣ በሀገሪቱ ላይ የተደቀነዉን አደጋ ለመግታት ብሎም ለመቀየር ይቻላል። ይህንንም በማድረግ ኦነግ ኦነግ የሚሸተዉ ብልጽግና ፓርቲ ሊፅዳና የሀገራችንም ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና የእውነተኛ የብልፅግና አቅጣጫ የያዘ ይሆናል ብለን እናምናለን።

 

በመጨረሻም እስካሁን በሀገሪቱ፣ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ለደረሰዉ ሰቆቃ እና እንግልት ከፍተኛዉን ድርሻ ከመንግስት ቀጥሎ የቀድሞዉ ብአዴን የዛሬዉ የአማራ ብልጽግና ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ዜጋ በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህንን ከግንዛቤ በመክተት፣ ለአድዋ ጦርነት አጼ ምንሊክ ካስለፈፉት የክተት አዋጅ ላይ “ … ቂምህን በጉያህ ይዘህ ተከተለኝ …” የምትለዋን ሐረግ ዛሬ በመተግበር ትግሉ ለሚጠይቀዉ መስዋትነት እያንዳንዱ ዜጋ መዘጋጀት ይኖርበታል ብለን እንመክራለን።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር። አሜን።

 

 

2 Comments

  1. Here are my humble comments.

    1. When PP is more OLF than OLF itself, the tile seems to be a case of appeasing the hyena. Libela yemeTa jib, abbo abbo bilut aymelesim.

    2. “በመጨረሻም እስካሁን በሀገሪቱ፣ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ለደረሰዉ ሰቆቃ እና እንግልት …………፣ እያንዳንዱ ዜጋ በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት አስተዋጽኦ አድርጓል።”
    That is right!

    3. ምንሊክ ካስለፈፉት የክተት አዋጅ ላይ “ … ቂምህን በጉያህ ይዘህ ተከተለኝ …”
    That is wrong! Menilik did not say that. “Amelhin beguya does not mean that. This would be an incorrect and dangerous misinterpretation. At any rate, had that been the case, instead of the glorious victory that we still celebrate 127 years later, our forefathers would have finished each other off before they even had a chance to engage the enemy. “Amelhin beguya” would translate closer to “Restrain your pettiness”.

  2. አይ ኮለኔል አብይ እንዲህ ለስለስ ብለው ገብተው ህዝቡን ጉድ ሰሩት? ሳናጣራ አናስርም ጉልበት ችግር መፍቻ አይሆንም ተብሎ የተነገረን ሞኝህን ፈልግ በሚለው ተቀይሮ መጀመሪያ ለማን ሲበሉት እነ ሽመልስና ጃልመሮን አባት ኦነጎችን ፈርተው ተዏቸው ለነገሩ ሌላ ሳይሆን እንዚህ ሰዎች እንደሚበሏቸው ጥር ጥር አይኖርም የቅን ጅቦቹ እንኳን እድል የሚያገኙ አይመስለኝም፡፡ ሁኔታዎች አስገድዷቸው ነው አጭበርብረውን ነው? ይህንን ከሳቸው በስተቀር የሚያውቅ የለም ጁዋር መሃመድ ግን ሲጀመር ጀምሮ ቀልቡ አልወደዳቸውም እሱም ቢላ እየሳለ ነው፡፡ ታየ ደንዳ ወደ ጎን ተግፍቶ መሳቂያ ሁኗል የዮሃን ክራፍት ልጆች ቀለበት ውስጥ አስገብተውታል፡፡ ዛሬ ዋናው አክተር ቀጀላ መርዳሳና አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡ አብይ ከነዚህ ሰዎች ካመለጠ ለዮሃንስ የተገጠመውን ማስታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.