የሄንሪ ቀመር በአንፊልድ ሊቨርፑል (ልዩ ትንታኔ)

የትልቅነት ማዕረጉን ተገፍቶ የቆየው ሊቨርፑል ወደ ክብሩ እየተመለሰ መሆኑን የዘንድሮ ስኬታማ ግስጋሴው ይጠቀላል፡፡ ለቀዮቹ ጥንካሬ ብሬንዳን ሮጀርስ ትልቅ አድናቆት ቢገባቸውም የክለቡ የሽግግር ጉዞ ዋናው ቀያሽ ጆን ሄንሪ ናቸው፡፡ አሜሪካዊው በአዲስ አስተሳሰቦች ስኬትን እንዴት ማምጣት እንደሚቻል የተገነዘቡ ናቸው፡፡ ይህንን አቅማቸውን በቢዝነሱ እና በስፖርቱ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ አዲስ እና የተለዩ ሀሳቦችን እያፈለቁ ውድቀትን ሳይፈሩ ያሰቡትን ይተገብራሉ፡፡
ሄንሪ በአሜሪካ ቦተን ሬድ ሶክስ የተሰኘውን ክለብ በባለቤትነት ሲረከቡ በቤዝቦል ስፖት እጅግ ስኬታማ ተብሎ ይጠቀስ ከነበረው ኒው ዮርክ ያንኪስ ጋር የነበረውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ አንድ የተለየ ሀሳብ ማፍለቅ ነበረባቸው፡፡ የአሜሪካው ኦክላንድ አትሌቲክ በቤዝቦል ስፖርት ራሱን መልሶ ለማጠናከር ጥናት ማድረጉን ያውቁት ሄንሪ በተመሳሳይ ሬድ ሶክስን መልሰው ለመገንባት ሊጠቀሙበት ሲንቀሳቀሱ ማንም አልፈቀደማቸውም፡፡
የውድቀት ፍርሃት’

ሊቨርፑል በሮጀርስ ስር ሲሰለጥን አንዱ የጠቀመው ከውድቀት ፍርሃት ነፃ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ያለመፍራት መንፈስ ደግሞ ከክለቡ አናት የመነጨ ነው፡፡ ሄንሪ እና የፌንዌይ ስፖርትስ ግሩፕ (FSG) ቀደም ሲል ስህተቶች ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን በስህተቶቻቸው እየተማሩ ሊቨርፑል ከሌሎች ተቀናቃኞቹ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ሞክረዋል፡፡ የአሁኑ የሊቨርፑል ትልቅ የጥንካሬ ባህርይ የክለቡን የስልጣን ተዋረድ ተጠቅሞ ከላይ የወረደ ነው፡፡
ሊቨርፑል የተለየ ነገር መሞከር ለመፈለጉ አንዱ ማስረጃ ዳሚዬን ኮሞሊን መሾሙ ነው፡፡ ሆኖም ይህ እንዳልሰራ ሲመለከቱ በቶሎ ሀሳባቸውን አረሙ፡፡ በዝውውር ገበያ ላይ አብዝቶ መሳተፍ ስኬትን እንደማያረጋግጥ ተገነዘቡ፡፡ ስለዚህ ሌላ አይነት ቀመር መሞከር ነበረባቸው፡፡
ሄንሪ ሁልጊዜም በሊቨርፑል ሰፋ አድርገው ማሰብ እና ጠቅለል ያለ ስዕል መመልከት ይፈልጋሉ፡፡ ሰውዬው ለሚፈጠሩ አደጋዎች መፍት ለመስጠት እጃቸውን አጣምረው የሚጠባበቁ ሳይሆኑ እያንዳንዷን እርምጃ አስቀድመው አስበው በስትራቴጂ መሄድ የሚመርጡ ናቸው፡፡ ደጋፊዎች እንደ ትልቅ ስህተት የሚመለከቱትን እርሳቸው የስኬታቸው ግስጋሴ ምስክር አድርገው በበጎ ያዩታል፡፡ በእግርኳስ የተለዩ እና አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማራመድ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ደጋፊዎች ምንም አይነት ውድቀትን አይታገሱም፡፡ ሆኖም ከውድቀቶች እየተማሩ እንጂ በቀጥት ስኬት ጋር አይደርስም፡፡
አለማችን ካፈራቻቸው ድንቅ እና ታላላቅ ስፖርተኞች አንዱ የሆነው ማይክል ጆርዳን በአንድ ወቅት ይህንን ብሏል፡፡ ‹‹በህይወት ዘመኔ ደጋግሜ ውድቀትን ተጎንጭቻለሁ፡፡ የተሰካልኝም ለዚህ ነው፡፡ ሄንሪ እና FSG ለፈጠራ በሰላም አዕምሮ ቢዝነስን ማሳደግን ያውቁበታል፡፡ ሊቨርፑልን እና ሬድ ሶክስን እያስተዳደሩ ያሉትም በዚህ መንገድ ነው›› ሄንሪ ይህንን ቀመር ወደ ውጤት ለማድረስ እና ሊቨርፑልን መልሰው ሃያል ለማድረግ የተከተሏቸውን መንገዶች መቃኘት እንችላለን፡፡
የሮጀርስ ሹመት
ሄንሪ የሊቨርፑልን ህዳሴ በበላይነት ይምሩ እንጂ ራዕያቸውን የሚጋራ፣ አዳዲስ ሀሳቦችን በመሞከር የሚያምን እንዲሁም ቡድኑን ሜዳ ላይ የሚመራ ሰው ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ሮጀርስ ይህንን ሁሉ በውስጣቸው የያዙ እውነተኛ መሪ መሆናቸውን አሜሪካዊው አመኑበት፡፡ ወጣቱ አሰልጣኝ ሜዳ ላይም አዳዲስ ሃሳቦችን እየተጠቀመ ለስኬት እንደሚሰራ እርግጠኛ ሆኑበት፡፡ ሄንሪ ሮጀርስን ሲሾሙ የእግርኳስ ፍልስፍናቸውንም እንዲያራምዱ ፈቀዱላቸው፡፡ ሮጀርስ ሄንሪን አላሳፈሩም፡፡ በተለይ መንገድ ሊቨርፑልን ውጤታማ አደረጉት፡፡ ሰውየው በቡድኑ የተለዩ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡ የሊቨርፑል ተጨዋቾች ለግጥሚያ በአዕምሯቸው ዝግጁ እንዲሀኑ በዓለም ላይ የላቁ ከሚባሉት የስፖት ስነ ልቦና ባለሙያዎች አንዱን አስቀጥረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በቀጥታ ቡድኑ ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ በጥናት ባይረጋገጥም የዘንድሮው የሊቨርፑል ተጨዋች አካላዊ እና አዕምሯዊ ጥንካሬ ግን አስገራሚ ሆኗል፡፡
ሮጀርስ ተጨዋቾቻቸውን ሲያቀናጁም እንደዚሁ የፈጠራ አቅማቸው ይንፀባረቃል፡፡ ከግጥሚያዎች በፊት ሊቨርፑል በየትኛው ጨዋታ ምን አይነት አጨዋወት ይዞ እንደሚቀርብ መገመት ያስቸግራል፡፡ ሮጀርስ የመጠቁ ታክቲክ አዋቂ ተብለው ባይፈረጁም ቡድናቸውን የማይገመት ማድረግን ያውቁበታል፡፡ ዘንድሮ ከቡድኑ የጥንካሬ ሰበቦች አንዱ ይኸው የማይጨበጥ የጨዋታ ስትራቴጂ ይዞ የመገኘት ባህሪዬ ነው፡፡ ይህ የሮጀርስ የፈጠራ ዝንባሌ በሄንሪ ፍላጎት እየተበረታቱ የሚተገብሩት ነው፡፡
የዝውር – ኮሚቴ
የኮሞሊ መምጣት እንደታሰበው ስኬታማ ሆኖ አይገኝ እንጂ ሀሳቡ በራሱ ስህተት አልነበረም፡፡ ሰውየው የተሾሙት በዝውውር ገበያው ሰዎች በቀላሉ ከሚያዩት አልፈው እንዲመለከቱ ነበር፡፡ ሆኖም አሰራሩ ችግር እንደነበረው ለማወቅ የአንዲ ካሮል ግዢ በቂ ነበር፡፡ ሉዊስ ሱአሬዝን የመሰለ ኮከብ በ22 ሚሊዮን ፓውንድ የገዙት ሰው ለቀድሞው የኒውካስል ወጣት ዝውውር 35 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፍል መስማማታቸውን ማመን ያስቸግራል፡፡
በዚህ የዝውውር ሂደት መቀጠል እንደማይችሉ የተገነዘቡት ሄንሪ በ2012 ክረምት የዝውውር ኮሚቴ አቋቁሙ፡፡ በእርግጥ የኮሚቴ አሰራር አዲስ አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ክለቦች እንዲህ አይነት መዋቅር አላቸው፡፡ የሊቨርፑሉ ኮሚቴ ግን በተለየ መልኩ የተጫዋቾችን ባህላዊ የምልመላ ስርዓት ከስታስቲካዊ ትንታኔዎ ጋር አነፃፅሮ የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሳል፡፡ ከኦክላንድ አትሌቲኮ ሞዴል የተቀዳ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተው ይህ አሰራር ምናልባት በእግርኳሱ ለቦሩሲያ ዶርትሙንድ የዝውውር ስትራቴጂ ይቀርባል፡፡
ኮሜርሺያል
የአሁኖቹ የሊቨርፑል ባለሀብቶች ከቀድሞዎቹ በተለየ መልኩ ክለቡ በኮሜርሺያል እንዲያድግ የትኛውን አካባቢ ኢላማው ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲሶቹ የክለቡ የቢዝነስ ዲፓርትመንት ሰዎች የሊቨርፑል ገቢ ያሳደጉበት ፍጥነት ያስደንቃል፡፡ ሬድ ሶክስ በFSG ባለቤትነት ስር ከገባ ወዲህ ከኒውዮርክ ያንኪስ ጋር የነበረውን ሰፊ ርቀት ለማጥበብ 90 የሚደርሱ ተጨማሪ የቢቢነስ አጋሮች ጋር በኮንትራት ተጣምሯል፡፡
የአሜሪካዊያኑ አዳዲስ ሃሳቦች ሊቨርፑል ለወደፊቱ የተደላደለ እና አስተማማኝ ፋይናንስ እንዲኖረው የሚያደርጉ ስትራቴጂዎችን ይዘዋል፡፡ በዓለም ዙሪያ እጅግ ከፍተኛ ደጋፊ ያለው የመርሲ ሳይዷ ክለብ መልካም አጋጣሚዎቹን ሁሉ ቀስ በቀስ በመጠቀም የገበያውን ስፋት ወደ ገንዘብ የመቀየር ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ለጊዜው የሊቨርፑል አጠቃላይ ሂብ ኪሳራ ቢያሳይም የኮሜርሺያል ትርፉ እያደገ ነው፡፡ የክለቡ ኮሜርሲያል ስትራቴጂ ምናልባትም በጥቂት ዓመታት ወስጥ ትርፋማ አድርጎት የቡድኑን ተፎካካሪነትም ከፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ምናልባትም በፋይናንሱ የበረታው ክለብ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ምርጥ ተጨዋቾችን ወደ አንፊልድ ይስባል፡፡
ስታዲየም
አንፊልድን የማስፋፋቱ ሀሳብ የሚሳካ አይመስልም ነበር፡፡ የሊቨርፑል ከተማ ምክር ቤትም ፈቃድ የመስጠት ምልክት አላሳየም፡፡ ስለዚህ ምናልባትም ክለቡ ይህንን ሀሳቡን ትቶ አዲስ ስታዲየም ለመገንባት ቢያቅድ እንደሚሻል ሲነገር ነበር፡፡ ሄንሪ ወደ እንግሊዝ ከመጡ በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ፡፡ አንፊልድን የማስፋፋቱ ሀሳብ የሚቻል መስሎ ታየ፡፡ እንዴት?
ይህ የሄንሪ ሁኔታዎችን ‹‹አይቻልም›› ከሚለው አልፎ የመመልከት ባህሪይ ያመጣው ነው፡፡ ለፈጠራ አዕምሮውን ክፍት ያደረገ ሰው ችግሮን ለማለፍ መፍትሄ ይመከታል እንጂ ወደ ኋላ አይመለስም፡፡ አሁን ሊቨርፑል ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚስማማ ስታዲየም እየተመለከተ ነው፡፡ ይህ ስታዲየም አንፊልድ ራሱ ነው፡፡
የFSG ሰዎች ለቦስተኑ ክለባቸውም ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅመዋል፡፡ በዚያም አይቻልም እየተባሉ በተለየ ብልሀት የቤዝቦሉን ክለብ ስታዲየም አግዝፈው ተጠቅመውበታል፡፡ ሰዎቹ ለስኬት አይተኙም፡፡ በሩጫቸው ሁሉ የሚገጥማቸውን ውድቀት ተቀብለው እና ተምረውበት ቀጣዩን እርምጃ ይጀምራሉ፡፡ በሬድ ሶክስ ደጋግሞ ውድቀት ቢጎበኛቸውም በመጨረሻ የስኬቱን ቀርም አግኝተውት በ10 ዓመታት ውስጥ ሶት የWorld Series (የአሜሪካ ቤዝቦል ሻምፒዮና ውድድር) አሸንፈዋል፡፡ አሁን FSG የቀደመ ልምዱን ታጥቆ ሊቨርፑልን በድጋሚ ትልቅ ሊያደርግ ተነስቷል፡፡ እያንዳንዱን እርምጃውንም በጥናት እና በእቅድ ተያይዟል፡፡ አሜሪካዊያኑ ሮጀርስን በአሰልጣኝነት ሲቀጥሩ ሰውየው ከገንዘብ በላይ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አውቀዋል፡፡ የአንፊልዱን ክለብ በሶስተኛው ዓመት ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ሊመልሱ ቃል ይገቡት አሰልጣኝ በሁለተኛ ዓመታቸው ሊቨርፑልን የዋንቻ ተፎካካሪ አድርገውታል፡፡ ከሜዳ ውጪ ደግሞ የክለቡ የኮሜርሺያል ባለሙያዎች የሊቨርፑልን ገበያ እያሰፉ እና የቢቢነስ ሽርኮቻቸውን በቁጥር እያሳደጉ አስገራሚ ግስጋሴ ላይ ናቸው፡፡ የሄንሪ ቀመር እየሰራ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያዊያን ትግል - (ክፍል አንድ)፡ የመድረክ የአደባባይ ውይይትን በመንተራስ

የሜርሲሳይድ መነቃቃት
በሜርሲ ሳይድ በአይነቱ ልዩ የሆነ መነቃቃት እየታየ ነው፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን የሊቨርፑል ከተማዎቹ ሁለት ክለቦች አስገራሚ ብቃት በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ተሰጥቷቸው ከነበረው ግምት በላይ መሆን ችለዋል፡፡

ከሊቨርፑል ምን ተጠብቆ ነበር?
ሊቨርፑል የውድድር ዘመኑን የጀመረው ቅይጥ የሆነ እምነት እና ግምት ይዞ ነው፡፡ በ2012-13 የውድድር ዘመን ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት የተገለፀው ‹‹ከተጠበቀው በታች›› ተብሎ ነው፡፡ ይህም አንባቢዎችን ‹‹ውድቀት›› ከሚለው ቃል ለመከለል የተደረገ ጥረት ነበር፡፡ የአዲሱ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ አጀማመር አስከፊ ነበር፡፡ ይህም የክለቡ ዝነና አሰልጣኝ ከኃላፊነት መነሳታቸው ስህተት ወይስ ለስራው ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት አንድሬ ቪያስ ቦአስ እድሉ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች በደጋፊው አዕምሮ ውስጥ እንዲመላለስ አድርጎ ነበር፡፡ ቀዮቹ የውድድር ዘመኑን የጀመሩት በቀድሞው የኬኒ ዳልግሊሽ ረዳት ስቲቭ ክላርክ በሚመራው ዌስት ብሮም በአሳማኝ ሁኔታ 3-1 ተሸንፈው ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ በራሱ ስቲቭ ክላርክ ኃላፊነቱ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ አጀማመሩን ይበልጥ አስከፊ ያደረገው በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀሉት ጆአለን፣ ፋቢዮ ቦሪኒ እና ኦሳማ አሳይዲ ውጤታማ መሆን አለመቻላቸው እና ክሊንት ደምፕሴይን ለማስፈረም የተደረገው ጥረት መክሸፉ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በይፋ የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉ የክለቡን ታማኝ ደጋፊዎች እንኳን ትንሽ ራቅ ባለ ጊዜ ቢሆንም ስሙ ከስኬት ጋር ተያይዞ ይጠቀስ በነበረው ቡድናቸው ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ አስገድዶ ነበር፡፡ ሆኖም ውጤታማ በነበረው የጃንዋሪ የዝውውር መስኮት ክለቡ ዳንኤል ስቴሪጅ እና ፊሊፔ ኩቲንሆን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉ መረጋጋትን አሰፈነ፡፡ የውድድር ዘመኑም ቅርፅ እየያዘ መጣ፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆኖ የውድድር ዘመኑን ያጠናቅቃል ተብሎ ተፈርቶ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፡፡ እንደ አጀማመሩ ቢሆን ከዚህም የከፋ ውጤት ይዞ ሊያጠናቅቅ ይችል የነበረበት ሰፊ ነበር፡፡ የውድድር ዘመኑ ሁለተኛ አጋማሽ ግን ጥርት ባለ መልኩም ባይሆን በቀጣዩ የውድድር ዘመን የሊቨርፑል ደጋፊዎች ምን ሊመለከቱ እንደሚችሉ የጠቆመ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኛ ነገር፡ የኔም ነገር፤ አንድ - (ከተክለሚካኤል አበበ)

2013-14 ዓለም አቀፍ ክብር
ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ሊቨርፑል የዘንድሮውን የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ አሸነፈ፡፡ ይህንንም ድል ያላሳከው ያለ ኮከብ ተጫዋቹ ልዊስ ሱአሬዝ እገዛ ነበር፡፡ እንደ ሲሞን ሚኞሌ እና ማማዱ ሳኮን የመሳሰሉ ተጨዋቾች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ቡድኑ መቀላቀሉ እጅጉን ጠቅሞታል፡፡ የአያጎ አስፓስ እና ኮሎ ቱሬ ዝውውር ግን ያገኘው ድብልቅ ምላሽ ነው፡፡ ከሊቨርፑል ተጠብቆ የነበረው ደጋፊዎቹ በሹክሹክታ ‹‹ቀጣዩ የውድድር ዘመን የእኛ ነው›› ሲሉ መስማት ነበር፡፡
ከተጫዋቾቹም የተጠበቀው አራተኛ አሊያም አምስተኛ ሆነው ለማጠናቀቅ የቻሉት ያህል እንዲታገሉ ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ያልተጠበው ነገር ዘጠን ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፉ ነበር፡፡ ቡድኑ ‹‹ጥልቀት እንደሌለው›› እየተነገረ ባለበት ሰዓት ከ34 ጨዋታዎች በኋላ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላ ይቀመጣል ብሎ የረጠረጠ አለመኖሩ እውነት ነው፡፡ ሌላው ያልተጠበቀ ነገር ባርሴሎና ብሬንዳ ሮጀርስን ወደ ባርሴሎና ለማስኮብለል ሙከራ እያደረገ ነው መባሉ ነበር፡፡ ምን ይሄ ብቻ ፔፕ ጋርዲዮላ ሊቨርፑል በውድድር ዘመኑ እያሳየ ያለውን ብቃት አድቆ የአንፊልዱ ክለብ ዳግም በቻምፒዮንስ ሊግ ሲጫወት መመልከት እንደሚፈልግ ይናገራል ብሎም የጠበቀ አልነበረም፡፡

ኤቨርተን፡- ሞዬስ ተረስተዋል
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኤቨርተን በፕሪሚየር ሊጉ ድብልቅ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በዴቪድ ሞዬስ የተመሩት ቶፊስ ስድስተኛ ሆነው አጠናቀቁ፡፡ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከከተማ ተቀናቃኛቸው ሊቨርፑል በላይ ሆነው መጨረሳቸው ነበር፡፡ የገዘፈ ስም የነበራቸው እና እንደ ‹ጣኦት› የሚቆጠሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ሲወስኑ ዩናይትድ ሞዬስን ወደ ኦልድትራፎርድ ወሰደ፡፡ ኤቨርተንም አሰልጣኝ አልባ ሆነ፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን እንዲመሯቸውም ሮቤርቶ ማርቲኔዝን ሾሙ፡፡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ስፔናዊው ከዓመት በፊትም ‹‹ንጉስ›› ዳልግሊሽን እንዲተኩ በሊቨርፑል ኃላፊነት በዕጩነት ከቀረቡ አሰልጣኞች መካከል ግንባር ቀደም ነበሩ፡፡
ማርቲኔዝ የአሰልጣንነት ዘመናቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩት ስዋንሊ ሲቲን የታችኛው ዲቪዚዮን ሻምፒዮን በማድረግ ነበር፡፡ በዊጋን በነበራቸው ቆይታም ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ቡድኑን ከመውረድ በመታደግ አድናቆት አትርፈዋል፡፡ በአራተኛው የውድድር ዘመን ግን ዊጋንን ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ባዶ እጁን አልሸኙትም፡፡ የማርቲኔዝ ልጆች የሮቤርቶ ማንቺንውን ማንቸስተር ሲቲ በማሸነፍ የኤፍ.ኤ ካፑን ድል ማጣጣም ቻሉ፡፡ ኤቨርተን እንዲህ ያለውን አሰልጣኝ ሲሾም ወደ ፊት እንዲያራምደው አስቦ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ
ማርቲኔዝ በተጫዋቾች ዝውውር በኩል ድንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ በተለይ በውሰት ውል ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች ብቃት ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ኤቨርተን እስካሁን ላደረገው ግስጋሴ በጊዜያዊነት ቡድኑን የተቀላቀሉት የዤራርድ ዴሌፋ፣ ጋሬት ባሪ እና ሮሜሉ ሉካኩ ሚና የጎላ ነው፡፡ ማርቲኔዝ ተጨዋቾቻቸውን የሚያስተምሩበት መንገድ ሙገሳን አስገኝቶላቸዋል፡፡ ሮስ ባርክሌይ ‹‹ቅን ሰው›› ብሎ ከገለፃቸው በኋላ ‹‹በርካታ የታክቲክ ልምምዶችን እንሰራለን፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ መልካም ነው፡፡ ወጣት በመሆኔ ብዙ እማራለሁ›› ሲል ለአሰልጣኙ ያለውን አክብሮት ገልጿል፡፡
ከኤቨርተን የተጠበቀው ምን ነበር? አምስተኛ አሊያም ስድስተኛ ሆነው እንዲያጠናቅቁ እና ታላላቆቹ ክለቦች በሚወዳደሩበት መድረክ የመሳተፍን ዕድል ለማግኘት መጣር ነበር፡፡ ከዚያም እንደተለመደው ባዶ እጅ መመለስ እና ከከተማ ባላንጣቸው ሊቨርፑል ጋር የበላይ ሆኖ ለመጨረስ እርባና ቢስ ፉክክር ማድረግ ተጠብቋል፡፡ ሆኖም ግምቶችን ሁሉ ውድቅ በማድረግ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ የሚያስገኘውን ስፍራ ይዞ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እንዳውም በአሁኑ ወቅት ቢያንስ በሂሳብ ስሌት ደረጃ የጉዲሰን ፓርኩ ቡድን ከአርሰናል በተሻለ አራተኛ ሆኖ የመጨረስ ዕድል አለው፡፡ ሌላው ቢቀር ባለፈው ክረምት ከፍተኛ ወጪ ካወጣቸው ቶተንሃም እና ከሞዬስ ዩናይትድ በላይ ሆኖ የማጠናቀቁ ነገር እርግጥ እየሆነ መጥቷል፡፡ በውድድር ዘመኑ መገባደጃ በርካታ ክለቦች ጫና ውስጥ በሚወድቁበት ሰዓት ስድስት ጨዋታዎችን ያለከልካይ ማሸነፍ ችሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቋሳ ምድር …መኮንን ብሩ`

የሜርሲ ሳይድ ደስታ እና ጥርጣሬ
ሁለቱ የመርሲ ሳይድ ክለቦች ምርጥ እግርኳስ ይጫወታሉ፡፡ የሚፈልጉትን ውጤት ማስመዝገባቸው ብቻ ሳይሆን ኳስን የሚጫወቱበት መንገድ በራሱ አስደናቂ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊጉ ሲያጠቃ እጅግ የሚያስፈራው ቡድን ሊቨርፑል ነው፡፡ በመልሶ ማጥቃት ቡድኖችን ከጥቅም ውጪ የሚያደርግበት መንገድ ለተመልካች አዝናኝ ነው፡፡ ኤቨርተንም ቢሆን መልካም እግርኳስ ይጫወታል፡፡ በተለይ በክንፍ በኩል ማጥቃት አሁንም የኤቨርተን መታወቂያው ነው፡፡ ስቲቭ ፒናር እና ሌይተን ቤይንስ በግራ መስመር የሚሰነዝሩት ጥቃት በሞዬስ ዘመንም የነበረ ነው፡፡
ሺመስ ኮልማን እና ኬቪን ሚራላስ በቀኝ መስመር የፈጠሩት የማጥቃት አማራጭ ግን የማርቲኔዝ ውጤት ነው፡፡ ባሪ እና ጀምስ ማካሪቲ የመሀል ሜዳውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት አማካይ ክፍሉ የበለጠ የተረጋጋ ሆኗል፡፡ ሁኔታውን ትኩረት ግቢ የሚያደርገው ኤቨርተን የከተማ ተቀናቃኙ ሊቨርፑል ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ማገዙ ነው፡፡ ኤቨርተን የሚገኘው ቀሪዎቹን ጨዋታ በሙሉ የሚያሸንፍ ከሆነ ቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ የሚያስችለው ደረጃ ማግኘት በሚችልበት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም ሊቨርፑል በማሸነፉ የሚገፉበት ከሆነ እና ኤቨርተን በሜዳው ከሲቲ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ የከተማ ተቀናቃኙ ሻምፒዮን እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ አበረከተ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ የኤቨርተን ደጋፊዎች ግን መራራ ባላንጣቸው ሊቨርፑል ለ19ኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሲሆን ከመመልከት ይልቅ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ቢቀርባቸው እንደሚመርጡ በመናገር ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም እንደ ስልቨ ደስቲን እና ሮስ ባርክሌይን የመሳሰሉ ተጨዋቾች የቻምፒዮንስ ሊግ ምሽቶች ወደ ጉዲሰን ፓርክ ቢመጡ ደስታቸው ወደር እንደማይኖረው በመናገር ላይ ናቸው፡፡

ገንዘብ ተሸንፏል
ሊቨርፑል እና ኤቨርተን በብሪታኒያውያን ተጨዋቾች ዙሪያ ቡድናቸውን መገንባታቸው ድንቅ ሀሳብ እንደሆነ በፌዝ መልክ በተደጋጋሚ ተነግሯቸዋል፡፡ አባባሉ የመነጨው በክለቦች የሚያድጉ ተጨዋቾች ከሌሎች ሊጎች ከሚመጡ ተጨዋቾች በብቃት ያነሱ ናቸው ከሚል እሳቤ ነው፡፡ ምፀታዊው ነገር ግን ሮይ ሆጅሰን ወደ ብራዚል ይዘውት በሚሄዱት ስኳድ ውስጥ ቢያንስ ስምንት ተጨዋቾችን ከሜርሲ ሳይድ ሊመርጡ የሚችሉ መሆኑ ነው፡፡ ስቲቨን ዤራርድ፣ ዳንኤል ስቱሪጅ፣ ራሄም ስቴርሊንግ፣ ጆርዳን ሄንደርሰን፣ ግሌን ጆንሰን፣ ሌይተን ቢይንስ፣ ፊል ጃግዬልካ እና ሮስ ባርክሌይ ወደ ደቡብ አሜሪካዊ ሃገር የመጓዝ ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ሊቨርፑል ዳግም እንደሚያንሰራራ አሊያም ወደ ክብሩ ሰገነት እንደማይመለስ ተገንብዮ ነበር፡፡ ኤቨርተንም ቢሆን የውጭ ባለሀብት የክለቡን ባለቤት ቢል ኬንራይትን እስካልተካ ድረስ ምንም የተለየ ነገር እንደማይፈጥር ተደምድሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሁለቱ የሊቨርፑል ክለቦች በእግርኳስ ከገንዘብ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባው ቴክኒክ፣ ክህሎት እና ጥሩ አሰለጣጠን ለመሆናቸው ጥሩ ማሳያ ሆነዋል፡፡ በቅርቡ ሊቨርፑልን የተቀላቀሉት ተጨዋቾች በሙሉ ለሊቨርፑል መነቃቃት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ አይካድም፡፡ ሱአሬዝን ማቆየት ከፍተኛ ወጪ እንደጠየቀም አይታበልም፡፡ ሲጀመር እርሱን ማግኘት በራሱ ፈተና ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር የተቀባባ አልነበረም፡፡ ሊቨርፑል በፕሪምየር ሊጉ አሁን ያለበትን ደረጃ የተቆናጠጠው ባለፈው ዓመት ባፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ ምክንያት አይደለም፡፡ ከሰባተኛ ወደ አንደኛ ደረጃ መምጣት የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ ኤቨርተንም ቢሆን ይህን ያሳካው በገንዘብ እርዳታ ብቻ አይደለም፡፡ አሰልጣኛቸው አዲስ ታክቲክ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪም ብልህ ነበሩ፡፡ ይህም ልፋታቸውም አንፀባራቂ የውድድር ዘመን አስገኘላቸው፡፡ ከነበሩበት ተራነትም ወደ ከዋክብትነት ተለወጠ፡፡
ሊቨርፑል እና ኤቨርተን የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ክስተቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀጣዩ ዓመት ለከተማዋ በጣም አስደሳች መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የቻምፒየንስ ሊግ ምሽቶች ወደ ከተማዋ የሚመለሱ ከሆነ በርካታ ጎብኚዎች መጉረፋቸው ስለማይቀር የከተማዋ ገቢም እመርታን ያሳያል፡፡ ከእግርኳሷዊ አንፃር ብቻ ከተመለከትነው ሁሉም ተገንታኞች፣ አሰልጣኞች እና የሌሎች ክለብ ደጋፊዎች ቆም ብለው እነዚህን ሁለት ክለቦች ለማየት ይገደዳሉ፡፡ አምነው ባይቀበሉም እንኳን በእነዚህ ሁለት ቡድኖች ትንሣኤ መማረካቸው እውን ነው፡፡