የህ.ወ.ሓ.ት ከሽብርተኝነት መሰረዝ ዘላቂ ሰላምን፣ እፎይታንና ቅቡልነትን የሚያመጣ አይደለም!

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው «ልዩ ጉባኤ» ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት)ን ከአሸባሪነት እንደሰረዘው ማወቅ ችለናል፡፡ ኢዜማ የትኛውም አይነት በሀገራችን ላይ የሚፈጠሩ ልዩነቶች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

በህ.ወ.ሓ.ት ጸብ አጫሪነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተነሳውም ጦርነት ላይ ከዚህ የተለየ አቋም አልነበረውም፡፡ በኢዜማ እምነት ውይይት ተደርጎ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው የሃሳብ ልዩነት ያላቸው አካላት በሙሉ ልብ ፈቃደኛ እስከሆኑ እና የመንግሥት ስልጣን በኃይል እንደማይያዝ መተማመን ሲኖር ብቻ ነው፤ ሕ.ወ.ሓ.ት እነዚህን ሃቆች ለመቀብል ሳይፈልግ ቀርቶ ጦርነትን ሲያውጅ በተቃራኒው ኢዜማ የሀገራችን ህልውና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በፅኑ ስለሚያምን እንደ ፓርቲም ሆነ አባላቱ በጦር ግንባር በመገኘት ከሀገራቸው ጎን ቆመው መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ይህንንም በማድረጋችን ትልቅ ሀገራዊ ኩራት ይሰማናል። የዛሬው የውሳኔ ሂደትም ጊዜውን የጠበቀና ትክክል ካለመሆኑም በላይ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም ዘላቂ ሰላምን፣ እፎይታንና ቅቡልነትን የሚያመጣ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ የወሰነው ውሳኔን ከዚህ በታች በተጠቀሱት ምክንያቶች የሕ.ወ.ሓ.ትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ በጽኑ ይቃወማል፤

  1. በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 6 መሠረት ህ.ወ.ሓ.ት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ አለመፍታቱ፤
  2. በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የትግራይን የሽግግር መንግሥትን የፌደራሉ መንግሥት በበላይነት እንዲያቋቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም አሁንም ሕ.ወ.ሓ.ት በብቸኝነት የሽግግር መንግሥቱ አውራ ኾኗል። ይኽም ሕ.ወ.ሓ.ት ዳግም የሀገር ስጋት የሚኾንበትን ዕድል እንደመስጠት የሚቆጠር ነው። የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እና ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት እንዳይሆን ያሰጋናል፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግሥቱ የስምምነት ግዴታዎቹን ሲወጣ ሕወሓትም ስምምነት ድንጋጌዎቹን ማክበሩን በጋራ በተቋቋመው ጥምር ኮሚቴ መረጋገጡን ከግምት እያስገባ መኾን ነበረበት፤
  3. በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙ፣ ሰብዓዊ ቀውስ ያደረሱ፣ ዜጎችን በጦርነት እንዲማቅቁ ያደረጉ፣ የሀገር ኢኮኖሚና፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ የከተቱ የሕ.ወ.ሓ.ት አመራሮች በሕግ አለመጠየቃቸው፤
  4. በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ትግራይን እንዲቆጣጠር አለመደረጉ፤
  5. የተጨፈጨፉ የሰሜን ዕዝ አባላት የመስዋዕትነት ምልክት የሚኾን ሐውልት ወይም ማስታወሻ በሰሜን ዕዝ ዋና ማዘዣ አለመደረጉ፤
  6. በህ.ወ.ሓ.ት ቆስቋሽነት ሀገራችን ላይ ለደረሰው ውድመትና ሰቆቃ ፍትሕ እና ካሣ አለመሰጠቱ፤
  7. ህ.ወ.ሓ.ት የሚለው የፖለቲካ ድርጅት ስም በሕግ እንዲታገድ አለመደረጉ
ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ቅርስ ቦታዎችን ለድርድር ማቅርብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስመልክቶ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች የተሰጠ መግለጫ

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የሕ.ወ.ሓ.ትን ቡድን ከሽብርተኝነት ሰርዞ ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት ነው። ከዚህ በኋላ በህ.ወ.ሓ.ት አማካኝነት ለሚደርስ ሀገራዊ ጉዳትም ዋነኛ ተጠያቂዎች ገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት እንደሚኾኑ ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን።

ምክር ቤቱ ሌላው ቢቀር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ግዴታዎች አየተፈፀሙ መሆኑን በቅጡ ሳያረጋግጥ፣ ሕ.ወ.ሓ.ት በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ ለፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል ተጠያቂ ሳይሆን እና በሕ.ወ.ሓ.ት የእብሪት ጦርነት የግፍ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ በተለይ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ለሚገኙ ወገኖቻችን ፍትሕ ሳይሰጥ ቡድኑን ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዝ መወሰኑ ታሪክ ይቅር የማይለው ፍርደ ገምድልነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነት እና እሱን ተከትሎ ለደረሰው ሀገራዊ ቀውስ ቁጥር አንድ ተጠያቂ የሕ.ወ.ሓ.ት የሽብር ቡድን እንደኾነ ያምናል፡፡ ሕ.ወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን በመጨፍጨፍ የሀገር ክህደት ፈጽሟል፡፡ የትግራይን ክልልን ሕዝብ ከወገኖቹ ኢትዮጵያዊያን ጋር እርስ በእርስ እንዲተላለቁ እንዲሁም የሀገር ኢኮኖሚ እንዲወድም ያደረገው ይኸው ህወሓት የተሰኘ ድርጅት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ታላቅ ወንጀል የፈፀመ ቡድን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲፋቅ ማድረግ በሕዝብ፤ በፍትሕ እና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ በደል መፈጸም ነው፡፡ የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ያለምንም ተጠያቂነት እና መተማመኛ ከሽብርተኝነት ነፃ ማውጣት ሽብርተኝነት እና የሀገር ክህደት መፈጸምን ለሌሎች ማለማመድ መኾኑን አለመገንዘብ ሀገር ከሚመሩ ኃይሎች የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ እጅ አውጥተው ይህንን ውሳኔ የደገፉ የሕዝብ ተወካዮች በስሙ እንደራሴ የኾኑለትን የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት እና ጥቅምም በአደባባይ እንደናዱት መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጉዳዩ፦ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ እና ራያ ጉዳይ የፍትህ እና የማንነት ጥያቄ ነው።

ኢዜማን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ እንደራሴዎቻችን ህ.ወ.ሓ.ት ከሽብርተኝነት እንዳይሰረዝ ብርቱ ሙግት አድርገዋል። ድምፃቸውንም በተቃውሞ አስመዝግበዋል። በዚህ አጋጣሚ ህ.ወ.ሓ.ት ከአሸባሪነት መነሳት እደሌለበት በምክንያት አስረድታችሁ ውሳኔውን በመቃወም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን ነፃ ያወጣችሁ የምክር ቤት አባላት ምስጋና ይገባችኋል፡፡

ህ.ወ.ሓ.ትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ ውሳኔ ያሳለፋችሁ የገዢው ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በህወሓት ቡድን ለተፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል፣ የሉዓላዊነት መደፈር፣ የሕዝብ ሰቆቃ እና የኢኮኖሚ ውድመት ዕውቅና በመስጠታችሁ እና ተጠያቂነት ባለማስፈናችሁ በእንደራሴነታችሁ የተጎናጸፋችሁትን “ለሕግ፣ ለሕዝብ እና ለህሊና” ተጠሪነታችሁን ከመደምሰሳችሁም በላይ የህወሓት ጥፋት ወራሾች እና የተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂዎች መኾናችሁንም እንገልጻለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.

1 Comment

  1. ውዳጄ ትግሬዎች አማራው ላይ ያደረሱትን በደል ምነው ዘለልከው የአማራው ቁስል ሳይሰማህ ምርጫ ሲደርስ አይንህን በጨዋ አጥበህ ትሄዳለህ አስብበት እንጅ አባ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.