ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች “እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በዓል አደረሳችሁ!” ጌታቸው ወልዩ (ከሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

በዓለማችን የትንሣኤ/ፋሲካ ደሴት ስለመኖሩ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?

በማለት ዛሬ ከትንሣኤ በዓል ጋር በተያያዘ በዓለማችን እጅግ አስገራሚ የሆነችውን “Easter Island” ወይም “የትንሣኤ ደሴት” የተመለከተ ጽሑፍ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁና ለደቂቃዎች አብራችሁኝ ትቆዩ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።

ውድ ወገኖቼ፦ በቅዱስ መጽሐፍ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ (Book of Genesis) አንድ ተወዳጅ ሃይማኖታዊ ታሪክ አለ። በዚህ ሃይማኖታዊ ታሪክ አካልነት ከተመዘገቡት መካከል ደግሞ ይሥሐቅና ርብቃ የሚሰኙ ባልና ሚስት ይጠቀሳሉ። እናም! ይስሐቅና ርብቃ ሁለት መንትያ ልጆችን ወለዱ። የመጀመሪያው ሕጻን “ቅድሚያ የተወለደ” ተሰኘና “ኢሳው” ተባለ፤ ከእናቱ ርብቃ ማህጸን ወጥቶ አዲሱን ዓለም እንደ ተቀበለ።

የኢሳውን እግሮች ተከትሎ ሁለተኛው መንትያ ወደዚች ምድር ተቀላቀለ፤ የአዲሱን ዓለም ሕይወት ሊያጣጥም በወላጆቹ እጆች ላይ እየዋለ። ይህ ተከታይ መንትያ ሕጻን ወንድሙ ኢሳውን እግሮች ተከትሎ የተወለደ፤ “አኃዜ ሰኮና” ማለትም “ተረከዝን ይይዛል!” ወይም “ተረከዝን የሚይዝ!” ተባለና በዕብራይስጥ ቋንቋ “ያዕቆብ” በሚል የተጸውዖ ስም ተጠራ፤ በአባትና እናቱ ልብ ውስጥም የሐሴት (የደስታ) አዝመራ እየዘራ።

ከጊዜ በኋላ አውሮፓውያንም “ያዕቆብ” የሚለውን ስም ይመርጡት ጀመር። እናም! ብዙ ወንድ ልጆቻቸውን “to follow”፣ “to be behind”-የሚከተል፣ የተከተለ፣ ተከታይ፣ ከኋላ የመጣና የወጣ፣ ከኋላ ወይም ቀጥሎ የተወለደ እያሉ ወንድ ልጆቻቸውን “ጃኮብ” እያሉ ይጠሯቸው ገቡ።

በዚሁ መሠረት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ፌብሩዋሪ 1 ቀን 1659 በቀድሞዋ “ደች” በአሁኗ አውሮፓዊቷ አገር “ኔዘርላንድስ” ወይም “ሆላንድ” አንድ ሕጻን ልጅ ተወለደ።

የሕጻኑ ልጅ አባት የሆነው የሥነ-ፈለክ (astronomy)፣ ጂኦግራፊ፣ ፍልስፍናና የመርከብ ጉዞ ኀልዮት (ንድፈ-ሀሳብ) “the theory of navigation) እውቀት የነበረው የሂሳብ ጠቢቡ አሬንድ ሮጌቪንና እናቱ ማሪያ ስቶርም ልጃቸው የአባቱን እግሮችና እውቀት ተከታይ አሉና “ጃኮብ” የሚል ስም አወጡለት። በጥሩ ሁኔታ አሳደጉት። አስተማሩትም። ጃኮብም በርድዊክ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በሕግ ዶክትሬት ዲግሪ ጭምር አገኘ። በደች ዌስት ኢንዲያ ኩባንያና በሌሎችም ኩባንያዎች ተቀጥሮ ሠራ። የውሃ ጉዞ ላይ ጥናት ጀመረ። በጥንታዊ የደች ሮያል ባህር ኃይል አባልም ሆነ። ጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቶት አድሚራል ጃኮብ ሮጌቪን የሚል ትልቅ ሹመኛ ሆነ፤ በስሙ ገነነ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያኒዝም (Utopia ምድረ ገነት) የእኛ ፍትሀዊ መንግሥት - በገ/ክርስቶስ ዓባይ        

እናም! ጎርጎሮሳዊያኑ አመት 1722 በ62 ዓመቱ፤ በባህር ኀይል አባልነቱ የባህር ጉዞ አመላክቶት፤ የአባቱ አሮንድ ሮጌቪን የመርከብ ጉዞ አሳሽነት ንድፈ-ሀሳብ ተግባራዊ ምንዛሬ ገብቶት፤ የፓስፊክ ውቅያኖስ ፈታኝ አሳሽነት ወልፍ ጠርቶት፤ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ታሪክ ለመሥራት ተዘጋጀ። ለጉዞ የሚሆኑት መርከቦችን እያበጃጀ።

ዝግጅቱን ካጠናቀቀ በኋላም ሦስት መርከቦችንና ምድብተኞቹን ይዞ በመጎዝ በዘመናችን እንግሊዝና አርጀንቲና “በይገቡናል” ጥያቄዎች ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ገብተውባቸው ወደ ነበሩባቸው ፎክላንድ ደሴቶች ገሰገሰ፤ እንዳሰበውም ደረሰ። የፎክላንድ ደሴቶች ስማቸውንም ቀይሮ “ቤልጂያ አውስትራሊስ” ብሎ ጠራቸው።

ከዚያም በ”ሊ ሜየር ባህር ሰርጥ ወይም ወሽመጥ” በኩል አቋርጦ ወደ ፓስፊክ ውቅያኖስ ተጓዘ። በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ተጉዞም ወደ ጁዋን ፈርናንዴዝ ደሴቶች በመድረስ ከፌብሩዋሪ 24 እስከ ማርች 17 ቀን 1722 ድረስ ደሴቶቹ ላይ ሰነበተ። ቀጠለና በታሪክ ትምህርት ወደምናውቀው የደቡባዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ አካል ወደሆነችውና የፖሊኔዥያ ሦስትዮሽ ማዕዘናዊ ሥፍራ (ፖሊኔዥያ ትሬያንግል) ላይ ወደምትገኘው ደሴት አመራ። እዚያም ትንሣኤ ወይም የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ዕለተ- እሑድ ኤፕሪል 5 ቀን 1722 ማለትም መጋቢት 27 ቀን 1714 ዓመተ-ምህረት ደረሰ።

ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሊ 2ሺ 237 ማይል ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ምትርቀው፤ በአገርኛ መጠሪያዋ “ራፓ ኑኢ” ወይም “ትልቁ ራፓ” (Big Rapa) ወደምትሰኘው፤

ከዓለማችን ዝቅተኛ ሥፍራዎች አንዱ ወደሆነችው ደሴት ላይ እግሮቹን እንዳሳረፈም፤ ደሴቷን በትንሣኤ በዓል ስም “Easter Island” በማለት ጠራት። ደሴቷም የትንሣኤ ወይም ፋሲካ ደሴት ተባለች። ስሟንም በአሳሽነት መዝገብ ላይ አስጻፈች።አሳሹ ጃኮብም ከሁለት እስከ ሦስት ሺ የሚገመቱ ነዋሪዎች ይኖሩባታል ሲልም ለዓለም አበሰረ። ከ63 እስከ 69 ማይል ስፋት እንዳላት ተናገረ። እሳተ-ገሞራ የሚበዛባቸው ክፍሎች፣ በባህር ዛፍና በሣር የተሸፈነ ምድርን ጨምሮ “ሀንጋ ሮኣ” የሚሰኙ በአስገራሚ ሁኔታ የተጠረቡና የተደረደሩ ጥንታዊ የድንጋይ ሐውልቶች እንዳሏትም መሰከረ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ርዕሠ አንቀጽ፡ የሙስናን ዛፍ ለማድረቅ ቅርንጫፉን ብቻ መቁረጥ በቂ አይሆንም

የትንሣኤ ደሴት ከፍተኛ ሥፍራ ከባህር ወለል በላይ 1ሺ 640 ጫማ ከፍታ ያለው “ቴሬቪካ” በትንሣኤ ደሴት ላይ ካሉ አጭር ዕድሜ ካላቸው አሥር የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታዎች የተፈጠረ መሆኑንም አመላከተ።

ሁለተኛው የሦስትዮሽ ማዕዘኑ እሳተ-ገሞራማ ክፍል ደግሞ በምሥራቅ የትንሣኤ ደሴት የሚገኘው “ፑካ ቲያኬይ” የሚሰኘው ሥፍራ እንደሆነም ገለጸ።

ሌላኛው የሦስትዮሽ ማዕዘኑ እሳተ-ገሞራማ ክፍልም “ራኖ ካዉ” እንደሚሰኝና በትንሣኤ ደሴት ደቡባዊ ክፍል እንደሚገኝ አሳወቀ። ነዋሪዎቹም በዛፍ ግንድ ጉማጅ ጀልባዎችና መርከቦች እየሠሩ በባህር ይጓጓዙ እንደ ነበር፤ እንሽላሊቶች፣ ጥቂት ዝርያ ያላቸው የዓሳ ዓይነቶችና ሦስት አጽቄዎች (ነፍሳት) እንዳሉ የአሰሳውን ውጤት ይፋ አደረገ።

በዚህን ጊዜም ዓለምም ስለፖሊኔዥያን ሦስትዮሽ ማዕዘን ሥፍራ (ፖሊኔዥያ ትሬያንግል) ለማወቅና ለማየት ይናፍቅ ገባ። አሳሹ አድሚራል ያዕቆብም ሁነኛ አሳሽነቱን አስመስከሮ፤ የግራሞት የአሰሳ ታሪክ ቀምሮ፤ በሕያው ዘላቂ ታሪክ የአሰሳ ጥያራ አሳፍሮ ለዘመናዊው ዓለም ትውልድ አስተላለፈ።

ጥንታዊ ታሪክና ሀይማኖት ያሏቸው አገሮችና ሕዝቦችም “ኢስተር አይላንድን” በየአገሮቻቸው ቋንቋዎች በፋሲካና ትንሳኤ በዓል መታሰቢያነት ደሴቷን መጥራት ጀመሩ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘመን ከ1888 አንስቶ የቺሊ አካል የሆነችውን የደሴቷን ታሪክም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በምኅጻረ-ቃል “ዩኔስኮ” ተጠንቅቆ ተረዳ እና እንደ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች የሆኑት አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ ጢያ ትክል ድንጋዮች፣ ላይኛውና ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ሁሉ የትንሿ ትንሣኤ ደሴት ትክል ድንጋዮችን በቅርስነት መዘገበ። ራፓ ኑኢ የተሰኘው ብሔራዊ ፓርክም በዩኔስኮ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ሰፈረ። የዚህን ጊዜም ዓለም አጥብቆ ስለ ትንሣኤ ደሴት ለማወቅ ሞከረ።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም የትንሣኤ ደሴት ታሪክን ከ12 አመታት በፊት በአንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ ለወገኖቹ አጋራ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሁላችንም ሰው ነን “ ።ብለን ካላመንን ሠላምን አናገኛትም -  መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እነሆም ዛሬ የትንሣኤ በዓል ሲከበር፤ በሃይማኖተ-አበው ዘሄራንዮስ በምዕራፍ 7፥16 “ተሰቅለ፤ በሥጋ ወተቀነወ ዲበ ዕፀ-መስቀል፤ ሞተ፤ ወተገነዘ፤ ወተቀበረ፤ ወተንሥአ እምነ ምውታን” ማለትም “በሥጋ ተሰቀለ፤ በመስቀል ላይም ተቸነከረ፤ ሞተ፤ ተገነዘ፤ ተቀበረ፤ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ።” የሚለውን ታላቅ መልእክት እያሰበ የትንሣኤ ደሴትን ታሪክ ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አካፈለ።

እናንተም ከፊል ሞቃታማ የአየር ንብረት ባላት፤ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ በአማካይ 60 ዲግሪ ፋራናይት ሙቀት፤ እስከ የካቲት ደግሞ ሙቀቱ 75 ዲግሪ ፋራናይት እንደሚደርስ፤ ከመጋቢት እስከ ጥቅምት ዝናብ በአብዛኛው ዝናባማ እንደሆነች በሚነገርላት፤ ግንቦት በእርጥበታማ ወርነት በተመዘገበባት የትንሣኤ ደሴት፤ አንድ ማዘጋጃ ቤት፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ የብሔራዊ ቡድን ያህል የሚቆጠሩ እግር ኳስ ተጫዋቾችና ደሴቷን የሚያስተዳድር ከንቲባ እንዳላት እኔ እነግራችኋለሁ።

የዛሬን የትንሣኤ ደሴት ቅኝቴን ሳጠቃልልም፦ የፋሲካ በዓልን ስናከብር አህያን ከጅብ፤ አዝመራን ከዝንጀሮ፤ ዶሮን ከሸለምጥማጥ-የበግና ፍየል ግልገልን ከቀበሮ፤ አህያና ፈረስን፤ በቅሎና ግመልን ከጎርፍና ከአጥቂ ዱር አውሬ ጥቃት፤ ላምና በሬን፤ በግና ፍየልን ወድቆ ከመጎዳት፤ ቤትንና የእህል ክምርን ከእሳት ቃጠሎ ጥፋት፤ የኢትዮጵያ ልጆችን ከፈተና መአት ለማዳን የምናደርገውን ቀደምት የኢትዮጵያዊኛ የመተዛዘንና የመተሳሰብ ስሜት ዛሬም እንድናጎለብተው አክብሬ በመጠየቅ ይሆናል።

በመጨረሻም፦ገባሬ ሠናይ የሆነው፤ የምድርን ጠርዝ በስንዝሩ የሚለካው፤ በይቅርታውና ምህረቱ ብዛት ወረታው ተከፍሎ የማያልቀው፤ አስቦ ማድረግን ጀምሮ መጨረስን የሚያድለው አምላክ ክብርና ምስጋና ይግባው እያልኩኝ፤ ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መልካምና የተሳካ የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ እላለሁ። በዓለ ሀምሳንም በሰላም፣ በፍቅርና በጤና ታሳልፉ ዘንድ የኢትዮጵያ አምላክ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንላችሁ በማለት አገራችን ኢትዮጵያንም በፈቃዱና ምህረቱ ይጎበኝልንና ይባርክልን ዘንድ እለምናለሁ።

ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ዲያብሎስን አሰረው፤ አዳምን ነጻ አወጣው፡፡ ሰላም! ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ኾነ፡።ሠናይ ዘመን! (ጌታቸው ወልዩ)

cgg335vbb

Leave a Reply

Your email address will not be published.