ጎበዝ፣ ወደቀልባችን ብንመለስ አይሻለንም? ሀገራችን እኮ አይናችን እያየ ከጃችን ልትወጣ ነው፡፡

Ethiopia 1 1ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትያን ሆኖ እስላሟን ቆንጆ ያላፈቀረ ወይም ያላገባ ወይም እስላም ሆና ሳለ ከክርስትያን አቻዋ ጋር ያልተዳራች ወይም ያልተሞሸረች ወገን ማየት ያን ያህል ብርቅ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው በአንድ በሆነ ቤተ-ሰብ ውስጥ አባዎራው ኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ እማዎራዋ ያሻት አይነት እስላምና ልጆቻቸው ደግሞ እንደየምርጫቸው የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት ወይም የሌላ የማናቸውም አይነት እምነት ተከታዮች ሆነው ብናገኛቸው እምብዛም ሊገርመን ከቶ የማይችለው፡፡

ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሀይማኖተኞች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በሚከተሉት እምነትም ሆነ በቅርጽ ተለያይተው በሚፈጽሙት አምልኮ ምክንያት ከመራራቅ ይልቅ አብዝቶ መቀራረብን የሚመርጡ ህዝቦች ናቸው ተብሎ በአለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ ዘንድ ሳይቀር ይታመናል፡፡

ይህ በሚገባ እየታወቀ በኢትዮጵያውያን መካከል ሆነ ብሎ የቡድን ጠብ መጫርና እስከደም መፋሰስ ሊደርስ የሚችል ግጭት ማቀጣጠል በምድር ከባድ ወንጀል ሲሆን በሰማይ ደግሞ ከሁሉም የባሰ መሪር ሀጢኣት መሆን አለበት፡፡

እኔ በተወለድኩበት አካባቢ የእስላሞችና የክርስትያኖች ልዩነት ሰው-ሰራሽ መስሎ እስኪታይ ድረስ በጅጉ የደበዘዘ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ ይህንኑ የሚያረጋግጥ አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጋራችሁ ወድጃለሁ፡፡

ኩነቱን በምድጃ ዙሪያ ለተሰባሰብነው ለኔና ለመሰል ዎንድምና እህቶቼ በልጅነታችን የተረከችልን አፈሩ ይቅለላትና ሴቷ አያቴ እማሆይ እማዋይሽ ታምራት ደርሶ ነበረች፡፡ መነኩሴዋ አያቴ እማዋይሽ፣ (በቤጌምድር እሚታችን ነው የምንላት)፣ በጊዜው አብዝታ የምትወዳትና ከእስላም ቤተ-ሰብ የሆነች ብርጭቆ መሃመድ የምትባል የልጅነት ጓደኛ ነበረቻት፡፡ እርሷ እንዳወራችልን ከሆነ በ14ና በ15 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙት ሁለቱ ፍልቅልቅ ኮረዶች በአካባቢው ዘይቤያዊ አነጋገር የቅቤ ቅል የሚያስንቁ ውብ፣ ወዛምና ማራኪ ቆነጃጅት ነበሩ፡፡

የትውልድ መንደራቸው በጎንደር፣ ደንቢያ ወረዳ መገጭ ወንዝን ተንተርሳ የተቆረቆረችውና ልዩ መጠሪያዋ ደብረ-ብርሃን የምትባል ስፍራ ስትሆን እስላሞችና ክርስትያኖች በከፍተኛ ደረጃ ተሰባጥረውና በስፋት ተጎራብተው ይኖሩባታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አጭር ቅኝት: የኦሮሙማ አፈግፍጉ ሴራ እስከ ግማሽ ነጻ መውጣትና ለድርድር እስከ መሞዳሞድ ድረስ (እውነቱ ቢሆን)

ወቅቱ የሰርግ ወቅት ሲሆን ከእለታት በአንደኛው ቀን ለአቅመ-አዳምና ለአቅመ-ሄዋን የደረሱ ወጣቶች ተሞሽረው፣ በአካባቢው ባህል መሰረት አምረውና ደምቀው እየተከበሩ ነው፡፡ ለእስላሙም ሆነ ለክርስትያኑ ታዳሚዎች እንደየእምነታቸው የየራሳቸው ፍሪዳ ተጥሎላቸው ጮማ ይቆረጣል፣ እስከፉንት ይበላል፣ ይጠጣል ይጨፈራል፡፡ ታዲያ ይህንን የተመለከቱትና ሰርጉን የተቀላቀሉት እነዚያ ሁለት ታዳጊ ልጃገረዶች የመብል ሰአት ሲደርስ ከየወላጆቻቸው በኩል በመጠነኛ ጥበቃና ቁጥጥር በነፍስ-ወከፍ የታደላቸውን የስጋ ጉማጅ ከተረከቡ በኋላ ተሯሩጠው ወደጓሮ ወሰዱና ግራ-ቀኙን ከተመለከቱ በኋላ በዙሪያቸው ማንም እንደሌለ ሲረዱ የተሰጣቸውን ስጋ እንደየእምነታቸው የተለያየ ማብሰያ ተጠቅመው ለየብቻቸው መጥበስን ወይም መቀቀልን ፈጽሞ አልመረጡም፡፡ ቀድሞ ነገር ሃሳቡ ራሱም ከናካቴው አልመጣላቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ወደአንድ የጋራ ብረት ድስት ጣዱና እስላሙም ሆነ ክርስትያኑ የባረከውን ስጋ በአንድ ላይ ቀላቅለው እየተሳሳቁ በቶሎ ይበስልላቸው ዘንድ ብቻ ተራ በተራ ያማስሉት ጀመር፡፡ ለነርሱ እስላምና ክርስትያን መባላቸው ያን ያህል ትርጉም የሚሰጣቸው ጉዳይ አልነበረም፡፡ በሰዋራ ስፍራ እንደመቀመጣቸው መጠን ወላጆቻቸው ከሚከተሉት እምነት ላለማፈንገጥና ከየቤተ-ሰቦቻቸው የተላለፈላቸውን ሀይማኖታዊ አስተምህሮ ሙሉ በሙሉ ላለመደርመስ ብቻ ብርጭቆም ሆነች እማዋይሽ ሀይማኖታቸውን ታሳቢ በማድረግ ከየጎራው የተቀበሉትን እእያንዳንዱን የስጋ ጉማጅ አብረው ለመቀቀል ቢወስኑም ስጋዎቹ ወደብረት ድስቱ ከመግባታቸው በፊት የብርጭቆ ድርሻ እየተለየ በሸማኔ ቁጢት እንዲታሰር ሀይለኛ ዘዴ ቀየሱ፡፡ ይህ ማለት ታስሮ የተቀቀለው እያንዳንዱ የስጋ ጉማጅ ከበሰለበት የጋራ ብረት ድስት ያው እንደታሰረ ይወጣና የብርጭቆ ድርሻ መሆኑ እየተረጋገጠ ይበላል ማለት ነው፡፡ በቁጢት ሳይታሰር ራቁቱን ገብቶ የበሰለውን ደግሞ የኔይቱ አያት እማዋይሽ አውጥታ ትበላለች ማለት ነው፡፡

አያቴ እንደነገረችኝ በእምነታቸው ሳቢያ በማእድ ላለመለያየት የወሰኑትን እነዚያን ሁለት ለጋ ልጃገረዶች የመረቁ አንድነት እምብዛም አላሳሰባቸውም፡፡ ከተጋለጡ ግን ሊደፉት አስበው ነበር፡፡
የፈሩት ነገር በርግጥ አልቀረላቸውም፤ ከእስላምና ከክርስትያን እርዶች በተናጠል የተወሰደው ስጋ ተቀላቅሎ አንድ ላይ በሚቀቀልበት የጋራ ብረት ድስት ፊት ሁለቱም አጎንብሰው በሰርጉ ስሜት እየተፍነከነኩ ሲያማስሉ ተመልካቾች ከርቀት አይተዋቸው ኖሮ በተደረሰባቸውና በተጠየቁ ጊዜ የብርጭቆ ድርሻ ተለይቶ እንዲታወቅ በሸማኔ ቁጢት እየታሰረ ወደብረት ድስቱ የገባ ስለመሆኑ በጣፋጭ የልጅ አንደበት እየተንተባተቡ ለማስረዳትና ራሳቸውን ለመከላከል ሞክረዋል፡፡ ያም ሆኖ ሁኔታውን አይተውና ሰምተው የተገረሙት ቤተ-ሰቦቻቸው በምክርና በተግሳጽ አለፏቸው እንጂ በጥፋተኝነት እንዳልቀጧቸው ውዷ አያቴ ሲቃ የሚያስይዝ ትዝታዋን እያስታወሰች አጫውታኛለች፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  (ለትውስታ) አቡበከር አህመድ ከመታሰሩ በፊት ከራድዮ ፋና ጋር ያደረገው ቃለምልልስ - [ሊደመጥ የሚገባና አዲሱን የወያኔ ሴራ የሚያጋልጥ]

ይህ ነው እንግዲህ የቆየውና ዘመናትን የተሻገረው ማሕበራዊ እሴታችን፡፡

በነገራችን ላይ ቁጢት ማለት በሀገር ቤት የሸማ ስራ ባለሙያዎች፣ (ሸማኔዎች ይባላሉ)፣ እንደኩታ፣ ጋቢና ቀሚስ የመሳሰሉትን ባህላዊ አልባሳት ሲሰሩ በአመራረት ሂደት ወቅት በቁርጥራጭ ተረፈ-ምርትነት የሚቀረው የተነባበሩ ክሮች ገመድ ነው፡፡፡ የአልባሳት ስራው ቅሪት በመሆኑ ጥቅም እንደማይሰጥ ተቆጥሮ በዘፈቀደ የሚጣል ቢሆንም ጠንካራው ቁጢት በገጠር እንደሲባጎ አንዳንድ ነገሮችን ለማሰር ወይም እርስበርስ ለማያያዝ ያገለግላል፡፡

Remark of the Author: This version is the revised and elaborated one following the original postage of its preliminary document.

Leave a Reply

Your email address will not be published.