የህይወት አልባ መግለጫ ፖለቲካ – ጠገናው ጎሹ

የህይወት አልባ መግለጫ ፖለቲካ

June 5, 2022

ጠገናው ጎሹ

የርዕሴ አንደኛው ቀጥተኛ ትርጉም ህይወት የሌው ወይም የሞተ ለማለት ሲሆን ሌላውና እኔ ለማለት የፈለግሁበት ትርጓሜ ደግሞ ማድረግ የምንፈልገውን በጎ  ዓላማና ግብ በፅዕኑ መርህ ፣ በማይናወጥ የሞራል ልእልና ፣ በማይሸበር የሥነ ልቦና ሰብእና ፣ ብቁ በሆነ  አእምሯዊ ንቃት ፣ እና በማይፍረከረክ ድርጅታዊ አቅም ሃላፊነታችንን መወጣት ተስኖንን የባለጌዎችና የግፈኞች ሥርዓት ሰለባዎች የመሆናችንን አስከፊ ሁኔታ የሚገልፅ ነው።

አዎ! በእኩያን የህወሃት ፖለቲከኞች የበላይነት እየተዘወረ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የዘለቀውን እና ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ደግሞ በተረኛ ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን የበላይነት እየተመራ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ በማውረድ  ሦስት አሥርተ ዓመታት ያስቆጠረውን ሥርዓት እንኳን ለማስቆም አደብ ለማስገዛት የማይችል መግለጫ በአካል ህይወት አልባ ባይሆንም የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን ከማድረግ የፖለቲካ የሞራል ልእልና  አንፃር  ግን ህይወት አልባ (በቁም የሞተ ነው) ።

በሦስት ማለትም እናት ፣ መኢአድ እና ኢህአፓ በተሰኙ የተቃውሞ (እነሱ ተፎካካሪ ነን ይላሉ) ፓርቲዎች የተሠራጨውን ሰሞነኛ መግለጫ በጥሞና ለመረዳት ሞክሬያለሁ ።  የሥርዓት ለውጥ እንጅ የኢህአዴግ ጉልቾች መቀያየር ጨርሶ እንደ ለውጥ ሊታይ አይችልምና ይልቁን የሚሻለው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ጊዜ መንግሥት በሚመሠረትበትና ወደ ሥራ በሚገባበት ሁኔታ ላይ መነጋገር ነው ። በአሳዛኝ መልኩ  እጅግ ጥቂት ከሆኑት በስተቀር አብዛኛው የተቃውሞ ፖለቲከኞች የተጠመዱት ለእኩይ ገዥዎች አቤቱታ በማቅረብና  የማስመሰል የውግዘት መግለጫ እያዘጋጁ እወቁልን በሚል እጅግ የወረደ የፖለቲካ ጨዋታ አካል መሆን ነው።

በዚህ  በሰሞኑ መግለጫቸው ጠብቄው የነበረው የእኩይ ገዥዎችን ጭራቃዊ ባህሪ ወይም ተግባር ማውገዙ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላውና ዋናው መልእክት በኢትዮጵያ ልዑላዊነት፣ አንድነት፣ በዴሞክራሲ አስፈላጊነት፣ በህግ የበላይነት እና ተያያዥ መርሆዎች ላይ ተመሳሳይ እምነትና አቋም ላላቸው አገራዊ ድርጅቶች እና በረጅም ጊዜም ቢሆን የዚህ እምነት ተጋሪዎች ሊሆኑ ለሚችሉ በጎሳ ማንነት ላይ ለተደራጁ ድርጅቶች ከምር የሆነ የእንመካከርና እንተባበር ጥሪን ነበር።

እንዲህ አይነት እጅግ ወቅታዊና አንገብጋቢ የሆነ የግፈኛ ገዥዎችን የሃይል ሚዛን የሚገዳደር የፖለቲካ ካምፕን (ሃይልን) የመፍጠር የጋራ ጥሪና ጥረት በሌለበት ህዝብን ለሰላም ፀንተህ ቁም (ታገል) የሚል እጅግ ደምሳሳ (ጅምላ) ጥሪ ተናግረናል ወይም አሳስበናል ከማለትና የመከራና የውርደት ሥርዓትን ከማራዘም ጨርሶ አያልፍም።

አዎ! በመከረኛው ህዝብ ላይ ይህንን ያህል ዘመን ማቆሚያ የሌለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲወርድ  የፋይል መደርደሪያዎቻችንን ያጣበቡ መግለጫዎች የት አደረሱን ወይም ምን ፈየዱልን ? በእነዚህ ለቁጥር በሚታክቱ መግለጫዎቻችን መካከል ምን የታየ ለውጥ (difference) ነበር? አሁንስ ይህ  መግለጫ መሬት ላይ ካለው መሪር ድክመታችን ጋር እንዴት ይጣጣማል? የዚህ ሁሉ መከራና ሰቆቃ ዋነኛ ምክንያት ፈፅሞ ሊፈወስ በማይችል የፖለቲካ ካንሰር የተመረዘው ኢህአዴጋዊ (ብልፅግናዊ) ሥርዓት መሆኑን  ከበቂ በላይ እያወቅን እንዴት ለእርሱ የአቤቱታ መግለጫ እየላክንና የይስሙላ  የውግዘት ጩኸት እየጮህን እንቀጥላለን ? ነገና ከነገ ወዲያ በዚሁ አይነት ህይወት አልባ ጩኸትና መግለጫ እንደማንመለስ ምንድነው ማድረግ ያለብን? ብሎ የማይጠይቅ ተቀዋሚ ተብየ ፖለቲከኛ በሚተራመስበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ዴሞክራሲያዊት የምትሆን አገርን ፈልጎ ማግኘት ይቸግራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሸባሪው ትህነግ አጥቂ ወይም ጠብ አጫሪ መንጋን ለእኩይ አላማው እይተጠቀመ ነው

የክፉ ገዥ ቡድኖችን ማቆሚያ ያልተገኘለት ጭራቃዊ ሥርዓት ማውገዙ እንደተጠበቀ ሆኖ ከህይወት አልባ መግለጫና ጬኸት ያለፈ በጋራ የመጠራራትና የመተባበር ትግል ያልተደገፈ የተቃዋሚነት እንቅስቃሴ እውን የሚያደርጋት ዴሞክራሲያዊት አገር ልትኖር አትችልም።

አዎ! በእውነት ከተነጋገርን አያሌ ንፁሃን ዜጎች በአራት ዓመቱ የአብይ አሀመድ አገዛዝ  ጨካኝ ፖለቲካ ወለድ ሰይፍ በአስከፊ ሁኔታ ከመኖር ወደ አለመኖር የተለወጡበትን ፣ ከገንዛ አገራቸውና ቀያቸው እተሰደዱ የቁም ስቃይ ሰለባዎች የተደረጉበትን  ፣ እና ሠርተው የእለት ጉርሳቸውን ማሸነፍ ይችሉ የነበሩዜጎች ፈፅሞ ሰላም በማጣት ምክንያት  ለፍፁም ድህነት (የርሃብና የበሽታ ቸነፈር) የተዳረጉበትን አስከፊ ሥርዓት በህይወት አልባ  የመግለጫ ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እየተንቦጫረቁ ለዴሞክራሲያዊት አገር እውን መሆን ቆመናል ማለት ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ከመንግሥት ተብየው ጡቻ ወይም የአድርባይነት ፍርፋሪ ነፃ የሆነ ዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ  ድርጅት (ተቋም) የለምና “ህዝብ ከፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አዙሪት ሰብሮ እንዲወጣ ማገዝ ምድራዊና ሰማያዊ የሆነ የጋራ ተልእኳችን ነውና በጋራ እንነሳ” ብሎ ከምር ከመጠየቅ ይልቅ “እባካችሁ” እያሉ መማፀን ጨርሶ የትም አያደርስም።  ይህ ደግሞ ክስተቶችን እየተከተሉ ህይወት አልባ መግለጫና ጩኸት ከማሰማት ክፉ ልማድ በመውጣት የድርጊት ስትራቴጅና ስልት ነድፎ ህዝብን ማንቃትንና ማደራጀትን ግድ ይላል።

በአመራር ሸፍጠኝነትና ሴረኝነት ክፉ ልክፍት የተለከፉት አብይ አህመድና ካምፓኒው (ፓርቲውና መንግሥቱ) የፈፀሙትንና እየፈፀሙ ያሉትን አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ዛሬ በመግለጫ አወገዝኩና ለህዝብ ጥሪ አቅርብኩ የሚል  መግለጫ  አወጣሁ ባለ በማግሥቱ ቤተ መንግሥት ተጠርቶ የምሳ ወይም የራት ግብዣ ላይ  የተለመደ የማደንዘዣ ዲስኩር (ሌክቸር)  ሲደረግለት “መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶልኛልና ከመንግሥት ጋር ተባብረን እንሥራ” የሚል የተቀዋሚ ድርጅት ተብየ  ፖለቲከኛ በበዛበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ምን አይነት ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ እንደሚቻል ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት በእጅጉ ይከብዳል ።

እንኳንስ የአገርን ያህል ታላቅ ጉዳይ የትኛውንም የግል ወይም የጋራ ጉዳይ በተመለከተ ሃሳብን ፣ አስተያየትን፣ አቋምን እና መወሰድ የሚገባውን መፍትሄ (እርምጃ) በይፋ የመግለፅ (የማሳወቅ) አስፈላጊነት የሚያጠያይቀን አይመስለኝም። የመግለጫ (staement) መሠረታዊ ትርጉምና ዓላማም የኸው ነው።

አዎ! መግለጫ ስንል ይመለከተናል የምንለው ጉዳይ ሃላፊነትና ተጠያቂነት በሚሰማቸው መሪዎች አማካኝነት በተፈለገው አቅጣጫ፣ መጠንና ፍጥነት እየሄደ ከሆነ ይበልጥ እንዲጎለብትና የታለመለትን ዓላማና ግብ እንዲመታ፣  በተቃራኒው ከሆነ ግን ገንቢነት፣ ወቅታዊነት ፣ አስተማማኝነትና ዘላቂነት ባለው የእርምት እርምጃ የባለጌና ግፈኛ መሪ ተብየዎችን ሥርዓት ማስወገድን በሚጨምር የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ተጋድሎ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ በማስገባት የታለመለትን መልካም ራዕይ ፣ዓላማና ግብ እውን ማድረግ እንደምንፈልግና እንደምንችል ግልፅ የምናደርግበት የመገናኛ ዘዴ (means of communication)  ነው ።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያችን በአምሳሉ ጠፍጥፎ ከሰራቸው የህወሃት ቡድን ጋር የፍፁም ታማኝ አገልጋይነት ቃል ኪዳን ገብተው የዘመናት ፍላጎቱና ጥያቄው ዴሞክራሲያዊት የሆነች የጋራ አገር እውን የማድረግ  እንጅ አገርን አሸንሽኖና ሸንሽኖ  እርስ በርሱ መናቆርና መገዳደል ያልነበረውንና ያልሆነውን መከረኛ ህዝብ በአስከፊው የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ  ከረጢት ውስጥ አስገብተው  የሁለንተናዊ መከራና ቁስቁልና ዶፍ ሲያወርዱበት  የነበሩ እኩያን የኢህአዴግ ውላጆች ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት ደግሞ  እጅግ አስከፊ በሆነ የሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ውስጥ ክፉኛ  ሲራኮቱ ከቆዩ በኋላ  ፈጣሪያቸውንና የበላይ ጠርናፊያቸውን ህወሃትን ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወደ መቀሌ ቤተ መንግሥት ሸኝተው ሥርዓቱን ግን ይበልጥ  አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ  ያስቀጠሉባትና ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል የሆነች ኢትዮጵያ ነች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሀገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ልቅምቅም አድርጎ ለማስወገድ

መቸም የገንዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ በመጋፈጥ የሚበጀንን ከማድረግ ይልቅ ለራሳችን የውድቀት አባዜ እጅግ ስንኩል (ልፍስፍስ) ምክንያት (ሰበብ) እየደረትን ራሳችንን ከማታለል ክፉ ልክፍት ሰብረን ለመውጣት ባለማቻላችን ነው እንጅ እጅግ ግዙፉና መሪሩ  እውነት ይኸው ነው።

ሥርዓቱን በማነኛውም ዘዴ (by hook or crook)  ለማስቀጠል ከቆረጡ ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ፣ ይህ ሥርዓት ተወግዶ   ዴሞክራሲ እውን የሚሆን ከሆነ ያለምንም እውቀትና ክህሎት የሚሰፈርለት ፍርፋሪ ይቋረጥብኛል በሎ ከሚጨነቀው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የካድሬ ሠራዊት ፣ በለየለት ወራዳና  አዋራጅ የአድርባይነት ደዌ ከተለከፈው  ምሁራን ነ ኝ  ባይ ወገን  ፣  ኢዜማንና አብንን ከመሰሉ  ወራዳና አዋራጅ የአብይና ካምፓኒው ልጣፎች (አሻንጉሊቶች)  ፣ እና የህዝብ ከመከራና ከውርደት የመላቀቅ ጥያቄ ከምር መልስ እንዲያገኝ ሳይሆን በስሙ እየማሉና እየተገዘቱ  ከቀጠሉ ተቀዋሚ ተብየ ፖለቲከኞች በስተቀር በተለይ በአራት ዓመታት የተፈፀመውና አሁንም የቀጠለው እጅግ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ዋነኛ ፈጣሪና ዘዋሪ በሆኑ ፖለቲከኞች መሪነት እውነተኛ አወንታዊ ለውጥን ተስፋ የሚያደርግ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

አገራችን ካለችበት እጅግ አስከፊ ሁኔታ አንፃር በመነሳት የምናዘጋጃቸውና ይፋ የምናደርጋቸው መግለጫዎች (official statements) ትኩረት የምናራምዳቸው ሃሳቦቻችንና  አቋሞቻችን ሊያሳድሩ የሚችሏቸው ተፅዕኖዎችን በሚያገናዝብ ፣ የድርጊት አካሄዶቻችን የሚያስከትሏቿው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤቶችን በአግባቡ እየገመገመ በሚራመድ እና በምን ይደረግ (what is to be done) ጥያቄ  ዙሪያ  በሚያጠነጥን ቁም ነገር ላይ  እስከሆነ ድረስ ሌላ አላስፈላጊ የጎንዮሽ ( (የተሽኮርማሚነት) መመዘኛ ጨርሶ  አያስፈልገንም።  መግለጫዎቻችን ህይወት አልባ እንዲሆኑ ከሚያደርጉብን የአስቀያሚ ፖለቲካ ባህሪያት አንዱ ይኸው ነው።

እንደ እውነት ከሆነ ግን ህይወት አልባ መግለጫ ለመፃፍና ለማሰራጨት የምንጠቀምባቸው ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች ዒላማን (target) ለይተው በግልፅና በቀጥታ በቃ የሚሉ ሳይሆኑ እጅግ ደምሳሳ (ጅምላ) የሆኑ ወይም ምን ማለታቸው ነው? የሚያሰኙ ናቸው ። “መከራውና ስቃዩ አስከፊ እየሆነ ነው ፣ የፌደራል መንግሥት ትክክል አይደለምና የእርምት ርምጃ ይውሰድ፣ የክልል መንግሥታት እንዲህ ወይም እንደዚያ ቢያደርጉ፣ ህዝቡ ለሰላም ጠንክሮ ቢቆም፣ ወዘተ”  የሚሉና እግጅ ግልፅና ፈታኝ ለሆነው የአገራችን የነፃነትና የፍትህ ትግል የማይመጥኑ ናቸው።

የገንዛ ራሳችንን መሪር እውነት ተጋፍጠን ከተደበቅንበት ልፍስፍስ (ስንኩል) የሰበብ ድርደራ ክፉ አዙሪት  ሰብረን ለመውጣት ባለመቻላችን አሁንም ክስተት እየጠበቅን የትም የማይደርስና  የአልኩ ባይነት ፖለቲካ መግለጫን እንደ ትልቅ  የፖለቲካ ሥራ ክንውን እየቆጠርን  እወቁልን በሚል ክፉ የፖለቲካ አባዜና የሞራል ጉስቁልና ውስጥ ከመዳከር አልወጣንም።

እንደ አጠቃላይ እውነታና መርህ የመግለጫዎችን አስፈላጊነት መረዳትና መቀበል አይቸግርም። ጥያቄው ይህ አይነት  አጠቃላይ ወይም ደምሳሳ ይድረስ ለክቡራንና ለክቡራት አይነት መግለጫና   እሮሮ የት ያደራሳል?  እስከ ስንት ጊዜ እና እስከ የትኛው የመከራና የውርደት ጠርዝ ነው በእንዲህ አይነቱ በእጅጉ የተንሸዋረረ የፖለቲካ አቋምና ቁመና መቀጠል ያለብን?  እና መሰል ጥያቄዎችን አግባብነትና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ መመለስ እንችላለን ወይስ የብርቱ ህመማችን ዋነኛ ምክንያት ከሆኑ ተረኛና ጨካኝ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጋር ፋይዳ ቢስ መግለጫ እየተለዋወጥን እንቀጥላለን?  የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡና በወቅቱ ለመመለስ የመቻል ወይም ያለመቻል ጉዳይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕዝባዊ ንቅናቄው መቀጠል አለበት - አንዱዓለም ተፈራ

ለሩብ ምእተ ዓመት ተዘፈቀው የኖሩበትንና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ደረጃ እያስቀጠሉት ያሉትን ሸፍጠኛ ፣ሴረኛ ፣ፈሪና የጨካኝ የፖለቲካ ቁማርተኞች   በሰላማዊ ህዝባዊ አንገዛም ባይነት ወደ የትክክለኛው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሽግግር ጠረጴዛ እንዲመጡ ለማስገደድ የሚያስችል የተባበረና የተቀነባበረ ትግል ከማድረግ ይልቅ ሁሉም የየራሱን ትንሽ ዘውዶች በኪሱ ይዞ እይዞረ የሚያወጣው መግለጫ ህይወት አልባ ነውና ቆም ብሎና ትንፋሽ ወስዶ ማሰብን ግድ ይላል።

ከልጅነት እስካሁን  በለየለት የግል ዝና ፍለጋ የናወዘ፣ “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” በሚል  እኩይ የሸፍጥ ፖለቲካ ሰብእና የተበከለ፣ በሃሰት (በማጭበርበር) የፖለቲካ ሰብእና የተካነ፣ በውስጣቸው የአሁንና እምቅ እውነት የያዙትን ንፁሃን ዜጎች እየገደለና እያስገደለ “መናፈሻየን መርቁልኝ” በሚል ጨካኝ የፖለቲካ ሰብእና የተለከፈ፣ ስለ ሚስት/እናት/ቤተሰብ ክብርና ኩራት እየደሰኮረ ፍፁም ተቃራኒ የሆነው የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሲፈፀም እንደ ሰው እንኳ “አዝናለሁ” ለማለት የተሳነው፣ መብቱን አግኝቶ ለማደግ እድሉን ቢያገኝ  አንድ ግድብ ወይም መናፈሻ ወይም የስንዴ ማሳ ይቅርና አገርን በእድገት ወርቅ ማልበስ የሚችልን ትውልድ በዘርፈ ብዙ ዘመቻው በመግደልና በማስገደል እኩይ መንፈስ የተለከፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ የሚመራው ን የሸፍጠኞች፣ የሴረኞች፣ የፈሪዎችና የጨካኞች ሥርዓት  ወደ መሬት ወርዶ ህይወትን በማይላበስ የመግለጫ ጋጋታ  ይስተካከላል ብሎ ከማሰብ የባሰ የፖለቲካ ድንቁርና እና የሞራል ጉስቁልና የለም።

ይህ የውድቀታችን አባዜ የሃይማኖት ተቋሞቻችንም ክፉኛ እየተጠናወተ የመቀጠሉን መሪር እውነት በድርጊት አልባ የእግዚአብሔር ያውቃል ስብከት ሸፋፍኖ ማለፍ ፈፅሞ አይቻልም ። ፈጣሪም አይወደውም። የአገር ልዑላዊነት ፣የህዝብ ደህንነት ፣ የፍትህና የነፃነት አስፈላጊነት ፣ የእኩልነት በረከት እና የሰላምና የጋራ እድገት ድንቅ እሴት  ቅድስት በምንላት ምድር  (ኢትዮጵያ) ላይ እውን እንዲሆ ኑ የሚያስችል ሥራ ሳይሠሩ የሰማያዊው በር ይከፈት ይመስል  ድርጊት አልባ ሃይማኖታዊ ጉባኤ ማካሄድንና መግለጫ ማውጣትን እንደ ታላቅ የተልእኮ ክንውን እየቆጠሩ ይታወቅልን ማለት ትክክል አይመስለኝም።

ወደ መሬት ወርዶ የንፁሃንን ህይወት በማተራመስና በመቅጠፍ እኩይ የፖለቲካ ሥራ ላይ የተጠመደው ሥርዓት ሲሆን እንዲወገድ ቢያንስ ግን በቅጡ እንዲሆን ለማድረግ የማይረዳ ጉባኤና መግለጫ ጨርሶ የትም አለማድረስ ብቻ ሳይሆን ለመከራውና ለውርደቱ ሥርዓት መራዘም ምክንያት ከሚሆኑት አንዱ ነው። የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሚያካሂዷቸው ጉባኤዎች እና የሚያወጧቸው መግለጫዎችም ከዚህ ክፉ ልማድ የራቁ አይደሉም።

መከረኛውን ህዝብ ለዘመናት የመከራና የውርደት ዶፍ ያወረዱበትንና እያወረዱበት ያሉትን ገዥ ቡድኖች በፍትህና ርትዕ ፊት ተጠያቂ በማይሆኑበት እና በወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓታቸውን በበላይነት ለመዘወር በሚያስችላቸው ሁኔታ አስታረቅን በሚል ዴሞክራሲያዊት የሆነችና ለምድሩም ሆነ ለሰማዩ ህይወት የምትመች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን ማለት ፈፅሞ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለምና ለማስታረቅ የመንግሥትን ፈቃድ እንደጠየቁ የሚነግሩን  የሃይማኖት መሪዎች ሊያስቡበት ይገባል።

ለሦስት አሥርተ ዓመታት በመከራና  በውርደት ቀንበር ሥር እየማቀቀ ያለውን ህዝብ “ለፈጣሪ ስትል  አንተም ተው አንተም  ተው” በሚል ውትፍትፍ (ልፍስፍስ) አስተሳሰብና አካሄድ የሚደረገውን “እርቀ ሰላም” በደፈናው ተቀብሎ የሚባርክ እውነተኛ አምላክ የለም። እውነተኛው አምላክ እውነት የሚነገርበትን ፣ ተገቢው ፍትህና ርትዕ የሚረጋገጥበትን ፣ እውነተኛ ይቅርታ የሚጠየቅበትን፣ ግፍ የሰራ በይቅርታ ስም የግፍ አገዛዙን የማይቀጥልበትን፣ የችግሩ ምንጭ የሆነው ጉዳይ (ጥያቄ) በዘላቂነት የሚፈታበትን እንጅ በእርሱ (በፈጣሪ ስም) የሚካሄደውን የሸፍጥና የሴራ “እርቀ ሰላም” ፈፅሞ አይባርክምም ፤ አይረግምም። የማይባርከው ትክክለኛና እውነተኛ እርቀ ሰላም  ባለመሆኑ ሲሆን የማይረግመው ደግሞ ማሰቢያ አእምሮና ማከናወኛ አካል ሰጥቶን ካልተጠቀምንበት እኛን  የምንቀጣው (የምንጎዳው) እኛው ራሳችን በመሆኑ ነው። በአጭሩ ፈጣሪ ከእንዲህ አይነት እራስን በገንዛ  እራስ የገረፉና እያስገረፉ እግዚኦ ለሚል ጩኸት ሃላፊነቱን አይወስድም።

ይልቁን ፈጣሪም ይረዳን ዘንድ ከህይወት አልባ መግለጫና እግዚኦታ ሰብረን በመውጣት እንደ ሰውም ሆነ እንደ ዜጋ በነፃነት፣ በፍትህ፣ በእኩልነት፥ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ በሰላም፣ በፍቅርና በጋራ እድገት የምንኖርባትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እንትጋ !

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.