“ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም!”

288661233 536727601466394 7180825154452219201 n

ለደቂቃ እናሰባት!  የኔ ልጅ ብለን ወይም እህቴ ብለን፤—– ብቻ በተረፈረፈ ሬሳ መሃል  በሞትና  በሽረት ውስጥ ያለን “ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም!”  የሚለውን  የተማጽኖ ድምጽ እንስማው። ዘር ሃረጓን ወይም ሃይማኖቷን እንርሳው፤ አማራ ነሽ  ወይም ነሽ ተብላለች። እሷግን  ህጻን ልጅ ናት። ህጻን ልጅ። ሰው። በኢትዮጵያ ምድር  እንደማንኛውም ሰው ሳትመርጥ የመጣች። አራጆቿ ግን መርጠዋታል።  ቢለዋ ስለው፣ ሳንጃ ደግነው፣  መትረጊስ አቅቀባብለውባታል።  እናም   የመታረድን ትዕይንት  በተረፈረፈ ሬሳ መሃል ሆነው፣ ገዳዮቹ እንደገደሏቸው የቆጠሯቸው፤  ግን በታምር የልተረሸኑት እናት እንደሚነግሩን ፤

“ራሴን በረፈረፈው ሬሳ ውስጥ አገኘሁት። ካንገቴ ቀና ስል አንዲት ህፃን በግምት 6 ዓመት ታጣቂዎች ተከባለች። እኔ እዛው አጠገባቸው ብሆንም ከተረፈረፈው  ሬሳ አንዱ ስለቆጠሩኝ አላስተዋሉኝም። ህፃኗን በአማርኛ ያናግሯቴል ፤ከዛ ሁሉም ባንዴ ድምጻቸው የገደል ማሚቱ እስኪያስተጋባ ይስቃሉ ።

በመጨረሻም ህፃኗ ጮክ ብላ ይህን ስትል ሰማኋት፤
“ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም”

ቀጥሎ የሰማሁት  ድምጽ የጥይት ሩምታ ነበር። ለማየት በሚያሣሣ ገላዋ ላይ እሽቅድምድም በሚመስል መልኩ ሁሉም የጥይት አረር አዘነቡባት። ሞታ የሚረኩ አይመስልም ነበር።”‘

የዚች ልጅ ድምጽና ታሪክ  ወደድንም ጠላንም በኔ፣ በአንተ፣ በአንችና በመሰሎቻችን  በህይወት እስከ አልን ድረስ አብሮን ይኖራል። ከትውልድ ወደ ትውልድም ይተላለፋል። ” የ’ኔ እጣ በሌሎች ህጻናት ላይ፣ በሰው ልጅ  ዘር ላይ እንዳይደገም!” እያለች የምትማጸን ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን ዘግናኝ ግፍ ለማውገዝም ሆነ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ምድር እንዳይፈጸም ለመታገልና ገዥዎቻችንን  ለፈጸሙት የዘረ ማጽዳት ተጠያቂ ለማድረግ ሰው መሆን በቂ ነበር።

ዛሬ በዚች ህጻን  የደረሰው  ነገ-ከነገ ወዲያ ሌላው ”የዘረውን የማይሰበስብበት” ምክንያት የለም።  አሁንም እንዲህ ሌት- ተቀን የምንቃትተውና ለሁላችንም መዳኛው ”አንድነት ፤ ብሎም  ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊንት ነው !” የምነለው ሌላ እልቂትና ሌላ  የዘር ማጽዳት በማንኛውም ሰው ላይ እንዳይፈጸምና ከ’ነ ውስጥ ቁስላችንና ዘላለማዊ ህመማችንም ፤ የዚች ህጻን ዋይታና አሟሟት የመጨረሻ እንዲሆን ነው። ለዚህም ነው “ ዓይን ላጠፋ ዓይን ይጥፋ ካልን ሁላችንም ዓይን ስውር እንሆናለን ።” የሚባለው።

ባደሙት ቁጥር – አዎ ደም ይደማል
ባፈሰሱት መጠን – አዎ ደም ይፈሳል
ደምም- ደም ነውና ፤ ድም-ድምን ይወልዳል።

ይህች ህጻን በታረደችበት ቀን በሺዎች ታርደዋል። ሬሳቸውንና የጅምላ መቃብራቸውን አይተናል። ከ20 ቀን ህጻን እስከ መቶ ዓመት አዛውንት በማንነታቸው ብቻ አዕምሮ ሊደርስበት፣ ብዕር ሊከትበው፣  በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ አረመኒያውነት  በገዛ አገራቸው፣ በገንዛ ወገኖቻቸው፣ መንግሥት አለ በሚባልበት ምድር፣  ተመርጠው ስጋቸው ተዘልዝሏል፣ ቆዳቸው ተገፏል። ነፍሰ ጡሮች ጽንሳቸው በጪቤ  ተተልትሏል። በ’ርግጥ እውነቱን እንናገር ካልን  ለአለፉት ሰላሳ ዓመታትም  ሆነ ላለፋት አራት ዓመታት  የአማራ ህዝብ  በማንነቱ የዘር ፍጅት ሊፈጸምበት የበቃው መንግሥት አለ ብሎ ማመኑና ራሱን ለመከላከል ምንም ዓይነት ሙከራ  አለማድረጉ ነው። ሙከራ ተደርጓል  ከተባለም አራጆቹን ማባበልና መለመን ነበር።  መመበሩን የተፈናጠጡት የጎሳ ገዥዎች  ታግለው ለሥልጣን የበቁት ”አማራን” ከቻሉ ማጥፋት፤ ካልቻሉ  ማንኛውንም መንገድ ተጠቅመው ማዳከም መሆኑ ተዘንግቷል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ  ዐለምነህ ዋሴ እንዳለው፤

“በአማራ ላይ ከናዚ የከፋ ዘር ፍጅት ደርሶበታል

abiymania 1የተፈጠረውን ጥቃት ለማቃለል የሚሞክሩ ለጥቃቱ ስልታዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ናቸው። 55 አመቴ ነው። ረጅም አመት በጋዜጠኝነት ሰርቻለሁ። ባለፉት 30 አመታት ከናዚ በተቀዳ አስተምህሮ የሚያልቀው አማራ ብቻ መሆኑን አረጋግጫለሁ። ዝምታው ደግሞ በዝቷል፣ ያለቀው አማራ እኮ ናዚ ከጨፈጨፋቸው ንፁሐን ቢበልጥ እንጂ አያንስም። የሚገርመው የገዳዩ ስም ይቀያየራል፣ ሟቹ ግን ያው አማራ ነው።”

ታዲያ ኢትዮጵያን በማለቱ በማንነቱ ብቻ የዘር ፍጅት ከሚፈጸምበትን ህዝብ ጎን መቆምና  በዚህ እኩይ ተግባር የተሰማሩትን ገዥዎቻችንም ሆኑ ፈጻሚዎቹን  ማውገዝ  ብቻ ሳይሆን፤ የሁላችን አገር ጸንትና ተከባብርን  በአንድነታችን እንድንኖር መታገል የያንዳንዱ ዜጋ ኃልፊነትና ድርሻ ነው።

ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ዛሬ መነሳትና አራጆቹንም ሆነ አሳራጆቹን በቃችሁ ልንላቸውና ልናስቆማቸው ይገባል። በወደቅን ቁጥር መነሳት እንደምንችል  ታሪክ ያስተምረናል።   እናም ፤

ባካችሁ ……… ’ባካችሁ……….

እናንት  በምድረ– ኢትዮጵያ  ያላችሁ፤

አትሂዱ …..ግራችሁ…”

ከቻላችሁ ….. “ብረሩ  ክንፍ  አውታችሁ።

ግን…….. አደራ……….. ……….

አንዳትረገጡት …….  መሬቱን

እንዳታዩት………  አፈሩን፤

ብታርሱት…… አትዘሩበት

ብዘሩበት …….. አይበቅልበት፤……..

ደም  ነውና – የትላንና– የዛሬ – የአሁን፣ ትኩስ…. የፈሰሰበት

አጥንት ነውና   ያልደረቀ  “አጸደህይወት” የወደቀበት

 እናንተም  ከእንግዲህ ፣ ”ዐጽም – ‘ርስቴ” የማትሉት፤………..

ያውም ………………………………..

 የባቶቻችሁ፣…….. የናቶቻችሁ

ያውም………………………………

የወንድሞቻችሁ፣……..  የህቶቻችሁ

ያውም……………………………………

የእቦቀቅላወቹ፣……  የታዳጊወቹ፣……..የልጆቻችሁ፤

 ዓይናችሁ  እያየ፣……. እየሰማ   ጆሮችሁ

የተመቱ! … የቆሰሉ!….. የተወጉ! …. የተፈነከቱ!…..

የተቀጠቀጡ!….  የተዘለዘሉ!……! ……የተረሸኑ!

….. በገዛ   ወገኖቻችሁ………..

ያውም …………”ወገን እኮ  ነን “ እያላችሁ።

በደመዋ   ልባችሁ……………………………….

 “ኤሉሄ …..ላማ ሰበቅተኒ!”……. ብላችሁ

 ወሰን – ድንበር  ለሌለው   ሰቆቃችሁ

ብትነግሩትም   “ለሰማይ   አባታችሁ”፤

ግን….. ለምንም –  ለማንም   አይመችም

ሀዘናችሁ   መልክ   የለውም……….

ያልተነገረ  እንጅ፣ ያልተፈጸመባችሁ   ግፍ  የለም።

ብትጎጉጡ፣ ደም  አልቅሳችሁ፣….. 

 እየየ …ብላችሁ –

ቢያዳርስም   ዓለም  …..  ሲቃ – ዋይታችሁ …

መቼም– መቼም  ቢሆን፣ ምንጩ   አይደርቅም   ምባችሁ::…..

እናማ………………………………………..

ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት – ሳታሰፍኑ – በመሀከላችሁ

አንድነትን  ሳታነግሱ  –  በምድራችሁ

ይቅር  ሳትባባሉ፣  ‘ርስ – በርሳችሁ

ሳይመለስ  ክብራችሁ፣  ጠፈር –  ድንበራችሁ

የድል  ችቦው –  ከፍ  ሳይል  ክብር  ሰንደቅ  ዓላማችሁ፤……

የወገናችሁን  ደምና– አጥንት  እንዳትረግጡት

ይወጋችሁልና   እሾኽ  ሆኖ፣  የኢትዮጵያ    ዐፈር – መሬት!

1 Comment

  1. አሁን የቢቢሲ ድህረ ገጽ ባናፈሰው ዜና ላይ “ሱዳን ከኢትዪጵያ ያለኝን መሬት በጉልበት አስመልሰኩ” አለች ሲለን በባህርዳር ደግሞ የቦንብ ፍንዳታ ከተማይቱን አናወጣት ይለናል። በሌላ በኩል ገበሬዎችን አስሮ የኤርትራ ወታደሮችን ማረኩ የሚለው የክፋት ኮሮጆው ወያኔ በራሱ ቴሌቪዥን ላይ እነዚህ ቀን የፈረደባቸውን ገበሬዎች አቅርቦ የግድ ኑዛዜአቸውን አስደምጦናል። ጥቁሩ ህዝብ ክፉ ነው። የበለጠ የሚከፋው ደግሞ ራሱን በሚመስሉት ሰዎች ላይ ነው።
    የኦሮሞ ደም አፍሳሾች በየዓለማቱ አማራ ጨቁኖን እያሉ የሰውን አስተሳሰብና ታሪክን ሲያወላግድ ቆይተው ዛሬ በፈጠራ ታሪክ የሰው አንገት እየቀሉ መለፋደዳቸው የቱን ያህል የብሄር ነጻነት የጅል ፓለቲካ እንደሆነ ያሳያል። እንዲህ ያሉ የሰው አውሬዎች እንዴት ባለ ሂሳብ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነትና ፍስሃን እንደሚያስገኙ ጭራሽ አይገባኝም። ግን በየሃገሩ የተበተኑ የጊዜውን የፓለቲካ እንዘጥ እንዘጥ ባዮች ሳያኝኩ የሚውጡ የብሄር ፓለቲካ ቆይቶ ማወራረጃ እንደሚያሳጣቸው ያለፈ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ግን አንማረም። ለምን ብለን እንማራለን። ዛሬን እንጂ ነገን የማያስብ ሰው የቁም ሙት ነውና ነገው አይታየውም።
    ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው “እግዜሩም ፓለቲከኛ መሆኑ ነው” በሃይማኖት እያሳበቡ ሰውን መግደል፤ ሰውን መዝረፍ፤ መቅደስና መስጊድን ማቃጠል አልፎ ተርፎ አንድ ከአንድ ጋር እንዲናከስ እሳት መጫር ሆን ተብሎ የሚሰራበት የፓለቲካ ሴራ ነው። እምነት የፓለቲካ ብልሃት ማስፈጸሚያ ሲሆን ምንኛ ያሳዝናል። ትላንት በወለጋ ምድር ወያኔ ወላጅ እናትን በተገደለው ልጇ አስከሬን ላይ እንድትቀመጥ ያደረጋውን ግፍ ረስተው እንደ በቀለ ገርባ ያሉት ከርፋፋ ፓለቲከኞች ዞረው ተመልሰው የወያኔ ተሟጋች ሲሆኑ ማየት እንዴት ይዘገንናል። ፌዴራሊዝም ገለ መሌ በለው በማንም ሃገር ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ የለም። አናሳ ጎሳዎችም ሆነ ሌሎች ያልተገፉበትና የማይገፉበት ሃገርም በምድር ላይ የለም። ግን ወስላታው የሃበሻ ፓለቲካ በደም በተነከረችው የሃበሻ ምድር ላይ ገነትን ይፈጥር ይመስል በየጊዜው ሲናቆርና ሲገዳደል መኖሩ የሃገራችን የፓለቲካ ኪሳራን ፍንትው አርጎ ያሳያል።
    ህጻን ልጅ ከፍርሃቷ የተነሳ ” ወላሂ ከአሁን በህዋላ አማራ አልሆንም” ስትል እየሳቁ በጥይት ሰውነቷን ከሚበሳሱ አውሬዎች የነጻነት ጮራ ለኦሮሞ ህዝብ ይመጣል ብሎ ማሰብ እብደት ነው። እነ መራራ ጉዲና፤ እነ ዳውድ ኢብሳ የእድሜ ልክ ፓለቲከኞቹ ለኦሮሞ ህዝብ ያመጡት ምን ነገር አለ? መልሱ ዜሮ ነው። ግን በኦሮሞ ህዝብ ቋሚ ነጋዴዎች ሆነዋል። የነዳጅ ማደያ፤ ቤቶች (የግልና የኪራይ)፤ የምግብ ቤቶች በድርጅቱ ስምና በሌላ ልዪ ልዪ አይነት የንግድ ጥልፍልፍ ያው ከሻቢያና ከወያኔ በተማሩት የዘረፋ ስልት መሰረት ለራሳቸውና ለጥቂት ተጠቃሚዎቻቸው አመቻችተዋል። ይህ ነው የብሄር ነጻነት እየለመኑ መከበር። በህዝብ ስም መነገድ።
    ኦነግ በሰላሙ ጥሪ መሰረት ከኤርትራ ጠቅሎ በትግራይ በኩል ሲገባ ወያኔ ታላቅ አቀባብል ከድግስ ጋር እንዳደረገለት ትውስ ሊለን ይገባል። ኦነግ የወያኔ ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ በራሱ ለራሱ ቆሞ ዓላማና ግብ ያለው ድርጅት አይደለም። የተደራጅ ሽፍቶች ማለቱ ይቀላል። ማንኛውም የብሄር ባንዲራ አውለብላቢ ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ ግን አብሮ መኖር ካልተቻለ ያንድ ቤት እየጋዬ የሌላው ይቆማል ብሎ መገመት ጅልነት ነው። ዛሬ ኦሮሞዎችንና ወያኔዎችን የሚያስታጥቁትና የሚያሰለጥኑት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ቆይተው ሌላ የዛሬ አሸባሪዎችን የሚገዳደር ሲነሳ ያን ሃይል ደግሞ ያስታጥቃሉ። ለብሄር ነጻነት፤ ለሰዎች መጨቆንና መሞት የውጭ ሃይሎች ገዷቸው አያውቅም። እኛ ስንተላለቅ ተንከትክቶ መሳቅ እንጂ!
    በአማራ ህዝብ ላይ ግልጽ የሆነ የማሳደድ ዘመቻ የተጀመረው ዛሬ አይደለም። መለስ ብሎ ታሪክን ማየት አስፈላጊ ይሆናል። አማራን ማተራመስ፤ የኢትዮጵያን ስም ማጣጣልና ማዋረድ፤ በአረቡ አለምና በነጩ ዓለም እርዳታ እሳት መለኮስ የተጀመረው በነጮቹ በ 1960ዎቹ ነው። ስንቶች በተላላነት ተገለዋል። ሃገር ብለው ለሃገራቸው ድንበር ላይ እየተዋጉ ከህዋላቸው ተገለዋል፤ ስንቶች በሴራ ገመድ ተንጠልጥለዋል። በዚህ ሁሉ ግን ሥራ አስፈጻሚዎቹ ዛሬ አስመራና መቀሌ ላይ ያሉ የፓለቲካ ጉዶች ናቸው። ገዳይን ገዳይ እየገደለው ይኸው እንርመሰመሳለን እንጂ የብሄር ተፋላሚዎች ለህዝባቸው ያመነጩት ከዚህ ግባ የሚባል አንድም ነገር የለም። ውሃን በሙቀጫ እንደማለት ያህል። ያ ተንኮላቸውና ደም አፍሳሽነታቸው ዛሬ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ከድግግም ውሸታቸው የተነሳ እውነትን አያውቋትም። ሰውም ያለ ማቋረጥ በሚዘንብበት የመከራ ዶፍ ምክንያት ደንዝዟል። እየመረጠ ያለቅሳል፡ እየመረጠ ይቀብራል፤ የእኛ ሰው አይደለም/ለችም ይሙት/ትሙት ተዋቸው ይላል። በዚህ ምድር ነው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ዘርግታ ፈጣሪ የሚሰማው? የነሲብ እምነት ይሉሃል ይሄ ነው በሾኬ ሰይጣን እናወጣለን እንደሚሉት የከተማ እብዶች አይነት። አታድርስ ነው። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.