የኢትዮጵያ ካሽሚር የሆነው የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በወታደራዊ ሃይል ብልጫ ነው!!!

መሰረት ተስፉ ([email protected])

welkeit

ህወሓት ትግራይን አገር ለማድረግ ፈለገ አልፈለገ በዝርፊያ ይዞት የነበረውን ወልቃይት ጠገዴን የሚቆጥረው እንደ ደም ስሩ ወይም እንደ ልብ ትርታው ነው። በመሆኑም መልሶ ለመንጠቅ ከሰማይ በታች ያሉ ዝግጅቶችን ሁሉ እያደረገ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። በተለይ ደግሞ አስገድዶም ሆነ በውዴታ መሳሪያ መሸከም የሚችለውን ሁሉ አሰልጥኖ እንዳስታጠቀ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ይህ ስብስብ አጠቃላይ ትግራይንም ውታደራዊ ካምፕ እንዳደረጋት ለማረዳት ብዙ ጥናት የሚያስፈልግ አይመስልም። ስለዚህ ብልጫ አለኝ ብሎ ባሰበ በማንኛውም ጊዜ በአማራ፣ በአፋርና በኤርትራ ላይ ጥቃት መክፈቱ አይቀርም። ይህን የሚያደርግው ደግሞ አሁን ላይ የፌዴራል መንግስት ስልጣን ለመያዝ አልሞ ሳይሆን ወልቃይትን፣ ከኤርትራና ከአፋር ደግሞ የተለያዩ ቦታወችን ከነጠቀ በኋላ Defensive Position ላይ ሆኖ ከሱዳን፣ ከግብፅና ክሌሎች ሃይሎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለመበተን ንው። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን በድርድሩ ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ እንዲመለስ ጥረት ማድረጉ አይቀርም። ለዚህ ደግሞ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ባከበረ መንገድ ሁሉም ነገር ወደነበረበት (Status Quo Ante) ይመለስ የሚል ማደናገሪያ እያቀረበ ይገኛል።

የአማራ ክልል በበኩሉ ወልቃይትን የሚመለከተው ከማንነት ጋር አቆራኝቶ ነው። በሌላ አነጋገር ይህ ክልል የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ የሚያየው እንደትግሉ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደገ ይገኛል። ነገር ግን ህወሐት ከሚያደርገው ዝግጅት አንፃር ከታየ የአማራ ክልል ዝግጅት በቂ ነው ሊባል የሚችል አይመስለኝም። ዝግጅቱ በቂ ነው ሊባል የሚችለው አማራ ክልልም ልክ እንደ ህወሐት ሁሉ ብቃት ያለውን የሰው ሃይል በሙሉ አሰልጥኖ ማዘጋጀት ሲችል ብቻ ነው። ምናልባት በተደጋጋሚ እንደምለው ክልሉ ወታደራዊ ስልጠናን የሚያካትት ብሄራዊ አገልግሎት ማወጅ ይኖርበታል። በነገራችን ላይ ብሄራዊ አገልግሎቱ ከወታደራዊ ስልጠና በተጨማሪ የስራ ባህልን ለማዳበር የሚያስችሉ አመለካከቶችን ለመቅረፅ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል መገንዘብም ጠቃሚ ይሆናል።

ድርድርን በተመለከተ የአማራ ክልል አቋም ከህወሐት አቋም የተለየ ነው። ምክንያቱም የአማራ ክልል ሁሉም ነገር ወደነበረበት ይመለስ ሲል ህወሐት በጊዜው የነበረውን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ተጠቅሞ ወልቃይት ጠገዴን ወደ ትግራይ ከማካለሉ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ይመለስ የሚል ጠካራ እምነት ስላለው ነው።

የኦህዴድና የአጃቢዎቹ እጆች የረዛዘሙበት የፊዴራል መንግስት የያዘው አቋም ደግሞ መሃል ላይ ይመስላል። ምክንያቱም በአንድ በኩል ድርድሩ ህገመንግትስታዊ ስርዓቱን የተከተለ መሆን አለበት ሲል ከህወሐት አቋም ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። ምናልባትም ወልቃይት ጠገዴ የምስራቅ አፍሪቃ የስበት ማዕክል ባይሆንና በህወሐት ቁጥጥር ስር መሆኑ ለስልጣኑ አደጋ ባይደቅንበት ኖሮ የፌደራል መንግስቱ ልክ ራያና ሌሎች ቦታዎች ላይ እንዳደረገው ሁሉ ከህወሐት ጎን ይቆም እንደነበር ማንም ሰው በዳበሳ ሊያውቀው የሚችል ሃቅ ነው።

እንዲያ ስለሆነ ግን የሰላም ድርድሩ “ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በተከተለና ያገሪቱን ደህንነት ስጋት ላይ በማይጥል ሁኔታ…” መካሄድ እንዳለበት አቋም ወስዷል። ይህ የፌዴራል መንግስቱ አቋም ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ ቢካለል ያገሪቱ ደህንነት፣ አንድነት፣ ሉዓላዊንትና ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። ስለዚህ ፌዴራል መንግስቱ ድርድሩ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ባማከለ መንገድ ብቻ ይፈታ የሚለውን የህወሐት ማደናገሪያ ሙሉ በሙሉ የተቀበለው አይመስለም። በሌላ በኩል (የኤርትራን አቋም ጨምሮ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ካልሆነ በስተቀር) የወልቃይት ጠገዴ ተጠሪነት ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲሆንም በሙሉ ፍላጎቱ ይደግፋል ለማለት ይከብዳል። እንዲያውም የወልቃይት ጠገዴ ተጠሪነት ለፌዴራል መንግስቱ መሆን አለበት አይልም አይባልም። ፌዴራል መንግስቱ እንዲህ አይነት በእሳት የመጫዎት ፖለቲካ ባይገባ ግን ይመረጣል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ደግሞ ፌዴራል መንግስቱ “የህወሀት ሃይል ካቅሜ በታች ነው” የሚል መግለጫ አውጥቷል። ነገር ግን ህወሐት እንደለመደው ጥልቅ ግምገማ በማድረግ ከዚህ በፊት የነበሩበትን ችግሮች ለይቶ መፍትሄ ማስቀመጡን፣ ሃይሉን አሟጦ መዘጋጀቱን እና አሁን ላይ ያለው ትኩረት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ስለሚሆን ሃይል የማይከፋፍልበት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ መግለጫ ነው ብየ አላምንም። ስለዚህ ፌዴራል መንግስቱ አቋሙን እንደገና በሚገባ መፈተሽ እንዳለበት ይሰማኛል።

ነገሮችን ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል የኢትዮጵያ ካሽሚር የሆነው የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው ከህወሓት ተቃራኒ የሆኑት ሃይሎች በተለይ የአማራ ክልል የፀጥታ ሃይል ብልጫ ሲኖረው ብቻ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። በሌላ አነጋገር ህወሐት ሰላምን ሊመርጥ የሚችለው በውድ ሳይሆን በግድ በተለይም በወታደራዊ ሃይል መፈናፈኛ ካጣ ብቻ እንደሆነ መተማመን ያስፈልጋል። ይህን እውነታ በሚገባ ተረድቶ ከበቂ በላይ ያልተዘጋጀ አካል “ቁማሩን” እንደሚበላ ምንም ጥርጥር የለውም።

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስድስት:- ቃል ኪዳን፤ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ (ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

Leave a Reply

Your email address will not be published.