አደገኛው የከተማ ላይ ከተማ ምስረታ ፕሮጀክት (መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)

 

ከግማሽ ክፍለ-ዘመን አስቀድሞ በባእዳን ቅኝ ገዢዎች ሴራ የተወጠነውና በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ) (ህ.ወ.ሀ.ት) ተልእኮ አስፈጻሚነት የተመራው ነገደ-አማራን አንገት የማስደፋቱና፣ ከተቻለም ህልውናውን ከምድረ-ኢትዮጵያ ጨርሶ የማጥፋቱ ፕሮጀክት በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚገኘውን የብልጽግና ፓርቲ የኦሮምያ ክንፍ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ተቋቁመው በኦሮሞ ስም በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አማካኝነት ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን እያስተዋልን ነው፡፡

በመሰረቱ ወያኔ በስሙ ከከለለለት አካባቢ ይልቅ የአማራው ማሕበረ-ሰብ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የዎርቅ ባድማዬ ነው በሚል መተማመን በመላዋ ኢትዮጵያ ከጽንፍ እስከአጽናፍ ነው በሰፊው ተሰራጭቶ የሚገኘው፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት መነሻውን አማራ ክልል ያደረገና የዚህኑ ክልል መታወቂያ የያዘ ማንኛውም ዜጋ ሌላው ቀርቶ ወደመዲናዋ አዲስ አበባ እንኳ ድርሽ እንዳይል ግልጽ የሆነ እገዳ የተጣለበት ይመስላል፡፡

በፌደራሉ መንግሥት ኀላፊነት መተዳደራቸው ከናካቴው ተዘንግቶ መዲናዋን ከአማራ ክልል ጋር የሚያገናኙት ሁሉም አውራ ጎዳናዎች ጥርቅም ተደርገው ተዘግተዉበታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በኦሮምያ ፖሊስና ጸጥታ ሀይሎች አስገዳጂነት ጉዟቸውን እያቋረጡ ወደኋላ እንዲመለሱ የሚደረጉት ወይም አውላላ ሜዳ ላይ የሚፈሱት ንጹሃን መንገደኞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥና በዙሪያዋ መዲናዋን ያለሀፍረት ለመሰልቀጥ ታስቦ በመደራጀት ላይ ከሚገኘው ከሸገር ከተማ ምስረታ ጋር በተያያዘ እንደሱሉልታ፣ ለገጣፎና ሰበታ ባሉት አነስተኛ የኦሮምያ አዋሳኝ ከተሞች ውስጥ የችግሩ ገፈት ቀማሾች እነርሱ ብቻ ናቸው ባይባልም በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሰሯቸው መኖሪያ ቤቶችና ጥረው ግረው ያፈሯቸው ሀብቶች እየተመረጡ በዘፈቀደ በሚወሰድ እርምጃ ሲፈራርሱና ሲወድሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

እኛ እስከምናውቀው ድረስ ሸገር የሚለው ቃል አዲስ አበባችን ስትንቆለጳጰስ የምትጠራበት የቁልምጫ ስያሜ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሶስቱ የህወሃት ቀለበቶች ታወቁ! ዳገት ላይ ሰው እንዳይጠፋ ይሁን !

ኦፊሴላዊ መቀመጫው በራሷ በአዲስ አበባ እንብርት ላይ እንዲሆን የተደረገውና እነአቶ ሽመልስ አብዲሳ የቆረቆሯትና እነዶ/ር ተሾመ አዱኛ በከንቲባነት የተሞሸሩባት ሸገር ግን ቀድሞ ነገር የሀገሪቱን መዲና በሁሉም አቅጣጫዎች አፍኖ ነዋሪዎቿን ለማስጨነቅና ዘላቂ ባለዋጋነቷን ለመቀነስ በስሌት ታቅዶ የተጠነሰሰ አደገኛ የከተማ ላይ ከተማ ምስረታ ፕሮጀክት መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ በነባር ከተማ ወገብ ላይ ዙሪያውን እንደእባብ ተጠምጥሞ አዲስ የቁጩ ከተማን መቆርቆር ፈጽሞ ያልተለመደና እንግዳ የሆነ ነገር ነው፡፡

እነሆ ሸገር በተሰኘው ከተማ መልክኣ-ምድራዊ አፈና ምክንያት መዲናችን አዲስ አበባ ሀገረ-ሌሶቶን መስላላችኋለች፡፡ እንደሚታወቀው ዙሪያዋን በደቡብ አፍሪካ ሪፓብሊክ የተከበበችው ትንሽቱ አፍሪካዊት አገር ሌሶቶ የከባቢዋን አገር ፈቃድና ይሁንታ ካላገኘች በስተቀር ከውጪው አለም ጋር የመገናኘት እድል የላትም፡፡

አዱ-ገነትም ብትሆን ከእንግዲህ በኋላ በሸገር በኩል ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች አቻ ከተሞችም ሆነ አጎራባች ክልሎች ጋር እንዳሻት የመገናኘት እጣ ፈንታ አይኖራትም፡፡

ይልቁንም ብዙዎቻችን ተስፋ እንደምናደርገው ሕገ-መንግሥቱ ተሻሽሎ በዚህ አገር በኦፊሴል የሚሰራበት መርዘኛ የብሔር ፖለቲካ አንዳች ለውጥ እስካልተደረገበት ድረስ ሸገር ቀስ በቀስ አዲስ አበባን ትውጣት/ትሰለቅጣት እንደሆነ ነው እንጂ አዲስ አበባ ትኩስ አቅም ኖሯት የሸገርን አደገኛ የብረት አጥር ሰብራ ትወጣለች ተብሎ በጭራሽ አይታመንም፡፡

በባንቱስታናይዜሽን ጋኔን ተይዘው አለቅጥ የሚቅበዘበዙት ስግብግብና ጽንፈኞቹ የኦሮምያ ገዢዎችም ከመነሻው የፈለጉት ይህንኑ የአዲስ አበባ ውድቀት ስለነበር ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡

በርግጥ ፊንፊኔ የኛና የኛ ብቻ ናት ሲሉ ጉሮሯቸው እስኪነቃ ድረስ ጫፍ የረገጠ ጩኸታቸውን በየደረሱበት ሲያስተጋቡ የምንታዘባቸው ይሉኝታቢስ ወገኖች ዙሪያዋን በሌላ የቁጩ ከተማ ክርችም አድርጎ ማጠር ለምን እንዳስፈለጋቸው የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፍቅር ፏፏቴ - (በፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.