የ2014ን ዓመት ፍልሰታ ጾምና ሱባዔዋን ፈጽማችሁ በ2015 ዓ/ም ላይ እንዴት ደረሳችሁ? – ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

እዌጥን ዛተ ጦማረ በስመ ሥሉስ ቅዱስ
እንዴት ደረሳችሁ? ወይም አደረሳችሁ? ጳጉሜ 5 2014 ዓ/ም

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

አጿማትና በዐላት በሆነ ምክንያት ባንድ ወቅት ተጀምረው በዐመታትና በወራት ታዝለው ገጠመኞቻቸውን ክስተቶች ደራርበው እያፈናጠጡ እስክንሞት ድረስ ይሽከረከሩብናል፡፡ የቅኔወቻችንም ማህጽናት በበዐላት ላይ የሚንተራሱት ክሰተቶች ናቸው፡፡

ያለፉት መምህሮቼ ባስተማርንህ ቅኔ በ2014 አመትና ፍልሰታ ላይ ተደራርበው የተከሰቱትን እንዴት ትቀምራቸዋለህ? ብለው የጠየቁኝ መሰለኝና ባንዲት የመወድስ ቅኔ ጭንቅላቴን ፈተሽኩት፡፡ የግእዙ ቅኔ ጽንሰ ሐሳቡን አፍታቶ ለሁሉም ስለማያደርስልኝ የተሻለ ስለመሰለኝ ወደ አማረኛ ቀይሬ አቀርብኩላችህ፡

 

የ2014 ዓመት ፍልሰታንና የመከራውን ዘምን ተሻግራችሁ ካዲሱ ዓመት እንዴት ደረሳችሁ?

ወላጆቻችን በተረጋጋና በሰላም ዘመን ፍልሰታን በጾምና በሱባዔ፤ ቋግሜን ውሐ በመራጨት አልፈው አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ “እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! ” በመባባል ደስታቸውን የለለዋወጡበት ነበር፡፡ የ2014ን አይነት ፍልሰታንና 2015 የመሰሉ ዘመነመንሱት ሲገጥሟቸው ግን እንዴት ደረሳችሁ? ይባባሉ ነበር፡፡ ወይም አሞጽ “በክፉ ዘመን አስተዋይ የሆነ ዝም ይላል”(አሞ 5፡13) ያለውን በመከተል አፋቸውን ይዘው ብዝምታ ይተክዙ ነበር፡፡

ዘመኑ የመከራና የዋይታ ዘምን መሆኑ እየታወቀ በሰላምና በደስታ የታለፈ ለማስመሰል “እንኳን በሰላም አደረሳችሁ! የሚሉ ካሉ ቋንቋውን ያልተርዱ ናቸው ወይም ችግሩ ያልዳሰሳቸው የተመቻቸውና አስመሳዮች ናቸው፡፡

የቀደሙ ወላጆቻችን ይህን በመሰለ አሰቃቂ ዘመን እንኳን እና ሰላምን ከአረፍተ ነገሩ መዘዘው እንዴት በምትለው ቃል በመተካት እንዴት አደረሳችሁ? ይባባሉ ነበር እንጅል፤ አርበኞች ፋኖወች የሀገር ተከላካይ ወታደሮች ከጠላት ጋራ በትንቅንቅ ላይ እያሉ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቅሶ በዋይታ በምህላ ላይ እያለ “እንኳን በሰላም አደረሰቻሁ” የሚል ካለ የለየለት የጠላት ቅጥረኛ ባንዳ መሆን አለበት ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡

እንኳን የምንላት ቃል ሁለት የሚቃረኑ የትርጓሜ ገጻት አሏት፡፡ የመልካምንና የደግን ምኞት የምታጎላምስ ቃለ አጋኖ ናት፡፡ አስደሳች አጋጣሚ ሲከሰት ለተከሰተለት ሰው ወዳጁ ዘመዱ “እንኳን ደስ አለህ” ይለዋል፡፡ በተቃራኒው ቂመኛ ሰው በሚጠላው ሰው ላይ ክፉ ደርሶበት ሲጭነቅ በማየት ደስ ካለው “እስየ እንኳን ደረሰበት” የሚል የአረመኔነትን ስሜት ይገልጻል፡፡

ወላጆቻችን ‘እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ከሚባባሉባቸው ዓመታውያን ወቅቶች አንዷ ፍልሰታ ናት፡፡ ፍልሰታን በምክንያት የጀመሯት ሐዋርያት ናቸው፡፡ የጀመሩበት ምክንያትም እምቤታችን ጠፋችባቸው፡፡ ለማግኘት ሕሊናዊ አሰሳ አደረጉ፡፡ አገኟት ፡፡ ቀበሯት፡፡ ተነሳች፡፡ እኛም ይህን ትውፊት በመቀበል በያመቱ ሱባዔ እንገባለን፡፡ ሱባዔ ማለት በየዘመኑ ተከናውነው በመደራረብ የተረሱትን መዳሰሻ፡ የተሰወረውን መርምሮ ማግኛና ተደራቢ አዳዲስ ክስተቶችንም ለመቃኘት የሚደረግ ሕሊናዊ ዘመቻ ነው፡፡

በዘመኔ ከፍልሰታዋ ጋራ ተደራርበው በመከሰት ያየኋቸው ብዙ ትዝታወች አሉ፡፡ ከብዙወቹ ጥቂቶቹን ብጠቅስ አንዱ ክብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴወፍሎስ ጋራ ተያይዞ በድሬዳዋ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በ1965 የተከሰተው፡ ሁለተኛው በ1967 ዓመተ ምሕረት በወላይታ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ የተያያዘው ክስተት ሲሆን፡ ሶስተኛው በ1969 አዲሳበባ ክአባ አእበራ በቀለ ጋራ የተያያዘው ከሰተት ነው፡፡ እዚህን ክስተቶች በሌላ ውቅት ለመግለጽ የ2014 አመተመከራና ፍልሰታ ባዘሏቸው ክስተቶች ላይ አተኩራለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ፍልሰታ ከመንደር እስከ ከዳማት ባሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ ጥልቅና ምጡቅ ተጽእኖ ያላት መንፈሳዊት ምልክት ናት፡፡ ዓለምን ንቀው መንነው በገዳም የሚኖሩት አባቶች የፍልሰታዋን ሰሞን ያሚያሳልፏት በተለመደው ገዳማዊ ኑሯቸው የሚኖሩባትን ጎጆ ለቀው በዋሻ በጫካ ይዘጋሉ፡፡ በየሶስት ቀናት እያሰገሩ በሁለቱ ሳምንታት ውስጥ 3 ጊዜ ብቻ እፍኝ ጥሬ ይመገባሉ፡፡

በየመንደሩ በየደብሩ ያሉ ባልቴት አዛውንቶች የሚተኙባትን ሰሌን ጠቅለው ይዘው ጥሬ ሽምብራ ሰንቀው የወሀ ቅላቸውን ይዘው ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ተሰናብተው መንደራቸውን ለቀው ወደ አቅራቢያቸው መቃብር ቤት ይሄዳሉ፡፡

በመንደር የሚቀሩት አልጋ ላይ ይተኙ የነበሩት ወደ መደብ፡ በመደብ ይተኙ የነበሩት ወደ መሬት ወርደው በሰሌን ጎናቸውን ያሳርፋሉ፡፡ ውለው ማታ እፍኝ ጥሬ እየቆርጥሙ ያሳልፏታል፡፡ ያለፈውን ያስታውሱባታል፡፡ የሚገኙበት ወቅት ደራርቦ ያዘላቸውን ይቃኙባታል፡፡ የሚመጣውንም አሻግረው በተስፋ ይመለከቱባታል፡፡

በዘንድሮው ፍልሰታና ዘመን መለወጫ ላይ ወያኔወችንና ኦነግ ሸኔወች ተጣምረው ያወጁብን ጦርነት የአቡነ ማትያስ ለህክምና ወደ አሜሪካ መምጣትና የአቶ እስክንድር ነጋ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የተደራረቡ ክስተቶች ፈጥረውብናል፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስና በተራ ክርስቲያን አቶ እስክንድር የተደራረቡት ክስተቶች በስንክሳራችን ከተመዘገቡት አሰቃቂና አስደንጋጭ ክስተቶች የማያንሱ ስለሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ዝክረታሪክ ከመመዝገብ ሊታለፉ አይገባም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልዩ የጥንቃቄ መልዕክት ከአማራ ፓሊስ ኮሚሽን - የአሸባሪው ትህነግ ሰርጎ ገቦች

ከልጅነቴ ጀምሮ በገዳም አደኩ፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ነገረ መለኮትና ቀኖና በቅኔው ባንድምታው እየተማርኩ አደኩ፡፡ ዓለምን ተጸይፌ ንቄ ወደ ገዳም ገባሁ መነኮስኩ የሚሉን ፓትርያርካችን በሚመሩት ሕዝብ ላይ ጦርነት ታውጆበት እይታረደ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻወች እየተቃጠሉ በዚያውም ላይ ሱባኤ በሚገቡበት በፍልሰታ ለሕክምና ብለው ወደ አሜሪካ መጡ፡፡ ያስኳላ ተማሪ በዚያም በአሜሪካ ተምረው ያደጉ በትዳር ያሉ ልጅ የማሳደግ ኀላፊነት ያለባቸው አቶ እስክንድር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡

ወደ ኋላ መለስ ብለን ሁለቱም በህዝበ ክርስቲያን ሕሊና ላይ ያስቀመጡትን የሕይወት ጉዞ ስንቃኝ፡ ሁለቱም ፓትርያርኩ በስደት አቶ እስክንድር በተማሪነት በአሜሪካ ኖረዋል፡፡ አቶ እስክንድር የትግራይ ወያኔወች በወገናቸው ላይ ያደረሱትን ግፍ ሲሰሙ በህዝቡ ላይ የደረሰውን ለመካፈል ከነ ቤተሰባቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ በአቡነ ተክለሃይማኖት ተወግዘው ለብዙ ዓመታት በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩት አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ውግዘቱ ሳይነሳላቸው የወያኔወች ደጋፊ

በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለመላ አሜሪካ ተሾመው ወደ አሜሪካ ተመለሱ፡፡ አቶ እስክንድር ከጽንኢት ባለቤታቸው ጋራ ሆነው ኦርቶዶክስንና አማራውን ሰበርኩት እያለ ሲፎክር ከነበረው ከወያኔ ምንግሥት ጋራ ትግላቸውን ጀመሩ፡፡ ከባለቤታቸው ጋራለ ብዙ አመታት የህዝቡን መከራና እስራት ተካፈሉ፡፡ ባለቤታቸው በእስር ቤት ወለዱ፡፡ ራሱን ብልጽግና ብሎ የሰየመው ምንግሥት “እንደመር” እያለ በወያኔ ተተካ፡፡

የተጠመቁባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናቸው “ደመረነ ምስለ ደቂቀ ብርሃን” (ሊጦን) ማለትም “ከብርሃን ልጆች ጋራ ደምረን” ብላ የምትጸልየውን በንባብ ያግኙት ወይም ቅዱስ መንፈስ ይግልጽላቸው አላውቅም፡፡ በ30 ዓመታት ውስጥ ላለቀው ህዝብ ተጠያቂ የሆኑትን አቶ ስብሐት ነጋን በነጻ ከሚለቅ፤ እነደነ አቶ ታዴውስ ያሉትን እይሳደደ ከሚያሰር መንግሥት ጋራ መደመርን አልፈለጉም፡፡

ያልተደመሩበት መንግሥት መጠልያ ምትክ ሳያዘጋጅ ወልዳ በተኛችው አራስ እናት ላይ ቤቷን በላይዋ ላይ ሲያፈርስ አታፍርሱባት በማለት ምንግሥትን መቃወማቸውን ቀጠሉ፡፡ መንግሥት ህዝብን እንደ ሜዳ ቁጥቋጦ የሚጨፈጭፉትን፤ ቤት ንብረት አብያተ ክርስቲያንት የሚያቃጥሉትን ሳይገስጽ ክበዕርና አንደበት በቀር ምንም በሌላቸው በአቶ እስክንድር ላይ ጠበንጃ እንማዘዛለን ብሎ ፎከረባቸው፡፡ ወያኔ ደጋግሞ የፈጸመባቸውን ያልተደመሩት መንግሥት ደገመባቸው፡፡ በታዛቢው ሕዝብ ጩኸት ከታሰሩበት ሲፈቱ ባሜሪካ ያሉትን ባለቤታቸውን ልጃቸውንና ደጋፊወቻቸውን ለመጎብኘት ወደ አሜሪካ መጡ፡፡ ወደ አሜሪካ መጥተው ወዳጅ ዘመድ ሲያነጋግሩ ከቆዩ በኋል ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወሰኑ፡፡ የቀርብ ወዳጆቻቸውና ጓደኞቻቸው “እስራት ይጠብቀወታልና” ወደ ኢትዮጵያ አይመለሱ ብለው ተማጸኗቸው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ተልእኮውን ለመፈጸም ወደሞትና ወደ እስር ለመሄድ በወሰነ ጊዜ “እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፡፡በዚያ ምን እንደሆነና ምን እንደሚቆየኝ አላውቅም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እስራትና መከራ ይቆይሀል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰከርልኛል ነገር ግን የተቀበልኩትን ሩጫየን እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በኔ ዘንድ እንደማትከበር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ ”(የሐው 20_22_) ብሎ የወሰደውን የሰማእትነት ውሳኔ አቶ እስክንድርም በኢትዮጵያ ደገሙት፡፡

ጓደኞቻቸውና ደጋፊወቻቸው “እኛን አልሰሙንምና እንዳይሄዱ ይምከሩልን” ብለው ወደኔ መጡ፡፡ እኔም የወዳጆቸዎን ምክር ለምን አይቀበሉም? ብየ ጠየኳቸው፡፡ አቶ እስክንድር “የጓደኞቼ ምክር ከእውነተኞች ወንድሞች የሚጠበቅ ተገቢ ነው፡ አመሰግናለሁ፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክኛቶች አልተቀበልኩትም” አሉ፡፡ ምክራቸውን ተቀብየ አሜሪካ እንደመጣሁ ብቀር ለኔና ለቤተ ሰቤ በተመቸ ነበር፡፡ ግን እዚህ እንዳልቀር የሚያደርጉኝ የሕሊና ግዳጆች አሉብኝ” አሉና የተሰማቸውን እንዲህ ብለው ገለጹልኝ፡፡

“በእስር ላይ ያሉ ወንድሞቼ በመሰቃየት ላይ ናቸውና እህል ውሀ አይዋጥልኝም፡፡ መቆም መቀመጥና መተኛት አልቻልኩም፡፡ እኔ እንደወጣሁ ብቀር በኔ ተስፋ ያደረጉ ሰዎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ድርጅቱም ይዳከማል፡፡ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የኔን እንደወጣሁ መቅረት ለራሳቸው ፖለቲካ በመጠቀም፤ እስክንድርም ትቷችሁ ወደ አሜሪካ ፈረጠጠ በማለት እኔን በምሳሌነት እየጠቀሱ ለወገን ለሀገርና ለእምነት የሚቆሙትን ወገኖች አንገት ለማስደፋት መጠቀሚያ ያደርጉታል፡፡ በመሳሰሉት ምክንያቶች ተመልሼ ሄጄ የሚገጥመኝን መከራ መቀበሉን እመርጣለሁ፡፡ “እርሰዎ በጸሎተዎ አይርሱኝ” ብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኃይሌ ሩትስ በሚኒያፖሊስ ቀለበት አሠረ

ከአቶ እስክንድር ጋራ መነጋገሬን ካቆምኩ በኋል ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በወሰነ ጊዜ አጋቦስ በሚባለው ነቢይና በቅዱስ ጳውሎስ መካከል የተካሄደው ትዝ አለኝ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በወሰነ ጊዜ በከተማው የነበሩት ወዳጆቹ እንዳይሄድ ተነጋገሩ፡፡ አጋቦስ የሚባለው ነቢይ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የራሱን እጅና እግሩ አስሮ “የዚህን መታጠቂያ ባለቤት አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል” ብሎ ነገረው፡፡ ጳውሎስ “ለእስራት ብቻ አይደለም ለመሞት ተዘጋጅቻለሁ እያለቀሳችሁ ልቤን የምትሰብሩት ለምንድነው?” (የሐዋ 21፡11)፡ ብሎ የገሰጻቸውን አስታወስኩና በተመሳሳይነቱ እጅግ ገረመኝ፡፡ የአቶ እስክንድር ቆራጥነት በዚህ ብቻ ተገልጾ የሚያበቃ አይደለም፡፡

ሌላም አቶ እስክንድርን የሚገልጽ አስደናቂ ተመሳሳይ ትዝታ እየተጎተተ መጣብኝ፡፡ ባንድ ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስና በጳውሎስ መካከል አስተዛዛቢ ታሪክ ተከሰተ፡፡ ጴጥሮስ የኔ ቢጤ አፈግፋጊ ፈሪና አድርባይ ነበር፡፡ ለእውነት ከቆሙት ጋራ ከመቆም ይልቅ እንደተሳሳቱ እያወቀ ባድርባይነት በፍርሀት ከተሳሳቱት ጋራ ተሰለፈ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጴጥሮስን በቅንነት እንዳልሄደ ባየው ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወመው፡፡ (ገላ 2፡11_14)፡፡

አቶ እስክንድር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ የጓደኞቻቸውን ምክር ባካፈልኳቸው ጊዜ “እርሰዎ በጸሎተዎ አይርሱኝ” ባሉባት ወቅት በአንደበታቸው ባይገልጹትም ፡ ማፈግፈግን በሚጸየፈው ሕሊናቸው “ያንተን አፈግፋጊነት ወደኔ አታጋባብኝ ! ” በሚል የተቃውሞ ሀሳብ እንደገፈተሩኝ አልተጠራጠርኩም፡፡

አቶ እስክንድር ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት ወቅት ወያኔወችና ኦነግ ሸኔወች እየተናበቡ አማሮችንና አማረኛ ተናጋሪወችን እየመረጡ በመጨፍጨፍ ላይ ነበሩ፡፡ ይልቁንም አንዲት አማረኛ ተናጋር ሙስሊም ልጅ “ወላሂ ከዛሬ ጀምሮ አማራ አይደለሁም ተውኝ አትረደሉኝ” ብላ ስትማጸን ያሰማቸውን የጣርና የጋር ድምጽ የሰሙ ክርስቲያኖች በምድር ላይ መኖራቸውን የጠሉበትና ክተጎዳው ወገን ቆሞ የሚያጽናና ፓትርያርክ በጥብቅ የሚፈልግበት ወቅት ነበር፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ የደብረ ሊባኖስ እጨጌ የአክሱምና ያዲስ አበባ ዙሪያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በዚህች ፈታኝ ቀውጢ ቅጽበት ከህዝቡ በፊት እኔን ግደሉኝ ማለት ሲገባቸው፡ አማሪካ ከሚኖር ዘመዳቸው “መሞቴ ነውና ተናዝዤ እንድሞት በነፍሴ ይድረሱልኝ” የሚል ጥሪ የደረሳቸው በመሰለ ዝግጅት በመጣደፍ ሁሉንም ጣጥለው ወደ አሜሪካ መጡ፡፡

በሚታረደው ህዝብ መካከል ለመቆም ባይታደሉም፡፡ ከመንበራቸው ወርደው ማቅ ለብሰው አምድ ነስንሰው ድንጋይ ተንተርሰው ወደ አምላክ መጮህ ሲገባቸው በምንኩስና ለሞተውና ለፈረሰው አካላቸው ሕክምናን ምክንያት አድርገው ወደ አሜሪካ መምጣታቸው ከዚህ ቀደም ከሚወቀሱበት ስህተታቸው ጋራ ተደምሮ ለበለጠና ለከፋ ትዝብት ዳረጋቸው፡፡

“ከመ ይዕቀብ ሥጋ ወነፍሰ እምኀጉል በከመ ነፍስ ትከብር እምሥጋ፤ ከማሁ ክህነትኒ ትትሌዓል በክብር እመንግሥት”(ፍ አ 9፡289) ማለትም፦ነፍስ ከሥጋ የከበረችና ሉዐላዊት እንደሆነች ፓትርያርካችንም በሞራላቸውና በመንፈሳዊነታቸው ከመንግሥት በላይ ነው፡፡ ከመንግስት ይልቅ በሥጋና በነፍስ ለህዝቡ ቀራቢ ናቸው፡፡ በልዕልናቸውና ቀራቢነታቸው የህዝብን ሁለንተና ጠብቆ የማስጠበቅ እጽፍ ድርብ ሀላፊነት ነበረባቸው፡፡

በፓትርያርካችን ላይ ካሉት ቀኖናችን ከሚገልጻቸው እጽፍ ድርብ ሐላፊነቶች አንዷን እንኳ ስትፈጸም በዘመናችን አለማየታችን አለመታደል ነው፡፡ የብዙ ልጆች የሥጋ አባት የሆነ አንድ ሰው አንዱ ልጁ ሞቶ ሬሳው ከፊቱ ተጋድሞ፡ ሌላው ልጁ ቀባሪ አጥቶ አሞራው እየበላው፤ ሌላው ልጁ ለመሞት በማጣጣር ላይ ሳለ፡ ራሱን ዘንግቶና ስቶ ከመውደቅ ባሻገር እግሩን ወግታ በጥቂቱ የምትቆነጥጠውን እሾህ የሚያወጣለት ሰው ፍለጋ እንደማይሄድ የተረጋገጠ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉት ፓትርያርካችን ሲፈጸሙ ያየናቸው ይህን የመሰለ ስሕተት ነው፡

የኢትዮጵያ ምድር በልጆቿ ሬሳ በተሸፈነበት፤ አፈሯ በሰው ደም ወደጭቃ በተቀየረበት ወቅት ያውም በፍልሰታ ሰሞን ፓትርያርኩ በህክምና አሳበው ውደ አሜሪካ መምጣታቸው ዲያቆን የመጾር መስቀሉን ተሸክሞ “እስከ ፍጻሚያችን ድረስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቀን ስለ አንድነታችን እንማልዳለን”(ቅ ገ 40፡ ቁ 69) በማለት የሚያውጀውን በየደረሱበት በማፍረሳቸው ለእኛ ልጆቻቸው ለመከፋፈል ምክንያት ሆኑብን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲን እንደ ማራቶን ይዞ ወደፊት መሮጥ ነው የሚፈልገው" - ሌንጮ ባቲ (ቃለምልልስ)

ጥበበኛው “ሀለወ ዘይጠበብ ወይጥናቀቅ እንዘ ይዔምጽ ወሀለወ ዘይመይጣ ለምክር ወያስተርኢ ከመ ያድሉ ለቢጹ ወከመ ያስተራትዕ ለማኅፈሩ” (ሲራ 19፡

  • እንዳለው፦ እንዳለው ብየ ከመጽሐፉ የጠቀስኩት የጠቢቡ ጽንሰ ሀሳብ ሲብራራ፤ “አመጸኛ ዋሾ አንደበተኛ በንግግር ችሎታው እየተራቀቀ ሲናገር በየዋሀን ዘንድ ለእውነት የሚጠነቀቅላት መስሎ ይታያል፡፡ በእውነት ላይ እየዘመተ መሆኑን የሚረዱት ጥቂቶች አስተዋዮች ብቻ ናቸው፡፡ አንደበተኛው ሸፍጠኛ ግን እውነትን በሀሰተኛ አንደበቱ እየሸፈነ የሚስማውን ተላላና የዋህ ሕዝብ ለሀሰተኛ ጓደኛውና ቡድኑ እያሰለፈ ደጋፊ ያደርገዋል” ማለት ነው፡፡

ገብተው ከማይወጡበት ቀኖናችን ሳይቀር ባልደከሙበት ሙያ በድፍረት ዘለው የሚገቡ እንደ ክረምት አግቢ ተሐዋስያን በኢትዮጵያ ለፈሉ አንደበተኞች ፓትርያርኩ በሚያቀርቡት ንግግራቸውና በሚያሳዩት አቋማቸው የሚጠሉትን ቡድን የሚወጉበት ጦር ሆነውላቸዋል፡፡ የሚደግፉትን ግለሰብና ድርጅት የሚደግፉበት ባላ ሆነውላቸዋል፡ “ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ስበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” (ሮሜ 2፡24) የሚለውን በመርሳትና ወያኔወች የሚያስተጋቡትን በመከተል የተሰለፉበትን ፓትርያርካዊ ተልእኮ ለነቀፋና ለትችት ዳርገዋል፡፡

አቶ እስክንድር ከተጠቃው ህዝብ ጎን ጸንተው ለመቆም ሚስታቸውንና ወንድ ልጃቸውን ትተው እስራትና ሞት ወደሚጠብቃቸው ኢትዮጵያ ሲመለሱ፤ የበለጠ እጽፍ ድርብ ግዴታና ሐላፊነት ያለባቸው ፓትርያርክ ግን ሞቶ ተገንዞ በምነኩስና ለተቀበረው አካላቸው ሕክምና ፍለጋ ወደ አሜሪካ መምጣት በቀኖናችን ሊደገፍ ቀርቶ በምንም ምክንያት የማይደገፍ መወገዝ የሚገባው ስህተት ነው፡፡

ከአሜሪካ ሲመለሱ መሬት ተሰብሮበት ሰማይ ተደፍቶበት በመከራ በስቃይ በዋይታ ላይ ላለው ሕዝበ ክርስቲያን “ለህክምና ወደ አሜሪካ ሄጄ ታክሜ ድኜ ተመለስኩ” ማለታቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ በሥጋም በመንፈስም ምንም ግንኙነት እንዳልነበራቸው ያሳያል፡፡

የማን መገድ ነው ለሕዝብ የቀረበው ሰላሙ ደፍርሶበት ህይወት መሮት እጅግ በክፉ ዘመን በማልቀስ ላለ ሕዝብ “እንኳን በሰላም አደረሳችሁ” የሚል ነው? ወይስ ነቢዩ አሞጽ “በክፉ ዘመን አስተዋይ የሆነ ዝም ይላል”(አሞ 5፡13) እንዳለው በአርምሞና በተደም ዝም ያለው አቶ እስክንድር ነው? በማለቅ ላይ ላለው ህዝብ እንኳን በሰላም አደደረሳችሁ ማለት በህዝቡ ቁስል እንጨት መስደድ ነውና ዝም ማለት የሚመረጥ ይመስለኛል፡፡ መናገር ካለባቸው በወያኔወችና በኦነግሸኔወች ጥምረት ከተሰነዘረባቸው ሰይፍ ተርፈው በሕይወት ላሉት ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው፦

ሰወች ሲታረዱ ቆማችሁ ያያችሁ
የሕጻናት እልቂት የዘገነናችሁ
በሰይፍ በመታረድ ከሞት አምልጣችሁ

ካዲሱ ዘምን ላይ እንዴት ደረሳችሁ? ብለው ቃለ ምእዳን ማሰማት ነበር፡፡

“ሙት ይዞ ይሞታል” እንዲሉ፦ “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ” የሚል መፍክር እያሰሙ ወደ ቤተ መንግሥት ገብተው የራሳቸውን ሕዝብ እየጨፈጨፍና እያስጨፈጨፉ ከኖሩ በኋላ በመጨረሻ ጊዜያቸው የራሳቸውን የትግራይን ሕዝብ የመቀበሪያቸው ሳጥን በማድረግ ላይ ላሉት ወያኔወች፦ የወያኔ አባላት ልጆቼ ሁላችሁ

  • 30 አመታት ወገን ያፋጃችሁ ማፋጀታችሁን አቁሙ ይብቃችሁ እጃችሁን ስጡ ሙቱ ተናዛችሁ እንዳይጥ አትሙቱ በየጉድጓዳችሁ እንደ አይጥ ከመሞት ሕዝብ አስጨርሳችሁ መማረክ ክብር ነው በወገኖቻችሁ

ብትሞቱ ይሻላል እኔ ፈትቻችሁ፡፡ ብለው አባታዊ ምእዳን ቢለግሷቸው፡ ላባትነታቸው የሚመጠን ተግባር በመፈጸም በራሳቸው ላይ የተከመረባቸውን ታሪክዊ ክስ በትንሹም ቢሆን የሚቀንስላቸው ይመስለኛል፡፡ በተረፈ እርዚአብሔር የጦርነቱን ጊዜ አሳጥሮ ከመከራው የተረፈው የበደለና የተበደለ ወገን ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብልሎ በመጭው ዘመን “እንኳን በሰላም አደረሳችሁ” ለመባባል ያብቃን”ይቆየን

 

ማሳሰቢያ

ፖለቲከኛ አንደበተኛና ጸሐፊ የበዙበት ወቅት ነው፡፡ እኔ ከየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት ንክኪ የለኝም፡፡ ቡድኔም ፓርቲየም የኢትዮጵያ ሕዝብና ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብቻ ናቸው ፡፡ የምጽፈውም ሳይመዘገብ ቀርቶ ተረስቶ የሚቀር ሲመስለኝ ብቻ እንጅ በብቃቴ ተመክቸ አይደለም፡፡ ታላቁ ሊቅ አትናቴወስ “መኑሂ ይጽሐፍ ግሙራ ከመ ቀዲሙ ወይእዜኒ ከመ ይኩን መጽሐፈ ዝክር ለእለ ሀለው ይዕዜ አው ለእለ ይመጽኡ እምድኅረዝ (ሃ አ ም 29፡9) እንዳለው ማለትም፦ “የተፈጸመው ክስተት እንዳይረሳ ዛሬ በሕይወት ያሉትም በበለጠ እንዲገነዘቡት፡፡ ቀጣዩ ትውልድም እንዲማርበት የሚጽፍ ዛሬም እንደ ቀድሞወቹ ሕሊና አዳማጮች ያላንዳች ግላዊ ጥቅም ይጻፍ” ብሎ ቅዱስ አትናቴወስ ለኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊወች የመከረውን ምክር በመከተል ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.