ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ!

መቼ ይሆን እንደ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል “ከምዕመና በፊት እኛን መስዋእት አድርጉ ምድሪቷም ለጭራቆች አትገዥ!” ብለው የሚገዝቱ አባቶች የምናየው?

ጳጳስ ሆይ ሕዝብ ታለቀ እንኳን አማኝ መሐራና ደመወዝስ ይኖራል ወይ?

በላይነህ አባተ ([email protected])

ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! በአለፉት ሰላሳ አንድ ዓመታት ሕዝብ እየተጨፈጨፈ እናንተ የቤተክርስቲያኗን ቋንጃ ልሰብር መጣሁ ያለውን ይህ አድግን እየተከተላችሁ ስለልማት ስትደሰኩሩ፣  በአስር ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እየተሰደዱ መኝታቸው ጪንጫ መሬት ትራሳቸው ድንጋይ ሲሆን እናንተ ትንቡክ ተሚል ፍራሻችሁ እንቅልፋቸውን ስትለጥጡ እንደኖራችሁ ይታወቃል፡፡ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ደመወዛችሁን የሚከፍሉት ምዕመናን አንገታቸው ሲቀሉና የእምነት ሥፍራዎች ባለቤት እንደሌለው ጫካ ሲቃጠሉ ተፎቃችሁ ተንፈላሳችሁ መኖርን እንደቀጠላችሁ መለኮትም ሕዝብም ያውቃል፡፡

ሮጠው ያልጠገቡ ልጃገረዶች በጭራቆች ታግተው በሚሰቃዩበት ሰዓት እናንተ በታገቱት ልጃገረዶች ስለት ፍትፍታቸውን እየበላችሁና በሽንጣም መኪና እየተሽከረከራችሁ አለማችሁን መቅጨት ቀጠላችሁ፡፡ አሁንም ከበፊቱም የከፋ አገር በእሳት እየነደደ ህፃን፣ እርጉዝ፣ አሮጊትና ወጣቶች  በገጀራ ሲቀሉ፣ በጦር ሲወጉ፣ በባሩድ ሲረግፉና መጤ እየተባሉ በላያቸው ቤታቸው ሲቃጠል አፋችሁን ምዕመናን በሚጋግሩት ዳቦና በሚሰሩት ዶሮ ወጥ ጠቅጥቃችሁ ዝም አላችሁ፡፡

መጽሐፉ እስተንፋስ ያለው ሁሉ እንዲተነፍስ ያዝዛል፡፡ ዳሩ ግን እናንተ ይህንን የመጽሐፍ ቃል በመሻር በመላ አገሪቱ የሰው ልጅ ደም እንደ ጅረት ሲፈስ እናንተ እንኳን እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ራሳችሁን ለመስዋእትነት ልታቀርቡ ያላዬ ያልሰማ መስላችሁ ተስገብግቦ ባቄላ እንደ ዋጠ አውራ ዶሮ ጪጪ ብላችኋል፡፡

ለክርስትናና ለፍትህ ሲሉ ተዘቅዝቀው የታረዱትንና የተሰቃዩትን ሐዋርያት ስም ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን፣ ማርቆስን፣ ሉቃስን፣ ዮሐንስን፣ ቴዎፍሎስን፣ ማትያስን፣ ገብርዔልን፣ ቀውስጦስን፣ ገሪማን ወዘተርፈ ወርሳችሁ እናንተ እነሱን ታሰቃዩአቸውና ታረዷቸው ጪራቆች ጋር ቆማችሁ ስትታዘዙ ይታያል፡፡ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካዔል የጨበጡትን መቋሚያ እየጎተታችሁ የሞሶሎኒን የአላማ ዲቃላዎችን ተከትላችኋል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ጎርጎሪዎስና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የጣፏችውን መጽሐፍት እያገላበጣችሁና በቆሙበት መንበር ተገትራችሁ ለከሀዲ ገዥዎች “የልማት” ካድሬ ሆናችሁ ስትታዘዙና ስታገለግሉ ይስተዋላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ፖለቲካ - ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

አንዳንዶቻችሁ እንዲያውም መጻሕፍተ መነኮሳት መነኩሴ ከገንዘብ በጣም ይራቅ የሚለውን ሕግ ሽራችሁ ከአገር ውስጥና በውጭ አገር ታሉ ቤተክርስቲያናትም ደመወዝ እየተቀበላችሁ በመክበር የክርስቶስንና የሐዋሪያቱን ተቃራኒ መንገድ በመከተል ላይ እንዳላችሁ በእግዜርም ሆነ በሕዝብ ደጅ ይታወቃል፡፡

ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነት፣ በሆዳምነትና በፍርሃት የሚቀልቧችሁን በጎቻችሁን ለቀበሮ ገብራችሁ ወደ እማይቀረው ዓለም ስትሄዱ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ልትሉት ነው?

“የእምነት ቦታ እየተቀጣለ ምእመናን ሲደደዱና በገጀራ ሲቀሉ እናንተ እነሱን ለማዳን እንደ ጳውሎስና ጴጥሮስ መስዋእት እንድትሆኑ ቤተክርስትያን አደራ ስትጥልባችሁ ድምጣችሁን አጥፍታችሁ ክትፏችሁንና ቁርጣችሁን ትዝቁ ነበር” ብሎ መለኮት ሲያፋጥጣችሁ ምን ልትመልሱ ነው?

“ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ተጠልፈው ሲሰቃዩና ወላጆቻቸውም የምድር ሲዖል ሲኖሩ እናንተ እነሱ ልጆቻቸውን እንዲመልስላቸው ያስገቡትን ስለት እየዋጣችሁ በምቾት ኑሯችሁን ትቀጩ ነበር” ብሎ ተሚዛን ሲያስቀምጣችሁ ምን ሊውጣችሁ ነው?

ሥራ የሌለው እምነት የሞተ ነው የሚለውን ጠቅሶ “የጨበጣችሁትን መስቀል፣ የደፋችሁትን ቆብ፣ የደረባችሁት ካባና የተሸከማችሁትን የሐዋርያትና የቅዱሳን ስም በምን ሥራ ተረጎማችሁት?” ብሎ ቢጠይቃችሁ በምን ግብር ተረጎምነው ልትሉት ነው?

ታሪክስ “በእናንተ ዘመን ምእመናን እንደ በግ በካራ ሲታረዱ፣ የክርስቶስ ማደሪያ ቤተክርስትያኖች ባለቤት እንዳጣ ጫካ በአሪዎሶች ሲቃጠሉ እናንተ ፓትሪያሪኮችና  ጳጳሳት ምንም ሳታደርጉ ጪጪ ብላችሁ ሆዳቸውን እየሞላችሁ በምእመናን አስራት በተገነባ የአማረ ህንፃ ውስጥ ትንቡክ በሚል አልጋ ስትንፈላሰሱ ታድሩ ነበር” እያለ በጦር እየወጋችሁ ሲኖር ህመሙን እንዴት ልትችሉት ነው?

ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! “በጎቻችሁን ለቀበሮ፣ ቤተክርስትያናችሁን ለእሳት ገብራችሁ ወደ እማይቀረው ዓለም

ስትጠሩ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ትሉት ይሆን? እስከምትጠሩ ሂሳቡን እምነታችሁን ክፉኛ እንደ ጦር ለወጋው ሥጋችሁ ብታሰሉትስ ሕዝቡ ታለቀ እንኳን አማኝ መሐራና ደመዎዝስ ይኖራል ወይ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሁላችንም ሰው ነን “ ።ብለን ካላመንን ሠላምን አናገኛትም -  መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

መቼ ይሆን እንደ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ህፃናትን፣ እርጉዞችን፣ አቅመ ደካሞችንና ሌላውንም ከመግደልህ በፊት እኔን ሰዋ መሬቷም ለጭራቆች አትገዥ ብሎ የሚገዝት የሃይማኖት አባት የምናየው?

መጀመርያ ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም. እንደገና ህዳር አስራ አምስት ዓ.ም.

1 Comment

  1. እንደ አቡነ ጴጥሮስ የመሆኑ ጊዜ አልፏል። ተመልሶ አይመጣም። መስቀል ያዘ ዝንባባ ሁሉ አታላይና እኖር ባይ ነው። ሰው በዘሩ እንደ ውሻ እየታደነ ሲገድል ፕሮቴስታንት በለው፤ መስጊድና ሸሁ፤ ካህን በለው ጳጳሱ ሰልፋቸውን በዘርና በቋንቋቸው አልፎ ተርፎም ከቆሙበት ሰገነት ሌላ ሌላው ዓለም ሁሉ የከረፋ እየመሰላቸው የምቾት ኑሮ ለመኖር እልፎችን በሰማይ ቤት አለህ እያሉ ያታልላሉ። ይህ ዛሬ በግፈኞች ለሚገደለውና ለሚሰደደው ህዝብ ዳቦ አይሆንለትም። ለተራበው፤ ለታረዘው፤ በየቀኑ ለሚሞተው የሚያሰሙት ጩኹት ካለ ጭራሽ አይሰማም። እወቁ ደ/አፍሪቃዊ ጳጳስ ዴዝመን ቱቱ በዓለም ፊት እንባቸውን አፍሰው የሞገቱት ያ የአፓርታይድ ጭካኔ በኢትዮጵያ ቆሞ ሲሄድ ቢመለከቱ ምን ይሉ ነበር? ግን ቀድመውን አሸልበዋል። ዛሬ በሃበሻዋ ምድር እየየ የሚያሰማው ንግድ የተደናቀፈበት፤ ሰርቆ የሚያበላው የተቋረጠበት፤ ዘሩንና ቋንቋውን ተገን አርጎ መዝረፍና መቀማት የቀረበት ነው። አሁን እንሆ ወያኔ ልብ ገዝቶ ሰላም ማለቱ ስንቶቹን እንዳስከፋ ስመለከት ምድሪቱ የአውሬዎች እንጂ የሰዎች እንዳልሆነች መረዳት ችያለሁ። በብዙ መቶ ሺህ ህዝብ አልቆ፤ ያ ሁሉ ህዝብ ለረሃብና ለመከራ ተጋልጦ አሁንም እንፋለም ይለይልን ማለት እብደት ነው። ግን ምን እንላለን የጦርነቱ መነሻ ራሱ እብደት አይደል? አታድርስ፤ የምችለው ስጠኝ ያሰኛል። ሌላው የጠ/ሚሩ ነገርን እያቀለሉ መወሽከት ዛሬም በፊትም የታዘብኩት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ከ30ሺህ በላይ የትግራይ ስደተኞች በጦርነቱ ምክንያት ሱዳን ይኖራሉ ሲባሉ “ምን አላት ሰላም ከሆነ እነርሱንም ወደ ሃገራቸው መመለስ ይቻላል ነበር ያሉት” በሌላ በኩል በወለጋና በተለያዪ ሥፍራዎች የአማራ ተወላጆችን ጥቃት እየሰሙና እያዪ ዝምታቸው የህመም እንጂ የጤና አይመስልም። የገደለን ፍርድ በማይዳኘው ሃገር፤ በክልል ልዪ ሃይል ስም የኦነግና የሸኔ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነን ሃይል፤ በአዲስ አበባ የኦሮሞን የህዝብ መዝሙር ዘምሩ በሚባልበት የሙታን ፓለቲካ ታጅሎ ብልጽግና ገለ መሌ ቢሉት ዋጋ ይብሉን።
    የሃገሪቱ መከራ ገና ጀመረ እንጂ አላለቀም። ቀጣይ ነው። አሁንም በፊትም እል የነበረው ይህኑ ነው። ጉዳዪ ከህገመንግስቱና ከክልል ፓለቲካው ጋር የተያያዘ ነው። በተለይ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንዲሉ አሁን ከሆነ ወዲህ ኦሮሞዎቹ ጭራሽ ከማበዳቸው የተነሳ ጊዜው የእኛ ነው ብለው ሰው ሲገደል ቆመው ያያሉ ወይም ከውጭና ከውስጥ የሰውን ግድያ ለማፋጠን በገንዘብም በሃሳብም ይረባረባሉ። የጥቁሮችን ሰላም ከማይሹ የነጭና የዓረብ ሃይሎች ጋር ያብራሉ። ይህ የሙታን ፓለቲካ ሌላውን የሚያጋድለው ለማይኖርበት ዓለም ነው። ጥቂት የማይባሉት የኦሮሞ ነጻነት ታጋይ ነን ባዪች እድሜአቸው ሂዶ ጥርሳቸው የወለቀ ነው። ሰው እንዴት የማይደቅ ውሃ ዝንተ ዓለም ሲወቅጥ ይኖራል? አያሳዝንም። ግን በሽተኛ ፓለቲከኞች የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ብቻ አይደሉም። እነርሱ ቀን የወጣላቸው ሆነው ቀዳሚ ተጠቃሽ ሆኑ እንጂ። ሌሎችም በየክልሉ የተነኩና ጭራሽ ያበድ እልፍ ናቸው። ብሄራዊ እይታ በሌለበት ሃገር ላይ ኢትዪጵያ አትፈርስም መባሉ ማፌዝ ይሆናል። ሃገሪቱን የሚያፈርሷት እንወዳታለን፤ እንሞትላታለን እያሉ ሌላውን ወደ እሳት የሚማግድት የዘርና የቋንቋ ብሄርተኞች ናቸው። ግን በዚህ ሁሉ የፓለቲካ ስርግብ አንድም አትራፊ አይኖርም። ዛሬ ያተረፈ የሚመስለውም ነገ በወረፋው ያለቅሳል። የበላውን ይተፋል! ታሪክ የሚያሳያው ይህኑ እውነት ነው። ስለዚህ በአንድ እጅ መስቀል በኪሱ ሽጉጥ ሰክቶ ስለ ሰማይ ጉዳይ የሚያወራው ቄስም ሆነ ጳጳስ፤ ፓስተር፤ ስመ ነብይና ሃዋሪያ፤ ወይም የእስልምና እምነት አስተማሪ ጠበንጃ ባነገቱ ግፈኞች የሚፈጸመውን በደል በመቃወም ድምጻቸውን እስካላሰሙ ድረስ የቁም በድኖች ናቸው። የሰው መኖር መስፈሪያው ዘርን፤ ቋንቋን፤ ሃይማኖትን ተገን ሳያረጉ ከራስ አልፎ ለሌሎች በሚደረግ በጎ ተግባር ነው። ደርግ ደብዛውን ያጠፋ እውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዲህ ብሎን ነበር።
    ከጎራው ወጥቼ እስቲ ልነጋገር፤ ካለሰው ቢወድት ምን ያደርጋል ሃገር?
    …. ህንጻው ምን ቢረዝም ምን ቢጸዳ ቤቱ መንገድ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ
    ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ?
    ዛሬ በዚህ በዚያም ሰውን እያሳደድ ያረድና የሚያርድ ሙታኖች ለራሳቸውም ሆነ ነጻ እናወጣሃለን ለሚሉት ወገን አይሆኑም። በወረፋ እየተገዳደሉ ዝንተ ዓለም ይኖራሉ እንጂ። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.