ኢትዮጵያ ውስጥ ስነስርዓት ሊይዝ የሚገባው የፖለቲካ ሃይል ቢኖር ብልፅግና ፓርቲ ነው!!!

መሰረት ተስፉ ([email protected])

እውነት ነው ግብፅ አባይን እንደፈለገች ለመጠቀም ስትል ለኢትዮጵያ ቀና አታስብም። ኢትዮጵያን በታትና በአባይ ላይ አለኝ የምትለውን ጥቅም  የማሳካት ህልሟን እስከም ሟላ ድረስ ከሱዳንና ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መተባበሯን ትቀጥላለች።

እርግጥ ነው  ሱዳንም የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ እና  የመንግስትን ዝርክርክነት ተጠቅማ ድንበር ጥሳ ገብታ አንድ ኢንች አላፈገፍግም ብላለች። ምናልባትም በአባይና በድንበሩ ላይ ያሰበችውን ጥቅም ለማሳደድ ስትል አገር ውስጥም ሆነ ውጭ ላሉ ጠላቶች አመች ሁኔታ አትፈጥርም ማለት አይቻልም።

ያለምንም ጥርጥር ህወሓቶች ከአርባ አመት በላይ አንድን ህዝብ እንደጠላት ፈርጀው ይህንኑ ህዝብ ለመበቀል ሲሉ ኢትዮጵያ ሃገራችን ውጥንቅጥ ውስጥ እንድትገባ አድርገዋ  አልፈዋል። ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ ቤታቸው ቆጥረውም የበላይ እንደሆኑ እርግጠኝነት ሲሰማቸው ሊኖሩባት ካልሆነ ግን ታላቋን ትግራይን ለመመስረት አልመው ተንቀሳቅሰዋል።  አሁን እየተንፈራገጡ ያሉትም የመጀመሪያው ህልማቸው ስላልተሳካ በሁለተኛ ደረጃ ባስቀመጡት እቅድ መሰረት ኢትዮጵያን በጥብጠው ታላቋን ትግራይን ለመመስርት ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።

ትክክል ነው ኦነጎችም በተመሳሳይ መንገድ አንድን የማህበረሰብ ክፍል እንደታሪካዊ ጠላት በመቁጠር የኢትዮጵያን ህልውና ሲፈታተኑ ቆይተዋል። አሁንም በዚያው መስመር የተጓዙ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች በርካታ ናቸው። እንዲያውም የነሱ የጦር ክንፍ የነበረው ሃይል በጠላትነት የፈረጀውን ህዝብና ከአብራኩ የተገኙ ህፃናትን ሳይቀር እንደሳር በመትረየስ ሲያጭዳቸው መመልከት የዘወትር ክስተት ሆኗል።

ሌሎች የሃገር ውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎችም ቢሆኑ ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ እንደ ሱዛን ራይስ፣ ኸርማን ኮኸንና አሌክስ ዲቫል ባሉ የ ወሓት ቤተኞች በሚቀርቡ  የተዛቡ መረጃዎች  መነሻነት  አሜሪካና ሌሎች አንዳንድ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለው አላስፈላጊ ጫና አንዱ መገለጫ ነው። ሌሎችንም ውጫዊ ተፅዕኖዎች መዘርዘር ይቻላል።

አዎ ከፍ ሲል የገለፅኳቸው ችግሮች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል ነው ብየ አልገምትም። ምክንያቱም ቢያንስ ቢያንስ ሃይል መከፋፈላቸው አይቀርም።  ነገር ግን ቁልፍ ችግሮቹ እነሱ ናቸው ብየ አላስብም። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ለገባችበት ውጥንቅጥና ትርምስ  ዋነኛውና ቁልፉ ችግር  ወይም ደካማ ቋጠሮ የብልፅግና ፓርቲ   ውስጣዊ ሁታ  እንደሆነ ይሰማኛል።

ምክንያቱም ብልፅግና ፓርቲ (ከዚህ በኋላ እንደየአግባቡ ፓርቲው እያልኩ ልጠራው እችላለሁ)፡

  1. ከአመሰራረቱጀምሮ ችግር እንዳለበት በተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብበት ፓርቲ ነው። ይህን ሃይል ልክ እንደ ኢህአዴግ የተለያዩ የብሄር ድርጅቶች ጥምረት (Coalition) እንጅ ሃገራዊ ውህድ ፓርቲ እንደሆነ አድርገው የማያዩት ሰዎች በርካታ ናቸው። እነዚህንና ሌሎች ምክንያቶችን በመጥቀስ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ሙህራንና ልሂቃን በብልፅግና ፓርቲ ላይ ቅሬታና እምነት ማጣት እንዳደረባቸው ሲገልፁ ይደመጣሉ።
  2. ተቋማዊአሰራር የማይታወቅበት ፓርቲ እየመሰለ መጥቷል። ራሱ ፓርቲውና ፓርቲው የሚመራው መንግስት የአንድ ግለሰብ ንብረቶች እንጅ ራሳቸውን የቻሉ አደረጃጀቶች የማይመስሉበት ሁኔት ከተፈጠረ ቆየት ብሏል።ጠቅላይ ሚ/ሩ ፈለጉትም አልፈለጉትም እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ግን ተከታዮቻቸው እርሳቸውን የማንገስ ፍላጎታቸው ጣራ እየነካ መምጣቱን ነው። ሃገሪቷ ንጉሳዊ ስርዓት እየተከተለች እንደምትገኝ በሚያስመስል ሁኔታ የእርሳቸው ውሳኔዎች  ሁሉ ከህግ በላይ ሆነው መታየት ጀምረዋል። በዚህ ረገድ  የተወሰኑ ማሳያዎችን ልጥቀስ። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት ጋር የምታደርጋቸው ስምምነቶች ቢያንስ የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው በሚባለው የተወካዮች ም/ቤት መፅደቅ ይኖርባቸዋል። ሩቅ ሳንሄድ ግን ጠቅላይ ሚ/ሩ ከኤርትራ ጋር ያደረጉትን “የሰላም ስምምነት” ሳይቀር ም/ቤቱ የሚያውቀው አይመስልም። ሌላው ከውጭ አገራት “በስጦታ” ተገኘ  ስለሚባለው ገንዘብም የተወካዮች ም/ቤት አባላት አይመለከታችሁም ሲባሉ አሜን ብለው ነው የተቀበሉት። ይህ ጉዳይ እንደቀላል የሚታይ አይደለም። በእኔ እምነት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሃገር ሉዓላዊነትን ሊነካ የሚችል የውጭ አገር የገንዘብ ስጦታን የተወካዮች ም/ቤት አያገባውም በሚባልበት አገር ውስጥ ተቋማዊ አሰራ አለ ብሎ ማውራት ሊያሳፍር ሁሉ ይችላል።  በፓርቲ ደረጃ ያሉ አደረጃጀቶችም  ቢሆኑ ጥቅም ላይ የሚውሉት ጠቅላይ ሚ/ሩ ሲፈልጉ ብቻ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ። አደረጃጀቶቹ መርህን በተከተለ መንገድ by default ጥቅም ላይ ቢውሉ ኖሮማ በየቦታው እየተፈጠሩ ባሉት ችግሮች ላይ ቀጣይነት ያለውና ጥልቅ ውይይት በማድረግ ማስወገድ ባይቻል እንኳ ቢያንስ መቀነስ በተቻለ ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ የፓርቲው አመራሮችና አባላት በቋሚነትና በቀጣይነት እየተሰባሰቡ ሃገራዊ የሆኑ እቅዶችን የሚያወጡበት፣ የሚወያዩበት፣ አፈፃፀማቸውን  የሚከታተሉበት፣ የሚቆጣጣጠሩበት፣ የሚገመግሙበት፣ ውሳኔ የሚያሳልፉበትና አቅጣጫ የሚተልሙበት መድረክ አለመኖሩንም ከእየለቱ የፓርቲው እንቅስቃሴዎ በመነሳት ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ይህ ደግሞ ፓርቲው ውስጥ ተቋማዊ አሰራር ምን ያህል የወረደ እንደሆነ ያሳያል።  በዚህ  ምክንያትም  የብልፅግና  አመራሮችና  አባላት  አንድ አይነት ማልያ ለብሰው ግን ለተለያዩ  rival  ቡድኖች የ ሚጫወቱ  የእግር ኳስ  ክለቦች  እየመሰሉ  መጥተዋል::
  3. ከኦሮሞህዝብ የዕኩልነት ጥያቄ ተፃራሪ በሆነ መልኩ ኦሮሚያ ብልፅግና ውስጥ የሃገሪቱ አውራ ኮርማ ሆኖ ለመውጣት የሚውተረተር ቡድን እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች በርካታ ናቸው። ይህ ቡድን ምናልባትም ህወሃቶችን ባስከነዳ መልኩ ሁሉንም የመጠቅለል ዝንባሌ እንዳለው ፍንጮች መታየት ጀምረዋል። ይህ ሁሉንም የመጠቅለል ዝንባሌ በአዲስ አበባ ጉዳይና የፀጥታ ተቋማቱን ጨምሮ በፌደራል መንግስቱ የስራ ሃላፊነት ምደባዎች ላይ እንደሚታይ በተለያዩ ሚዲያወችና አካላት ሲገለፅ መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
  4. ሌሎችክልሎች ላይ ያሉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላትም  መርህ የተከበረበት፣ ተቋማዊ አሰራር የሰፈነበት፣ የሁሉም አቻነትና እኩልነት የሚንፀባረቅበት ስርዓት ሊገነባ ይችል ዘንድ የሚያደርጉት መተክላዊ ትግል አለ ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻል አይመስለኝም። በእርግጥ የአማራ ብልፅግናዎች የሚያደርጉት ትንሽ  ጥረት ቢኖርም እንቅስቃሴያቸው ብዙውን ጊዜ በስሜትና በእልህ የታጀበ ስለሚሆን የአካሄድ መዛነፎችን ወደመስመራቸው ለማስገባት ያላቸው እድል የጎላ ነው ብሎ መውሰድ አስቸጋሪ ነው። በርከት ያሉት ሌሎች ደግሞ ምናልባትም  በፍርሃት፣ በጫና፣ በይሉኝታ ወይም በሌላ ምክንያት ተሸብበው አድርባይነትን እንደመረጡ የሚሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው። እንዲያውም እነዚህ አካላት ከጊዜ በኋላ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ዘመን  እንደነበረው ሁሉ “አሰፈፃሚዎች እንጅ ወሳኞች አልነበርንም” እንደማይሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
  5. በየአከባቢውያሉ ግጭቶችን እስከመጨረሻው ድረስ ተከታትሎ ለመፍታት የተሳነው ፓርቲና መንግስት  እንደሆነ እየታየ ነው። በዚህ ረገድ ትግራይ ውስጥ ያለውን ምስቅልቅል እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል። እንዲያውም አሁን ያለው የመንግስት የተዝረከረከ አሰራር ካልተስተካከለ  ህወሃት እንዲያንሰራራ ወይም ከወደቀበት እንዲነሳ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አድሮብኛል። በአፋርና በሶማሊ፣ በአማራና በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች ለሚታዩ ትርምሶችም በአፍተተኝ መንፈስ እንጅ በመርህ ላይ ተመስርቶ  መፍትሄ የማበጀት ሁኔታ አይታይም። የዚህ ውጤት ደግሞ ለሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምን ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።
  6. የፍርድቤት ትዕዛዝን የማያከብር ፓርቲ ነው። ከዚህ ጋ በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ፍርድ ቤት እንዲፈቱ የወሰነላቸውን የኦነግ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ፖሊስ አልፈታም እንዳለ የሚያሳዩ ሪፖርቶች ሲወጡ መመልከት የተለመደ ሆኗል። ዜጎችን የሚያፍን የመንግስት አካል እንዳለም በተለያዩ ጊዚያት የተከሰቱ ሁኔታዎች ያሳያሉ።
  7. በኢኮኖሚረገድም ፓርቲው ወይም የሚመራው መንግስት ያስመዘገበው እድገት መኖሩን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ቢያንስ የኑሮ ውድነት ማሻቀቡና የሸቀጦች ዋጋ መጨመሩ ኢኮኖሚው ላይ ችግር እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች ናችው። በዚህ ረገድ ያለው ችግር ተባብሶ ህዝቡ የሚበላው ካጣ ማን ላይ ሊዞር እንደሚችል ለማወቅ የተለየ ስጦታ ያለው ሰው ሆኖ መፈጠርን አይጠይቅም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  አንድ ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ነው? ወይስ ሲፈቀድለት?

ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም የፅሁፌ አላማ እርምት እንጅ ውንጀላ ባለመሆኑ ለማሳያ ያህል እነዚህን ከጠቀስኩ የሚበቃ ይመስለኛል። ይልቁንም ጥያቄው እናስ ምን ተሻለ??? የሚል መሆን አለበት። እናማ  ብልፅግና  ፓርቲ  በተለይም  ከውስጡ  ኮርማ  ሆኖ  የመውጣት ፍላጎት ያለው  ቡድን ስነስርዓት ሊያደርግ  ይገባል  እላለሁ።   ስነ ስራዓት እያልኩ ያለሁት ፓርቲው ውስጣዊ የሆኑ ደካማ ቋጠሮዎቹን ፈትቶ ወደጤናማ የፖለቲካ ሂደት ለመግባት በጊዜ የለኝም መንፈስ እንዲንቀሳቀስ ለማሳሰብ ነው። ፓርቲው በዚህ መንገድ ለመጓዝ ቁርጠኝነት ካሳየ ህዝቡን አስተባብሮ ሃገርን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠርለታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በሚከተሉት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከልብ መስራት ይጠበቅበታል።

  • እንደፓርቲየሁሉንም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አቻነት፣ እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት በአመለካከትም በተግባርም ማረጋገጥ መቻል አለበት። ከአሁን በኋላ ለጊዜው ሊመስል ይችላል እንጅ በማንኛውም ሁኔታ የአንድን ቡድን ባለጊዜነትና የበላይነትን የሚቀበል የህዝብ ትከሻ እንደሌለ ግልፅ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ በየትኛውም ተቋምና የስራ መስክ የሚደረጉ ሹመቶች፣ የስራ ምደባዎች፣ ውሳኔዎች፣ በጀት ድልድሎች፣ የልማት እንቅስቃሴዎችና ሌሎችም የሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ፍትሃዊ ጥቅሞች የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠይቃል ።
  • ፓርቲውለተቋማት ግንባታና ለተቋማዊ አሰራር ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች ተቋማዊ አሰራር በጣም አስፈላጊ ነው እያሉ የሚጮኹት መሪዎች የቱንም ያህል ቀና ቢሆኑ  ተቋማዊ የሆነ አሰራርን ካልተከተሉ በግል ፍላጎቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው ተጠልፈው ሊወድቁ ይችላሉ ከሚል ስጋት ነው፡ ይህን ችግር በሚገባ ለመረዳት እንግሊዛዊዩ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ የሳይንስ ሊቅና የታሪክ አዋቂ Thomas Hobbes የሰውን ባህሪ የገለፀበትን መንገድ መረዳት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንደ Hobbes እምነት “ሁሉም ላይስማማበት ቢችልም ሰው በተፈጥሮው የለየለት ግለሰበኛ ነው”።  በዚህ እሳቤ መሰረት ደረጃው ይለያይ እንጅ ከመደበኛ ዜጋ ጀምሮ እስከከፍተኛው የሃገር መሪ ድረስ መጀመሪያ ለራሱና ለቤተሰቡ፣ ቀጥሎ ለጎጡ፣ ከፍ ሲል ለቀበሌው ከዚያም ለወረዳው፣ ብሎም ለዞኑና ክልሌ ነው ለሚለው አከባቢ ማዳላቱ አይቀርም። ይህን ግለሰበኛ የሆነን የሰው ባህሪ መገደብና መግራት የሚቻለው ደግሞ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ፣ ግልፅ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ፍትሃዊና ጠንካራ የሆኑ ተቋማትን በመፍጠር፣ አሰራርና ህግ በመዘርጋት  ብቻ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝኝ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  የአገርና የመንግሥት ሦስቱ ሥላሴዎች (National trinity) - አገሬ አዲስ   

ከተቋማዊ አሰራር ጋ ተያይዞ መነሳት ያለበት ሌላው ጉዳይ ቋሚ የእቅድ ውይይት፣ ምክክር፣ ክትትል፣ ቁጥጥር፣ ግምገማና የተጠያቂነት ስርዓት መኖሩን ማረጋገጥም ተገቢ ነው። እነዚህ መድረኮች በቅንነት ላይ የተመሰረቱ፣ ቋሚና ችግር ፈች ሊሆኑ ይገባል። አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንዲሉ ላይ ላዩን የሚደረግ ማንኛውም አይነት ውይይትና ግምገማ ዘላቂነት እንደማይኖረው መታወቅ አለበት። በሌላ አነጋገር ትኩረት መደረግ ያለበት እሳት በማጥፋት ላይ ሳይሆን እሳቱ እንዲፈጠርና እንዲባባስ እያደረጉ ያሉትን የአመለካከትና የስተሳሰብ ችግሮችን ከልብ ፈትሾ  ማረቅና ማስተካከል ላይ ነው።

  • ፓርቲውናእሱ የሚመራው መንግስት አፈናን፣ ማሳደድን፣ ህግወጥ እስርን አስወግደው ለህግ መገዛትና ለህግ የበላይነት መከበር ግንባር ቀደም ሆነው መገኘት አለበቸው። ፓርቲውም ሆነ መንግስት እንዲሁም ሁሉም አመራሮቹ ከህግ በታች እንደሆኑ በአፍ ሳይሆን በተግባር ሲፈፅሙት ለህዝቡ ማሳየት ይገባቸዋል። ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውንና እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አሁንም በአፍ በመለፈፍ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል። የህግ የበላይነትን ሳያከብሩና ሳያስከብሩ ዴሞክራሲም፣ መልካም አስተዳደርም፣  እድገትም፣ ፍትሃዊነትም፣ ህጋዊነትም  ቅዠት ብቻ መሆናቸውን ሊረዱ ይገባል።

ፓርቲው እነዚህንና በመርህ ላይ የተመሰረቱ ሌሎች የማስተካከያ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ግትር አቋም ይዞ  በሸውክ፣ በሴራ፣ በቁማርና በጥሎ ማለፍ የፖለቲካ ሂደት እቀጥላለሁ የሚል ከሆነ የሃገርን አንድነት ለማናጋት የመጨረሻውን መጀመሪያ ወንጀል ለመፈፀም እየተዘጋጀ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል።

 

ቸር እንሰንብት!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.