ብአዴናዊነት (ከበሃይሉ ምኒልክ)

“የብልጽግና  አባል ወይም  ደጋፊ መሆን ለነፍስ አባታችን ልንናገረው የሚገባ ትልቅ ሀጢያት ነው” ትንግርቱ ገ/ፃዲቅ
ስለ ብአዴን ታሪካዊ ዳራ መናገር ማንበብና መጻፍ ለሚችልና ሚዲያ ለሚከታተል ሰው ማደናቆር ይመስለኛል፡፡ የብአዴን አባላት የነበሩና ሌሎች ጸሐፊዎች እንደነገሩን ኢህዴን    መርህና ስትራቴጅ የለሹ ኢህአፓ በደረግና በወያኔ ሲዳከም ማምለጫ ያጡ ጥቂት ሰዎች የወያኔ መሪዎችን ርዕዮተዓለም ተቀብለው ያቋቋሙት ድርጅት ነው፡፡ ምንም እንኳ አገራዊ ፓርቲ ቢመስልም የድርጅቱ አመራሮች ከወያኔ በላቀ ደረጃ ለአማራ የነበራቸው ጥላቻ ከፍተኛ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የደርግን መንግሰት በመጣል ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስማቸውን ወደ ብአዴን ቀይረው የፈጸሟቸው ድርጌቶችም ለአማራ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ ጥልቅ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡  እዚህ ላይ ላነሳው የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ አንዳንድ የአሕዴን መካከለኛ አመራር የነበሩ ሰዎች የህወሐትን አቅጣጫ ተረድተው ተጋድሎ ለማድረግ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ህወሐትና የኢህዴን የበላይ አመራሮች የእነዚህን ጥቂት ግለሰቦች ቆራጥነት ተረድተው ወጥመድ በማጥመድ በእንጭጩ አስቀሯቸው እንጂ፡፡

እንደሚታወቀው የአማራ ክልል ከተዋቀረ በኋላ ከላይኛው ክልላዊ መዋቅር እስከታችኛው የቀበሌ አስተዳደር ያሉትን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮችን ቦታ የሚሸፍን ካድሬዎችን መመልመል፤ ማሰልጠንና መመደብ የመጀመሪያ ተግባር ነበር፡፡ በየደረጃው የተመደቡ ካድሬዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ማለፍ ያልቻሉ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጨረስ የተሳናቸው፤ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን፤ በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ሰራተኞች፤ ሰው ገድለው በደርግ ዘመን በወንጀል ይፈለጉ የነበሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ዋና አላማ የአማራ ህዝብ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች በመታገል ለመፍታት ሳይሆን ስራ የሌላቸው ስራ ለማግኘት፤ ዝቅተኛ ስራ የነበራቸው የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት ነበር፡፡ ይህንንም ለማሳካት ከወያኔ የሚወርድ ትዕዛዝ ያለምንም ማመንታት በመፈጸም ታማኝነታቸውን ማስመስከር የዕለት ስራቸው ነበር፡፡ ለህዝብና ለአገር ይጠቅማል አይጠቅምም የሚል ሀሳብ አንስቶ መሟገትና መታገል ፈጽሞ የሚታሰብ አለበረም፡፡ ብዙ ሰዎች የፖለቲካና የብሄር ንቃተ-ህሊና (political and ethnic consciousness) ስለሌላቸው ነው ብለው ይሟገታሉ፡፡ በእርግጥ አብዛኛዎቹ ብአዴንን የተቀላቀሉ ሰዎች የትምህርት አቅማቸው የደከመና ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሚሰጣቸው ስልጠና ውጭ የማያውቁ ደናቁርት ናቸው፡፡ ከተወሰኑ የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመናት በኋላ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ የመንግስት መዋቅር የመጡ የማስተርስና PhD ድግሪ ያላቸውም ሰዎች የፖለቲካና የብሄር ንቃተ-ህሊና (political and ethnic consciousness) አላቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ተገናኝተን ስንወያይ በመንግስት ወይም በፓርቲ ሚዲያዎች የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ እውነት ነው ብለው የሚከራከሩ ናቸው፡፡ ኢፍትህአዊ የሀብት ስርጭት፤የአማራ ህዝብ መፈናቀልና ሞት አይታያቸውም፡፡ በጣት የሚቆጥሩ ሰዎች  የኢህአዴግ ጸረ-አማራነትና የስርዓቱን ኢፍትአዊነት ተረድተው ለመታገል የሞከሩ ቢኖሩም እንኳ በግምገማና በሴራዎች በራሱ በብአዴን መዋቅርና በደህንት አካላት ከድርጅቱ እንዲባረሩ ተደርገዋል ወይም ተገድለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህወሃት አመራር ሀገር የማተራመስ ተግባር ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይገባል! - አበጋዝ ወንድሙ

በአጠቃላይ  የብአዴን አባላት ስናዳራዊ ካድሬዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ምንዳርያለው ዘውዴ  አባባል ስናዳራዊ ካድሬ ማለት “ነፍሱን ለከርሱ፤ ህሊናውን ለኪሱ፤ ነጻነቱን ለእለት ጉርሱ የሸጠ ኑባሬ ማለት ነው፡፡” በሌላ መልኩ ብአዴናዊነት ማለት ባንዳነት ማለት ነው፡፡ ባንዳ ወይም ባንዳነት የሚለውን ቃል  የተለያዩ ስዎች የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡ ብዙ ጸኃፊዎች ባንዳነት ማለት ወገኑንና ሀገሩን በመክዳት ከጣሊያን ጋር የወገነ ከሀዲ ማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡  የፕሮፌሰር ምንዳርያለው ዘውዴ  ትርጉም ግን  በፊት ከነበሩት ትርጓሚዎች የተለየ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ የባንዳነት ትርጉምን እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

“ባንዳነት ማለት በጣም ትንሽ ጭንቅላት ላይ የተቆለለ ትልቅ ሆድ  ማለት ነው፡፡ በ ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበችና ከዘንጋዳ ፍሬ በኮሰሰች ህሊና ውስጥ ለሞራል፤ ለእውነት፤ ለእውቀት፤ ለአገር ፍቅር ምንም ቦታ የሌለው ማለት ነው፡፡ ያለችውን የኮሰሰች ህሊና በሙሉ እንደ ተራራ የገዘፈውን ከርስ ለመሙላት ቀለብ ፍለጋ የሚማስን ማለት፡፡ ከርሱን ለመሙላት ብቃት ስሌለው በምድር ላይ ያለ ወንጀል በሙሉ ለመፈጸም ወደኋላ የማይል ማለት ነው፡፡”

ከላይ የተገለጸው ትርጉም በትክክልም ብአዴናዊነትና ባንዳነት አንድ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብአዴኖች የህዝቡን ንሮ በማኮስመን እነሱ የተሻለ ኑሮ ኖረዋል፡፡ ከቀበሌ አስተዳዳሪነት ጀምሮ እስከ ክልል መዋቅር የሰራ የብአዴን አባል ቢያንስ በየከተሞች ሁለትና ሶስት ቤት ያልገነባ የለም፡፡ የህዝብን ሀብት በመመዝበር ትልቅ ሀብት ያፈሩ ካድሬዎች የትየሌሌ ናቸው፡፡ አላማቸውን ለማሳካት የአማራን ህዝብ አንድነት ከማስጠበቅ ይልቅ በየጎጣቸው ተቧድነው የምዝበራ ኔትወርክ ሲዘረጉ ኖረዋል፡፡ ከዘህ በላይ የሞራል ልሽቀትና ባንዳነት ምን መገለጫ አለ፡፡

በ2010 ዓ.ም ከትህነግ የ27 አገዛዝ ወደ ኦሮሙማ አገዛዝ ስርዓት ለውጥ ወቅት የብአዴን መሪዎች ቀደም ሲል የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰ ግፍ የለም ብለው ይከራከሩት የነበረውን አቋም ቀይረው በትህነግ አገዛዝ ወቅት ኢፍትአዊ የልማት ስርጭትና ኢድሞክራሲያዊነት ተስፋፍቶ እንደነበር ይህ አካሄድ ከአሁን በኋላ እንደማይደገም ደመቀ መኮንን ወይም አምስት ብሩና ሌሎችም ብአዴናዊያን በየመድረኩ ሲደሰኩሩ ብዙዎች ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች አገልጋይነታቸውን ወይም ባንዳነታቸውን ትተው ለአማራ ህዝብ ጥቅም ሊቆሙ ነው የሚለው መወያያ ነበር፡፡ ብዙዎች የብአዴን ንስሐ መግባት እውነት መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የብአዴን ለአማራ ህዝብ ጥቅም እቆማለሁ የሚለው ቃል ሳይውል ሳይድር ወሬ ሆኖ መቅረቱን ከብዙ ክስተቶች መረዳት አብዛኛው የአማራ ህዝብ መረዳት እንኳን አልቻለም፡፡ በየክልሎች በተለይ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የአማራን ብሄር መሰረት ያደረገ መፈናቀልና ግድያ ሲፈጸም በሽግግር  ወቅት የሚከሰት ክስተት ነው ብለው ብአዴኖችም ሆነ ሌሎች ተስፈኞች ሲያስተባብሉ ቆይተዋል፡፡ የኮሌኔል አብይ መንግስት አማራ ላይ ትኩረት ያደረገ ግድያና ማፈናቀል ሆን ብሎ እያስፈጸመ መሆንን ሳይረዱ፡፡ ለነገሩ ብአዴን የፖለቲካል ታክቲክና ስትራቴጂ የሚባል ጽንሰ-ሀሳብ የማይረዳ ግኡዛን ስብስብ ነው፡፡ ቢረዳስ የአማራ ህዝብ ስቃይ ምኑ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ካድሬ የዛሬ ንሮው ከተመቸው ከዚህ በላይ አላማ የለውም፡፡ ለነገሩማ የብአዴን ካድሬ ብቻ ሳይሆን ኮለኔል አብይ አህመድ “ኢትዮጵያ ኢትየጵያ” ሲል አብዛኛው የከተማ ህዝብ እውነት መስሎት ነበር፡፡ የፖለቲካ ታክቲክ መሆኑን አልተረዳውም፡፡ በጸረ-ኢትዮጵያዊነትና በጸረ አማራ እሳቤ ያደገ ሰው መልካም መሪና ለአገር አሳቢ አይሆንም ብሎ የገመተ የለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   ትግሉ ከቤተእምነቶች በላይ አገር የማዳን ትግል ነው!

በመጀመሪያዎቹ አመታት የተከሰቱ ቀውሶች የኮለኔሉ አስተዳደር ስላልጠና ነው ሲጠነክር የታዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ይፈታሉ የሚሉ ብአዴናውያን የትየሌሌ ነበሩ፡፡ ይሁንና ችግሮች እየተፈቱ ከመሄድ ይልቅ እየተወሳሰቡ ሄደዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸሙ ድርጊቶች ዘግናኝ ናቸው፡፡ከተለያዩ የአማራ ክልል ቦተዎች ለህክምና፤ ለንግድና ለሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ሰዎች ወደ አገራቸው ርዕስ ከተማ አትገቡም ተብለው ተከልክለዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት ያፈራቸው ንብረቶች በታጠቀ ሃይል ዘረፋ ተፈጽሞበታል፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ላቡን አንጠፍጥፎ የሰራውን ቤት በማፍረስ ንበረቱ ተዘርፏል፡፡ በሚለዮን የሚቆጠረው አማራ ለብዙ አመታት ይኖረባቸው ከነበሩ የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ቦታዎች ተፈናቅሎ በድንኳን ንሮውን እየመራ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም ብአዴኖች የተለመደውን አገልጋይነታቸውንና ከህዝብ ይልቅ ለከርሳቸው ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡

ሰሞኑን ባወጧቸው አንዳንድ መግለጫዎች ብአዴናውያን ሊያመሩ ነው የሚል አንዳንድ ሞኞች ሲታለሉ ከሶሻል ሚዲያው መረዳት ችያለሁ፡፡ ከርስን መሰረት ያደረገ የህሊናና- አቅመ ቢሶች ስብስብ እንዴትስ አንደነትን ፈጥሮ የህዝብን ብሶት ሊቀርፍ ይችላል፡፡ ፈሪ ቢሸፍት ከጓሮ አያልፍም እንደሚባለው ነው የብአዴን ነገር፡፡ ከየካቲት 21-22 ቀን 2015 ዓ.ም   የሁለቱ ብልግና ክንፎች 4 ኪሎስብሰባ ላይ እንደ ነበሩ ተባራሪ ወሬዎችን ስንሰማ እውነትም አነዚህ ሰዎች መረዋል ብለህ ስታሰብ በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ አብረን ልንሰራ ተስማምተናል የሚል መግለጫ ሲሰማ ምን ሊባል ይችላል፡፡ ስናዳራዊነት የሚለው የምንዳርያለው ትንታኔ የብአዴንን ባህሪ በትክክል የሚገልጽ ነው፡፡ መግለጫው ለኮለኔል አብይ ኦሮሙማ መንግስት የብአዴንን አገልጋይነትና ታማኝነት በትክክል ያሳየ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የተሸናፊነት ስነ-ልቦና ያጎለበቱ በመሆናቸው ጥያቄ ባነሱ በማግስቱ ወደነበሩበት አቋም ይመለሳሉ፡፡ ከዝንብ እንዴት ማር መጠበቅ ራስን ማታለል ነው፡፡ እናም የአማራ ህዝብ ሆይ ብአዴንን እንደራስህ አካል አትቁጠረው፤ የራስህ ተወካይ አይደለም፤ ይልቁንስ ሰቆቃህ የተራዘመ እንዲሆን እየሰራ ያለ ስብስብ ነው፡፡ የህዝብ ግፍ አንገፍግፏቸው ለመደራጀትና ትግል ለማድረግ የሚፍጨረጨረውን ፋኖ ማሳደድ እንጂ የአማራ ህዝብ ጠላቶችን ለመታገል አይደለም ብአዴን የተፈጠረው፡፡ስለሆነም አማራ ከመጥፋት ለመታደግ ብአዴንን መታገል የመጀመሪያ አማራጭ ሊሆን ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ በአምሳሉ የፈጠረው የአየር ሃይል ሲፈተሽ | አርበኞች ግንቦት 7

 

ከበሃይሉ ምኒልክ



ብአዴን

ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን በቅርቡ ያካሂዳል።

ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን በቅርቡ ያካሂዳል። ምን ምን አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣል? ምን ማድረግስ ይጠበቅበታል? የሚሉ ጥያቄዎች በብዙዎች ሲነሳ ነበር።ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

1 Comment

  1. ሽመልስ አብዲሳን ኦሮምያን ማስተዳደር ስላልቻለ ከቦታው ይባረር ይታሰር ተጠያቂ ይሁን

Leave a Reply

Your email address will not be published.