ጎብላንድ ፣ አጭበርባሪው ጦጣ – አገሬ አዲስ

ሚያዝያ 6 ቀን 2010ዓም (14-04-2018)

ከአርባ አምስት ዓመት በፊት ተዋቂው ጋዘጠኛ፣ ታሪክና ትችት አቅራቢው አቶ ጳውሎስ ኞኞ በአንድ ወቅት ላይ ባስነበቡን ጽሁፋቸው የጎብላንድን ወይም የአጭበራባሪውን ጦጣ ታሪክ  አቅርበውልን ነበር።ታሪኩ ሲጨመቅ በጥቂቱ ይህን ይመስላል።

ከጅንጀሮዎች ጋር ሲሆን ጅንጀሮ፣ ከሰዎችም ጋር ሲሆን እንደሰው ለመሆን የሚቃጣው፣በደረሰበት ሁሉ የሄደበትን የመምሰልና እንደ እስስት የመቀያዬር ችሎታ የነበረው ጎብላንድ የተባለ ጦጣ ነበር።በዚህም ጸባዩ በስሙ ላይ ለምግባሩ ገላጭ ቃል  አጭበርባሪ የሚል ቅጥያ  ተለጥፎበት ” ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ” ተብሎ ለመጠራት በቃ።

ከዚያ ወዲህ እንደ ጎብላንድ የሚያደርጋቸው ሰዎች ብቅ ሲሉ የዚሁ ጦጣ ስም መጠሪያቸው ይሆናል።ምንም እንኳን ጦጣና ሰው የተለያዩም ቢሆንም በብዙ ስራዎቻቸው ይመሳሰላሉ፤ለዚያም ነው የሰው ልጅ ከጅንጀሮ የፈለሰ ፍጡር ነው ተብሎ በሳይንስ ዓለም የሚነገረው።አሁን ግን የተፈጥሮ ጥናት የሚጠይቅ እርእስ ለማንሳት ሳይሆን ፣እንደ ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ ሆኖ ያገኘሁትን ሰው በሚመለከተው ዙሪያ የታዘብኩትን ለማካፈል ነው።

ከላይ እንደገለጽኩት ጎብላንድ በሄደበት ቦታ ሁሉ ከባቢውን የመምሰል ችግር የለበትም፤የሆኑትን የመሆን ችሎታ አለው። የመገለባበጥ ፍጥነቱ  ወይም የአክሮባት ችሎታው የሚገርም ነው። ታሪኩን ካነበብኩት ከአርባ አምስት ዓመት በዃላ ዕድሜ ደጉ ሰሞኑን ይህን አይነት የመገለባበጥ ችሎታ ያለው ጦጣ ሳይሆን ሰው ለማዬት በቅቻለሁ፤ያም ሰው አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ ነው።ሆድ ከባሰው ጋር ሲሆን ሆድ ሲብሰው፣ከቄሮ ጋር ሲሆን ቄሮ፣ከወያኔ ጋር ሲሆን ወያኔ፣ ከሶማሌው ጋር ሲሆን ሶማሌ፣በዳዩን በመደበቅ ተበዳዩን በማጽናናት፣የማስመሰል ቋንቋ በመናገርና  የፖለቲካ ጭዋታ በመጫወት ፣የተጀመረው ሕዝባዊ ትግል ላይ ውሃ በማፍሰስ የሁሉንም ትጥቅ አስፈትቶ የተዝረከረከውን ኢሕአዴግ የተባለ አጥፊና የዘረኞች ጥርቅም ድርጅት መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገው መገለባበጥና ሙከራ የዚያን  የጎብላንድን የአጭበርባሪውን  ጦጣ ታሪክ እንዳስታውሰው አደረገኝ።ከሱ ይበልጥ የሚያስገርመው ሌላው  ደግሞ  ከበሮ በተመታ ቁጥር ዳንኪራ የሚረግጠውና  የሚገለባበጠው  በተቃዋሚ ጎራ ሲጮህ የነበረው በተለይም ምሁር ነኝ የሚለው ክፍል ነው። መታደል ይሁን መበደል አገራችን  አንድ ጎብላንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጎብላንዶች የሚተራመሱባት እንደሆነች ለማዬት በቅተናል፤ነገ ደግሞ ብዙ ጎብላንዶችን ለማዬት እንችል ይሆናል፤ጊዜው የመቀነስ ሳይሆን የመደመር ነው ተብሏልና!

አሁን ለደረሰበት የስልጣን ደረጃ ያበቃው የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ትግልና መስዋእትነት መሆኑ እየታወቀ ትግራይን ለመጎብኘት መቀሌ በገባበት ወቅት ለወያኔ ካምፕ ባሰማው ንግግር እነዚህን ለዚህ ስልጣን ያበቁትን ወጣቶችና የሕዝብ ትግል የወሮበሎችና ሕገወጦች እረብሻ እንጂ የሕዝብ ብሶት የፈጠረው ሕዝብ የደገፈውና የተሳተፈበት  ትግል አይደለም በማለት በይፋ አውግዟል።ሁለተኛም እንዳይደገም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብቷል።ሌላው አስገራሚው ንግግሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ በወርቅ፣በመዳብ፣በነሃስና፣በብረት መልክ ደረጃ ያወጣለት በሚመስል መልኩ ወርቅነትን ለትግራይ ሕዝብ ሲሰጥ ዝቅ ያለ ዋጋና ክብር ያለውን ደግሞ ለሌላው ማህበረሰብ በልቡ መድቦ ያስቀመጠው ይመስላል። ለመሆኑ ከወርቅ የበለጠ ክብርና ዋጋ ያላቸውን የአልማዝነትና የእንቁነትን ስያሜ ለየትኛው ጎሳ ለመስጠት አስቦት ይሆን?ከወርቅ በላይ የለም የሚል ስህተኛ አባባል እንደማይናገር ከሱ አልጠብቅም። ይህንን አይነት የትግሬ ጎሳን ነጥሎ የማወደስ አባባል ሟቹ የወያኔ መሪ የነበረው መለስ ዜናዊም ደጋግሞ ብሎት ነበር።ተከተል አለቃህን ሆነና ይኸኛውም የኢሕአዴግ ሹመኛ ደግሞታል። የወልቃይት አማራ፣የኮንሶ፣የኦጋዴ፣የጎንደር፣የወልድያ፣የቆቦ፣የአምቦ፣የአሶሳ፣የጋምቤላ፣ የባህርዳር፣የደብረዘይት፣የድሬዳዋ፣የቆቦ(ሐረር)የ ኦጋዴን፣የሞያሌ…ወዘተ አውራ መንገዶች ላይ የፈሰሰው የህጻን፣የወጣት፣ የሽማግሌና አሮጊት ደም ለእረብሻ የተሰማሩ በጥባጮች ደም ሆኖ ተቆጠረ፤  ለሞቱት የትግራይ ተወላጆች ግን                                                                                                                      የአበባ ጉንጉን ተቀመጠላቸው፤ጀግንነታቸውም ተወደሰ። ለሌሎቹ  አገር ወዳድ ታጋዮችና በግፍ በወያኔ/ኢሕአዴግ ሰራዊት ለተጨፈጨፉት በተለይም በእሬቻ ክብረበዓል ላይ ደማቸው ለፈሰሰው ወጣቶች የአበባ ጉንጉን ያልተቀመጠላቸው በሕይወት እንደሚታዬው በሞትም የትግራዮች ሞትና መቃብር ከሌሎቹ የተለዬ ክብር ስለሚሰጠው ይሆን?ይህም ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ አንድነትና ነጻነት ሌሎቹ ያደረጉት መስዋእትነትና አስተዋጽኦ ተሽሮ በብዛት በባንዳነት ላገለገሉት ለትግራይ ተወላጆች በብቸኛ ባለቤትነት መሰጠቱና ዋና ሚና ተጫዋች አድርጎ ማቅረቡ ለምን ፋይዳ

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዬነው ጽናቱን የጴጥሮስ ህይወቱን። (ሥርጉተ ሥላሴ)

ይሆን?ከዚህስ በፊት ለኢትዮጵያ ነጻነት ከደቡብ፣ከምስራቅ፣ከምእራብና ሰሜን ተጉዞ በተዋጋው ሕዝብና በከፈለው የህይወት ዋጋ መሆኑን፣ስጋው ከአድዋ፣ከይጨው፣ከካራማራና ከባድም አፈር ጋር መቀላቀሉን መግለጹን እረስቶት ይሆን?ወይስ ሕዝቡ የማስታወስ አቅም የለውም በማለት? ወይንስ በየሄደበት ቦታ ተመሳሳይ ዲስኩር ለማድረግ የወጠነው ስልት ይሆን? ለስርዓት ለውጥ የታገሉትና ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡት የትግራይ ወጣቶች ብቻ ነበሩን?ሌሎቹስ ጎመን ሲሰርቁ ነው የተገደሉት፣የታሰሩት፣አካለጎደሎ የሆኑት፣የተሰደዱት?መቼም ወርቅነቱን ከትግራይ ነጥቆና ለአትዮጵያ አንድነት በፊታውራሪነት ተዋግተሃል ብሎ የሰጠውን ምስክርነት ያጥፈዋል ብዬ አልገምትም።አሁን ኢትዮጵያ  ላለችበት የመበታተን አደጋ ዋናውን ሚና የተጫወተው ማን ሆነና ነው የትግራይ ሕዝብ ለአገሪቱ አንድነት ማገራና መከታ ነው ተብሎ የሚወደሰው።ሕዝብን ለማስደሰት በሚል ሰበብ ሃቅን መካድ ያስተዛዝባል።በእኛ ዘመን ውስጥ መቼ ይሆን አካፋን አካፋ የሚል ሀቀኛና ደፋር መሪ በዚያች አገር ላይ ብቅ የሚለው?

እውነትን መካድ አይገባም፤ብዙ የትግራይ ተወላጆች ለጣሊያን በባንዳነት  ያደሩ ቢሆኑም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጎን ተሰልፈው  ጣልያንን የወጉም መኖራቸው አይካድም።በዘመነ ወያኔም ባላቸው ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አቋማቸው የተገደሉ፣የታሰሩ፣የተሰደዱና አሁንም መከራቸውን የሚያዩ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸው አይካድም።በዚህ አቋም የጸናውና  ከወያኔ አገር አጥፊ ፍልስፍና የራቀው የትግራይ ተወላጅ ቁጥር በጣም ጥቂቱ ቢሆንም አሁንም አሉ። ብዙሃኑማ በስሙ ብቻ እረክቶ የወያኔ አወዳሽ ሆኗል።ያማ ባይሆን ኖሮ ወያኔ እስከ አሁን ድረስ መቼ ተዝናንቶ የፈለገውን እያደረገ ለመኖር ይችል ነበር?ጋሻና ደጀን ያደረገው የትግራይን ሕዝብ ነው።የትግራይም ሕዝብ ብዙሃኑ  ወያኔ የሚፈጽመውን በደልና ግፍ፣አገር ክህደት እንደ ቀላል ነገር አልፎታል።እያጨበጨበም ተቀብሎታል። አጼ ዩሃንስ የሞቱለት የድንበር መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ለምን ብሎ አልጠየቀም፣ አልተቃወመም፤ልጆቹ ለጨካኝ የአጋዚ ጦር ሲመለመሉና በየቦታው ደም ሲያፈሱ አልጠየቀም፣አልተቃወመም።ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመና ደጀንና ጋሻ ቢሆንማ ኖሮ አገር የሚበታትን ሕግ ሲወጣና ጎሰኛ ስርዓት ሲዘረጋ አጨብጭቦ አይቀበልም ነበር።ባይደግፍማ ኖሮ እነመለስ ዜናዊን ማቀፍና ታላቁ መሪ ብሎ ከማወደስ ይልቅ ሞሶሎኒን ዘቅዝቆ እንደሰቀለው የጣልያን ሕዝብ ዘቅዝቆ በሰቀላቸው ነበር።አሁንም አልዘገየም፤እውነት የትግራይ ተወላጅ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚቆረቆር ከሆነ ወያኔንና ፍልስፍናውን ከትግራይ ምድር ነቅሎ ለመጣል ጊዜው አልመሸምና ሊያሳይ ይገባዋል።በሌሎቹ ወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ተቃውሞ ከጎናቸው መሰለፍ ይኖርበታል።በስሙ ወንጀል የፈጸሙትን ይዞ ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔና ብልሹ ምግባሮቹ

ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ ቀደም ሲል በአምቦ ከተማ ባደረገው ንግግር የቄሮና የሁሉንም ወጣት ትግል አመስግኖ እንዲቀጥሉበት ጥሪ ማድረጉን ሁሉም የሚያውቀው ነው። በመቀሌው ንግግሩ ግን ይህንንም አፈር ድሜ አስግጦታል። በአንድ እራስ ሁለት ምላስ! የዶር/ኮሎኔል አብይ  ግን ከሁለትም ብዙ ምላስ እየሆነ ለሰሚው ግራ በማጋባት ላይ ነው። እኔንም ግራ ሊያጋባኝ ይችል ነበር ግን እድሜ ለአቶ ጳውሎስ ኞኞ የጎብላንድን ታሪክ አስቀድመው ስለነገሩኝ አልተጭበረበርኩም።ለሚጭበረበረው ባተሌ አዝናለሁ።ዳግም እንዳይጭበረበርም በማሰብ ነው የጎብላንድ አጭበርባሪውን ጦጣ ታሪክ ለማካፈል የወሰንኩት።

ለዶር/ኮሎኔል አብይ ያለኝ ምክር ቢኖር ሚናህን ለይ!ወያኔና ግብረአበሮቹ ከተጠቀሙብህ በዃላ እንደሚገፈትሩህ ወይም ከማጥፋትም እንደማይመለሱ ተረዳ።ከሕዝብ የበለጠ መከታና ጋሻ የለምና ሕዝቡን ምረጥ፤ ከቃላት ባለፈ ደረጃ የተግባር ሰው ሁን።ለእውነተኛ ለውጥ የተነሳህ፣የኢትዮጵያን አንድነት የምትሻና ለዚያ የቆምክ ከሆነ አገራችንን አደጋ ውስጥ የጣለውን የጎሳ ፖለቲካና የኢሕአዴግን  አገር አጥፊ መመሪያ የሆነውን ምለህ የተቀበልከውን  ሕገ አራዊት ጥለህ በሕዝቡ፣ ለሕዝቡ፣የሕዝቡ በሆነ ሕግ የመተዳደር ዕድል እንዲኖር ጥረት አድርግ፤በሩን ክፈት።በቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገውን ክልል የሚል የልዩነት ግምብ አፍርስ።አገሪቱንና ሕዝቡን አንድ አድርጎ የኖረው አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ሌጣ ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ፣ሲግባባበት የኖረው  አንድ ቋንቋ አማርኛ እንዲነገር ለማድረግ ጣር። እርግጥ እነዚህን ሁሉ ተግባሮች ለመፈጸም  አዳጋች ቢሆንም፣ በየመድረኩ ላይ ይህንን ከማንጸባረቅ አታፈግፍግ። ቁም ነገር ሰርቶ ወይም ለመስራት ሲሞክሩ ወይም ለእውነት መሞት በአድር ባይነት ከሚኖሩት የድሎት ኑሮ ይበልጥ ዋጋና ክብር እንዳለው አትዘንጋ። ከሕዝብ ጋር ከሆንክ በአሸናፊነት ትወጣለህ።ከወያኔና ከኢሕአዴግ ጋር ከሆንክ ደግሞ ትወድቃለህ።ከእንግዲህ ወዲያ ምርጫው ያንተ ነው።

በየሄድክበት በተለያዬ ቋንቋ ማውራትህ ችሎታህን ቢያሳይም፣ሌላ ቋንቋ መናገር የማይችለውን ቢያስደስትም  የልዩነት መስመሩን ያሰፋዋል፣ብሔራዊ ቋንቋውን እንዳይናገር ይገፋፋዋል።በዚህ ላይ ከሌሎች አገር መሪዎች ትምህርት መቅሰም

ትችላለህ።ብሔራዊ ቋንቋን የሚያስከብረው መሪ ነውና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቋንቋ አክብረህ አስከብር።የአንድ ብሔራዊ ቋንቋ መኖር ለአንድ አገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት የመሰረት ድንጋይ ነው።የምትቀርበው በአገር መሪነትህ ነውና የአገሪቱን ብሔራዊ ቋንቋ መናገር ይጠበቅብሃል።መቀሌ ላይ በትግርኛ ስትናገር የተሰበሰበው የወያኔ አወዳሽ በደስታ የዘለለው የአንተን ችሎታ በማድነቅ ሳይሆን የወያኔ አወዳሽና በሚጠላው አማርኛ ባለመናገርህ እንደሆነ ልትረዳው ይገባል።ወያኔ/ኢሕአዴግም ፍልስፍናውን ብቻ ሳይሆን ቋንቋውንም ሳይቀር  ግቶ ያሳደገህ መሆንህን በማስመስከርህ፣ የወያኔ ፍሬ በማድረግ እነ ደብረጽዮን ይኮራሉ።እነሱ ሲኮሩብህ ተስፋ የጣለብህን ብዙሃኑን እንደምታስቀይም አትዘንጋው። ሁሉም በሚገባው ቋንቋ ቢነገረው ተቃውሞ የለኝም።ሌሎቹም ቋንቋዎች ከሕዝቡ አሰፋፈር አኳያ የመነገር ጥቅማቸው እንዲዳብርመደገፍና ማበረታታት ይገባል።ቋንቋ ለመጥፎ ነገር፣ለልዩነት ካልዋለ መልካም ጌጥና ሃብት ነው።ለሁሉም ጎሳ የምታስተላልፈው መልእክትና የምታሰማው ንግግር  በ80 ቋንቋዎች መሆን እንዳለበት አትርሳ።እራስህ የጀመርከው ግድታ ነውና ተወጣው።  ሌላው ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር ቢኖር ባለፉት ጊዜያቶች ብዙ ጉዳዮችን አንስተህ የሕዝቡን ቀልብ የሚስቡ ቃላት ወርውረሃል።ከነዚያም ውስጥ ” ከአሁን በዃላ ጉዟችን መደመር እንጂ መቀነስ አይደለም” የሚል ነው።ተስፋ ያነገበው ሕዝብ በቀና እዬተረጎመው በጉጉት ሲጠብቅ፣እኔ ግን ድምሩ ባሉት ሂደቶች ሁሉ ላይ ይሆናል ብዬ ተረዳሁት። ድምሩን ከሂደቱ ጋር ሳመዛዝነውና ሳገናዝበው በፎቅ ላይ ፎቅ፣በእስር ቤት ላይ እስርቤት፣በዘረፋ ላይ ዘረፋ፣በእስረኛ ላይ እስረኛ፣በግድያ ላይ ግድያ፣በችግር ላይ ችግር፣በርሃብ ላይ ርሃብ፣በስደት ላይ ስደት፣በግጭት ላይ ግጭት፣በስራአጥነት ላይ ስራ አጥ፣በተፈናቀለ ላይ ተፈናቃይ ይሆንና የመጨረሻው ግቡ አገር የመበታተኑ ይሆናል የሚል ስጋትና ድምዳሜ ላይ እንድደርስ አስገደደኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዛሬስ - ትንሽዬዪቱ አብረህት ስታለቅስ ሕወሃታውያኑ ልባቸው ራርቶ ይሆን? -  በየነ ከበደ

እንደው ስህተቶችን ለመጠቆም ብዬ እንጂ ወያኔ ከቀየሰው የጥፋት መንገድ ትወጣለህ የሚል  እምነት የለኝም።አነሳስህንና አሁን በማድረግ ላይ ያለውን ስከታተል ከእጅ አይሻል ዶማ ሆነህብኛል።እኔ እንደ ሰውና ኢትዮጵያዊነቴ አንተ በምትወክለው  ኢሕአዴግ በተባለ አገር አጥፊ የጎሳ ስብስብ ድርጅት ተስፋ አላደርግም። ተስፋዬ ሕዝብን አንዱን ወርቅ ሌላውን መዳብና ነሃስ ወይም ሌላ ነገር አድርጎ በማይከፋፍል፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት፣ለሰብአዊ መብትና ለእኩልነት ፣ ጎሰኝነትንና የክልል ግንብን ለማፈራረስ በሚታገል፣የሰለጠነ ፖለቲካ በሚያራምድ፣ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ሕዝባዊና ዴሞክራቲክ የተደራጀ ሃይልና ትግል ብቻ ነው።የእኔም ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑ ምኞት፣ፍላጎትና  ተስፋ ይኸው ነው።ሕዝቡ  በነጻነት ድምጹን እንዲሰጥ ቢፈቀድለት ከዚህ የተለዬ ምርጫ እንደሌለው ባሳዬ ነበር።ያ ነጻነት በሌለበት በአሁኑ ሁኔታ ግን ለመኖር ሲል ለጎብላንድ እያጨበጨበና  ጎብላንድን መስሎ ለማደር ተገዷል። የጊዜ ጉዳይ ነው የጎብላንድ ማጭበርበር የማይሰራበት ጊዜ ይመጣል።ለሁሉም ጊዜ አለው ተብሏልና!

“ብልህ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሊታለል ይችላል፤ደጋግሞ ግን አይታለልም!ደጋግሞ ከታለለ ብልህ ሳይሆን ጅል ነው!” ከዚህ ቀደም እንዳልኩት አሁንም

“እግር ወዲያ ሄዶ እግር መጣ ወዲህ፣ እጅን የሚያወጣው እጅ ነው ከእንግዲህ።”

በወያኔ/ኢሕአዴግ የዳማ ጠጠር መቀያዬር መታለልና መደናበር አይኖርብንም።በጥቃቅን ሽንገላ ከዓላማችን የምናፈገፍግና ዥዋዥዌ የምንጫወት ከሆነ ጎብላንድን ሆነናል ማለት ነው።ለመሰረታዊ ለውጥ የምንታገል ከሆነ ለዚያ ዓላማ በጽናት መቆም አለብን።እርግጥ ስልተኛ መሆን አስፈላጊ ቢሆንም ከዓላማችን የሚለያዬን ከሆነ ስልት ሳይሆን በጠላት ስለት ስር የሚጥለን ይሆናል።በችኮላ ከማጨብጨብ ይልቅ በረጋ መንፈስ ሁኔታውን ማጥናትና መከታተል ይጠቅማል።

የሚያዋጣው ትግላችንን በተቀናጀና በተያያዘ መልኩ መቀጠል ነው፣በጎሳ ተዋረድ የሚወረወርልንን በማር የተለወሰ መርዝ አብረን ልንደፋው ይገባናል።አንዱ ከሌላው ተነጥሎ ወይም በሌላው ጉዳትና ኪሳራ የሚያገኘው ዘላቂ ሰላምና  ጥቅም አይኖረውም።የሁላችንም እጣ ፈንታ ከኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው።

ትግል እስከ ድል!

አገሬ አዲስ