የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት አስመልክተው ለመነጋገር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ ተገለጸ።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ እንዳስታወቀው አምባሳደር ማይክ ሐመር በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ዋነኛው አጀንዳቸው የሰሜን ኢትዮጵያው ቀውስ ይሆናል።

አምባሳደር ሐመር ከኢትዮጵያ ከነገ ነሐሴ 29/2014 ዓ.ም. ጀምሮ አስከ መስከረም 05/2015 ዓ.ም. ድረስ በሚያደርጉት ጉዞ፣ ከኢትዮጵያ ባሻገር በአካባቢው አገራት ጉብኝት እንደሚያካሂዱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጿል።

ሰኔ ወር ላይ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ኃላፊነታቸውን የጀመሩት አምባሳደር ሐመር፣ ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አዲስ አበባ እና መቀለ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

ከአስር ቀናት በላይ በኢትዮጵያ እና በአካቢው አገራት የሚቆዩት ልዩ መልዕክተኛው፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት እና የአገሪቱን የተለያዩ ክልሎችን ከሚወክሉ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።

የዚህ ጉብኝት ዋነኛ ትኩረት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆምና የሰላም ድርድር እንዲጀመር ግፊት ለማድረግ እንደሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አመልክቷል።

ባለፈው መጋቢት ወር የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ጦርነት ፈርሶ በበርካታ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የትግራይ ኃይሎች እና መንግሥት በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን እና የትግራይ ክልል በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን የአሁኑን ጦርነት በመጀመር አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚከሱ ሲሆን፣ በአፋር ክልል በኩልም ግጭት መኖሩ ተገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጀግናው አርበኛ ጎቤ መልኬ ከተሰዋ አንድ ዓመት ሞላው

ባለፉት ቀናት ጦርነቱ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋቱ የተነገረ ሲሆን፣ መንግሥት “የህወሓት ኃይሎች ጦርነቱን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከፍተዋል” ሲል ከሷል።

የትግራይ ኃይሎችም አዋሳኝ ከሆኑት የአማራ ክልል ቦታዎች በተጨማሪ በኤርትራ በኩልም መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶብናል ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አሁን የሚያደርጉት ጉዞ የተኩስ አቁም ፈርሶ ጦርነት ካገረሸ በኋላ ሲሆን ዋይት ሐውስ ስለ ሐመር ጉብኝት እንዳለው፣ ልዩ መልዕክተኛው ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነት አቁመው የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ የፕሬዝዳንት ባይደንን መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ዋይት ሐውስ በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደተመለከተው አሜሪካ “ኤርትራን ተመልሳ ወደ ግጭቱ መግባቷን፣ ህወሓት ከትግራይ ውጪ ጥቃት መቀጠሉን፣ እና የኢትዮጵያ መንግሥትን የአየር ጥቃቶች ታወግዛለች” ብሏል።

ጦርነቱ ሲቀሰቀስ የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጥቃት መክፈታቸውን መንግሥት የገለጸ ሲሆን፣ በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው የቆቦ ከተማንም መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት በአራት አቅጣጫ ጥቃት ከፍተዋል ሲሉ ከሰዋል።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የትግራይ አመራሮች የሰላማዊ ሰዎች አካባቢዎች ናቸው ያሏቸው ቢያንስ ሁለት ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የአየር ጥቃቱ ያነጣጠረው ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ መሆኑን በመግለጽ ሰላማዊ ሰዎች ከእነዚህ ቦታዎች እራሳቸውን እንዲያርቁ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ ለተከሰተው ቀውስ ወታደራዊ መፍትሔ የለውም ያለ ሲሆን፣ ግጭት መልሶ ከማገርሸቱ በፊት ለአምስት ወራት የዘለቀው የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም አበረታች ነበር ብሏል።

ነገር ግን ለሰብአዊ አገልግሎት የቀረቡ እርዳታዎች ለወታደራዊ ጠቀሜታ እየዋሉ መሆናቸው አሜሪካን በጣሙን እንዳሳሰባት መግለጫው ጠቅሷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመብራት መቆራረጥ ያማረረው የአዲስ አበባ የሽሮሜዳ አካባቢ ነዋሪ ሰልፍ ወጣ

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች መቀለ ውስጥ ከሚገኘው ማዕከሉ በ12 ቦቴዎች የተጫኑ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ በኃይል ወስደውብኛል ብሏል።

የትግራይ አመራሮች ግን ነዳጁን ከወራት በፊት ለድርጅቱ በብድር የሰጡት መሆኑን በመግለጽ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

ዋይት ሐውስ ጨምሮም ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጠይቆ፣ ውጥረቱን በማርገብ በተለይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሁሉ አቅርቦቱ መልሶ እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።

ሁለት ዓመት ሊሆነው የተቃረበውን ጦርነት በውይይት ለማስቆም አሜሪካንን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎችም ባለፉት ስድስት ወራት ጥረት ቢያደርጉም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይገኝ ጦርነቱ መልሶ አገርሽቷል።

ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ይህ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚታመን ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በተጨማሪም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው

1 Comment

  1. ይሄ ሰውዬ ወንጀለኛ ትግሬ ገና ሳይነካ ተንደርድሮ የሚመጣው ማን ፈቅዶለት ነው? ኢትዮጵያ የአሜሪካ 52ኛው ስቴት ሆነች እንዴ? ለመሆኑ መንግስት አለን አሸባሪና ነብሰ ገዳይ ሲቀጣ ትነኩትና ወዮላችሁ ይላል እንዴ ከኢሳይያስ አፈወርቅ ምንም እንኳን እርጉም ቢሆንም ትንሽ ነገር ከእሱ መውሰድ ደህና መሰለኝ፡፡ ይግደላችሁ ነዳጅ ስጡት ጠግቦ ይግደላችሁ በሺህ የሚቆጠር ምግብ በተሳቢ አስገቡለት፡፡ ለትግሬዎች እንዲወጉን የሚሰፈረው እህል እኮ ከኢትዮጵያውያን አፍ እይተነጠቀ ነው እረ በዛ በልኩ ይሁን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.