ከስሜታዊና ከሆይሆታ  “ትግል” እንውጣ!!! – ፊልጶስ

እየተከፈለ ያለውና የሚከፈለው መሰዋአትነት የሕይወት ነው።  ያውም ካልተወለደ ፅንስ ፣ እስከ ሽማግሌ። ከምድረ ገፅ እድንጠፋ የሚፈልጉት ደግሞ ከውስጥ የተደራጁና የታጠቁ ፣ ከሰበአዊነት ውጭ የሆኑ መንግሥታዊ መምበሩን የሚዘውሩ  በጎሰኝነትና በበታችነት ያበዱ ናቸው።  እነዚህ ደግሞ በዓለማችን አሉ በሚባሉ አገሮች ይደገፋሉ፣ ይታጠቃሉ፣ ይመከራሉ፤ እለንላችሁ ይባላሉ።

በአጠቃላይ ውጫዊና ውስጣዊ ድጋፍ ያላቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን አድደው መሞቅ የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆኑ እያደረጉም ያሉ እኩይ ፍጥረቶች  “የእፍኝት ልጆች”” ናቸው።

ታዲያ ለዚህ ዓይነቱ  የህልውና ጥያቄ የሚመጥን  የተደራጀ፣ ፅናት፣ መርሕና ዕራየ ያለው ሁለገብ ትግል ማድረግ እንጅ፤ ሆን ተብሎ ገዥዎቻችን አጀንዳ በሰጡን ቁጥር በስሜትና በሆይሆታ  የምናደርገው መስዋእትነት እስከ አሁንም ከዕልቂትና ርስ-በርስ ከመቆራቆስ ውጭ ያተረፍነው ነገር የለም። ፈረሳዮች “ መሳሳት ያለ ነገር ነው፤ ከስህተት  ያለ መማር ግን ‘ጌኛነት’ ነው።” ይላሉ።

ስለዚህም  በወሬ ሳይሆን በተግባር ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚታገሉት በሚደርስባቸው እስራት ሆነ ግድያ ሳንዘናጋቸውና ለቤተስቦቻቸውም ጋሻና መከታ በመሆን፣ ብሎም ዋናው ትግል ላይ አንድነታችን አስከብረን፤ ከመንደርተኝነትና ከጎሰኝነት ነፃ የሆነች፤ ሁላችንም  በእኩልነትና በነፃነት  የምታስከብር ሃገር እንድትኖረን ከሚያሻው ትግል ላይ  ማተኮር ይጠብቅብናል። ድሮም  ታጋይና የህዝብ ልጅ ይታሰራል። ይገደላል። ቁምነገር ግን መሰዋአትነታቸው ለፍሬ እንዲበቃ፤ የትግሉ ቀጣይነትና በፅናት ከግብ  ማድረሱ ላይ ነው።

እንደ ምሳሌ  በስንት መስዋአትነት  የተያዙትን የወያኔ አድራጊ ፈጣሪዎችን እነ ስብሃት ነጋን የፈታ መንግሥት በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትንና የብዕር ዓርበኞችን  የማሰር ሞራል ሊኖር ባልተገባ ነበር።  ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የሚታገሉትን ለማጥፋትና ለማሰር የዘመተውን ያህል፤ የሰውን ልጅ በማንነቱ ብቻ እንደ እንሰሳ የሚያርዱቱን የዳቦ ስም በሰጣቸው በኦነጋዊ -ሸኔ ላይ ግን እጁን አያነሳም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነመላኩ ፈንታን የሙስና ጉዳይ ከማጣራት ቢላደንን ማግኘት ይቀል ነበር ማለት ነው?

በዚች ሰዓት ዜጎች ከወያኔ ጋር በሚተነቁበት ወቅት በመሃል ሃገር በየምክንያቱ የሚያስረውና የሚያሳድደው የትግሉን አቅጣጫ ለማዘናጋትና ነገ – ከነገ ወዲያ እንደ ተለመደው ” ከወያኔ ጋር ለሰላም ስል ተኩስ አቁም አድርጊያለሁ።” ቢል፤ ለምን ብሎ  የሚጠይቅና የሚገዳደረው ኃይል እንዳይኖር መሆኑን መገንዘብ አለብን።

የስሜትና የሆሆታ ትግል ማለት የጀበና ቡና ማለት ነው። ጀበናው እሳቱ ሲጠፋ መፍላቱን ያቆምን ሌላ እሳት ካላገኘ ይሰክናል። የስሜትና የሆሆታ ትግልም እንደዚሁ ነው። ገዥዎቻችን አንድ እጀንዳ ሲሰጡን በስሜትና በሆይሆታ እንወራጫለን። ለዋናውን ትግላችን መዋል የሚገባውን ግዜ፣ እውቀትና መስዋእትነት በገዥዎች ማዘናጊያ አጀንዳ ላይ እናውለዋለን።  ግዜው ሲያልፍ ደግሞ ስንተፋተፍ አዲስ አጀንዳ ይዘጋጅልናል።

እናም እንዘናጋ፤ ትግላችን የህልውና፣ የመኖርና ያለመኖር ብሎም አገርን የመታደግ ነው።  ይኽችን መጣጥፍ በምከትብበት ሰዓት እንኳን የስሜኑ ጦርነት አልበቃ ብሎ በኦነጋዊ ብልፅግና ክንፍ  በሸኔ፣  ወለጋ ውስጥ ዜጎች “ድረሱልን” እያሉ እየተማፀኑ፤ ሰሚ  አጥተው  እንደተለመደው በመታረድ ላይ ናቸው።

ስለዚህም  በዘርፈ-ብዙው ጠላቶቻችን  ሳንበገርና በስሜትና በሆይሆይታ ሳንነዳ፣ ለረጅሙ ግባችን፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነታችን በፅናት እንታገል። ቅድም የምንሰጠውን ትግልና ፍልሚያ እንወቅ።

የጥንት አያቶቻችንና አባቶቻችን ከሁሉም ጠላቶቻቸው ጋር ታግለው አሸንፈው እኛ ከዚህ ደርሰናል። ምን መከራው ቢበዛና ጠላትና ሆድ አደር ባንዳ  እንደ አሸን ቢፈላ፤ የግዜ ጉዳይ እንጂ ዙሮ-ዙሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸነፊ መሆኑን የታሪክ  ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ትላንት ዛሬም ፤

—ሙቼ እየተነሳሁ፣ ልሞት እንደገና

እንድ ሞት ለአገሬ አይበቃኝምና።-++

የሚሉ ሚሊዮን  የአብራኳ ክፍይ ልጆች አሏት።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

———//———ፊልጶስ

E-mail: [email protected]

መስከረም -2015

1 Comment

  1. ችግሩ ለምድሪቱ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ የሰው ሃይል ማጣት አይደለም። ግን እኛ እየሞትን እነማን እየኖሩ ነው? በእኛ ደም ላይ ማን በለጠገና ተመነደገ ለሚሉት ጥያቄዎች መፍትሄ መጥፋቱ ነው። ዘንተ ዓለም በሃገርና በአንድነት ስም እልፍ የሃገሪቱ ልጆች ረግፈዋል። ዛሬም እየረገፉ ነው። በዚህ ሳቢያ ወላጅ አጥተው መንገድ የወደቁ ቤተሰቦች እልፍ ናቸው። እርግጥ ነው ስሜታዊ ሆኖ እውነትን ማየት አይቻልም። ለነገሩ ረጋ ተብሎም በእኛ ሃገር እውነትን ፍለጋ የተሰማሩ ጦማሪዎች፤ ጋዜጠኞችና ከያኔዎች ከዘብጥያ እስከ መሰወር ከዚያም ባለፈ እስከ ሞት ተዳርገዋል? ለመሆኑ የምድሪቱ ሰው በአማካኝ የሚኖረው እድሜ ስንት ሆነና ነው ሁሌ የምንራኮተው? ግን አውራ ጣት ከአመልካች እጣት ትበልጣለች ብሎ ለሚከራከር የዘርና የጎሳ እንዲሁም የቋንቋ ሰካራም ዶክተር ሆነ ፕሮፌሰር እውነትን ማሳየት አይቻልም። ረጋ ብሎ ላሰበ የሃበሻው ፓለቲካ ማጥ ውስጥ እንደ ተወሸቀ የመኪና ጎማ ሊወጣ በተሽከረከረ ቁጥር የራሱን ጉድጓድ እየቆፈረና በዙሪያው ሊያወጡት የሚታገሉትን ሰዎች ጭቃ እየቀባ እንደሚዘቅጥ አይነት ነው። መላቢስ፤ ጥላየለሽ፤ ሁሉን ቀርጣፊ ፓለቲካ! አታድርስ ነው። ዛሬ የሚርመሰመሱት የፓለቲካ ጊዜ ሰጦች ሳያስቡት ይቀነጠሳሉ፤ ሰካራም እንደ ረገጠው ጣሳ ይጨራመታሉ። በታሪክ ያየነው ይህን ነው። ሌላው የተራበና ጊዜ ያነሳው ይሰባሰብና ማታለያና መላሾ ይዞ መሰሉን እያስከተለ በተራው ደግሞ ዘርፎና ገድሎ ይከስማል። ታሪካችን ባጭሩ ይህን ይመስላል። በፊውዳሉ ዘመን ስለሆነው ጉዳይ ለመረዳት የዳኛቸው ወርቁ አደፍርስን፤ የአቤ ጉበኛን አልወለድም መጽሃፍቶች ማገላበጡ ጊዜው ልክ እንደዛሬው ግፍ አይፈሬ መሆኑን ያሳያል። የደርጉን ለቋሚ እስከ አሁንም ከነጠባሳቸው ላሉ የዘመኑ የፈተላ ፓለቲከኞች እተወዋለሁ። ከዚያ በህዋላ በወያኔ የሆነው በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ የአውሬ ሥራ በመሆኑና እየሆነም ስለሆነ አይን ያለው ያያል፤ ጀሮ ያለው ይሰማል። ባጭሩ ፓለቲካችን የመገዳደል ፓለቲካ ነው። አሁን እምናየው እንዘጥ እንዘጥም ቢረግብ ወይም ቢገታ ሌላ የሚያፋጀን ፈልገን መፋለማችን አይቀሬ ነው። የምድሪቱ ችግር እትየ ለሌ ነው። በመግደል፤ በማሰር፤ በማፈን የሚያምን መንግስት ቢዘገይም በሰፈረበት መስፈሪያ መሰፈሩ አይቀርም።
    አሁን እንሆ የራሻው መሪ የኒኩለር መሳሪያ ሳይቀር እጠቀማለሁ እስከ ማለት ደርሷል፡ አይሆንም አይደረግም አያደርጉትም የምትሉ ሁሉ ሂሮሽማና ናካሳኪ ላይ የተደረገውን የማታውቁ ናችሁ። ግን በእርግ የራሺያው መሪ እንዲያ ካደረገ ጀርመን፤ ጃፓን በሁለተኛው ዓለም ማለቂያ ላይ የገቡትን ቃል በመጣስ እነርሱም በጥቂት ወራታት ውስጥ ኒኩለየር ይታጠቃሉ። ይህ ክስተት ደግሞ ሌሎችን ያነቃቃል ዛሬም ጅራት ለሆነው የአፍሪቃ አሃጉር ደግሞ ሌላ ስጋትን ይጭራል። የዳግም ቀኝ ተገዥነትን መከራ!
    ስለዚህ በትግራይና በአፋር፤ በወለጋና በሌሎችም የሃበሻ ምድር ወንድምና እህቱን እያረደ ዘራፍ የሚለው የእንስሳ ጥርቅም ሁሉ እንደ ቄራ ከብት በየተራ የሚታረድ እንጂ አንድ ተረግጦና ተዘርፎ ሌላው በእፎይታ የሚኖርበት ምንም አይነት ሂሳብ አይኖርም። በውጭና በሃገር ውስጥ የኢንተርኔት የፈጠራ ወሬ በመንዛት የሳንቲም ሽርፍራፊ የሚለቃቅሙት ሁሉ በግንባር እጅን አንስቶ ማሩኝ የሚለውን ከሚረሽኑት ጨካኝ ሰዎች ተለይተው መታየት የለባቸውም። እንዴት ሰው በውሸት በወንድምና በእህቱ ሞት እልል እያለ ሳንቲም ይሰበስባል? በዚህ የተገኘው እንጀራስ ጤና ይሆናል? ግን ደንዝዘናል። ዘርፎ፤ አታሎ፤ ገድሎ መኖር መኖር እየመሰለን ተላምደነዋል። ስናሳዝን። የማያስቧርቀው ሲያስቧርቀን እድሜአችን የሃሰት ካባ እንደለበሰ አፈር ሆኖ አፈር መመለስ። ክራራይሶ ያሰኛል የሚሰማ ካለ። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.