አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት የመቸገር የፖለቲካ ባህል – ጠገናው ጎሹ

October 8, 2022

ጠገናው ጎሹ

ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን ለመሰንዘር ምክንያት የሆነኝ በሥርጉት ካሳሁን የቀረበውን ሂሳዊ ፅሁፍና በዚሁ ጽሁፍ ላይ Tesfa በተሰኘ ስም  የተሰጠ  ሂሳዊ ትችት መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ። የፅሁፉን አቅራቢ ስም ምናልባት ከእኔ ድክመት ካልሆነ በስተቀር ብዙም የማውቀው አይደለም።

በፅሁፉ አቀራረብና ይዘት ላይ ትችት የሚያሰጥ አንዳችም ነገር የለም የሚል ደምሳሳ አስተያየት የለኝም። እንደ አንዳርጋቸው አይነት በአንፃራዊ ግምገማ ከራሳቸው የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ሰብእና እና የሞራል ከፍታ ወርደው እጅግ በአስከፊ አኳኋን ቁልቁል በመምዘግዘግ የህወሃትን የበላይነት አስወግዶ ሥርዓቱን ግን እጅግ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ላስቀጠለው ሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ አንጃ (ኦህዴድ/ብልፅግና) ህሊናቸውን (ውስጠ ነፍሳቸውን) ላስረከቡ ወገኖች  መነገር ያለበት ግዙፍና መሪር እውነት ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ  የቀረበበት የመሆኑን እውነታ ግን ማስተባበል ወይም ማጣጣል አይቻልም የሚል ጠንካራ አስተያየት አለኝ።

በፅሁፉ ላይ  Tesfa  በሚል ስም ሂሳዊ ትችት የሰጡትን  በግል ባላውቃቸውም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በባህላዊ መገናኛ ዘዴዎችና በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰጧቸው ቅንነትና አገር ወዳድነት በሚንፀባረቅባቸው ነፃ አስተያየታቸው እንደማውቃቸው ለመግለፅ እወዳለሁ። ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ላይ በሰጡት አስተያየት መነሻነት የምሰጠው ሂሳዊ አስተያየት ከፖለቲካ አስተሳሰብና አመለካከት ልዩነት ላይ እንጅ ከግል ባህሪና አስተሳሰብ ጋር ግንኙነት የሌለው ስለመሆኑ ግንዛቤ እንዲወሰድ ለማስገንዘብ እወዳለሁ። ይህ  አይነት የግንዛቤ ማስታወሻ  የሚነሳው ማነኛውም ሰው በመርህ ደረጃና በሌላው  መብትና ህልውና ላይ ሥጋት ወይም አደገኛ አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል እስካልሆነ ድረስ  በተረዳውና በሚያምንበት ልክ (መጠንና አይነት) ሃሳቡን ወይም አስተሳሰቡን የመግለፅ መሠረታዊ መብቱ ነው ከሚል ፅዕኑ እምነት ነው።

ለመግቢያዬ ይህን ያህል ካልኩ ወደ ሂሳዊ አስተያየቴ ነጥቦች ልለፍ፦

1) ዘመናትን ላስቆጠረውና አሁንም ተዘፍቀን ለምንገኝበት አጠቃላይ ቀውስና ውድቀት አስተዋፅኦ ያደረጉትን ፣ እያደረጉ ያሉትንና መነሻቸው የግለሰብ ወይም የግለሰቦች የፖለቲካ ሰብእና እና የሞራል ዝቅጠት የሆኑትን ጉዳዮች እንደማናቸውም አይቶ መታለፍ እንዳለባቸው ተራና ጊዜያዊ ጉዳዮች አድርጎ ማቅረብ የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የመፍትሄ ፍለጋ መንገድ  አካል  ሊሆን አይችልም።

2) “በየትኛው መሥፈርት ነው አንዳርጋቸው የአማራ ጠላት የሚሆነው? ” የሚለውን ጥያቄ እድሜ ልኬን ታገልኩለት የሚሉትን የመሠረታዊ ነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እርግፍ አድርገው በመተው አጥብቀው ይፀየፉት የነበረውን ህወሃት መራሽ የጎሳ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ቁማር የተካውንና ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኢትዮጵያን ህዝብ በአጠቃላይና በተለይ ደግሞ የአማራን ማህበረሰብ የቁም ስቃይና የግፍ ግድያ ሰለባ ላደረጉት ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን እና ወራዳና ጨካኝ ብአዴናዊያንና ደህዴናዊያን ህሊናቸውን ለሸጡ  እንደ አንዳርጋቸው አይነት የፖለቲካና የሞራል ኮስማኖች  ለምን የአማራ ጠላቶች ይባላሉ በሚል ጉዳዩን ወደ የተራ (የአረቤነት) ደረጃ ለማውረድ መሞከር መሬት ላይ ላለው ግዙፍናመሪር ሃቅ ፈፅሞ ይመጥንም።

3) አዎ! የአማራ አመራር ተብየው የአማራውም ሆነ የሌሎች ንፁሃን ወገኖች ዋነኛ ጠላቶች መካከል አንዱ ነው። ህወሃትን ተክቶ በህዝብ ላይ የማያቋርጥና እጅግ አስከፊ የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረደ ካለውና የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ ከተቆጣጠረው ገዥ ቡድን ጋር እጅግ ፀያፍና አደገኛ በሆነ የፖለቲካ አመንዝራነት የተዘፈቁት እንደ አንዳርጋቸው አይነት ወራዳ ወገኖች አይደሉም እንዴ ታዲያ አገርን በማቆየት በተደረገውና ለማቆየትም እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የእራሱን ጉልህ ሚና የነበረውንና ያለውን የአማራ ማህበረሰብ ከግፈኞች ጋር ሆኖ መከራውንና ውርደቱን ከማራዘም የከፋ የአማራ ጠላትነት አለ ወይ?

4) አዎ! ዛሬም ንፁሃን ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብቶች መደፍጠጥ ያሳስበናል ያሉና የሚሉ ወገኖች ዘብጥያ እየወረዱ ናቸው። ታዲያ ይህንን አይነት ግፍና መከራ እንደ ዶፍ እያወረዱ ከቀጠሉት ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት እየተሻሹ ያሉት እንደ አንዳርጋቸው አይነት ወገኖች ከግማሽ እድሜያቸው በላይ ከቆዩበት የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሃዲድ ተንሸራተው እራሳቸውን ቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ (Garbage In And Garbage Out) በሚል የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ የሚርመጠመጡ  ወገኖች አይደሉም እንዴ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥቃትን እንደ ግጭት ማቅረብ የግፉአንን ጩኸት መቀማት ነው – ያሬድ ሃይለማሪያም

5)  አገርና ህዝብ እንኳን ማቆሚያ ሊገኝለት አንፃራዊ የእፎይታ እስትንፋስ የሚያሳጣ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ ሆነው እንዲቀጥሉ ካደረጉና በማድረግ ላይ ከሚገኙት ዋነኛ  እኩያን ወገኖች መካከል ህወሃትና ኦነግ (ሸኔ) የመሆናቸው ሃቅ መሬት ላይ ተዘርግቶ የሚነበብ በመሆኑ ፈፅሞ ማብራሪያ የሚሻ ጉዳይ አይደለም። ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአንድ በኩል የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ በተቆጣጠረው ኦህዴድ/ብልፅግና እና በሌላ በኩል ደግሞ  ለምን  ዙፋኔን ተነጠቅሁ በሚል አካኪ ዘራፍ በሚለው ህወሃትና አምሳያዎቹ ጥምረት ከሥልጣን ሽኩቻ በስተቀር ሌላ ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የሌለውን የመግደል፣ የማገዳደልና የመገዳደል እጅግ አሰቃቂ የፖለቲካ ምንነትንና ማንነትን ከምር ለሚያስተውል እውነተኛ የነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገን ህሊናን አያቆስልም እንዴምንም አይነት ይሉኝታ በሌለበት አኳኋን ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው የበጎ ህይወታቸው መንገድ ዋስትና የሆነውን አንጡራ ህሊናቸውን (ውስጠ ነፍሳቸውን) ለባለጌና ለጨካኝ ተረኛ ኢህአዴጋዊያን ብልፅግናዊያን አሳልፈው የሰጡ እንደ አንዳርጋቸው አይነት ከንቱዎችን የእራሱም ሆነ የአገሩ የኢትዮጵያ ነፃነትና ክብር ከመከራና ከውርደት መውጣት አለበት የሚል ፅዕኑ ፍላጎት ያለው የአማራ ማህበረሰብ ጠላቶች ለይቶ ማየት አይቻልም በሎ እቅጩን መናገርና መነጋገር ተራና የማይጠቅም ወይም አጉል አቴካራ (እሰጥ አገባ) ለምና እንዴት ይሆናል? ለዚህ ነው ነገረ ሥራችን ሁሉ እየፈጩ ጥሬ አይነት ሆኖብናልና ከግልብ የፖለቲካ ስሜትና ከክስተቶች ትኩሳት ጋር ከመውጣትና ከመውረድ ያለፈ የፖለቲካ ማንነቱን ምንነቱን እየለዩና እያስለዩ የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰላባ እንዲሆን ካደረጉት እኩያን ገዥቡድኖችና ሌሎች ቡድኖች ለይቶ ለማየት እንዴት ይቻላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ፌዴራል መንግሥት” ሆይ! አማራ ሲያልቅልህ ወታደሮችህን የዒላማ ተኩስ በምን ልታሰለጥን ይሆን?

6)  አዎ! የህወሃት ፖለቲከኞች ለዘመናዊውም ሆነ ለባህላዊው የእርቅና የሰላም ጥረት የሚመች የፖለቲካ ሰብእና እና የሞራል እሴት በእጅጉ እንደሚጎላቸው ለመገንዘብ አስተዋይና ቅን ህሊና እንጅ የተለየ ጥናት ወይም ምርምር አይጠይቅም።

በሌላ በኩል ግን ለሩብ ምዕተ ዓመት የህወሃት እኩይ ዓላማና ግብ ታማኝና ርህራሄ ቢስ አገልጋዮች ሆነው የዘለቁትንና ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ደግሞ የሥልጣን የበላይነት ሽኩቻውን ወራዳና አዋራጅ በሆኑ ብአዴን ፣ ደህዴን እና ሌሎች  አጋር ተብየዎች አሽከርነት አሸንፈው አገርን ፈፅሞ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ምድር ያደረጉትንና በማድረግ ላይ የሚገኙትን ኦህዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ለአገር አንድነትና ለህዝብ ደህንነት ሲሉ የሚጋደሉ አድርጎ ከማሰብ የከፋ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የሞራልና የመንፈስ ድቀት (ዝቅጠት) ይኖራል እንዴአንዳርጋቸውና መሰሎቹስ የዚህ አይነት እጅግ አስከፊ የፖለቲካ ቁማር ውስጠ አዋቂዎችና አማካሪዎች አይደሉም እንዴ? ታዲያ ከዚህ የከፋ የግፍ ሰለባ የሆነው የአማራ ማህበረሰብ ጠላትነት የትኛውና እንዴት ያለ ነው?

7) ሁለቱ የኢህአዴግ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ አንጃዎች በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት እንደ በጎና ትልቅ የታሪክ ሂደት በምዕራፍ እየከፋፈሉ ላካሄዱትና እያካሄድት ላሉት እጅግ አስከፊ የወንድማማች/እትማማቾች ጦርነት እና እየተካሄደ ነው ለሚባለው ድርድር ተብየ የመክሸፍ (የመጨንገፍ) ፈተና ህወሃትን ብቻ ተጠያቂ የማድረግ እጅግ የተዛባና የመከራውን ዘመን ለማሳጠር የማይረዳ የፖለቲካ አስተሳሰብ  ለምንና ለማን ነው የሚጠቅመው? ሁለቱም አንጃዎች እኩይ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ በተዘፈቁበትና መከረኛውን ህዝብ በደም እንዲቃባ ባደረጉበት ፣ እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ እና ይህንኑ የሚያስቆምና ወደ ትክክለኛው የጋራ መፍትሄ የሚወስድ የፖለቲካ ሃይል ከመፍጠር ይልቅ እጅግ መያዣና መጨበጫ በሌለው የፖለቲካ አዙሪት  ውስጥ እየተርመጠመጥን ባለንበት መሪር እውነታ ውስጥ የህዝብ የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ አንደኛው አንጃ ሌላኛውን ከምድረ ገፅ በማጥፋት ይመለሳል የሚል አይነት እጅግ የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚቀነቀነው እንደ አንዳርጋቸው በመሰሉ ሃፍረተቢስ አድርባዮች አይደለም እንዴ? ይህንን አይነት ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ድንቁርና እና የሞራል ዝቅጠት  ቆም ብለን ለማየት ለምንና እንዴት እንደተሳነን አሁንም እራሳችንን ለመመረመርና ተገቢውን የእርምት እርምጃ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ለመውሰድ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ካልሆን ነየፃነትና ፍትህ ፈላጊነታችን እንዴት ትርጉም ሊኖረው ይችላል

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴን ሆይ! ነፍስ ይማር!!

8) “አባቶች ፣ እናቶች ፣ ቀሳውስትና የእስልምና እምነት ወንድሞችና እህቶች እያለቀሱ ሲለምኗቸው አሻፈረኝ ብለው አሁን ሰላም ፍለጋ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ለመሄድ ማሰብ ርካሽነት ነው” የሚለውና አሁንም የቀድሞውን የኢህአዴግ የበላይ ጠርናፊ ህወሃትን ብቻ የመወንጀል የፖለቲካ አስተሳሰብ ከምንመኘው የእውነተኛ ሰላምና ፍትህ ሥርዓት እውን መሆን ጋር እንዴት ሊጣጣም ይችላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሴት የሁላችንም እናት በመሆኗ ሠላምን እና ዳቦን አጥብቃ ትሻለች - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

እውን ከማልቀስ ያላለፈው የእናቶች ጥሪ ለዘመናት በአስከፊ የፖለቲካ ወለድ ወንጀል እጆቻቸው የተዘፈቁትን ሁለት የአንድ ሥርዓት አንጃዎች (ህወሃትና ብልፅግና) ወደ እውነተኛ (የሥርዓት ለውጥን በሚያስከትል ደረጃ) ለማስጠጋት ይችል ነበር ወይ?

የቤተ መንግሥቱ የኢህአዴግ አንጃ ቡድን የሚግታቸውን የለየለት የሸፍጥ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ  መልእክት እንደሚያደርስ ፖስተኛ ከማመላለስ ያለፈ ፋይዳ ያልታየበት የአባቶች፣ የቀሳውስትና የእስልምና ተካይ ወገኖች ተማፅኖና ልመና  ለዘመናት  ለመጣንበትና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ተዘፈቅን ለምንገኝበት ግዙፍና መሪር ፈተና ፍቱንና ዘላቂ መፍትሄን አምጦ የመውለድ አቅም እንዴት ሊኖረው ይችላል?

10)  አዎ! የመደመሩ ሂሳብ ወደ መቀነስ ተለውጦ ይኸው አቦይ ስብሃትን የፈታው የብልፅግና መንግሥት ለአገር  አንድነትና ለወገን እኩልነት የሚፋለሙትን እየሰወረ ነው የሚለውን አገላለፅ አጠቃላይ እውነትነት ያለው መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም።

ገረፍ ከማድረግ አልፈን ልብ ካልነው ግን ፦

) “ከመደመር ወደ መቀነስ ተለወጠ” ስንል ከመጀመሪያውም የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞችን በተለይም በጎ ሠርቶ በራስ የመተማመን ሳይሆን እጅግ ልክ በሌለው የግል ዝናን ሊያተርፍለት በሚችል መናቸውም የውሸት፣ የማታለል ፣ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰብእና ክፉኛ የተለከፈውን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ ድርሰት ወንዝ እንደሚያሻግር ፍልስፍና በመውሰድ የራሳችን የፖለቲካ ኮስማናነት ያሳየንበት መሆኑን

)  ለዚህ አይነት በለየለት ሸፍጥ፣ ሴራና ጨካኝ የፖለቲካ ኦርኬስትሬሽን መሳካት እጅግ ጉልህ ሚና ከተጫወቱት መካከል አንዳርጋቸውና መሰሎቹ  የመሆናቸውን መሪር ሃቅ በግልፅና በቀጥታ የሚገልፁትን ወገኖች ተራ በሆነና  በማይጠቅም የፖለቲካ ጨዋታ እንደተጠመዱ አድርጎ የማየትን በእጅጉ የተንሸዋረረ አመለካከታችንን

ሐ) በራሳቸው በነስብሃት ነጋ እጅግ ፀያፍና አስከፊ በሆነ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ሥር ለሩብ ምእተ ዓመት በፍፁም ታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩና የሥልጣን ሽኩቻውን አሸንፈው የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ የበላይነት በመቆጣጠር አገርን ወደ ምድረ ሲኦልነት የለወጡት ወንጀለኛ የኢህአዴግ አንጃ ቡድኖችን እነ ስብሃት ነጋ ከፈፀሙት ወንጀል ነፃ ሆነው የፍትህና የርትዕ ጠበቃዎች እንደሆኑ አይነት አድርጎ የማሳየትን እጅግ የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ነው የሚነግረን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ በርግጥ ዴሞክራሲ ይገባታል ወይ?

11) ጀኔራል ፃድቃን ባካሄደው ቃለ መጠይቅ ውስጥ ከቆመበትና ከቆመለት ዓላማ አንፃር የፈለገውን አይነትና ይዘት ያለውን ትርክቱንና የአቋም መገለጫውን መናገሩን እንደ አዲስ ነገር ለማመሳከሪያነት የተጠቀምነውን ያህል የአንዳርጋቸውንና የመሰሎቹን የህዝብን የነፃነትና የፍትህ ትግል ከድተው እነ ፃድቃን አስወልደው ካሳደጓቸውና ያንኑ ሥርዓት እጅግ አስስከፊ በሆነ የተረኝነት የፖለቲካ ሥልጣን በመጠርነፍ አገርን ምድረ ሲኦል እያደረጉ ካሉት ጋር ርካሽ የፖለቲካ አመንዝራነት የሚፈፅሙትን እንደ አንዳርጋቸው አይነት ወገኖች ማሄስ ተራ ወይም ፋይዳ የሌለው ነው የሚሉት የፖለቲካ ትርክት ምን የሚሉት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ አስተሳሰብ ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  መከራ ሲመጣ አይነግርም ዐዋጅ … ነፃነት ዘለቀ

12) ምናባዊና ንደፈ ሃሳባዊ ከሆነው ዓለም አልፈን የገሃዱን ዓለም የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ልብ ካልነው በየአንዳንዱ አገር የውስጥ ሁለገብ አቅምና ችሎታ ላይ የተመሠረተ ነው ። በዚህ የገሃዱ ዓለም እውነታ ውስጥ እንኳንስ ሞራልና ሥነ ምግባር የዓለም አቀፍ ህጎችና ልማዳዊ አሠራሮች (International Laws And Norms) ወደ መሬት ወርደው የሚፈለገውን በጎ ውጤት የመፍጠር እድላቸው በእጅጉ በፈተና የተሞላ ነው። ይህ ደግሞ የዓለም ፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እውቀት ወይም ግንዛቤ ሀሁ ነው።

ይህንን እጅግ ቀላል በሚመስል ግን መሪር እውነትነት ባለው ምሳሌ ማሳየት ይቻላል። አንድ ይበላው ያጣን የምስኪን ድሃ ልጅ ኬክ የመሰለ ዳቦውን በመተከዣነት እየገመጠ መንገድ ላይ የሚዝናና የሃብታም ልጅ ቢያገኘውና እግሩን ተጎንብሶ ከሳመ ከጥጋብ ያተረፈውን ዳቦ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለት ፈፅሞ አያደርገውም ብሎ መከራከር በራበው ሰው (ያውም በህፃን) መፍረድ ነው የሚሆነው ። የህዝብን ርሃብ፣ ጥማትና ደህንነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለሃያላን ተፅዕኖ (አላስፈላጊም ቢሆን) የማይንበረከኩ ገዥዎች ፈፅሞ አይኖሩም ለማለት ባይቻልም አብዛኛዎቹ ከእራሳቸው ልክ የሌለው ሥልጣናቸውና ከእርሱ የሚገኘው የግልና የቡድን ጥቅም ሥጋት ላይ የወደቀ መሆኑን ሲረዱ ብቻ ነው ለውጭ ተፅእኖ ፈጣሪ ሃይሎች የሚንበረከኩት።

ይህንን የሚያደርጉት ግን “የእኛ ዘመን ጠገብ መሪር ሃዘንና የደም እንባ ሳይገዳችሁ የውጭ ሃይላትን ተፅዕኖ በመቀበል ያንኑ ክፉ ሥርዓታችሁን ለማስቀጠል ወሰናችሁ?” የሚልን የህዝብ ጥያቄና እሮሮ በሚያመክን ወይም ቢያንስ በሚያለዝብ  የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ይህንን ስል በውጭ ሃይሎች ተፅኖም ቢሆን ጦርነት መቆም የለበትም እያልኩ ሳይሆን መሠረታዊ በሆነና ቀጣይነት (ዘላቂነት) ባለው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ የእነዚህን እኩያን የፖለቲካ ሃይሎች የመከራና የውርደት ሥርዓት ለመስወገድ እስካልቻልን ድረስ ማቆሚያ የሌለው የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻቸው እያገረሸ በሚያስከትለው የእርስ በርስ ጦርነት (እልቂት) ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን ነው።

የትኛውም የውጭ ግንኙነት ጥንካሬና ድክመት በወሳኝነት የሚለካውና የሚወሰነው በውስጣዊው ሁለንተናዊ ጥንካሬና ዝግጁነት እንጅ በተቃራኒው አይደለምና የገንዛ ራሳችንን ቤት ለሸፍጠኛ ሴረኛ ገዥ ቡድኖች የእኩይ ፖለቲካ  መጫወቻነት አሳልፈን እየሰጠን ከእንዲህ አይነት ክፉ ገዥ ቡድኖች ጋር ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ አመንዝራነት የተዘፈቁ እንደ አንዳርጋቸውና መሰል ወገኖች ተግባርና ስም በተነሳ ቁጥር አሜሪካኖች ፣ የአውሮፓ ህብረት ሃይላት ፣ ወዘተ ጣልቃ ገቡብን እያሉ ማላዘን ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።

13) ” ከሁሉም ጋር ትግልና ከሁሉም ጋር ፉክክር ለማንም አይጠቅምም” የሚለው ማስጠንቀቂያ አይነት መከራከሪያ ግልፅና ግልፅ ከሆነው ከአንዳርጋቸውና መሰሎቹ  የፖለቲካ ዝቅጠትና የሞራል ጉስቁልና ጋር በምንና እንዴት እንደሚገናኝ ለማሳመን አይቻልምና በስሜት ከሚነጉድና የማይገናኘውን እያገናኙ የመከራውንና የውርደቱን እድሜ ማራዘም የለብንም ። እናም  ልብ ያለው ልብ ይበል !!!

 

5 Comments

  1. ግሩም ትንታኔ ነው፡፡ መልካም ልቦና ላለው አስተማሪ ጽሑፍ ነው፤
    ከአክብሮታዊ ምሥጋና ጋር፡፡

  2. በቅድሚያ በሰለጠነ መልኩ ያለምንም ትርፍ ቃል ሃሳብህን ማጋራት በመቻልህ/ሽ አክብሮቴ ይድረስህ/ሽ። የእኔው እይታ በጭራሽ የሃበሻ ፓለቲከኞችን በተለይም አንዴ እዚህ አንዴ እዛ የሚሉትን የፓለቲካ ቀላዋጮች ለመደገፍ አይደለም። ግን ከስንቱ የፓለቲካ ሸፍጠኛ ጋር ተፋልመን ይዘለቃል? ቢቻል የሚወጉንና የሚያዋጉንን ለይተን እንይ ነው። ሲጀመር የሃበሻ ፓለቲካ ስሜታዊና ግልፍተኝነት ያጠቃዋል። ለዚያ ነው ከዘመናት በፊት ” ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ባሉን ማግስት 61 ሰዎችን ከበሮ መትተው አንድ ጉድጓድ የከተቱት። አሁን ላይ የተሳከረው የዘር ፓለቲካም በአንድ ቀን የበቀለ አረም ሳይሆን ለግማሽ ምዕተ ዓመት የተዘራ እንክርዳድ ነው። ፈረንጆች “Admitting Fault is not defeat”ይላሉ። ችግራችን አጥፍቻለሁ፤ ተሳስቻለሁ የማለት ባህል የለንም። ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው የመገዳደል ፓለቲካ ከዚሁ እብደት ጋር የመነጨ ነው። የአውሮፓ ህብረት ይህን አለ፤ አሜሪካ እንዲህ አለች፤ የአረብ ሃገራት በሱዳን በኩል እንዲህ ሊያደርጉ ነው፤ እያደረጉም ነው እንባላለን። ይህ ግን ዛሬ የተጀመረ ሴራ ሳይሆን ለዘመናት ሲሰሩበት የኖሩት የፓለቲካ የውጭ ፓሊሲያቸው ነው። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንዲሉ እኛ ስንገዳደል ለእነርሱ ሰርግ ነው። ለኢትዮጵያ ወይም ለትግራይ ህዝብ እነዚህ ሰዎች ያስባሉ ብሎ ማሰብም ጅልነት ነው። በየትኛው የዓለም የፓለቲካ ግርግር ነው ተመድ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመኮነን በግልጽና በዝግ ስብሰባ እንደተቀመጠው የተቀመጠው? አለ በታሪክ? በጭራሽ። አሜሪካ በየተኛው አስተዳደር ነው አንድ ክፍለ ሃገር አሻፈረኝ ማለቱን እያወቁ ወገባቸውን ይዘው ለወያኔ የሚከራከሩት? ልብ ያለው ትርፋቸው የቱ ላይ እንደሆነ ይመረምራል እንጂ ለትግራይ ህዝብ ተሟጋች እንደሆኑ አድርጎ መውሰድ ጅላጅል መሆን ነው። እንግዲህ የሃበሻውን የፓለቲካ ሽኩቻም ማየትና መመዘን ያለበን ሃገራዊነቱን ብቻ ሳይሆን ተያያዥነቱንም ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን እኔ በግል አላውቀውም። በቀደመው ሃሳቤ ላይ እንዳሰፈርኩት በሚሰጣቸው ሃሳቦችና በመጽሃፉ በኩል ነው የማውቀው። አንዳርጋቸው ጽጌ በየጊዜው በኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች አንገታቸው የሚቀነጠሰውና ቤታቸው የሚቃጠልባቸውን አማሮች የሚጠላ፤ የሚያጣጥል ከሆነ ራሱን ይንቃል እንጂ ሌላ ትርፍ አያገኝም። አሁንም ሆነ ያኔ መከራውን የሚቆጥረው የአማራ ህዝብ ለምን ይጠቃል ብሎ ለሚጠይቅ መልሱ አንድ ነው። የአማራ ህዝብ አጥቂዎች ኢትዮጵያን የሚጠሉ ናቸው። በከተማና በበረሃ ህዝባቸውን የጨቆነህ፤ ድሃ እንድትሆን ያደረገህ አማራ ነው። መሬትህን የቀማህ፤ ሃይማኖትህን የቀየረብህ አማራ ነው እያሉ ለዘመናት ህዝባቸውን የፈጠራ ፓለቲካ ሲግቱት ኖረዋል። ለዚህ ቀዳሚው ሻቢያ ነው። አሁን በህይወት ያሉ እውነተኛ የሻቢያና የሌሎች ተቆራቋሽ የፓለቲካ ትራፊዎችን ፈልጎ ማነጋገር ነው። እውነቱን ይናገራሉ። የዛሬው እንዘጥ እንዘጥ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ህሳቤ ነውና! ወያኔ የሻቢያን የአማራ ጥላቻ ተቀብሎ ጣራ ላይ በመስቀል እልፎችን አፈር መልሶባቸዋል። ያው የሃበሻው ፓለቲካው የድላ ቅብብሎሽ ሆነና ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ አለቆቻችን አማራውን በሻሸመኔና በሌሎች አካባቢዎች ሲታረድ ዝም ብለው ያያሉ። ምድሪቱ የሽኮች ናት። ሰው በሰውነቱ የሚመዘንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አይመስለኝም። ስለሆነም አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት ችግር የለብኝም። ለዘመናት ፊት ለፊት የተጋፈጥኳቸው ይህን ይመሰክራሉ። ግን ፊልሚያችን፤ ትግላችን አንድ ወድቆ በተኮታኮተበት መሰላል ያለምንም ማሻሻያና ጥገና መልሶ መውጣት እንዳይሆንብን እሰጋለሁ። መርጠን፤ አይተን፤ ለይተን እንፋለም ባይ ነኝ። በቃኝ።

  3. ጠገናው ጎሹ እንዲህ አብሰልስሎህ መመለስ አልነበረብህም tesfa እንዲህ ነው። በፊተኛው ወቀሳው አንዳርጋቸውን ተከላክሎ እላፊ ቃል ሲናገር ነበር እዚህ ላይ ደግሞ የት አውቀዋለሁ አይነት መልስ ሰጥቶሀል። አንተም ከግማሽምእተ አመት በላይ የታገለ ብለኸዋል አልገባኝም አንዳርጋቸው ከግማሽ ምእተ አመት በላይ የታገለው ለማፍረስ ነው ለመገንባት? ይህንን ለማጠናከር ገብሩ እስራትና እራሱ የጻፈውን መጽሀፍ ማየት ነው አንዳርጋቸው ክፉ የአማራ ደመኛ ነው ለምን በአማርኛ እንደሚጽፍና በአማርኛ እንደሚናገር አይገባኝም። እንግዲህ አንዳርጋቸው ስንል ግምቦተኞች ብርሀኑ ነጋና እነ ኤፍሬም ማዴቦ አሉልህ። አንዳርጋቸው በድርጊቱ ከልደቱ አያሌው ይበልጥ እንደሆን እንጅ የሚያንስ አይደለም። tesfa ካልተቆጣ አንዳርጋቸው በጽሁፉ ፩ ምንሊክ ከኡያቴ ሀምሳ ሽህ ቀንድ ከብት ሰርቋል ፪ በአድዋ ጊዜ እስላሞች እየተመረጡ አልተቀበሩም ፫ ዩኡማራን ፋኖን እሱ ላበላሸው ስርአት ህይወት ለመክፈል የሄዱትን ሲሳደብ የከረመ ነውረኛ ሰው ነው። ከዚህም በላይ አንዳርጋቸው ህወአት ሲደናበር ጣቱን ይዞ ከእዲስ አበባ ህዝብ ጋር አስተዋውቆት ህወአት የሾመው በክብር የሸኘው ከመሆኑም ባሻገር በኢሳት ዘመኑ ለኦነግና ጁዋር መሀመድ ምን ያህል ሽፋን እንደ ሰጡት tesfa ወደ ሗላ ጎጉሎ ሊመለከት ይገባዋል። ነገሮች እየጠሩ ሲሄዱ ብዙ የማይደፈሩ ነገሮች ይወጣሉና በትእግስት እንጠብቅ። ጠገናውም ምዘናህን አስተካክል ግንቦት ፯ እና መሪዎቹ ትላንት እዳ ነበሩ ዛሬም በኢዜማ ሾልከው እዳ ናቸው ነገም እዳ ነው የሚሆኑት እነዚህ ስዎች ስለማይላቀቁን። ተስፋን አትቀየመው ጽሁፍ ያደምቃል

  4. የውስልትናው ፓለቲካ ልክ እንደ ውሻ የተቀበረ ነገር ጎትቶ በማውጣት አየሩን ይበክላል። የ Birega አስተያየት ሁሉን ጥላሸት እየቀባ የሚያልፍ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ለማየት የሚናፍቅ ሳይሆን በደልን እንደ ገበጣ ጫወታ ጠጠር እየቆጠረ እድሜ ልክ መቀጣቀጥን የሚመርጥ ይመስላል። እኛ ሳንጨመርበት ትላንት የገደሉ እየተገደሉ፤ ትላንት ያሰሩና ያሰቃዪ እየታሰሩ አይደል እንዴ? አሳሪና ገራፊው፤ ገዳይና ቀማኛው በወረፋ በሚገዳደልባት በሃበሻ ምድር ምን ሌላ እሳት መለኮስ ያስፈልጋል? ደግሞስ አሁን ማን ይሙት በሃበሻ ምድር በሰው ላይ ክፋት ያልሰራ፤ ሃገርና ህዝብን ያልበደለ ሰው ይገኛል? እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለቱ ከንቱ ነው። በሃገሪቱ ጉዳይ የምንጠየቀው ኢትዮጵያ አትፈርስም እያለን በየቀኑ በተግባርና በሴራ የምናፈርሳት የፓለቲካ ዲስኩረኞች ሁሉ ነን። የእኔ ሃሳብ ይህንም ያንም እየዘነጠሉ ጠላት ከማራባት ረጋ ባለ መልኩ ነገሮችን እንይ ነበር። ግን ላንባቢው የታየው ሌላ ጉዳይ ነው። ብዙው የፓለቲካ ክስ መረጃ አልባና ሆን ተብሎ በየድህረ ገጽ የሚሰራጭ ምንጭ የለሽ የጥላቻ ወሬ በመሆኑ እንዳለ መጨለጡ ራስን ማሳመም ነው። በእኔ በኩል መጽሃፍን ሳንብም ሆነ ሌሎችም ነገሮችን ሳዳምጥ እኔን የሚያስደስተኝ የቱ ነው ሳይሆን ይህንና ያን ለማለት ጸሃፊው ወይም ተናጋሪውን ያበቃቸው ምንድን ነው በማለት ለማወቅ እጥራለሁ። የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መጽሃፍም ያየሁት በዚህ መልኩ ነው። ባጭሩ ከዘርና ከቋንቋ ፓለቲካ የእኔ አመልካች እጣት ከአንተ ይሻላል የሚለውን የተሳሳተ እይታ እስካላቆምን ድረስ ችግራችን ይቀጥላል። እኔ በፊትም ሆነ አሁን ለጻፍኩት ነገር የማንንም ጉልበት በመሳም ይቅርታ አልጠይቅም። ስለሆነም ከድምሩም ሆነ ከቅነሳው ወይም ከመንጋ የፓለቲካው አስተሳሰብ የሚመነጭ ምንም ነገር አያስደነግጠኝም። ስንት ሌላ የሚባል ነገር እያለ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ጊዜ ማባከኑም ተገቢ አይመስለኝም።

  5. በዓለም ላይ እንደአማራ ጠላት የበዛበት
    ፍጡር ፈልጉ እስኪ፡፡ በጭራሽ አታገኙም፡፡ እንደአማራ ለበርካታ ዘመናት በተካኪ (በሚተካኩ) ገዢዎች የተሰቃዬ ሕዝብ ፈልጉ፡፡ አታገኙም፡፡ እንደአማራ ራሱ አማራ ዋና አስገዳይ የጠላቶቹ ባንዳና ምስለኔ የሆነ ፈልጉ፡፡ አታገኙም፡፡ ለዚህ ነው የአማራውና በጥቅሉ የኢትዮ ትንሣኤ የራቀብን፡፡ አሁን ግን ለአክራሪ ኦሮሞ ምሥጋን ይድረሳቸው በነሱ ለከትየለሽ የሞኝነት ሥራ ምክንያት አማራው ከእንቅልፉ እየባነነ ስለሆነ ትንሣኤ ቀርባለች፡፡
    አማራ ላይ ድንጋይ ያልወረወረ አይጸድቅም የተባለ ይመስል ሁሉም ፖለቲከኛ አፉን የሚከፍተውና ታጣቂውም ጠበንጃው የሚፈትሸው አማራ ላይ ነው፡፡
    በነገራችን ላይ ቢረጋ የተባለው አስተያየተኛ በጣም ግሩም ሃሣብ ማስፈሩን ሣልጠቁም ብቀር ኅሊናየ ይወቅሰኛል ፧ ተስፋን ጨምሮ የሌሎቹም ጨዋነት የተሞላበት አስተያየት ጨምሮ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.